በተመድ የሰብዓዊ መብት ረዳት ጸሐፊ ማርክ ሎኮክ

በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ወቅታዊ ቀውስን በተመለከተ ለአምስተኛ ጊዜ የተሰበሰበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታ ምክር ቤት፣ እንዳለፉት አራት ስብሰባዎች በተጠናቀቀው ሳምንት ስብሰባውም አንድ አቋም ላይ መድረስ ሳይችል ቀረ።ሐሙስ መጋቢት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በዝግ የተሰበሰበው የፀጥታው ምክር ቤት በተመድ የሰብዓዊ መብት ረዳት ጸሐፊ ማርክ ሎኮክ፣ በትግራይ ያለው ውጊያ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ እያስከተለ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ግዝፈት የተመለከተ ማብራሪያ ለምክር ቤቱ መቅረቡን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተጨማሪም በትግራይ ክልል ግጭት ውስጥ መሳተፉ የተረጋገጠው የኤርትራ ሠራዊት ለቆ እንደሚወጣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ቢገለጽም፣ የኤርትራ ጦር ለቆ አለመውጣቱን ሚስተር ሎኮክ ለፀጥታው ምክር ቤት ዝግ ስብሰባ ሪፖርት ማቅረባቸውን ከተመድ የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። በትግራይ ስላለው ሁኔታ ሪፖርት ያቀረቡት ማርክ ሎኮክ፣ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ለቀው አለመውጣታቸውንና የኢትዮጵያን ሠራዊት ዩኒፎርም ለብሰው በክልሉ ግጭት ውስጥ አሁንም እየተሳተፉ እንደሚገኙ ማብራሪያ መስጠታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።

ምክር ቤቱ ባደረገው ዝግ ውይይት ላይ ሩሲያና ቻይና የፀጥታው ምክር ቤት በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጣዊ ጉዳይ ላይ መግባት እንደሌለበት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተም ለብቻው መታየት እንደሚገባው መከራከራቸው ተሰምቷል።አየርላንድ፣ እንግሊዝና ፈረንሣይ ግን በትግራይ ክልል ያለው ቀውስ እንደሚያሳስባቸው በመጥቀስ፣ የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ጠንካራ አቋም ሊይዝ ይገባል የሚል ክርክር ማንሳታቸው ታውቋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፈን ዷሪክ፣ የትግራይ ክልል ቀውስ አሳሳቢ እንደሆነ የገለጹ ቢሆንም፣ በዝግ የተካሄደውን ውይይት አስመልክቶ ግን የተብራራ ምላሽ አልሰጡም። በትግራይ ያለው ቀውስ አሁንም አሳሳቢ እንደሆነ ነገር ግን የተወሰኑ መሻሻሎች እንደሚታዩ፣ ይህንን አስፋፍቶ መቀጠልና ኢሰብዓዊ ጥሰቶች በገለልተኛ አካል መጣራታቸው አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ውይይት ከመካሄድ አንድ ቀን አስቀድሞ በተካሄደ ሌላ የፀጥታ ምክር ቤቱ ግልጽ ስብሰባ ግጭትን መሠረት ያደረጉ ፆታዊ ጥቃቶችን የተመለከተ ውይይት የተካሄደ ሲሆን፣ በዚህ ውይይትም በትግራይ ክልል ያለውን ጦርነት ተገን ያደረገና ሆን ተብሎ የሚፈጸም ፆታዊ ጥቃት መኖሩ ተወስቷል።ከኢትዮጵያ በተጨማሪም ተመሳሳይ ጥቃቶች በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በየመን፣ በማይናማርና በመሰል አገሮች በስፋት እየተፈጸመ መሆኑ ውይይት ተደርጎበታል።

የዚህ ውይይት ዋና ዓላማ ግጭትን ተገን አድርገው የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶችንና ፆታዊ ጥቃት መፈጸምን የውጊያ ሥልት አድርጎ እንደ መሣሪያ መጠቀምን የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ከማውገዝ ባለፈ፣ በወንጀሉ ፈጻሚዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል በተመድ የማዕቀብ ውሳኔ ማሳለፊያ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲካተት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ውይይትም በፀጥታ ምክር ቤቱ አባል አገሮች መካከል ስምምነት አልተደረሰበትም።

ምንጭ – ሪፖርተር

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *