በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ለቀናት የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የተቋቋመው የዕዝ ማዕከል በአንዳንድ የጸጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስን መከልከሉን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ፣ በተለይ በአማራ ክልል ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ ያለውን የሠላም መደፍረስ ለመቆጣጠር የዕዝ ማዕከል [ኮማንድ ፖስት] መመመስረቱን ገልጿል። የመከላከያ ሚኒስቴር በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን ወረዳዎች በተለይም ባለፉት ቀናት በአጣዬ ከተማና በአካባቢው በታጠቁ ኃይሎች በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ውድመት መድረሱን አመልክቷል።
በዚህም መሠረት የዕዝ ማዕከሉ ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ ባለው መስመር አዋሳኝ ወረዳዎች ከመንገድ ግራና ቀኝ ባለው 20 ኪሎ ሜትር ውስጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻል አሳውቋል። በተጨማሪም በአካባቢዎቹ መንገድ መዝጋት፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የግለሰብ መኖሪያና ንብረት ማውደም ወይም “ለዚህ ተግባር በተናጥልም ይሁን በቡድን መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ” መሆኑን ገልጿል።
ጥቃት በተፈጸመባቸውና የተቋቋመው የዕዝ ማዕከል መረጋጋትን ለማስፈን በሚንቀሳቀስባቸው በእነዚህ አካባቢዎች የተጣሉትን ክልከላዎች ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም አካል ላይ “ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት” ጨምሮ አስታውቋል። የመከላከያ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ እንዳለው ከተጠቀሱት በተጨማሪ “ቀጣይ በኮማንድ ፖስቱ ለኅብረተሰቡ የሚገለጹ ክልከላዎች” ሊኖሩ እንደሚችሉም አመልክቷል።
ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮ በሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኙት በአጣዬ፣ በካራቆሬ፣ በሸዋሮቢት፣ በማጀቴ፣ በአላላ፣ በአንጾኪያና የታጠቁ ናቸው በተባሉ ኃይሎች ለቀናት በተፈጸሙ ጥቃቶች ከባድ ጉዳት መድረሱን የክልሉ ባለሥልጣናት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። ቢቢሲ አርብና ቅዳሜ ያናገራቸው የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ጥቃቱ አስፈሪና በከባድ የጦር መሳሪያ የታገዘ መሆኑን ገልጸው በርካታ ሰዎች መሞታቸውን፣ ቤቶችና የእምነት ቤቶች መውደማቸውን ገልጸዋል።
ቅዳሜ ዕለት ጥቃቱ ከአጣዬ ባሻገር ወደ ሌሎች ከተሞች በመሸጋገሩ በአቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ወደ ደብረ ብርሃንና እና መሃል ሜዳ ለመሸሽ መገደዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የጸጥታ ኃላፊ አቶ አበራ መኮንን ለቢቢሲ እንደገለፁት ጥቃቱ የተፈፀመው በዞኑ በሚገኙ አምስት ወረዳዎች ውስጥ ሲሆን “በጣም ከፍተኛ” ቁጥር ያለው የታጠቀ ኃይል “ወረራ” መፈፀሙን ተናግረዋል።
ኃላፊ አቶ አበራ ቅዳሜ ዕለት “ችግሩ በአጠቃላይ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ” እንደነበር ገልጸው፤ በአካባቢው ከባድ ጉዳት ቢደርስም በወቅቱ ዋነኛ ሥራ አድርገው እየሰሩ ያሉት ሕዝቡን ከጉዳት መጠበቅና ማረጋጋት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። የአማራ ክልልና የዞኑ ባለሥልጣናት በተጠቀሱት ጥቃት በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ከባድ ጉዳት እንደ ደረሰ ከመናገር ውጪ በሰውና በንብረት ላይ ስለደረሰው ጥፋት ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
ጥቃቱን ለማስቆምና ለመቆጣጠር የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና የክልሉ ልዩ ኃይል በአካባቢዎቹ መሰማራታቸው የተነገረ ሲሆን የጸጥታ ኃይሉ ከባድ ውድመት የደረሰባትን የአጣዬ ከተማን ቅዳሜ ዕለት መቆጣጠሩ ተገልጿል። የአማራ ክልል የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት “በሰሜን ሸዋ ዞን በተፈጸመው ጥቃት ንጹሃን ተገድለዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሷል፣ ሀብትና ንብረት ወድሟል” ብለዋል።
የታጣቂ ኃይሉ ጥቃት ቀዳሚ ኢላማ በሆነችው በአጣዬ ከተማ ላይ የተፈጸመውን ከባድ ጥቃት ተከትሎ በስፍራው በሚገኘው ማረሚያ ቤት ውስጥ የነበሩ እስረኞች እንዲወጡ መደረጉም ተነግሯል። ለቀናት የዘለቀው በዚህ የታጣቂዎች ጥቃት ከአጣዬ አቅራቢያ የሚገኙትን ካራቆሬ፣ ማጀቴ፣ አንፆኪያ፣ መኮይና ሸዋሮቢትንም የነካ ሲሆን የእነዚህ ከተሞች ነዋሪም ከባድ ስጋት ውስጥ ወድቆ እንደነበር አቶ ሲሳይ ገልጸው ነበር።
የዞኑም የሆነ የክልሉ ባለሥልጣናት እንደተናገሩት በተፈጸመው ጥቃት የጸጥታ ኃይሎችን ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ ገልጸዋል። ነዋሪዎችና የክልሉ ባለሥልጣናት ለተፈጸመው ጥቃት “ኦነግ-ሸኔ” የተባለውን ቡድን ተጠያቂ አድርገዋል።
ይህ አሁን የተከሰተውና ለቀናት የዘለቀው ከባድ ጥቃት በዚህ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መከሰቱ ሲሆን፣ በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የበርካታ ሰዎችን ህልፈት ያስከተሉ ተመሳሳይ ጥቃቶች ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ማጋጠማቸው አይዘነጋም።
ከሦስት ሳምንት በፊት በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ውስጥ ተከስቶ በነበረ ተመሳሳይ አለመረጋጋት ከ300 መቶ በላይ ሰዎች መሞታቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋምን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።
ምንጭ – ቢቢሲ