ባሳለፍነው ሳምንት ከ700 በላይ ተፈናቃዮች ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ከኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ጥቃትን ሸሽተው አማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ገብተዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ማሩ ተፈናቃዮቹ አርብ መጋቢት 17 እና እሁድ መጋቢት 19/ 2013 ዓ.ም እና ከዚያ ወዲህ ባሉት ቀናት ደሴ ከተማ መግባታቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። ከተፈናቃዮቹ አብዛኛዎቹ ሕፃናትና ሴቶች መሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች በአካባቢዎቹ በተደጋጋሚ የሚፈፀም “ማንነት ተኮር ጥቃት”ን ሸሽተው እንደመጡ ገልጸዋል። “ከተወለድንበት፣ ካደግንበት፣ ቤተሰብ ከመሠረትንበት፣ ሀብት ንብረት ካፈራንበትና አገራችን ነው ብለን ከኖርንበት ነው የተፈናቀልነው” ብለዋል። በመሆኑም ጥቃቱን በመሸሽ በሕይወት ዘመናቸው አይተው ወደማያውቁትና ቀደምት አያቶቻቸው ኖረውበታል ወደተባለ በዘር ሐረግ ብቻ ወደሚያውቁት አካባቢ ለመሰደድ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

ወ/ሮ ተጓዳ የሱፍ ኑሯቸው በኦሮሚያ ክልል ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ነበር። አሁን ግን ቀሪ ቤተሰባቸውንና በሕይወት ዘመናቸውን ያፈሩትን ሐብት ንብረታቸውን ጥለው ወጥተዋል። ሦስት ልጆቻቸውን ብቻ ይዘው ነው የወጡት። “ሕዝቤም፣ ማቲየም [ቤተሰቤም] እዚያው ናቸው። ሞት ሲበዛብን፣ ኦነግ ሸኔ እያሉን፣ ሕጉም ተጽዕኖ አድርጎ ሲቀጠቅጠን ጥለን ወጣን” ብለዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ባለፈው ሰኔ በእነርሱ ቀበሌ ለእርሻ ሥራ በወጡበት አራት ሰዎች ተገድለዋል። ይህንንም ለመንግሥት አቤት ሲሉ “ፌደራል ይታዘዝላችኋል” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውና ይህንን ተስፋ አድርገው በተቀመጡበት በነሐሴ ወር ደግሞ ሌላ ግድያ ተፈፀመ። “ከሰኔ ጀምሮ እንጀራ እንኳን በአግባቡ ጋግረን በልተን አናውቅም። ሲጠናብን ወንዶቻችን እየጠበቁን አቡክተን እንጋግራለን፤ እርሱን ይዘን እንደ አውሬ ነው መልሰን ወደ ጫካ የምንገባው። ከሰኔ እስካሁን ድረስ አንድ ቀን ቤት አድረን አናውቅም” ይላሉ።

“ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰው ከመሞት አርፎ አያውቅም” የሚሉት እኝህ እናት፤ አሁንም ዘመዶቻቸው ይኑሩ ይሙቱ የሚያውቁት ነገር እንደሌለና ነፍሳቸውን ለማትረፍ ብቻ ሲሉ ተበታትነው መውጣታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል። “ቅድመ አያቶቼ አማራ ክልል ይሁኑ፤ አማርኛ ተነጋጋሪ እንሁን እንጅ፤ እኛ የምናውቀው ወለጋን ነው። ግን ሲብስብን ጥለን ወጣን” ብለዋል።

ሌላኛዋ እናት ወ/ሮ አረጋሽ ተፈያ ይባላሉ። ከኦሮሚያ ክልል፣ ሆሮጉድሩ ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ፤ አጋምሳ ቀበሌ ነው የተፈናቀሉት። እርሳቸውም ማቄን ጨርቄን ሳይሉ አራት ልጆቻቸውን ብቻ ይዘው ነው የወጡት። እርሳቸው እንዳሉት ሁሉም ልጆቻቸው ከ14 ዓመት በታች ናቸው። “ግድያው ሲበዛብን ነፍሳችንን ለማትረፍ እየተሹለከለክን፣ በከተማም እየለመንን ነው የወጣነው” ይላሉ።

ወ/ሮ አረጋሽ የተወለዱት፣ ያደጉት፣ ጎጆ ቀልሰው ልጆች ያፈሩትም እዚያው ወለጋ ነው። አሁን ግን ግማሽ ቤተሰባቸው አካባቢውን ለቆ እንደወጣ ተናግረዋል። “ሌሎቹ ግን አሁንም ጫካ ለጫካ እየተንከራተቱ ናቸው” ብለዋል። “ወንድሞቻችን ሲገገደሉ፤ አራስ ልጆች ሳይቀሩ እየተገደሉ አይተናል። የጸጥታ አካላትም ቶሎ አይደርሱልንም፤ ጎረቤቶቻችን አልቀው እያደሩ ምንም መፍትሔ የለም” ይላሉ በምሬት።

በዚህም ምክንያት ነፍሳቸውን ለማትረፍ ቀያቸውን ለቀው እንደወጡ ይናገራሉ። አሁን በደቡብ ወሎ ሐይቅ ከተማ በሚገኝ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ። አለሙ ካሳየ የተባሉ ሌላኛው ተፈናቃይ ደግሞ ባለቤታቸውን ጨምሮ አምስት ቤተሰብ ይዘው ነው የወጡት። ከዚህ ቀደም በተፈፀሙ ጥቃቶችም “የቅርብ ዘመዶቼን አጥቻለሁ” ይላሉ።

“እዚህ ከመጣን ቤታቸው የተቃጠለባቸው አሉ፤ ወንዶቹም የት እንደደረሱ አናውቅም” ብለዋል። የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ የጸጥታ ችግር ካለባቸውና ተደጋጋሚ ጥቃት ከሚፈፀምባቸው አካባቢዎች በቅርቡ የተፈናቀሉት ሰዎች በሁለት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ዕለታዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

መጠለያ ጣቢያዎቹ ሐይቅ ከተማ የሚገኘውና ከዚህ ቀደም የሕጻናት ማሳደጊያ የነበረ የመካነ እየሱስ ካምፕ እንዲሁም ቀደም ሲል የሕፃናት ማሳደጊያ የነበረው ጃሪ ካምፕ ናቸው። ተፈናቃዮቹ በሚገኙበት መጠለያ ጣቢያም ለዕለት የሚያስፈልጋቸው ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው ገልጸዋል።

ተፈናቃዮች

በኦሮሚያ ክልል እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በተፈፀሙ ጥቃቶች በርካቶች ተገድለዋል። ባሳለፍነው ማክሰኞ መጋቢት 21/2013 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል ወረዳ በሚገኘው ቦኔ ቀበሌ ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ በተፈፀመ “አሰቃቂና ዘግናኝ” በተባለ ጥቃት ቢያንስ 28 ሰዎች ሲገደሉ 12 ሰዎች ለጉዳት ተዳርገዋል።

ቀደም ሲል በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይም በአማራ ተወላጆች ላይ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ 22 ሰዎች ሲገደሉ 20 ሰዎች ተጠልፈው ተወስደው በኋላ ላይ መለቀቃቸው ተዘግቧል። በጥቅምት ወርም በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ለስብሰባ በሚል ትምህርት ቤት ውስጥ የተሰበሰቡ ነዋሪዎች በታጣቂዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ይህ ግድያ ማንነትን መሰረት ያደረገ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲሁም ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ በወቅቱ ገልፀው ነበር። ኮሚሽኑ ጥቃቱ ሦስት ቀበሌዎች ላይ የሚኖሩ የአማራ ነዋሪዎች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ለጥቃቶቹ ኦነግ-ሸኔንና ህወሃትን ተጠያቂ ያደርጋል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በቅርቡ የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ ባወጣው መግለጫ ባለፉት ወራት በኦነግ-ሸኔ ላይ በተወሰደ እርምጃ 1 ሺህ 947 አባላቱ መገደላቸውን፤ 489 አባላቱ ደግሞ መማረካቸውን አስታውቋል።

የፖለቲካ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የመብት ተሟጋቾች በበኩላቸው ይህንን የማስቆምና የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ የመንግሥት ግዴታ ነው በማለት “ለሚፈፀመው ተደጋጋሚ ጥቃት በዋናነት ተጠያቂው መንግሥት ነው” ብለዋል። በአሜሪካ የአማራ ማኅበር የአዲቮኬሲ ዳሬክተር የሆኑት አቶ ሆነ ማንደፍሮ ለቢቢሲ ለዚህ ጥቃት “በዋናነት ተጠያቂው መንግሥትና በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ናቸው” ብለዋል።

“ከዚህ በፊት በሰብሰብናቸው መረጃዎች መሠረት አብዛኞቹ ጥቃቶች የተፈፀሙት፤ ወይ የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ከአካባቢዎቹ እንደወጣ አሊያም ሳይደርስ፤ እንዳንዴም እዚያው እያሉ በቸልተኝነት ነው” በማለት ይህ አንድ የሚያመላክተው ነገር መኖሩን ተናግረዋል። በመሆኑም የዜጎችን ደኅንነት ከመጠበቅ ባሻገር የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በእነዚህ ጥቃቶች ሳቢያ የተፈናቀሉ ሰዎችን ሊደግፉና ሊያቋቁሙ ይገባል ብለዋል።

ማኅበሩ ላቀረበው ክስ ከፌደራል መንግሥትና ከኦሮሚያ ክልል ምላሽ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ፣ እናት ፓርቲ፣ ትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ [ትዴፓ] እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ -ኢዜማ ስለሚፈጸሙት ጥቃቶች በጋራ መግለጫ አውጥተው ነበር።

በዚህም በአማራ ተወላጆች እና ‘መጤ’ ተብለው በተፈረጁ ንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለማስቆም መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፤ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ገለልተኛ ኮሚሽን አቋቁሞ እንዲመረምር ጠይቀዋል። የአማራ ክልል መንግሥት ጥቃቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ በአማራ ብሔር አባላት ላይ የሚፈጸመውን ግድያ የፌደራል መንግሥት በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ አሳስቧል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በአማራ ላይ የሚፈጸመው ግድያ እንዲቆም የክልሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ውይይት እንደሚፈልግም ማስታወቁ አይዘነጋም። የአሜሪካ ኤምባሲም በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ውስጥ የተፈጸሙትን የሰላማዊ ሰዎች ግድያን በጥብቅ አውግዟል።

በደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ጥቃት ሸሽተው የወጡ ከ11ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ መሃመድ ሰይድ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *