የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ቤተሰብ ከዘጠኝ ወራት በላይ ከቆየ ዝምታ በኋላ በወንጀል ምርመራው እና በፍርድ ሂደቱ ላይ አስተያየት ሰጥተዋል።

ታናሽ ወንድሙ ሲሳይ ሁንዴሳ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ “ላለፉት ዘጠኝ ወራት ምንም ካለመናገር የተቆጠብነው ማንኛውም አካል ግድያውን ለፖለቲካ ትርፍ እንዳይጠቀምበት በማሰብ ነበር” ይላል። ከሃጫሉ ግድያ ጋር ተያይዞ ያለው የወንጀል ምርመራ እና አሁን ያለው የፍርድ ሂደት “የፖለቲካ ጨዋታ ነው። ቤተሰብ ይህንን ጠንቅቆ ያውቃል” ይላል ሲሳይ። ከዘጠኝ ወራት በላይ ያስቆጠረው የምርመራ እና የፍርድ ቤት ሂደት ችሎት እንዳይገቡ መከልከልን ጨምሮ የተለያዩ መከልከሎች ሲያጋጥማቸው እንደነበር ይናገራል።

ጉዳዩን የያዙት የፌደራሉን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በበኩላቸው የወንጀል ምርመራውም ሆነ የፍርድ ቤት ሂደቱ የአገሪቱን ሕግ መሰረት ባደረገ እና በገለልተኝነት እየተካሄደ መሆኑን ይናገራሉ። አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ባለፈው ዓመት ሰኔ 22/2012 ምሽት ላይ አዲስ አበባ ውስጥ መኪናው ውስጥ ነበር የተገደለው።

ግድያውን ተከትሎ አራት ሰዎች ተጠርጥረው የተያዙ ሲሆን ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸውም በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል። የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራተኛ ተከሳሽ ላምሮት ከማል፣ በነጻ በእንድትሰናበት ሦስተኛ ተከሳሽ አብዲ አለማየሁ በ10 ሺህ ብር የዋስ መብቱ ተጠብቆ እንዲወጣ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ሁለተኛው ተከሳሽ ከበደ ገመቹ ከአርቲስቱ ግድያ ጋር በቀጥታ ተሳትፎ እንዳለው የሚያረጋግጥ መረጃ አልተገኘም ያለው ፍርድ ቤቱ ወንጀል አይቶ ለፖሊስ አለመናገር በሚል ክስ ራሱን እንዲከላከል ውሳኔ ሰጥቷል። አንደኛ ተከሳሽ ጥላዬ ያሚ በቀጥታ የሃጫሉ ግድያ መፈፀሙን የሚያረጋግጥ በቂ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ስለተገኘ ራሱን እንዲከላከል ብሎ ፍርድ ቤቱ መወሰኑ ይታወቃል።

ቤተሰብ እና ቃቤ ሕግ ምን ይላ?

ከመጀመሪያው አንስቶ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ “ገለልተኛ በሆነ ሦስተኛ አካል” እንዲመረመር ቤተሰብ ፍላጎት እንደነበረው የሃጫሉ ሁንዴሳ ወንድም ሲሳይ ሁንዴሳ ተናግሯል። ነገር ግን ይህንን ፍላጎታቸውን የሚያመለክቱበት አካል እንዳልነበረ እና መንገዱም ዝግ እንደነበር ይናገራል። የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቃል አቀባይ አቶ አወል ሱልጣን ለዚህ የቤተሰቡ ቅሬታ ምላሽ ሲሰጡ፣ አገሪቱ ካላት ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ ውጪ ይህንን ማጣራት የሚችል ሌላ ገለልተኛ አካል የለም ይላሉ።

በእርግጥ ውስብስብ የሆኑ እና ከአገሪቱ የመመርመር አቅም በላይ የሆኑ ወንጀሎች ሲያጋጥሙ ሌሎች አቅሙ ያላቸው ወዳጅ አገራትን መጋበዝ እና ድጋፍ እንዲያደርጉ ማድረግ ይቻላል ሲሉ ያክላሉ። ነገር ግን በዚህ ምርመራ ይሄ የሚያስፈልግበት አግባብ የለም ብለዋል። “የሃጫሉ ቤተሰብ ይህንን እንደ ጥያቄ ማንሳታቸው ስህተት ላይሆን ይችላል” የሚሉት አቶ አወል ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል የሕግ አግብ እንደሌለ ግን ያስረዳሉ።

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ወንጀል ምርመራ ለየት ባለ መልኩ ፈጣንና ጠንካራ የሆነ ምርመራ መደረጉ ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም የያሉት የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቃል አቀባይ አቶ አወል ሱልጣን፤ የምርመራ ሂደቱን የሃጫሉን ቤተሰብ ጨምሮ ለምርመራው ያስፈልጋሉ የተባሉ ሰዎችን ሁሉ ያሳተፈ እንደነበር ይናገራሉ። “በወንጀል ምርመራ ሂደቱም ሆነ በፍርድ ቤት የክርክር ሂደት ከሃጫሉ ቤተሰብ ጋር የነበረን የሥራ ግንኙነት ጠንካራ ነበር” ብለዋል።

“የምርመራ ሂደቱ ጠንካራ እንደነበር ሲያስረዱ ከአዲስ አበባ ፖሊስ በወንጀል ምርመራ ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው ባለሙያዎች፣ ከጠቅላይ አዐቃቤ ሕግ ደግሞ የወንጀል ምርመራ ዳይሬክተሮችን ሳይቀር ያሳተፈ ቡድን ተዋቅሮ ነው ምርመራው የተካሄደው። “በዚህም ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀርበው ወንጀሉን መፈጸማችን የሚያሳይ እና ፍርድ ቤቱንም ሊያሳምን የሚችል ማስረጃ ቀርቦባቸው ወንጀሉን ይከላከሉ መባሉ የተደረገው ምርመራ ጠንካራ እንደነበር ማሳያ ነው” ይላሉ።

ከሃጫሉ ጋር በአንድ ቤት ይኖር እንደነበር የሚናገረው ሲሳይ፤ ሃጫሉ በተገደለበት ምሽት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ እስር ቤት እንዳደረ፣ እናም ጠዋት ላይ እንደተለቀቀ ለቢቢሲ ተናግሯል። ከተለቀቀ በኋላ የዚያን ዕለት ምሽት ምን እንደተፈፀመ ያየውን የጠየቀው አካል እንደሌለ፣ በአጠቃላይም የወንጀል ምርመራው ሂደት ቤተሰብን በበቂ ሀኔታ ያሳተፈ እንዳልነበር እና ትክክለኛ የሆነ ምርመራ ተደርጓል ብሎ ቤተሰቡ እንደማያምን ሲሳይ ጨምሮ ያስረዳል።

“ለምሳሌ፣ ሙሉ መረጃ ያለበት እና ሃጫሉ ከሰዎች ጋር ለመገናኘት የሚጠቀምበት የእጅ ስልኩ፣ በእነርሱ [መርማሪዎች] እጅ ነው ያለው። ኤግዚቢት ነው ብለው ሲመልሱልን 480 ሺህ ብር እና ሌላ ተለዋጭ የሚጠቀምበትን ስልክ ሰጥተውናል። “ነገር ግን ሙሉ መረጃ ያለበት የእጅ ስልኩ እና ሽጉጡ አልተመለሰልንም። ይህ የእጅ ስልኩ አለመመለስ ያለ ምክንያት አይደለም ብለን ነው የምናስበው።”

ቤተሰብ አርቲስት ሃጫሉ ተገድሏል በተባለበት ስፍራ መገደሉን ጥርጣሬ እንዳለውና አሁን ባለው ሂደት “ፍትህ እናገኛለን ብለን አናምንም” ብሏል። የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቃል አቀባይ በበኩላቸው የእጅ ስልኩና ሽጉጡን እንዲሁም ሌሎች መኪና ውስጥ የተገኙ መሳሪያዎች በሙሉ በሚገባ መመርመራቸውንም ይናገራሉ። ቤተሰብ አልተመለሰልንም በማለት ያቀረበውን ስልክ እና ሽጉጥ በተመለከተ በፍርድ ቤት የክርክር ሂደት ውስጥ አስፈላጊ ናቸው ተብሎ ከታመነባቸው እቃዎች ውጪ በሙሉ ለቤተብ መመለሱን ይናገራሉ።

የሃጫሉ ወንድም ቅሬታውን ለቢቢሲ ሲገልጽ “እኛ ተስፋ የቆረጥነው በነጋታው፣ እርሷ [አራተኛ ተከሳሽ ላምሮት ከማል] መክሰስ አያስፈልግም የምታውቀውን ነገር ከነገረችን ልትለቀቅ ትችላለች ተብሎ መግለጫ የተሰጠ ጊዜ ነው” ሲልም ያክላል። ሲሳይ እንደሚለው ከሆነ የሃጫሉ ቤተሰብ አራተኛ ተከሳሽ የሆነችው ላምሮት ከማል ከአርቲስቱ ግድያ ላይ ተሳትፎ አላት ብሎ ያምናል።

ነገረ ግን “እርሷ ተጠያቂ እንዳትሆን ድራማ ሲሰራ ነበር” ይላል። “ሂደቱ ድራማ ነው፤ በጣም አስቀያሚ ድራማ፣ ደካማ በሆኑ ሰዎች የተጻፈ፣ ደካማ የሆኑ ሰዎች የሚተውኑበት፣ እኛ ተጎጂዎቹ ቀርቶ ሌላ ከውጪ ተመልካች የማይመስል ነገር ብሎ የሚንቀው ድራማ ነው” ይላል። “በአጠቃላይ አሁን ባለው ሂደት ሄዶ ሄዶ አንደኛው ተከሳሽ ላይ አላኮ ድራማውን እርሱ ላይ ለመጨረስ ነው እየተሄደ ያለው።”

በፍርድ ቤት በኩልም ገለልተኛ ሆኖ ጉዳዩን እያየ እንደሆነ ቤተሰብ እምነት እንደሌለው በመጥቀስ፤ ቦታ ሞልቷል ተብሎ ከችሎት መከልከልን ጨምሮ “ሰው እውነቱን ከመጠየቅ ወደ ኋላ እንዲል እንዲፈራ ብዙ ነገር ተደርጓል” ይላል ሲሳይ። “ሰው አይኑ እያየ ድራማ ከሚሰራበት ተትቷል ወይም ቀርቷል ቢባል ይሻላል” የሚለው ሲሳይ “ፍርድ ቤት ከጉዳዩ ላይ እጁን ያውጣ” ሲል ይጠይቃል።

“ይህ ማለት ግን ሙሉ ለሙሉ ጉዳዩን ጥሎ ይውጣ ሳይሆን አሁን እየሄደ ካለው የፖለቲካ ጨዋታ ይውጣ፣ ጉዳዩ ገለልተኛ በሆነ አካል ተጣርቶ ወንጀሉ አንድ በአንድ ከተመረመረ በኋላ ፍርድ ቤትም ገለልተኛ ሆኖ ይይልን” ማለት እንደሆነ አብራርቷል። የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቃል አቀባይ በበኩላቸው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ተከሳሾች እንዲከላከሉ የተባለበት ወንጀል አንቀጽ መቀየሩን በተመለከተ አሁንም በፍርድ ሂደት ላይ ያለ ስለሆነ ምናመልባት ውሳኔ ሲያገኝ ይግባኝ የሚያስጠይቅ ከሆነ ያኔ የሚገለጽ መሆኑን አመልክተዋል።

አራተኛ ተከሳሽ ላምሮት ከማል በነጻ እንድትሰናበት ፍርድ ቤት መወሰኑን በተመለከተ ጠቅላይ ዐቃቤ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ ጉዳዩ በቀጠሮ ተይዞ እንዳለም ተናግረዋል። እስከዚያ ድረስ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ትፈታ ብሎ ስለወሰነ እርሱ ውሳኔ ታግዶ እንዲቆይ ተደርጎ፣ ተከሳሿ አሁንም በፖሊስ ቁጥጥጥር ስር እንደምትገኝ አቶ አወል አስረድተዋል።

ተከሳሿ መጀመሪያ ላይ ስለግድያው የምታውቀውን ከተናገረች እርሷን እንደምስክር በመቁጠር ዋነኛ ወንጀል ፈጻሚዎች ላይ ክስ የመመስረት የተለመደ አሰራር እንደሆነ እና አቃቤ ሕግም በዚሁ መሰረት መግለጫ ሰጥቶ እንደነበር ይናገራሉ። ነገር ግን በምርመራ ሂደት እርሷ ወንጀሉ ውስጥ ተሳትፎ እንዳላት የሚያሳዩ መረጃዎች ስላገኘን እርሷንም ተከሳሽ አድርገን ፍርድ ቤት አቅርበናታል ይላሉ አቶ አወል።

ስለዚህም እርሷ እንዳትከሰስ ለማድረግ ወይንም እርሷ ነጻ እንድትወጣ ዐቃቤ ሕግ የሚሰራበት ምንም አግባብ አለመኖሩን ይናገራሉ። በዚህ ዘገባ ላይ የላምሮት ከማልን ወይንም የጠበቃዋን ሃሳብ ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ነገር ግን በማንኛውም ወቅት ምላሻቸውን ለማካተት ዝግጁ ነን።

ፍርድ ቤቱ ምን ይላል?

የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ እያየ ያለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ብርሃነ መስቀል ዋቅጋሪ ቤተሰብ በሚያነሳቸው ቅሬታዎችና ትችቶች ዙሪያ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል። አቶ ብርሃነመስቀል እንደሚሉት ፍርድ ቤቱም ሆነ ጉዳዩን እየተከታተሉ ያሉ ዳኞች ከየትኛውም ወገን ገለልተኛ ሆነው ጉዳዩን እያዩ እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን “በፍትህ ሥርዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ብቻውን አይደለም የሚሰራው፤ ፖሊስ ይመረምራል፣ ዐቃቤ ሕግ ክስ ይመሰርታል ከዚያ በኋላ ነው ፍርድ ቤት የሚመጣው” ይላሉ።

“ከመጀመሪያ ጀምሮ ፖሊስ እንዴት ነው የመረመረው፤ አቃቤ ሕግ በምን አግባብ ነው ክስ የመሰረተው፤ እንዴትስ ነው ክስ የመሰረተው የሚሉ ነገሮች የመጨረሻ ውጤቱ ፍርድ ቤት ላይ ስለሆነ የሚንፀባረቀው ትችቱ ፍርድ ቤት ላይ ይበዛል” ይላሉ። ነገር ግን በፍርድ ቤት በኩል “ዳኞች ነጻና ገለልተኛ ሆነው ሕግና ሕግን ብቻ መሰረት ባደረገ፣ በጥሩ ሞራል እና መንፈስ ነው ሥራቸውን እየሰሩ ያሉት” ይላሉ።

አራተኛ ተከሳሽ ላምሮት መለቀቋን ተከትሎ ቤተሰብ የሚያነሳውን ቅሬታ በተመለከተ “ፍርድ ቤት የቀረበለትን ነገር ነው የሚመዝነው፤ ሚዛን የሚደፋ ነገር ከቀረበለት ፍርድ ቤት ምን ሊያደረግ ይችላል?” የአርቲስት ሃጫሉ ግድያን የፍርድ ቤት ሂደት በተመለከተ ለፍርድ ቤቱ የቀረበ ምንም ዓይነት ቅሬታ እንደሌለ “ነገር ግን ቅሬታ ካለ ነገም ከነገ ወዲያም በራችን ክፍት ነው” ይላሉ አቶ ብርሃነ መስቀል።

ቤተሰብ በገለልተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩ እንዲታይልን ሲሉ የጠየቁትን በማስመልከት “ፍርድ ቤት አንድ ነው ሌላ አዲስ የሚቆም ገለልተኛ ፍርድ ቤት የለም ሊኖርም አይችልም፤ ባለው ፍርድ ቤት ላይ እምነት ማጣት የለብንም” ይላሉ።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *