የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ከታወቀ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የጽኑ ታማሚዎች ቁጥር ከአንድ ሺህ ማለፉን ተገለጸ።

የጤና ሚኒስቴርና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ሐሙስ ሚያዝያ 07/2013 ዓ.ም ባወጣው ዕለታዊ የወረርሽኙ መግለጫ ላይ እንዳመለከተው በበሽታው በጽኑ የታመሙ ሰዎች ቁጥር 1 ሺህ 031 መድረሱን አመልክቷል።

ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ከታወቀ ከአንድ ዓመት በኋላ ባሉት ሦስት ወራት፤ ማለትም ባለፉት ጥር፣ የካቲትና መጋቢት ውስጥ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ቀስ በቀስ እያሻቀበ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን የኢትዮጵያ የጤና ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ነበር።

የወረርሽኙ በማኅበረሰብ ደረጃ መስፋፋቱ አሳሳቢ ከመሆኑ በተጨማሪ በወረርሽኙ ሳቢያ በጽኑ የሚታመሙና ለሞት የሚዳረጉ ሰዎችም ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ከወራት በፊት ምርመራ ከሚያደርጉ ሰዎች መካከል ቫይረሱ ይገኝባቸው የነበሩት ከአምስት መቶ ብዙም ሳይርቅ በመቶዎቹ የሚቆተሩ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በየቀኑ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘው ይገኛሉ።

ከዚህ በተጨማሪም በበሽታው ክፉኛ ታመው የጽኑ ህሙማን ክትትልና ድጋፍን የሚሹ ሰዎች ቁጥር ከአምስት መቶ በታች ሆኖ ለረጅም ጊዜ የቆየ ሲሆን፤ ባለፉት ሁለት ወራት ግን አሃዙ ከአምስት መቶ አልፎ አሁን ከአንድ ሺህ በላይ ደርሷል። በተመሳሳይ በየቀኑ በበሽታው ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአስራዎቹ የሚቆጠር ሆኖ ለረጅም ጊዜ ቆይቶ አሁን ግን ከሃያዎቹ አስከ ሰላሳዎቹ የሚደርሱ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ እየተመዘገበ ነው።

በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የጽኑ ህሙማን ህክምናና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የሰው ሰራሽ መተንፈሻ መሳሪያና የኦክስጂን እጥረት እያጋጠመ መሆኑ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጾ የነበረ ሲሆን ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩ ችግሩን የበለጠ ያባብሰዋል።

ተቋሙ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ የባለሙያ ድጋፍና እንክብካቤ የሚሹ ሰዎች ቁጥር “የህክምና ማዕከላት ማስተናገድ ከሚችሉት አቅም በላይ” እየሆነ መምጣቱን ጨምሮ ገልጿል። በዚህም ሳቢያ በኮሮናቫይረስ በጽኑ ታምመው በህክምና ተቋማት ድጋፍ ለማግኘት ለሚመጡ ህሙማን አገልግሎት የሚውሉ “የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ (ቬንትሌተር) እና የኦክስጅን እጥረት እያጋጠመ ነው” ሲል ገልጿል።

የኮሮናቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን በተለይም ሳንባን የሚያጠቃ ሲሆን በበሽታው ክፉኛ ለተጠቁ ጽኑ ህሙማን ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መርጃ (ቬንትሌተር) እና ኦክስጂን ህይወታቸውን ለመታደግ ለሚደረገው ጥረት በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው። በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ በጽኑ የታመሙ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ በአሁኑ ወቅት በአገልግሎት ላይ የሚገኙት የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መርጃ ቬንትሌተሮች ቁጥር ከ500 ብዙም የበለጡ እንዳልሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል።

በየዕለቱ በበወረርሽኙ በጽኑ ታመው ድጋፍ የሚሹት ህሙማን ቁጥር በመቶዎች ከመቆጠር አልፎ በአሁኑ ጊዜ ከአንድ ሺህ በላይ መድረሱ የጤና ተቋማት ለህሙማኑ እንክብካቤና ድጋፍ ለመስጠት ችግር እየገጠማቸው መሆኑ ቀደም ሲል መገለጹ ይታወሳል። በተለይም በወረርሽኙ በጽኑ ታመው የቬንትሌተርና የኦክስጂን ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ህሙማን ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ የነፍስ አድን አገልግሎቱን መስጠት ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ከደረሰ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ሊያሻቅብ ይችላል።

በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ በየዕለቱ የሚመዘገበው በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የገለጸው ኢንስቲትዩቱ፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በወረርሽኙ ሳቢያ የጽኑ ህሙማን የህክምና አገልግሎት የሚፈልጉ ህሙማንና ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር “አስደንጋጭ በሆነ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል” ይገኛል ብሏል። ሐሙስ ዕለት በወጣው የበሽታው ዕለታዊ ሪፖርት መሠረትም 33 ሰዎች በኮቪድ-19 በሽታ ምክንያት መሞታቸው ተገልጿል።

በዕለቱ 8 ሺህ 878 ሰዎች ምርመራ ተደርጎላቸው 2 ሺህ 149ኙ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ቀደም ሲል በበሽታው ተይዘው ከነበሩት መካከል ደግሞ 1 ሺህ 288 አገግመዋል። አስካሁን በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ 236 ሺህ 554 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ሲረጋገጥ ከእነዚህ መካከል 3 ሺህ 285 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ 175 ሺህ 879 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው አገግመዋል።

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *