የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አመራሮች መካከል በተፈጠረ መከፋፈል እና ውዝግብን የተመለከቱ እግዶች፣ አቤቱታዎች እና ከሁለቱም ወገን የሚመጡ ማሳወቂያ ደብዳቤዎችን ሲቀበል መቆየቱ እንዲሁም ችግሩን ለመፍታት ቡድኖቹን በተናጠል እንዲሁም የፓርቲውን የስነስርአት እና የቁጥጥር ኮሚቴን በማነጋገር ያሉትን አስተዳደራዊ እና ህጋዊ መንገዶች ሁሉ እንደተጠቀመ መፍትሄዎችን ለመስጠት ጥረት ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል። በመጨረሻም ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት ፓርቲው ካለበት ችግር ብቸኛ መውጫ መንገድ መሆኑን በመረዳት እና በውዝግብ ውስጥ ያሉ አመራር ክፍሎችም ያመኑበት በመሆኑ በአመራሮች መካከል ያለው ችግር በጠቅላላ ጉባኤ እንዲፈታ መወሰኑ ይታወሳል።

ኦነግ መጋቢት 7 ቀን 2013 ዓ.ም በቁጥር 19/ABO/2013 በተጻፈ ደብዳቤ ድርጅቱ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ በማካሄድ አዲስ የአመራር አባላት መምረጡን በመግለጽ፣ በውስጥ ችግሩ ምክንያት የጠቅላላ ጉባኤ ሳያካሂድ በመቆየቱ የምርጫና የእጩ ምዝገባ ጊዜ አልፎብናል በማለት ቦርዱ የነበረበትን ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት የምልክት መረጣና የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እንዲያደርግ እንዲፈቅድለት ጠቅላላ ጉባኤውንም እንዲያጸድቅለት ጠይቋል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም የቀረቡትን ሰነዶች በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 እና በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት ምርምሯል።

ፓርቲው ያደረገውን ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ፣ በስብሰባው ላይ የተገኙትን አባላት ስም ዝርዝርና ፊርማ፣ በመጋቢት 5 ቀን 2013 ዓም ያደረገውን የድርጅቱን ብሄራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ቃለ ጉባኤ፣ የተሻሻለውን የፓርቲውን የመተዳደሪያ ደንብ በኦሮሚኛ የተመዘገበና በአማርኛ የተተረጎመ ሰነድ፣ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓም ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን፣ ምላተጉባኤው የተሟላ መመሆኑን በማሳየት ፣ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የተደረጉት ማስተካከያዎች በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት የተደረጋቸውን ገልጾ ጠቅላላ ጉባኤው እውቅና እንዲያገኝለት ጥያቄ አቅርቧል። ቦርዱም ሰነዶቹን በመመርመር

1. ፓርቲው መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም የተደረገውን የጠቅላላ ጉባኤ ማስፈጸም የሚችለውን አስፈጻሚ ኮሚቴን ያቋቋመበት ስብሰባ በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 23(4) በተመለከተው መሰረት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው 2/3ኛ አባላት በተገኙበት መሆን ሲገባው የተባለው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ 2/3ተኛ አባላት የተገኙበት ሳይሆን ሶስት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ብቻ ያከናወኑት ምልዓተ ጉባኤው ያልተሟላ ስብሰባ ነው። ስለዚህ የጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ የተቋቋመው ኮሚቴ በደንቡ መሰረት ምልዐተ ጉባኤ ሳይሟላ የተቋቋመ በመሆኑ የጠቅላላ ጉባኤውን መጥራትና ማስፈጸም አይችልም ሲል ወስኗል።

2. በሌላም በኩል በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 16.2 የጠቅላላው ጉባኤ የሚያቅፋቸውን አካላት በግልጽ የተመለከቱ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ላይ ሊሳተፋ የሚገባቸው የብሄራዊ ምክር ቤት አባላት፣ሙሉ የአባልነት መብት ያላቸው የቀድሞ የኦነግ አመራር አባላት፣ በየደረጃው ከሚገኝ መዋቅር የሚወከሉ የኦነግ አባላት፣ ለኦሮሞ ህዝብ የነጻነት ትግል የተለየ ድርሻ በማበርከት የሚታወቁ ሰዎች (የጉባኤተኛው 5% የማይበልጡ)፣ ከፓርቲው ጋር በቅርበት በመስራት ላይ የሚገኙ ህዝባዊ ድርጀቶች ማለትም የሴቶች ፣ወጣቶች፣ ባለሙያዎች …ወዘተ ማህበራት ተወካዩች (ብዛታቸው በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚወሰን) መሆናቸው ተመልክቶ እያለ ፓርቲው አካሄድኩት በማለት ባቀረበው የጠቅላላ ጉባኤ ተካፋዩች ዝርዝር ከፍ ብሎ የተመለከቱት የጉባኤው የሚያቅፋቸው አካላት መኖራቸው አልተመለከተም፣ በመሆኑም ተሳታፊዎቹ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ለመወከላቸው ቦርዱ ማረጋገጥ አልቻለም።

3. እንዲሁም በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 17.1 ተወካይ ሆኖ ለጠቅላላ ጉባኤ የሚመረጥ አባል ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ያለማቋረጥ ያገለገለና ግዳጁን በአግባቡ የፈጸመ መሆን እንዳለበት በሚደነግገው መሰረት መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የተሳተፉ አባላት ይህንን በደንቡን የተመለከተውን መስፈርት ማሟላታቸው ለማረጋገጥ የቀረበ ነገር የለም።

4. የተከናወነውን ጠቅላላ ጉባኤ የድርጅቱ ሊቀመንበር እና ጠቅላላ ጉባኤ ለማከናወን ከአመራሮቹ ውዝግብ በፊት ተቋቁሟል የተባለ ኮሚቴ እውቅና ውጪ የሆነ የድርጅቱን ህገደንብ እና አሰራር የተከተለ አይደለም በማለት ለቦርዱ ተቃውሞ የቀረበበት መሆኑንም ተገንዝቧል።

5. ቦርዱ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ የፓርቲው አመራሮችን ፣ መዋቅሮቹን እና አባላቶቹ የተለያዩ በፓርቲው ህገ ደንብ ላይ በተቀመጡ መንገዶች በመጠቀም በጠቅላላ ጉባኤ ችግሩን እንዲፈቱ የወሰነ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ይህንን መሰረት አድርጎ የተከናወነ ጉባኤ መሆኑን አያሳይም። ጠቅላላ ጉባኤውን የሚያደራጅ ኮሚቴ ያቋቋሙትም ሶሰት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ብቻ መሆናቸው ቦርዱ ጥር 19 ቀን ከወሰነው የፓርቲው አመራሮች መዋቅር እና አባላቶች የተለያዩ ህጋዊ መንገዶችን በመጠቀም ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ አለባቸው ከሚለው አንጻር ሲታይ የቦርዱን ውሳኔ አያሟላም።

በመሆኑም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች የተከናወነውን ጠቅላላ ጉባኤ ተቀባይነት የለውም ሲል ቦርዱ ወስኗል። ውሳኔውን መሰረት በማድረግም በዚህ ጉባኤ የተመረጡትን አዲስ አመራሮች እንደኦነግ አመራሮች መቀበል አይችልም።ከዚህም በተጨማሪ ምርጫው ውስጥ ለመሳተፍ እና እጩዎች ለማቅረብ ያቀረቡትን ጥያቄ አሁን የተመረጠው አመራር ተቀባይነት ካለማግኘቱ ጋር ተያይዞ ቦርዱ ጥያቄውን ማየት እንዳላስፈለገው ለማሳወቅ ይወዳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
መጋቢት 19 ቀን 2013 ዓ.ም

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *