ፌስቡክ መቀመጫቸውን በግብጽ አድርገው በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ መልዕክት የሚያስተላልፉ ገፆችን መዝጋቱን አስታወቀ።

ኩባንያው እነዚህ ገጾች የተዘጉበትን ምክንያት ሲገልፅ የውጭ አገራት ጉዳይ ውስጥ አለመግባት የሚለውን ፖሊሲ በመጣሳቸው እንዲሁም እውነተኛ ያልሆነ ዘመቻ ውስጥ በመሳተፋቸው እንደሆነ ገልጿል።

ፌስቡክ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ላይ “ግብጽ ተቀምጠው በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በቱርክ ላይ ያነጣጠሩ 17 የፌስቡክ አካውንቶችን፣ ስድስት ገጾችን እንዲሁም ሦስት የኢንስታግራም አካውንቶች አጥፍተናል” ብሏል።

ድርጅቱ ይህንን ያስታወቀው፣ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር ላይ የተቀናጀ ሐሰተኛ ባህሪያት በሚል ባወጣው ሪፖርት ላይ ነው።

ፌስቡክ በዚህ ሪፖርቱ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ በመጋቢት ወር ውስጥ የደረሰበትን ግኝት ይፋ አድርጓል።

ግብጽ መቀመጫቸውን አድርገው ኢትዮጵያ ላሉ ተከታዮች መልዕክት ከሚያስተላልፉ ገፆች መካከል አንደኛው “በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ትችት የሚያቀርብ” እንደነበር ፌስቡክ አስታውቋል።

እነዚህ ገጾች እና አካውንቶች ራሳቸውን ለማስተዋወቅ 525 ሺህ ዶላር ወይንም 21 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ማውጣታቸውንም ገልጿል።

ኢትዮጰያ፣ ግብጽ እና ሱዳን ከሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ ውጥረት ውስጥ መሆናቸው ይታወቃል።

ከቀናት በፊት ሦስቱ አገራት በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኪንሻሳ ያደረጉት ምክክር ያለስምምነት ተጠናቅቋል።

ቱርክ በበኩሏ አሁን ስልጣን ላይ ከሚገኘው የግብጽ አስተዳደር ጋር ያላት ግንኙነት መልካም የሚባል አይደለም።

በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያም ሆነ ከግብጽ መንግሥት የተሰማ ምንም ነገር የለም።

ፌስቡክ ምን አለ?

ይህ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ያሉት እና ትልቁ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት የሆነው ፌስቡክ የማኅበረሰቡን አጀንዳ እና አመለካከት ለመቀየር የተቀናጀ ዘመቻ በፌስቡክ እና እርሱ በሚቆጣጠራቸው ሌሎች ማኅበራዊ ሚዲ መድረኮች ላይ በሚደረጉ ዘመቻዎች ለመቆጣጠር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

በመጋቢት ወር ውስጥ ደርሼባቸዋለሁ ብሎ ካጠፋቸው መካከል በሌሎች አገሮች ያሉ ተከታዮችን ዒላማ አድርገው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ገፆች እንደሚገኙበት በሪፖርቱ አመልክቷል።

በዚሁ በተገለፀው ወር ውስጥ በ11 አገራት ተቀምጠው “ሐሰተኛ ዘመቻ” ሲያሰራጩ ደርሼባቸዋለሁ ያላቸውን 14 ኔትወርኮችን ማጥፋቱን ገልጿል።

ፌስቡክ ትኩረታቸውን ካሉበት አገር ውጪ በማድረግ ሐሰተኛ ዘመቻ ሲያሰራጩ ከነበሩ ኔትወርኮች መካከል አንዱ መቀመጫው ግብጽ ውስጥ እንደነበር ተገልጿል።

በእነዚህ ገፆች ላይ ከሚጻፉት ጉዳዮች መካከል አንዱ በሕዳሴ ገድብ ላይ የሚቀርብ ትችት ነበር

የፎቶው ባለመብት, Facebook

በእነዚህ ገጾች ላይ ምን ተጻፈ?

ፌስቡክ ከእነዚህ ኔትወርኮች ጀርባ ያሉት ግለሰቦች እውነተኛ እንዲሁም ሐሰተኛ አካውንቶችን በማቀላቀል በመጠቀም፣ ስማቸውን ጭምር የሚቀየይሩ ነበሩ ሲል አስታውቋል።

በተጨማሪም እነዚህ ገጾች ተከታዮቻቸው ያሉበት አገራት የሚገኙ ለማስመሰል የሞከሩ ሲሆን፤ በተለይም እነዚህ ገፆች በ2020 የበጋ ወራት በስፋት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ፌስቡክ አስታውቋል።

እነዚህ ገፆች ተከታዮቻቸው ባሉባቸው አገራት የሚነገሩ ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ በአረብኛ እና የቱርክ ቋንቋን በመጠቀም ዜናዎች እና ፖለቲካዊ ክስተቶችን ሲያቀርቡ ነበር።

“ስለግብጽ መንግሥትና እንዲሁም ስለ ሱዳን እና እስራኤል ሁለትዮሽ ግንኙነቶች መልካም ነገሮች በሌላ በኩል ደግሞ የቱርክን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እና የኢትዮጵያ አባይ ግድብ ላይ ትችቶችን ሲያቀርቡ ነበር።

“ከእነዚህ ገፆች ጀርባ ያሉ ሰዎች ማንነታቸውን እንዲሁም ቅንጅታቸውን ለመደበቅ ቢጥሩም ባደረግነው ምርመራ እና ክትትል ግብጽ ውስጥ የሚገኝ ቢ ኢንተራክቲቭ የተሰኘ የማርኬቲንግ ኩባንያ ጋር ትስስር እንዳላቸው ደርሰንበታል” ብሏል።

እነዚህ የታገዱ ገፆች በአጠቃላይ ከ300 ሺህ በላይ ተከታዮች ያላቸው ሲሆን ይዘታቸውንም ገንዘብ በመክፈል ሲያስተዋውቁ ነበር ተብሏል።

“በፌስበክ እና ኢኒስታግራም ላይ ለማስታወቂያ 525 ሺህ ዶላር ወጪ ተደርጓል” የተከፈለውም በዋነኛት በግብጽ ፓውንድ እና በአሜሪካ ዶላር እንደሆነ አመልክቷል።

ፌስቡክ እንደዚህ አይነት እርምጃዎችን ሲወስድ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። በፈረንጆቹ አቆጣጠር ታኅሣሥ ወር ላይ ድርጅቱ ከ2000 በላይ የሚሆኑ ሐሰተኛ አካውንቶች፣ ገጾች እና ቡድኖችን ማጥፋቱን ገልጾ ነበር።

ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት በተለያዩ አገራት ምርጫዎች ላይ ያነጣጠሩ እንዲሁም ራሳቸውን የመገናኛ ብዙሃን ተቋም አስመስለው የሚያቀርቡም ነበሩ ብሏል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *