ችግሮች ቢኖሩም በሰላማዊና በሠለጠነ መንገድ እንዲፈቱ ጠይቃለች

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸውን እያጡ ያሉ ንፁኃን ዜጎች ጉዳይ በእጅጉ እንዳሳሰባት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን (ቤተ ክህነት) አስታወቀች፡፡ መንግሥትና በአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አካላት ሁሉ ለአገርና ለዜጎች ደኅንነት ቅድሚያ እንዲሰጡም ጠይቃለች፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ሌሎች ብፁዓን አባቶች በተገኙበት ዓርብ ሚያዝያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ መንግሥትና በአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አካላት ሁሉ ለአገር ሰላም፣ ሉዓላዊነት፣ እንዲሁም ለዜጎች የሕይወት ዋስትና መረጋገጥ ከምንም በፊት ቅድሚያ ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ፣ የሲዳማና የጌዴኦ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እንደገለጸት፣ ከምንም በላይ የአገርና የዜጎች ደኅንነት ጉዳይ መቅደም አለበት፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነትና የዘለዓለማዊ ሕይወት መማፀኛ በመሆኗ ለዜጎች መልካም አኗኗር፣ ለአገር ሰላምና አንድነት፣ በፀሎት፣ በምህላ፣ በትምህርትና በማኅበራዊ ተልዕኮ የድርሻዋን እየተወጣች እንደምትገኝ ተገልጿል። ዜጎች ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ በሚያጋጥማቸው ወቅትም ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ሰብዓዊ ዕርዳታ፣ ትምህርትና መንፈሳዊ ማፅናኛ እያደረገች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በሁሉም አካባቢዎች ንብረት ለወደመባቸው፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ለተፈናቀሉና ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ሁሉ አቅም የፈቀደውን፣ ሃይማኖታዊና ወገናዊ ድጋፍ እንዲደረግም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ ሥጋት እየፈጠረ በመምጣቱ፣ ካህናትና ምዕመናኑ፣ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በሌሎች ማኅበራዊ ግንኙነቶች አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።

‹‹በሰው ልጅ ላይ አሰቃቂ መከራን ማድረስ ውጤቱ ከድርጊቱ የባሰ መሆኑን በመገንዘብ፣ የሰው ሕይወት ተከፍሎ የሚሳካ ማንኛውም ምድራዊ ፍላጎትና ዓላማ ጠባሳው ለትውልድ ነውና በአስተዋይ አዕምሮ ለአገራችንና ለሕዝባችን በማሰብ፣ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የሰላም ጥሪያችንን እናስተላለፍለን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹መንግሥትና በአገር ጉዳይ ያገባናል የምትሉ አካላት በሙሉ ለአገር ሰላምና ሉዓላዊነት፣ ለሕዝብ አንድነትና መተሳሰብ፣ ለዜጎች ሁለንተናዊ ደኅንነትና የሕይወት ዋስትና ቅድሚያ መስጠት አለባችሁ፤›› ብለዋል።

ችግሮች ቢኖሩም እንኳን በሰላማዊና በሠለጠነ መንገድ እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚገባም አክለዋል።

ቀጣይ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከቅስቀሳው እስከ ፍፃሜ ያለውን ሒደት ሰላማዊ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ለአገራዊ ሰላም፣ ልማትና ዕድገት፣ ለዜጎች ሁለንተናዊ ደኅንነት የበኩሏን ኃላፊነት እየተወጣች ሲሆን በቀጣይነትም አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *