በምሥራቅ ኢትዮጵያ የአፋር እና የሶማሌ ክልሎች በሚዋሰኑበት አካባቢ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በተቀሰቀሰ ግጭት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሎቹ መስተዳደሮች አስታወቁ።
በአፋር ክልል ቅዳሜ ዕለት 25/2013 ዓ.ም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በዞን 3 ሀሩካ ወረዳ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ50 በላይ መቁሰላቸውን የክልል ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ኻሎይታ ለቢበሲ ተናግረዋል። ማክሰኞም በተመሳሳይ ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በዞን ሶስት ሀሩካ፣ ገልአሉ፣ ገዋኔ በሚባሉ ሦስት ወረዳዎች ጥቃት መድረሱን እና ቤቶች መቃጠላቸውን ጨምረው ገልፀዋል።
የሶማሌ ክልል በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ባለፈው ሳምንት አርብ መጋቢት 24/2013 ዓ.ም ደአዋዲ እና ቀረፋ በተባሉ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ላይ ጥቃት ደርሶ “ከ25 በላይ አርብቶ አደሮች ሲገደሉ ከ30 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውና ንብረት መውደሙን” አመልክቷል።
ማክሰኞ መጋቢት 28/2013 ዓ.ም ጠዋት በአራት የሶማሌ ክልል ቀበሌዎች ማለትም በደዋዲድ፣ በገውረአን፣ በቀላሌና በደንለሄ ላይ ጥቃት በመፈፀሙ ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል። የአፋር ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር፣ አህመድ ሁመድ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ከአርብ ጀምሮ በነበረው ግጭት 100 ያህል ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ ለጥቃቱ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይልን ተጠያቂ አድርገዋል። የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ቃል አቀባይ አሊ አብደል በበኩላቸው፣ አርብ ዕለት ብቻ 25 ሰዎች መሞታቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል። አክለውም ማክሰኞ ዐዕለት በአፋር ልዩ ኃይል “ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ተገድለዋል” ያሉ ሲሆን ለአፋር ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ውንጀላ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ሁለቱም ክልሎች ጥቃቱን ያደረሱት የሌላኛው ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት መሆናቸውን በመጥቀስ እርስ በእርሳቸው ይወነጃጀላሉ። በተጨማሪም የሶማሌ ክልል የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ‘ኡጉጉማ’ ከሚባል “የሽብር ክንፍ” ጋር ተቀናጅቶ ጥቃት መፈፀሙን በመጥቀስ ወንጅሏል። የአፋር ክልል ኮምዩኑኬሽን ኃላፊ በእንደፎ፣ አዳይቱ እና ገዳማይቱ አካባቢዎች የኮንትሮባንድ ንግድ ለመቀነስ በተወሰደ እርምጃ የሶማሌ ክልል ታጣቂዎች ንፁሃን አርብቶ አደሮች ላይ ግድያ ፈጽመዋል ሲሉ ይከሳሉ።
አቶ አህመድ አክለውም በቅዳሜው ግጭት ተሳትፈው የተያዙ የሶማሌ ልዩ ኃይል አባላት መኖራቸውን ገልጸዋል። በተደጋጋሚ በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች መካከል እርቅ እንዲወርድ ጥረት መደረጉንና አለመሳካቱን የሚናገሩት አቶ አህመድ፤ እስካሁን ድረስ ግጭቱ በተከሰተበት ስፍራ የፌደራል ፖሊስም ሆነ የመከላከያ ሠራዊት ኃይል አለመድረሱን ገልፀዋል።
በአፋርና በሶማሌ ክልል መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን አለመግባባት በየጊዜው ለሚያገረሽ ግጭት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል። መጋቢት 15/2013 ዓ.ም ምርጫ ቦርድ የአፋር ክልል መንግሥት በተወሰኑ የምርጫ ጣብያዎች አደረጃጀት ላይ ያቀረበውን ቅሬታ ተከትሎ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። በዚህም “ቦርዱ ምርጫ በምንም መልኩ የሰላም መደፍረስ ምክንያት እንዳይሆን በማሰብ” በማለት ሊከፍታቸው የነበሩ 30 የምርጫ ጣቢያዎችን በአካባቢው እንዳይቋቋሙ መወሰኑ ወስኗል።
የአፋርና የሶማሌ ክልሎች በአዋሳኝ አካባቢዎቻቸው በሚገኙ ቀበሌዎች ላይ በሚያነሷቸው የይገባኛል ጥያቄዎች ሳቢያ ውዝግብ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህም ሳቢያ በሚከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶች ሳቢያ ባለፉት ሦስት ዓመታት የበርካታ ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከፍተኛ የንብረት ውድመትም ማጋጠሙ ተዘግቧል።
ምንጭ – ቢቢስ