ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከመጀመሯ በፊት መረጃ ለመለዋወጥ እንዲቻል ግብጽና ሱዳን ባለሙያዎችን እንዲሰይሙ ያቀረበችው ጥሪ አገራቱ ሳይቀበሉት እንደቀረ ተዘገበ።

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በያዘችው መርሃ ግብር መሠረት ሁለተኛውን ዙር የግድቡን የውሃ ሙሌት በመጪው የክረምት ወር እንደምታካሂድ ገልጻ ነው አገራቱን ባለሙያዎቻቸውን እንዲያሳውቁ የጠየቀችው። ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ እየገነባቸው ያለውን ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫን በተመለከተ አስገዳጅ ሕጋዊ ስምምነት ላይ ሳይደረስ የውሃ ሙሌት እንዳይካሄድ አጥብቀው ሲወተውቱ መቆየታቸው ይታወቃል።

ኢትዮጵያ የሱዳንና የግብጽን ጥያቄ በተደጋጋሚ ውድቅ ያደረገችው ሲሆን ግድቡን ውሃ እንዲይዝ የማድረጉ ሥራ በአገራቱ መካከል የሚደረገው ድርድር እየተካሄደም ቢሆን የማይቀር እንደሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።

ባለፈው ሳምንት የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር በሆነችው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰብሳቢነት ኪንሻሳ ላይ የተካሄደው ድርድር ያለ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ ኢትዮጵያ ስለሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ከሱዳንና ግብጽ ጋር መረጃ ለመለዋወጥ እንዲያመች ባለሙያዎቻቸውን እንዲያሳውቁ ጠይቃለች።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ከካይሮ እንደዘገበው ግብጽና ሱዳን ከኢትዮጵያ የቀረበላቸውን ጥሪ ተከትሎ አገራቱ ሲያቀረቡ የቆየው ሕጋዊና አሳሪ ስምምነት ላይ ሳይደረስ መረጃ ለመለዋወጥ የሚያግዙ ባለሙያዎችን እንዲያሳውቁ የቀረበውን ጥያቄ አልተቀበሉትም።

የሱዳን ዜና ወኪል የአገሪቱ የውሃ ሚኒስቴር መግለጫን ጠቅሶ እንደዘገበው በግድቡ ሙሌት ላይ የመረጃ ልውውጡ አስፈላጊ አካሄድ እንደሆነ ጠቅሶ ነገር ግን ከስምምነት ላይ ከተደረሰው ክፍል ውስጥ በተወሰኑት ላይ የሚያተኩር መሆኑ ጥርጣሬን እንደፈጠረ ገልጿል።

አገራቱ ኢትዮጵያ አከናውነዋለሁ ያለችው ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተመለከተ ስምምነት ሳይደረስ እንዳይካሄድ በተደጋጋሚ ተቃውሟቸውን ቢያሰሙም የማይቀር መሆኑን በመገንዘብ ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑ ታውቋል።

በሱዳን በኩል 600 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የሚይዘውን የጀበል አወልያ የውሃ ማከማቻ ግድብን፣ ለመጠጥ ውሃና ለግብርና የሚያስፈልጋትን ውሃ መጠን ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር ሙሌት ከመጀመሯ በፊት እንደምትሞላ ሱና ዘግቧል።

የግብጽ የመስኖ ሚኒስትርም ለአንድ የአገሪቱ ቴሌቪዥን ኢትዮጵያ የምታካሂደውን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በግዙፉ የአሰዋን ግድብ ውሃ እንደሚያካክሱት ገልጸው፤ ዋና ስጋታቸው የድርቅ ወቅት እንደሚሆን ማመልከታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የሆኑት ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ ኢንጂ.) ኢትዮጵያ ወደ መጠናቀቁ የተቃረበውን የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማታራዝመውና ለዚህም የሚያበቃ አሰራርና ምክንያትም እንደሌለ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም መጋቢት ወር ላይ ለአገሪቱ ምክር ቤት ላይ እንዳስረዱት፤ ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ አሞላል በተመለከተ ከድርድሩ ማብቃት በኋላ ይከናወን የሚባል ከሆነ አገሪቱን “በዓመት አንድ ቢሊየን ዶላር ያሳጣታል” በማለት የውሃ ሙሌቱን ማዘግየት እንደማይቻል አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሌት ያከናወነችው ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ ከሱዳንና ግብጽ እየቀረበ በነበረበት ጊዜ መሆኑ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ አምስት ቢሊየን የሚጠጋ ዶላር አውጥታ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሊጠናቀቅ 20 በመቶ ያህል የቀረው ሲሆን፤ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ካሉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ሁሉ ቀዳሚው ይሆናል ተብሏል።

ግድቡ ተጠናቅቆ ሙሉ ለሙሉ ሥራውን ሲጀምር ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም አለው።

ግድቡ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ያደረገ ሲሆን ሁለተኛውን ዙር ደግሞ በመጪው ክረምት ሐምሌና ነሐሴ እንዲሁም አስፈላጊ ከሆነ በመስከረም ወር ላይ እንደሚከናወን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።

ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው የግድቡ የግንባታ ሥራ መከናወኑ የተነገረ ሲሆን በመጪው ዓመትም በተወሰነ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል።

ግብጽና ሱዳን ግድቡ የውሃ አቅርቦታችንን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል በሚል ከግንባታው መጀመር አንስቶ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቢቆዩም፤ ከግማሽ በላይ ለሚሆነው ሕዝቧና እያደገ ላለው የኢንዱስትሪ ዘርፏ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ ዋነኛ ግቧ አድርጋ የተሳችው ኢትዮጵያ በግንባታውና ቀጥላ ወደ ማጠናቀቁ ተቃርባለች።

የግብጽና የሱዳን መንግሥታት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተለያዩ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ግድብ ሳቢያ አገሮቻቸው ከወንዙ በሚያገኙት የውሃ መጠን ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው ስጋታቸውን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን የምትጠቀመው ውሃውን በግዛቷ ውስጥ ለሚያስቀሩ ፕሮጀክቶች እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ብታስረዳም ሱዳን በተለይም ግብጽ የትኛውም አይነት በውሃው ላይ የሚከናወን ሥራ የእነርሱን ስምምነት ሳያገኝ መካሄድ እንደሌለበት ሲገልጹ ቆይተዋል።

ግንባታው ከተጀመረ አስረኛ ዓመቱን የያዘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና ቀጣይ የሥራ ሂደትን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል ለዓመታት ሲካሄድ የቆየው ድርድር ውጤት ሳያስገኝ እስካሁን ዘልቋል።

የአፍሪካ ሕብረት የሚያሸማግለው ይህ ድርድር ቀደም ሲል በአዲስ አበባ፣ በካርቱም፣ በካይሮና በዋሽንግተን ላይ የሦስቱ አገራት ልዑካን ተገናኝተው ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ በበይነ መረብ አማካይነት ቀጥሎ ነበር።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በታላቁ የሕዳሴው ግድብ የውሃ አሞላልና ቀጣይ ሂደት ላይ ለዓመታት ሲያካሂዱት የነበረው ድርድር ቀጣይ ባለፈው ሳምንት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋና ከተማ ላይ ለሦስት ቀናት ተካሂዶ ያለውጤት ከተጠናቀቀ ከቀናት በኋላ ነበር ኢትዮጵያ አገራቱ ባለሙያዎቻቸውን እንዲሰይሙ ጥያቄ ያቀረበችው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅ ከሚጠበቅበት በታች እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ፣ የግብፅና የሱዳን መንግሥታት የተበዳይነት መንፈስን ለዓለም በማስረዳት በኢትዮጵያ ላይ ብልጫ እያሳዩ እንደሆነ ምሁራን ገለጹ፡፡

ከተጀመረ አሥር ዓመታትን ያስቆጠረው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ አፈጻጸሙ ከ79 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ ሱዳንና ግብፅ የግድቡን የውኃ ሙሌት አስመልክቶ አሳሪ የሆነ ስምምነት ከኢትዮጵያ ጋር መፈራረም ይፈልጋሉ፡፡

በዚህም ለበርካታ ጊዜያት የተካሄዱ ድርድሮችና ውይይቶች፣ በአሜሪካ፣ በአፍሪካ ኅብረትና በሌሎች ወገኖች አደራዳሪነት እየተጀመሩ ያለ ስምምነትና መቋጫ መጠናቀቅ አየተለመዱ መጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የመጀመርያውን የውኃ ሙሌት ባለፈው 2012 ዓ.ም. የጀመረች ሲሆን በተያዘው ዓመትም ሙሌቱን ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኗንና በታችኛው ተፋሰስ አገሮች በተለይም በሱዳንም ሆነ በግብፅ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንደማያሳድር በተደጋጋሚ ስትናገር ትደመጣለች፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት ታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ መረጃ በመስጠትና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የግንባታውንና የውኃ ሙሌቱን ሒደት አስመልክቶ እየተሄደበት ያለው መረጃን የመስጠት ዝንባሌ ከግብፅና የሱዳን መንግሥታት ጩኸት ጋር ሲነጻጻር ተመጣጣኝ አለመሆኑንና ይባሱንም ኢትዮጵያ እንደ በዳይና እምቢተኛ አገር የማስመሰል እንቅስቃሴ ሲያልፍም የማስፈራሪያ ዛቻ እያስተናገደች እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና ኤስያ ጥናት ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተፈራ ለሪፖርተር አንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ በኩል እየታየ ያለው የመረጃ ክፍተት በተለይም በግድቡ ግንባታ ዙሪያ በቂ መረጃ አለመገኘት፣ የግብፅና የሱዳን ፉከራና ለቅሶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ‹‹እውነትም ተበድለዋል›› የሚል ዓይነት አዝማሚያ እየያዘና በኢትዮጵያ በኩል እውነታው ምን እንደሚመስል ለማሳወቅ እየተሄደበት ያለው ጥረት ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ በኩል እየታየ ያለው ሕዝባዊ መነሳሳትና በግለሰብ ደረጃ ከሚደረገው አስተዋጽኦ አንጻር፣ መንግሥት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል በማስተባበር በተለይም የዳያስፖራውንና በውጭ አገር ኢትዮጵያን የሚወክሉ ኤምባሲዎችን የጉዳዩን ግልጽነት ለማሳወቅ የተሄደበት ጉዞ ደካማ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ሳሙኤል፡፡

ግድቡ ከተጀመረ ምንም እንኳ ከአሥር ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ በመረጃ አቅርቦትና የግንባታውን ሒደት እየተከታተለ ለሚመለከተው አካል በተለይም የጉዳዩ ጥልቀት በግልፅ ላልገባቸው የዓለም ማኅበረሰብ ክፍሎች የበሰለ መረጃ ለማድረስ እየተሄደበት ያለው መንገድ አጥጋቢ አለመሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

አሁንም ቢሆን ግድቡ ተጠናቆና ኢትዮጵያ ኃይል ማመንጨት ብትጀምር ተቋማዊ የሆነና አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ማቅረብ የሚችል ተቋም እስካልተፈጠረ ድረስ፣ ከግብፅና ሱዳን በኩል የሚመጡ ቅሬታዎች ወይም ለዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያደርጉት ጩኸት ቀጣይነት እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ምንም ውኃ ያላስቀረ የግድብ ግንባታ ላይ ‹‹ስምምነትን መቀበል አለባችሁ›› ብሎ ተፅዕኖ ማሳደር፣ የዓለም ሕዝብ ላይ ትልቅ ሚና ሲፈጥሩ ማየት እንደተበደለና እንደተጎዳ መምሰል በጣም አሳዛኝ ከመሆኑም በላይ፣ በኢትዮጵያ በኩል ያለው ደካማ የመረጃ አሰጣጥና የመረጃ ክፍተት እንደሆነ አመላካች መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት አቋሙን በቶሎ ማሳወቅ ለሚጽፉና ለሚናገሩ ሰዎች የመረጃ ምንጭ እንዲኖር ማድረግ የአገር ጉዳይ በመሆኑ አሁንም በትኩረት ሊሠራባቸው የሚችሉ ጉዳዮች እንደሆኑ ረዳት ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ሕግ መምህር አቶ ዘውዱ እንደገለጹት፣ መንገሻ ከግብፅ በኩል እየተሰነዘረ ያለው ዛቻና ማስፈራሪያ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ዝም ተብሎ ሊታለፍ የሚገባው ጉዳይ አለመሆኑንና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የኃይል ማስፈራሪያ ማድረግ የተከለከለ መሆኑንና አላስፈላጊ የሆነ ንግግር መደረጉን ማሳወቅና ወደ ሰላማዊ የንግግር መድረክ እንዲመጡ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ግድብ ሳቢያ አገራቸው የምታገኘው የውኃ መጠን ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር ከሆነ፣ ‹‹የከፋ አካባቢየዊ ችግር ይከሰታል›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ዝምታ በመጠቀም ግብፅና ሱዳን ሲፈልጉ የውስጥ  ኃይሎችን በመደገፍ ማሸበርና ሰላም መንሳት፣ ወይም ከዚያም ሲያልፍ በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ እየሄዱበት ያለው ጫና የመፍጠር እንቅስቃሴ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል ግን ዝምታን በመምረጥ አስፈላጊውን መልስ ያለመስጠት ሁኔታ እየታየ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ የቤት ሥራው የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንጂ የመንግሥት የግል ኃላፊነት ብቻ እንዳልሆም ተናግረዋል፡፡

መንግሥት  በተለይም የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ከግብፅና ሱዳን በኩል እየተነሳ ያለው አልሸነፍም ባይነት አንዲመከት የግድቡ ባለቤት የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በቂ መረጃ እንዲኖረውና አልፈው ስለጉዳዩ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ለማስረዳት እንዲችሉ አድርጎ አቅማቸውን መገንባት ይገባል ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አለመግባባትና የሰላም ችግር በመጠቀም፣ ግድቡ እንዳይሞላ እንቅፋት መፍጠር፣ እውነተኛና ሐቀኛ በመምሰል አገራትን በመማፀን ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ስምምነትን ተቀብላ ለግብፅ ይሁንታ እንድትሰጥ እየሄዱበት ያለው መንገድ፣ በኢትዮጵያ በኩል ያለው መረጃን ያለመስጠትና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ቅስቀሳ ያለማድረግ፣ እንዲሁም የማሳመንና የማሳወቅ ሥራ በበቂ ሁኔታ ባለመሠራቱ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

ዓባይን መጠቀም ማለት በኢትዮጵያ ሕዝብ የመኖርና ያለመኖር ወይም የህልውና ጉዳይ ነው›› የሚሉት ደግሞ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁሩ ዓለማየሁ እርቅይሁን (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በመሆኑም እያደገ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር ፍላጎት ለማርካት ኢትዮጵያ አስፈላጊ ከሚባሉት ትላልቅ መሠረተ ልማቶች ውስጥ የሚመደበው ታላቁ የህዳሴ ግድብ መጨረስና ማጠናቀቅ ግዴታ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት ከግብፅም ሆነ ከሱዳን በኩል ሊሰነዘሩ የሚችሉ ማናቸውም የቃላት ወይም ሌሎች ማስፈራሪያና ዛቻ ለመመለስ በበቂ መረጃና  ጥናት ተደግፎ መልስ ለመስጠት መዘጋጀት አለበት በማለት የታሪክ ምሁሩ ይገልጻሉ፡፡

በዚህ ረገድ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ልዩነት ቢኖራቸውም እንኳ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከመንግሥት ጋር በእኩል መቆምና መልስ ለመስጠት መዘጋጀት እንዳለባቸው አክለው ይናገራሉ፡፡

በተጨማሪም አገር ውስጥ የሚኖር ምንም ዓይነት ልዩነት ቢኖርም ከዚህኛው አገራዊ ፕሮጀክት የማይበልጥ በመሆኑ ልዩነቶችን በመተዉ ሁሉም አካል እኩል ተሰላፊ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *