መጋቢት 20 እና 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል ወረዳ ሰዴቃ ቀበሌ፣ እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን በርካታ ንፁኃን ላይ የተፈጸሙትን ግድያዎች የፌዴራል መንግሥት በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ እናት ፓርቲና የአማራ ክልል መንግሥት የፌዴራል መንግሥት እየሄደበት ያለውን የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ እንዲያስተካከል ጠይቀዋል፡፡ኢዜማ ዓርብ መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣  ቃቱ ሆን ተብሎና ታቅዶበት ለመፈጸሙ የአካባቢው ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ተሳትፎ እንዳለበት ማሳያ ነው ብሏል፡፡

በተጠቀሱት አካባቢዎች በዜጎች ላይ በተደጋጋሚ ለከት ያጡ ኢሰብዓዊ የወንጀል ድርጊቶች የተፈጸሙት፣ በታወቁና ውስን በሆኑ ቦታዎች መሆናቸውን፣ በክልሎችም ሆነ በፌዴራል መንግሥት በኩል ችግሩን የሚመጥን ትኩረት ላለማግኘቱ አመላካች እንደሆነ የኢዜማ መግለጫ ያትታል፡፡

‹‹በተደጋጋሚ የተከሰቱት ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እንደ አገር እንዳንረጋጋና ዜጎች ከፍርኃት ተላቀው የዕለት ተዕለት ሕይወታቸውን እንዳይመሩ እንቅፋት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ሉዓላዊነታችንና የአገር ደኅንነታችን ላይ ላነጣጠረ አደጋ ተጋላጭ አድርጎናል፤›› ብሏል፡፡

የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት፣ ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር በመሆኑ፣ በዜጎች ላይ ጥቃት እየተፈጸመባቸው ባሉ አካባቢዎች ያለው የመንግሥት መዋቅር በጥልቅ ተፈትሾ፣ በየደረጃው የሚገኙ ኃላፊዎች ላይ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የዕርምት ዕርምጃ መንግሥት በአስቸኳይ እንዲወስድ እንጠይቃለን በማለት ኢዜማ አስታውቋል፡፡

ጥቃት በተደጋጋሚ የደረሰባቸውንና ሊደርስባቸው የሚችሉ አካባቢዎችን በመለየት በአስቸኳይ በፌዴራል መንግሥት የፀጥታ አካላት ቁጥጥር ሥር በማድረግ፣ ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወሰድና በእነዚህ አካባቢዎች አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት፣ የደኅንነት ዕቅድ እንዲቀረፅና በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግም ጠይቋል፡፡

ሰላምና ደኅንነት ከማስጠበቅ በተጨማሪ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር የማኅበረሰብ አቀፍ ሰላምና ደኅንነት ሥራ የሚሠራ ኃይል የማደራጀት፣ የማሠልጠንና የማስታጠቅ ሥራ እንዲከናወን ኢዜማ አሳስቧል፡፡ በተመሳሳይ እናት ፓርቲ በተደጋጋሚ በንፁኃን ላይ የሚደርሰው ጭፍጨፋ መልኩን እየቀያየረና አሰቃቂነቱም እየጨመረ መሄዱን፣ ዓርብ መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

እናት ፓርቲ በለውጥ ማግሥት ሃይማኖታዊና ዘርን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ አድሏዊነት፣ ኢትዮጵያ ጠል ትርክትና አፈናዊ ሥርዓት፣ ወዘተ ይቆማሉ፣ ኢትዮጵያ ወደ ክብሯ ልትመለስ ነው ብሎ ከፍተኛ ተስፋ የነበረው ሕዝብ፣ ተስፋው እንደ ጉም ተኖ የሟችና የስደተኛ ቁጥር ማስላት ሥራው ሆኗል ሲል ገልጿል፡፡ እነዚህ ፍጅቶች በተፈጸሙባቸው ቦታዎችና ክልሎች በመዋቅር ውስጥ ያሉና  የሌሉ አካላት እንደ ተሳትፏቸው ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ የፍትሕ ፀሐይም እንድትወጣ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሌላ በኩል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ በአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመው ግድያ እንዲቆምና የክልሉ መንግሥት በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ውይይት እንደሚፈልግ አስታውቀዋል። ‹‹እንደ አማራ ክልል መንግሥት አስቸኳይ ምክክርም ንግግርም እንፈልጋለን፤›› ያሉት አቶ አገኘሁ፣ ጥቃቱ እንዲቆምና በአማራነታቸው ብቻ ለሚገደሉ ዜጎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናቸው እንዲቆምም ሐሙስ መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ገልጸው፣ ‹‹ስሜታችንን መላው የአገራችን ሕዝብ ሊረዳን ይገባል፤›› ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የአማራ ሕዝብ በአገረ መንግሥት ግንባታ ያለውን ድርሻ አጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ አማራ የኢትዮጵያ አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚፈልግና በኢትዮጵያዊነት የማይደራደር ሕዝብ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል ወረዳ ሰዴቃ ቀበሌ በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ ያወገዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የፌዴራልና የክልል የፀጥታ ኃይሎች በመተባበር በሕገወጥ ገዳይ ቡድኑ ላይ የማያዳግም ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ምንጭ – ሪፖርተር

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *