ረቡዕ ታኅሣሥ 14/2013 ዓ.ም ንጋት የ41 ዓመቱን አርሶ አደር በላይ ዋቅጅራን ሕይወት እስከወዲያኛው የቀየረ ክስተት ተከሰተ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩጂ ተብላ በምትጠራው ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት በላይ ዋቅጅራ ባለቤታቸው እና 9 ልጆቻቸው አይናቸው እያየ በግፍ ተገደሉ። ታዳጊ ልጆቻቸው በመኖሪያ ቤታቸው ላይ ከተለቀቀው እሳት ራሳቸውን ለማዳን ከቤት ሲወጡ፤ የጦር መሳሪያ ደግነው በሚጠብቋቸው ታጣቂዎች ሰላባ ሆነዋል። “አጠገቤ ገደሏቸው” ይላሉ። “ባለቤቴ፣ 5 ሴት ልጆቼ እና 4 ወንድ ልጆቼ ናቸው የተገደሉት” ይላሉ የልጆቻቸውን እና የባለቤታቸውን ስም በሐዘን በተሰበረ ድምጽ እያስታወሱ።

ሌላኛው ነዋሪ አቶ ተስፋ [በጥያቄው መሠረት ስሙ የተቀየረ] እናትና አባቱ ሠርግ ለመታደም በወጡበት እንደቀሩ ይናገራል። ታጣቂዎች በተለያየ ወቅት ባደረሱት ጥቃት ወላጆቹን ጨምሮ በርካታ ዘመዶቹን አጥቷል። በተለያየ ጊዜ የመንግሥት ጦር የሚወስደውን ጥቃት በመሽሽ ወደ ሱዳን ድንበር ሲሽሽ እንደቆየ የሚናገረው የጉሙዝ ተወላጁም፤ ንሑሃን የጉሙዝ ተወላጆች ሲገደሉ አይቻለሁ ይላል። የመተከል ዞንን ችግር ውሰብስብ እንደሆነ የሚያሳየው ደግሞ የኢንስፔክተር ነጋሽ ኩቲል ታሪክ ነው።

ኢንስፔክተር ነጋሽ የክልሉ የፖሊስ አባል እና የጉሙዝ ተወላጅ ናቸው። ኢንስፔክተሩ በተሰጣቸው ግዳጅ ላይ ተሰማርተው ሳለ ከታጣቂዎች ጋር ውጊያ መግጠማቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። “ጉሙዝ ነኝ። ሚስቴም ጉሙዝ ናት። ግዳጅ ተልኬ ከጉሙዝ ጋር ውጊያ አጋጠመን። ‘ነጋሽ ነው መከላከያን መርቶ ያመጣው’ ብለው ጠቆሙብኝ። ከዚያ እኔን ለመግደል ሲመጡ አጡኝ። እዚያው ሚስቴን እና ልጆቼን በጥይት ጨረሷቸው” ሲል ኢንስፔክተር ነጋሽ ይናገራል። ይህን መሰል የሰቆቃ ታሪክ በቤኒሻንጉል ክልል የሚኖሩ የተለያዩ ብሔር ተወላጆች የሚጋሩት ሃቅ ነው።

ከቅርብ ወራት ወዲህ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኘው መተከል ዞን በሚፈጸሙት ጥቃቶች እና በሚያጋጥሙት ግጭቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የሺናሻ እና ጉሙዝ ብሔር ተወላጆች በግፍ ተገድለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።

መሰል ጥቃቶች ለምን ይፈጸማሉ? ይህ እልቂትስ ሊቆም የሚችለው እንዴት ነው? ትኩረታችንን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በማድረግ፤ በስፍራው የሚኖሩ የተለያዩ ብሔር ተወላጆችን፣ የአካባቢውን ባለስልጣናት እና ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ ፖለቲከኞችን ጠይቀናል።

ከዚያ በፊት ግን ጥቂት ስለክልሉ እና የአከባቢውን በአጭሩ እንመልከትline

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን በጨረፍታ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት አድን ድርጅት እአአ 2019 ባወጣው የሁኔታ መግለጫ ሪፖርት (ሲቹዌሽን ሪፖርት) ላይ የክልሉ ነዋሪ ቁጥር ወደ 1.1 ሚሊዮን እንደሚጠጋ አስቀምጦ ነበር። ከእነዚህ የክልሉ ነዋሪዎች መካከልም 44 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ነው።

በክልሉ ከሚኖሩ የተለያዩ ብሔር ተወላጆች መካከል የጉሙዝ፣ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የሺናሽ እና አገው ብሔር ተወላጆች ደግሞ ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።በክልሉ ሶስት ዞኖች የሚገኙ ሲሆን መተከል፣ ካማሺ እና አሶሳ በመባል ይታወቃሉ። ትኩረት የምናደርግበት መተከል ዞን ከኦሮሚያ፣ አማራ እና ሱዳን ጋር ይዋሰናል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የክልሉ ነዋሪ ኑሮውን መሠረት ያደረገው በእርሻ ሥራ ላይ ነው።

የክልሉ ታዳጊዎች በጨዋታ ላይ
የክልሉ ነዋሪ ቁጥር ወደ 1.1 ሚሊዮን የሚጠጋ ሲሆን ከዚህም መካከል 44 በመቶ የሚሆነው እድሜው ከ18 ዓመት በታች ነው

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ መሬት ለም ነው። በርካታ አልሚዎች ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመውሰድ ያለማሉ። የግጦሽ መሬትም ሠፊ ነው። ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ይሁን እንጂ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በተለያዩ ጊዜያት ከሌሎች ስፍራዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንዲሰፍሩ ተደርጓል።

የሕጻናት አድን ድርጅቱ በሁኔታ መግለጫ ሪፖርቱ ክልሉ ከተቀረው የአገሪቱ ክልሎች በተነጻጻሪነት ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ቁጥር ጭማሪ እንደሚያሳይ ይገልጻል። ከከፍተኛ የወሊድ መጠን በተጨማሪ የእርሻ እና የግጦሽ መሬት መኖሩ እና በክልሉ ያሉት ሰፋፊ የእርሻ ኢንተርፕራይዞች ሰዎች ወደ አካባቢው እንዲፈልሱ እና የክልሉ ሕዝብ ቁጥር በፍጥነት እንዲጨምር ምክንያት ናቸው ይላል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ወቅታዊ ኔታ

የፌደራሉ መንግሥት እና የአካባቢው ባለስልጣናት የመተከል ዞን ከዚህ ቀደም ከነበረበት የደህንነት ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር አንጻራዊ ሰላም አለ ይላሉ። ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ግን አሁንም ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ስጋት እንዳላቸው ይናገራሉ። የመተከል ዞን ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር አብዲ ጎረና ዞኑ በፌደራል ኮማንድ ፖስት ስር እንደሚገኝ በማስታወስ “የጸጥታው ሁኔታ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው። ኮማንድ ፖስቱ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ አንጻራዊ ሰላም አለ” ከማለት ውጪ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ተደጋጋሚ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው በመተከል ዞን ውስጥ ከሚገኙት ወረዳዎች አንዷ የሆነችው የድባጤ ወረዳ ፖሊስ አዛዥም፤ በተመሳሳይ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ መስጠት ባይሹም፤ “ምን ሰላም አለ?” በማለት የፀጥታ ስጋት እንዳለ ተናግረዋል። ታኅሣሥ ወር ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡባት ቡለን ወረዳ ፖሊስ አዛዥ በበኩላቸው በወረዳዋ የተሻለ መረጋጋት ቢኖርም፤ በዙሪያዋ በሚገኙ አካባቢዎች ግን አሁንም የጸጥታ ስጋት እንዳለ ገልፀዋል።

ኮማንደር ቢራቱ ተሰማ፤ “በወረዳው የተሻለ ቢሆንም፤ በወረዳው ዙሪያ ግን አሁንም ስጋት አለ” በማለት ታጣቂዎች የጸጥታ ስጋት ሆነው መቀጠላቸውን ይናገራሉ። ከመተከል ዞን ተፈናቅለው በቻግኒ ከተማ የተጠለሉ ሰዎች ቁጥርም 65000 መድረሱን የቻግኒ ከተማ አስተዳዳር የሰላምና ደህንነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ማስረሻ ይትባለ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥት የስደተኞች ከፍተኛ ድርጅት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሸሽተው ወደ ሱዳኗ ናይል ስቴት እየተሰደዱ እንደሆነ ገልጿል። ድርጅቱ ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ 7ሺህ 393 ሰዎች ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው በሱዳን በአምስት የተለያዩ ስፍራዎች ሰፍረው ይገኛሉ። ስፍራዎቹ ሩቅ እና መሠረታዊ አገልግሎቶች የሌሉባቸው ቦታዎች መሆናቸውንም ድርጅቱ ገልጿል።

የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን መጋቢት 14 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ስደተኞቹ ክልሉን በመሸሽ ወደ ሱዳን መግባት የጀመሩት ከኅዳር 7 2013 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን አስታውሶ፤ በቅርቡም መጋቢት 8 2013 ዓ.ም. ላይ ተጨማሪ 370 ሰዎች ሱዳን ደርሰው እንደስደተኛ መመዝገባቸውን አስታውቋል። የተመድ የስደተኞች ድርጅት የሱዳን ተወካይ ሶፊያ ጄሰን ስደተኞቹ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ተሰድደው ወደ ሱዳን የሚሸሹት በደህንነት ስጋት እና በግጭቶች ምክንያት መሆኑን እንደነገሯቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ካርታ
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካርታ
line

ጥቃቶች/ግጭቶች ለምን ይፈጸማሉ?

የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ የተለያዩ ብሔር አባላት እና ጉዳዩ ይመለከተናል የሚሉ ፖለቲከኞች በተደጋጋሚ ለሚከሰቱት ግጭቶች እና ጥቃቶች ምክያቶቹ ከማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ባሻገር ፖለቲካዊ ይዘቶች እንዳላቸው ያስረዳሉ።

ስሜ አይጠቀስ ያለው የጉሙዝ ብሔር ተወላጅ የሆነ ወጣት፤ የጉሙዝ ብሔር ተወላጆች ባለፉት ዓመታት “ደሃ እንዲሆኑ ተደርገዋል” ይላል። ይህ ወጣት እንደሚለው ከሆነ የጉሙዝ የእርሻ እና የግጦሽ መሬቱን እንዲነጠቅ ተደርጓል፤ “ስለዚህ ጉዳይ ማንም ማውራት አይፈልግም” ሲል ሁኔታውን ያስረዳል። ወጣቱ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ትክክል ናቸው ብሎ እንደማያምን ገልጾ፤ የጉሙዝ ሕዝብ “ሲጎዳ ዝም መባል የለበትም” ብሏል።

የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆነው እና ስሜ አይጠቀስ ያለ ሌላ ወጣት ደግሞ፤ መተከል መወለዱን እና ማደጉን በመግለጽ “አባቴ ከሌላ ስፍራ ይመጣ እንጂ፤ አገሬ እዚሁ ነው። ሠርቶ የተለወጠ ሰው ነው እንደ ጠላት የሚታየው እንጂ ሌላ ነገር የለም” በማለት ይናገራል። ነዋሪነታቸው የክልሉ መዲና በሆነችው አሶሳ ከተማ የሆነው ፖለቲከኛው አብዱልሰላም ሸንገል በበኩላቸው፤ የግጭቶቹ መነሻዎች ምላሽ ሳይሰጥባቸው የቀሩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንደሆኑ ያስረዳሉ።

ፖለቲከኛው እንደሚሉት በመተከል ዞን ማንነትን መሠረት ያደረገ መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘር ከመጀመራቸው በፊትም በግለሰቦች ደረጃ በግጦሽ መሬት እና በውሃ ይገባኛል ግጭቶች ይከሰቱ እንደነበረ ያስታውሳሉ። “መጠነ ሰፊ ብሔር ተኮር የሆነው ግጭት የጀመረው ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ነው። ከመተከል ዞን ጋር በሚዋሰነው ጃዊ ወረዳ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጉሙዞች ተገድለው ነበር። ስለ ግድያው ምንም ሳይባል ቀረ። ማንም ተጠያቂ ሳይሆን ቀረ። ከዚያ በኋላ እዚህ ያለው ጉሙዝ ስሜት ውስጥ ገባ። ከዚያም እዚህ ካለው አማራ ጋር ግጭት ፈጠረ” ይላሉ።

አቶ አብዱልሰላም እንደሚሉት የተለያዩ ማህበራዊ አንቂዎች መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም “መተከል የእኛ ነው። የጉሙዝ አይደለም። እናስመልሳለን የሚሉ ዛቻዎች” ማሰራጨታቸውን ተከትሎ፤ “እዚህ ያሉ ፖለቲከኞች ‘መሬትህ ሊወሰድ ነው’፣ ‘ራስህን አድን’ የሚሉ ፕሮፖጋንዳዎችን በጉሙዙ ውስጥ ረጩ” ይላሉ። በተለይ በገጠር ያለው የጉሙዝ ማህበረሰብ በትምህርት ያልገፋ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመሰል ቅስቀሳዎች ተገፋፍተው “ስሜት ውስጥ የመግባት ነገር አለ” ብለዋል።

አቶ አብዱልሰላም እንደሚሉት በክልሉ የተለየዩ ለውጦች ቢኖሩም፤ የጉሙዝ ሕዝብ ከዚህ ተጠቃሚ ሳይሆን እንደቀረ ይናገራሉ። “መተከል ስትመሠረት በከተማዋ በስፋት የነበሩት የጉሙዝ እና የሺናሻ ብሔር ተወላጆች ናቸው። አሁን ላይ ከተማዋ ሰፍታ ትልቅ ሆናለች። በከተማዋ ያለው ሁኔታ ተቀይሯል። ጉሙዝ ግን በጊዜ ሂደት ከከተማው ወጥቷል” ሲሉ ያስረዳሉ።

ይህንንም ሲያብራሩ “ባለሆቴሉ እና ባለሱቁ ከሌላ ማህብረሰብ የመጡ ናቸው። ንብረት ያፈሩት ጉሙዞች በቁጥር በጣም ጥቂት ናቸው። አርሶ አደሩ ከቀዬው እየተፈናቀለ መሬቱ ለኢንቨስተር የሚሰጥበት ሁኔታ አለ።” አቶ አብዱልሰላም ፍትሃዊ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት አለመኖሩ በሕዝቦች መካከል አለመግባባት እንዲፈጠር አንዱ ምክንያት አንደሆነ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይገኛል።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ያለችው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይገኛል

“በግጭቱ ባስልጣናት፣ ባለሃብቶች እና የውጪ ኃይሎች እጅ አለበት”

መብራቱ አለሙ (ዶ/ር) የሺናሻ ብሔር ተወላጅ ናቸው። የክልሉን ሁናቴ በቅርብ ስከታተል ቆይቻለሁ ይላሉ። መብራቱ (ዶ/ር) በክልሉ በተለያዩ የስልጣን ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችም ግጭት በመቀስቀስ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል ሲሉ ይከስሳሉ።

ከዚህ በተጨማሪም በስፍራው በኢንቨስትመንት ፍቃድ መሬት የወሰዱ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶች የጉሙዝ ወጣቶችን ዳንጉር ወረዳ ጠረፍ እና ወደ ሱዳን ድንበር አቅራቢያ ወስደው ስልጠና ስለመስጠታቸው እና ስለማስታጠቃቸው ይናገራሉ።

“እውነት ለመናገር ጉባ፣ ዳንጉር እና ወንበራ አካባቢ ያሉ ሰፊ መሬቶች ለኢንቨስትመንት ተብለው ተሰጥተዋል። ግን ስጋት ካልሆነ በቀር አሁን ያለው መሬት ለእነርሱ [ጉሙዝ] በቂ አይደለም ማለት ይከብደኛል። ለግላቸው የሚሆን የእርሻ መሬት አላቸው። ሰፊ መሬት አርሰው የመጠቀም ልምድ የለም። በእጅ ነው የሚቆፍሩት” ይላሉ።

የግጭቱ አንዱ መንስኤ እውነታው ከፖለቲካው ፍላጎት ጋር ተደማምሮ ነው

ተመስገን ገመቹ የሕግ ባለሙያው ሲሆን ትውልድ እና እድገቱ መተከል ዞን ድባጤ ወረዳ እንደሆነ ይናገራል። ተመስገን አሁናዊ የሆኑ ይፋዊ አህዞች ባይኖሩም በመተከል ዞን ላይ በብዛት ያለው የጉሙዝ ተወላጅ እንደሆነ መገመት ይቻላል ይላል። ባለፉት ዓመታት ወደ አካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በሰፈራ ምክንያት መምጣቱን አስታውሶ፤ የኦሮሞ እና አገው ሕዝብ ግን የአካባቢው ቀደምት ነዋሪዎች ናቸው ይላል።

ተመስገን በስፍራው የሚስተዋለውን “ግጭት” የተለያዩ ምክንያቶች ድምር መሆኑን ተናግሮ ዋነኛው ምክንያት ግን በሕዝቡ ውስጥ ያለው እውነታ ከፖለቲካ ፍላጎት ጋር ተደማምሮ የሚከሰት ነው ብሏል።

“በጉሙዝ ሕዝብ ዘንድ ከዚህ ቀደም ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ወይም በጥርጣሬ የሚመለከታቸው ነገሮች አሉ። በክልሉ በሚደረግ የኢንቨስትመንት እድሎች ላይ የጉሙዝ ሕዝብ በስፋት ተሳታፊ አይደለም። ከተማ ሲስፋፋ ሁሉ ጉሙዞች በብዙ ኪሎ ሜትሮች እንዲርቁ እየተደረገ ነው። በዚህ መካከል ‘ቀዩ መሬትህን ሊውስድ ነው፣ ህዝበ ውሳኔ ተብሎ አገርህን ልትነጠቅ ነው’ የሚል ቅስቀሳ ፖለቲከኞቹ ይመግቧቸዋል። ፖለቲከኞቹ ብሶትን ነው ለህዝባቸውን የሚናገሩት። ህዝቡ እውነታው አለው። ይህ እውነት ግን ለዚህ መሰል ግጭት ብቻውን ምክንያት ሊሆን አይችልም” በማለት ጠበቃው አቶ ተመስገን ይናገራል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ‘መተከል ርስት ነው። እናስመልሳለን’ የሚሉ ቅስቀሳዎችም በሕዝቡ ዘንድ መረጋጋት እንዳይፈጠር ምክንያት መሆኑን ያስረዳል። ከዚህ በተጨማሪም የአንድ ብሔረሰብ ተወላጅ በሚበዛበት አካባቢ የአመራር ስብጥር አለመኖሩ ሌላው የግጭት መንስዔ አንደሆነ ጠበቃው ተመስገን ይናገራል። “ውክልና የለም። አማራው፣ ኦሮሞ፣ አገው ባሉበት ቦታ ውክልና የላቸውም ማለት ይቻላል። ‘የክልል ባለቤት’ የሚባሉት ብቻ ናቸው ስልጣን ላይ ያሉት” ይላል።line

መፍትሄው ምንድነው?

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጥር 15 2013 ዓ.ም. በመተከል የተከሰተውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥት የአካባቢውን ነዋሪዎች አሰልጥኖ በማስታጠቅ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ያደርጋል ስለማለታቸው ኢዜአ ዘግቦ ነበር።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በበኩሉ መተከል ዞን የአመራር ስብጥር በዞኑ የሚኖሩ የሌሎች ብሄር ተወላጆችን ታሳቢ ያላደረገ መሆኑ በዞኑ የጸጥታ ችግር እንዲባባስ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን በአካባቢው የተሰማራው የተቀናጀ ግብረ ኃይል አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።

የካቲት 14 በተላለፈው ዘገባ ላይ የግብረ ኃይሉ አባል እና የሰላም ሚንስቴር ዲኤታ ፍሬዓለም ሽባባው፤ “ይህን ዞን ፈተና ውስጥ ያስገባው አንዱ ማዳላት ነው። ፊት አይቶ ማዳላት የመሪ ባህሪ አይደለም” ሲሉ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተደምጠዋል።

ፖለቲከኛው አቶ አብዱልሰላምም የጠፋ ያለ አድልኦ ቢነገር እና ፍትሃዊነት ቢኖር ሰላም ማምጣት ይቻላል ባይ ናቸው። “አማራው እና ኦሮሞ ሲገደል ነው የሚነገረው እና ጉሙዝ ብዙ ሞቷል። ከዚህ በላይ ሞቷል። ተሰድዷል። ለጉሙዙ ድምጽ ሆኖ የደረሰበትን የሚናገርለት የለም። ስንት እንደሞተ፣ እንደቆሰለ፣ እንደተሰደደ መንግሥት እንኳን በአግባባቱ ለይቶ ያደረገው ነገር የለም። በግጭት ይሞታሉ። በረሃብም ይሞታሉ። የታሰሩትም ለሕግ አልቀረቡም” ይላሉ።

እንድ አቶ አብዱልሰላም ከሆነ፤ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ መፍትሄውን ማምጣት ችግር ይሆናል። “ሁሉም እኩል ካልታየ ችግሩ በቀላሉ ይቀረፋል የሚል እምነት የለኝም። ፍትሃዊነት ከሌላ ሰዎችን ወደመጥፎ ነገር ይገፋፋል” ይላሉ። “ችግሩ የፖለቲካ ችግር ነው። መፍትሄውም ፖለቲካ ነው” የሚሉት ደግሞ መብራቱ አለሙ (ዶ/ር) ናቸው።

“ለአንዲት ዞን ተብሎ ኮማንድ ፖስት የተቋቋመው መስከረም 11 2013 ዓ.ም ነው። ችግሩ ግን በጭራሽ አልተፈታም። ሰዎች አሁንም እየተገደሉ ነው። ቤቶች እየተቃጠሉ ነው። ከብት እየተዘረፈ” ነው። የችግሩ መንስዔዎች ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ባለሃብቶች እንደመሆናቸው፤ መፍትሄው የሚሆነውም ፖለቲካ ነው ይላሉ። “ከሁሉም ብሄረሰብ የተውጣጡ ምሁራን እና የአገር ሽማግሌዎች ቁጭ ብለው ችግራቸውን መፍታት አለባቸው። በተናጠል በየሚዲያው የሚባለው የባሰ ያቀቅረናል” ይላሉ።

ጠበቃው ተመስገን በበኩላቸው የችግሩ ዋነኛ ምክንያቶች ፖለቲከኞች እንደመሆናቸው መጠን ”ፖለቲከኞች እጃቸውን ካልሰበሰቡ” ሰላም አይወርድም ይላል። “ለማይደርሱላቸው ሕዝብ የርስት ስሜት እየቀሰቀሱ ችግር ውስጥ ከሚከቷቸው እጃቸውን ቢሰበሰቡ ይሻላቸዋል። በጉሙዝ በኩል ያሉትም ፖለቲከኞች ሕዝቡን ለአመጻ ከመቀስቀስ ካልተቆጠቡ ግጭቱ ሊቆም አይችልም” ይላል።

ሌላኛው መፍትሄ የሚሆነው ይላል ተመስገን፣ ጉሙዞች በአገራቸው የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ ነው። “አሁን ላይ እኮ ገበያ ወጥተው ከሌላ ማህብረሰብ ጋር እየተገበያዩ አይደለም። በደህንነት ስጋት አገር ጥለው ወደ ሱዳን ተሰድደዋል። የእነሱን ‘ኮንፊደንስ’ መመለስ አስፈላጊ ነው” በማለት ሃሳቡን ያብራራል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *