በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባታቸው የተነገረው የኤርትራ ወታደሮች መውጣት መጀመራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ይህንን ያለው ባለፈው አርብ የቡድን ሰባት አገራት ትግራይ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ላወጡት መግለጫ በሰጠው ምላሽ ላይ ነው። ዩናይትድ ኪንግደምን፣ አሜሪካንና የአውሮፓ ሕብረት ያሉበት ይህ ቡድን ሰባት የሚባለው የአገራት ስብስብ ትግራይ ውስጥ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ተሰልፈዋል ያላቸውን ኤርትራ ወታደሮች እንዲወጡ ጠይቆ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ እንዳለው ባለፈው ሳምንት ይፋ እንደተደረገው የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው ገብተው የነበሩ “የኤርትራ ወታደሮች አሁን መውጣት መጀመራቸውንና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም የድንበር አካባቢውን እየተቆጣጠሩ” መሆናቸውን ገልጿል። አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል ሲሉ ይከስሳሉ።

የኤርትራም ሆነ ኢትዮጵያ መንግሥት ለረዥም ጊዜ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ጦርነት ላይ መካፈላቸውን ሲያስተባብሉ ከቆዩ በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኤርትራ የደህንንት ስጋት ስላለባት ጦሯ የኢትዮጵያን ድንበሩን አልፎ መግባቱን ተናግረዋል። ኤርትራ እስካሁን ድረስ ጦሯ በኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱን ያላመነች ሲሆን የሚቀርቡትንም ውንጀላዎች በአጠቃላይ ስታስተባብል ቆይታለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመግለጫው የቡድን ሰባት (ጂ7) አባል አገራት የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማሻሻል በወሰደው እርምጃ የሚታዩ አዎንታዊ ውጤቶችን ከግንዛቤ ያላስገባ መግለጫ አውጥቷል ሲልም ወቅሷል።

የቡድን ሰባት አባል አገራት ባወጡት መግለጫ ላይ “በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችን፣ ጾታዊ ጥቃቶችን፣ ኢላማ ያልለየ የከባድ መሳሪያ ድብደባዎችና ነዋሪዎችንና ስደተኞችን በኃይል ማፈናቀልን እንደሚያወግዝ ገልጾ፤ ተፈጸሙ በተባሉት ወንጀሎች ላይ ግልጽና ገለልተኛ ምርመራ ተደርጎ የሰብአዊ መብት ጥሰቶቹ ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲደረጉ ጠይቆ ነበር።

በቡድኑ ጨምሮም በግጭቱ አካባቢ “እየተባባሰ ያለ የምግብ ዋስትና ችግር” እንደሚያሳስበው በመግለጽ “አስቸኳይና ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት” እንዲመቻች ጠይቋል። ለዚህም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ወደ ትግራይ ክልል እንዲገቡ መፍቀድን ጨምሮ ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ማመቻቸቱን እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ምርመራው በቅርቡ እንደሚጀመር አመልክቷል።

ነገር ግን ምንም እንኳን መንግሥት እነዚህ እርምጃዎችን ቢወስድም የሰብአዊ እና የልማት አቅርቦትን በተመለከተ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኩል ያለው ድጋፍ ግን ከሚጠበቀው በታች እንደሆነ ገልጿል። ስለዚህም በክልሉ ያሉትን ተግዳሮቶች በሙሉና በወቅቱ ለመፍታት የሚያስፈልጉትን ድጋፎች የማቅረቡ ሥራ ከሁሉ በፊት ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባቸው አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥት ለ4.2 ሚሊዮን ሰዎች ድጋፍ ለማቅረብ የሚችለውን ሁሉ ጥረት እያደረገ ቢሆንም ከዓለም አቀፍ አጋሮች የሚቀርበው ድጋፍ ከሚያስፈልገው አንድ ሦስተኛው በእጅጉ ያነሰ መሆኑን በመጥቀስ የሚቀርበውን ድጋፍ አናሳናትን አመልክቷል።

ሚኒስቴሩ በቡድን ሰባት አባላት በኩል የቀረበውን ስጋት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚያደንቅ ገልጾ ነገር ግን የመግለጫው ትኩረት መሆን የነበረበት ግልጽ በሆነው የምግብና የህክምና እርዳታ አቅርቦትን የተመለከተው ጉዳይ ላይ ነበር ብሏል። በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከ70ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን መሰደዳቸውን የእርዳታ ድርጅቶች ይናገራሉ።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚለው አስካሁን ድረስ ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ ሰዎች በክልሉ ውስጥ የተፈናቀሉ ሲሆን፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ የሰብዓዊ እርዳታ ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያ በትግራይ ግጭት ውስጥ የገባችው ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም ካለው የሕወሓት ኃይል የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ ነው።

ከሶስት ሳምንት በኋላ የፌደራል ኃይሎች መቀለን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የጦርነቱን መጠናቀቅ ቢያስታውቁም፤ እሁድ ዕለት መከላከያ በሰሜን እና በምዕራብ በስምንት ግንባሮች ጦርነት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። በትግራይ ያሉ የሕወሓት ተዋጊዎች በሕዝቡ መካከል በመሆን የሽምቅ ውጊያ እንደሚያካሄዱም በዚሁ ንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል።

ምንጭ –  ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *