ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ፣ ጠ/ሚ አብደላ ሐምዶክ እና ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ

በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ ያልቻሉት ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የቃላት ጦርነታቸው የደራ ይመስላል።

አልፎም የሱዳን ጦር የግዛቴ አካል ናቸው ያላቸውና የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ሰፍረውባቸው የነበሩ ለም የድንበር አካባቢ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ የድንበር ፍትጫ ተከስቷል።በቅርቡ ሱዳንና ግብፅ የጋራ ስምምነት ደርሰዋል። ስምምነቱ ከወታደራዊ ሥልጠና አንስቶ እስከ ምጣኔ ሃብታዊ ትብብር የሚመዘዝ ነው።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ማክሰኞ መጋቢት 14 /2013 ዓ. ም በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ካነሷቸው ነጥቦች አንዱ የሕዳሴ ግድቡ ጉዳይ ነው።

“ኢትዮጵያ ግብፅንም ይሁን ሱዳንን የመጉዳት ፍላጎት የላትም። ሆኖም ግን ጨለማ ውስጥ መኖር አንፈልግም። የእኛ መብራት እነሱን የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሁለቱን አገራት በማይጎዳ መልኩ መገንባቱን እንደሚቀጥል አስረግጠዋል።ለመሆኑ ሦስቱ አገራት ከሌላው ጊዜ በተለየ ወደ ከረረ ወደ ውዝግብና ፍጥጫ መግባታቸው ለምንድነው? ዋነኛው ምክንያት የሕዳሴ ግድብ ይሆን?

ሱዳን ድኅረአልባሽር

መቀመጫቸውን ለንደን ያደረጉትና የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አጥኚ የሆኑት አብዱራህማን ሰኢድ አቡሃሽም፤ “አንዱ የጡዘቱ ምክንያት የሱዳን አቋም መቀየር ነው” ይላሉ።”አባይን በተመለከተ የሱዳንና የኢትዮጵያ አቋም አንድ ነበር ማለት ይቻላል። አሁን ሱዳን ያሳየችው የአቋም ለውጥ በፊት ከነበረው በጣም የተለየና ያልተጠበቀም ነው ሊባል የሚችል ነው” ይላሉ።

ለዚህ እንደ ምክንያት የሚጠቅሱት በሱዳን ያለው የሽግግር መንግሥት አቋም አንድ አለመሆንን ነው።በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተነሳው የድንበር ፍጥጫ ይህን ያህል የሚያጋጭ ነው ብዬ አላስብም የሚሉት ተንታኙ፤ ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት መግባቷን የተመለከተው የሱዳን የጦር ኃይል ክፍተቱን ለመጠቀም ያሰበ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

አቶ አብዱራህማን እንደሚሉት፤ የሱዳን ጦር ኃይል የድንበር ጉዳዩን የፈለገው ለውስጥ ጉዳይ መጠቀሚያ ለማድረግና ተቀባይነት ለማግኘት ይሆናል እንጂ ድንበሩን የሚመለከተው የሁለቱ አገራት ኮሚቴ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ሊፈታው ይችል ነበር።

ተንታኙ ሱዳን አቋሟን የቀየረችው አሁን ባለው የአገር ውስጥ ሁኔታ ምክንያት ነው ይላሉ።ኔዘርላንድስ የሚገኙት የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች የፖለቲካ ተንታኝ አደም ካሴ (ዶ/ር) በዚህ ጉዳይ ከአቶ አብዱራህማን ጋር ይስማማሉ።

“ሱዳን በተለይ በአል ባሽር ጊዜ ከኢትዮጵያ ጋር የሚመሳል አቋም ነበራት። ነገር ግን አል ባሽር ከተወገዱ በኋላ የአገር ውስጥ ሁኔታዋን ስንመለከት ወጥ የሆነ ገዢ የሌላት አገር ሆናለች። የጦር ኃይሉ የሚመራው ክፍል አለ። እዚያ ውስጥ ደግሞ ‘ራፒድ ፎርስ’ የሚባለው አለ። ከዚያ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ የሚመራው የሲቪል አመራር አለ። ሁለቱ አመራሮች የሚያራምዱት አቋም ተመሳሳይ አይደለም” ይላሉ አደም።እንደ ተንታኙ ከሆነ ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት ያለው አቋም ሲያራምድ የነበረው በጠቅላይ ሚንስትር ሐምዶክ የሚመራው የሲቪሉ አመራር ነው።

ነገር ግን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ውስጥ ቀውስ ከተከሰተ በኋላ የሱዳን ጦር ኃይል አቅሙን እያጠናከረ መሆኑን የሚገልጹት አደም (ዶ/ር)፤ “የሲቪሉ ክፍል ደግሞ ቀድሞ ከድርድሩ ማግኘት እንችላለን ከሚሉት የተሻለ ጥቅም አሁን ማግኘት እንችላለን የሚል እሳቤ ያደረባቸው ይመስለኛል” ይላሉ።ሁለቱም ተንታኞች የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ውዝግብ ለግድቡ ድርድር እንደ አዲስ መጦፍ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው።

ሱዳንና ግብፅ ግንኙት አትራፊ ማነው?

ሱዳን አቋሟን መቀየሯን ተከትሎ ወደ ግብፅ አድልታለች። ሁለቱ አገራት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከላይ እንደተጠቀሰው የተለያዩ ስምምነቶችን አድርገዋል። ታድያ ከዚህ ስምምነት የበለጠ ተጠቃሚ ግብፅ ወይስ ሱዳን?አደም (ዶ/ር) አሁን ሁኔታው የግድብ ብቻ ሳይሆን የድንበርም ሆኗል ይላሉ። በዚህ ምክንያት ሱዳኖች አሁን ጉዳዩን ነጣጥለው የግድብና የድንበር ብለው ማውራት አይፈልጉም ብለው ያምናሉ።

“ሱዳንና ግብፅ የደረሱት ስምምነት ሰፊ ነው። የዲፕሎማሲ ግንኙነትም አለው፤ ሌሎች ሌሎች ስምምነቶችም አሉ። እንግዲህ ኢትዮጵያ ግፊት ደርሶባት በአባይ ላይ ያላትን አቋም ብታቀዘቅዝ ግብፅም ትጠቀማለች፤ ሱዳንም ትጠቀማለች። ስለዚህ ጥቅሙ የሁለቱም ነው” ይላሉ።ነገር ግን ይላሉ አደም. . . “ነገር ግን ጉዳዩ አንዳንድ ሰዎች እንደሚፈሩት ወደለየለት ጦርነት የሚያመራ ከሆነ ሱዳን ከምታተርፈው በላይ ልትጎዳ ትችላለች።”

“እንደሚታወቀው ኢኮኖሚዋ የደከመ ነው። በየቦታው ግጭት አለ። ጦርነት ቢጀመር ኢትዮጵያ እንደምትጎዳው ሁሉ ሱዳንም በጣም ትጎዳለች። ነገር ግን ጦርነት ከተጀመረ ዋና ተጠቃሚ የምትሆነው ግብፅ ናት። ጦርነት እስካልተጀመረ ድረስ ግን ሱዳን ከግብፅ ድጋፍ እያገኘች ስለሆነ ተጠቃሚ የሚሆኑት ሁለቱም [ግብፅና ሱዳን] ናቸው።”አቶ አብዱራህማን በበኩላቸው ኢትዮጵያና ሱዳን አለመረጋጋታቸው ለግብፅ ጠቃሚ ይሆናል ቢባልም እሳቸው ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም።

“እርግጥ ነው ሱዳን ለበርካታ ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መቆየቷ ለግብፆች ተስማምቷቸው ነበር። ምክንያቱም ከሚገባቸው በላይ የውሃ ድርሻ ሲያገኙ ነበር። የሱዳንን ድርሻ ጭምር ነው እነሱ [ግብፆች] ሲወስዱ የነበረው። ነገር ግን ይህ ጉዳይ ስትራቴጂክ አልነበረም። ምክንያቱም የአሁን ጥቅምን እንጂ የወደፊቱን ያሰበ አልነበረምና” ይላሉ።

“አኔ በግብፅ ሚድያዎች ላይ ቀርቤ በአረብኛ ቃለ መጠይቅ በምሰጥበት ጊዜ እናንተ ዕድል ነበራችሁ። ምክንያቱም እናንተ የምትፈልጉት ውሃውን ሌሎች አገራት የሚፈልጉት ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል ነው። ስለዚህ ይህን ፍላጎታቸውን በሌሎች አማራጮች [የነፋስም ሆነ የፀሐይ] ማሟላት ብትችሉ ኖሮ ይህ አይመጣም ነበር ነው የምላቸው።”

አሁን የአባይ ግድብ እውን በመሆኑ ግብፆች ያላቸው አማራጭ ከናይል ተፋሰስ አገራት ጋር የሚያስማማ ስምምነት ገብተው የሁሉም ጥቅም የሚከበርበትን አማራጭ መፈለግ እንጂ የሌሎች አገራት አለመረጋጋት ላይ የተመሠረተ ጥቅም አያዋጣም ይላሉ አቶ አብዱራህማን።

እውን የለየለት ጦርነት ይነሳ ይሆን?

በአባይ ውሃ አጠቃቀም ምክንያት ጦርነት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው አደም (ዶ/ር) ይናገራሉ።”ጦርነት ውስጥ ለመግባት ፍላጎት ባይኖር እንኳ የተሳሳተ ስሌት ሊኖር ይችላል። ሌላኛው ወገን ምን ሊያደርግ ይችላል እያልክ እያሰብክ ነው እርምጃ የምትወስደው። ሙሉ መረጃ ከሌለህ የተሳሳተ እርምጃ ልትወስድ ትችላለህ። እና እንደዚህ ዓይነት የተሳሳቱ ውሳኔዎች ነገሮችን ከቁጥጥር ውጪ ሊያደርጓቸው ይችላሉ የሚል ስጋት አለኝ” ይላሉ።

አደም አክለውም ሁሉቱ አገራት [ኢትዮጵያና ሱዳን] ካላቸው የአገር ውስጥ ችግር አንፃር ጦርነቱን ይፈልጉታል ብለው አያስቡም።”ነገር ግን የጦርነት ድግሱን ይፈልጉታል ብዬ አምናለሁ። በተለይ በሱዳን የጦር ኃይሉ አገሪቱን ለማንቃት ሊጠቀምበት ይችላል። በኢትዮጵያም በኩል እንደዚያው ሊፈለግ ይችላል። ወደ ዋናው ጦርነት የመግባት አቅሙም ፍላጎቱም አላቸው ብዬ አላምንም። ነገር ግን እንዳልኩት ስህተቶች ሊሠሩ ይችላሉ።”

የአብደላ ሃምዶክ መንግሥት በሱዳን ጦር ኃይል ላይ ቁጥጥር እንደሌለው እንደ አብነት በመጥቀስ በሱዳንም ሆነ በኢትዮጵያ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ኃይሎች አሉ የሚሉት አደም (ዶ/ር) “የጦርነት ፍላጎት ባይኖራቸው እንኳ ስህተቶች ሊሠሩ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ።”

አቶ አብዱራህማን በበኩላቸው ጦርነቱ ላይነሳ ይችላል የሚል እምነት አለኝ ይላሉ።”በመቶኛ አስቀምጥ ካላችሁኝ ምናልባት ሃምሳ ከመቶ ወይም ከዚያ በታች ነው ባይ ነኝ። አሁን ያለው ጡዘት አንዱ አገር ሌላኛው ላይ ጫና ለማድረግ ነው እንጂ ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት አለ ብዬ አላምንም።”

የለንደኑ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ በእርግጥ አሁን ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ጉዳይ ተወጥራ ስላለች ሱዳንና ግብፅ ሁኔታዎቹ አመቺ ናቸው ሊሉ ይችላሉ ይላሉ።”ሱዳንና ግብፅ ይህ ጉዳይ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ካልመጣለት በቀላሉ ሊፈታ እንደማይችል ያውቁታል። ይህ ጉዳይ አሁን ባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ባይነሳ እንኳ ቀጥሎ በሚመጣው መንግሥት መነሳቱ አይቀርም። ምክንያቱም ይህ ጉዳይ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ወደ ተግባር እስኪገቡ ድረስ ባለፉት መንግሥታትም ሲነሳ ቆይቷል።”

ስለዚህ ነገሩ አቅምን የማሳየትና ጫና የመፍጠር ጉዳይ ነው እንጂ ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት የለም ይላሉ።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከሱዳን ጋር ያለውን ሁኔታ በተመለከተ “ወደ ጦርነት ገብተን የማያባራ ነገር ውስጥ አንገባም” ሲሉ ለአገሪቱ ፓርላማ በተናገሩበት ወቅት አገራቸው ፈጽሞ ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌላቸውና “ነገሮችን በውይይት የመፍታት ጥረታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

ጦርነቱ ምን ዓይነት ሊሆን ይችላል?

አቶ አብዱራህማን ሱዳንና ኢትዮጵያ የድንበር ጦርነት ውስጥ የሚገቡ ከሆነ ግብፅ ደግሞ ሱዳንን ከመደገፍ አልፋ በቀጥታ ልትሳተፍ ትችላለች ይላሉ።ቢሆንም ግን ሱዳን አሁን ግብፅን ተማምና እንጂ እንኳን በወቅቱ ባለችበት ሁኔታ ቀርቶ በተነፃፃሪ የተረጋጋች በነበረችበት ጊዜ የጦርነት አቅም አላት ብዬ አላምንም ሲሉ ያክላሉ።

“ስለዚህ ከጦርነቱ ሱዳን አንዳችም ነገር አትጠቀምም። ነገር ግን ጦርነቱ አይምጣ እንጂ ቢመጣ ሱዳንና ግብፅ አንድ ላይ ይሆናሉ። የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በአሁኑ ወቅት ወዳጅነት አለው። የሁለቱ አገራት ስምምነት እስከ ሴኩሪቲ ስምምነት የሚደርስ ነው። ሱዳንና ግብፅ አንድ ላይ ካበሩ የኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጅነት በዚህ የሚገታ አይመስለኝም።”

አደም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ምን እንደሚሆን መገመት ቢከብድም ሁሉም የአቅሙን ከማንቀሳቀስ ወደኋላ አይልም ይላሉ።”ግብፆች አስፈላጊ ነው ብለው የሚያምኑ ከሆነ ከአገራቸው ሆነው ሊተኩሱ ይችላሉ። ሱዳንንም በሚያስፈልገው መልኩ በሰው ኃይልም በጦር መሣሪያም ሊያግዙ ይችላሉ። አስፈላጊ ነው ብለው ካመኑ ግድቡንም ሊመቱ ይችላሉ። በአጠቃላይ ጦርነቱ ከተጀመረ ማን ምን ያደርጋል የሚለውን መገመት አስቸጋሪ ነው።”

አደም የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ሊወግን እንደሚችል ግን እምነት አላቸው።”የኤርትራ መንግሥት ዋነኛ ዓላማ ህወሓትን ማጥፋት እንደመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ትኩረቱ በሱዳን አሊያም በሌላ አገር እንዲያዝ አይፈልግም። ኤርትራ በተቻላት መጠን በተለይ ከሱዳን ጋር ሰላም እንዲፈጠር ነው የምትፈልገው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግሥት ሥራ በበዛበት ቁጥር ህወሓትን የማጥፋት ዓላማቸው አይሳካላቸውም።

“ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ደቡብ ሱዳን የሄዱትም ጫና ለመፍጠር ይመስለኛል።”

የሌሎች አገራት ሚና

ሁለቱ ተንታኞች በሌሎች አገራት ሚና በኩል አይስማሙም። አደም (ዶ/ር) ከትግራይ ክልል ጦርነት ወዲህ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቋም እየተዳከመ ነው ይላሉ።አቶ አብዱራህማን ግን ኢትዮጵያ በተለይ በአፍሪካ ሕብረት ዘንድ ያላት አቋም ከግብፅና ከሱዳን የላቀ ነው ይላሉ።አደም የታችኛው ተፋሰስ አገራት ጦርነት ቢቀሰቀስ ቀጥተኛ ተሳታፊ አይሆኑም። ነገር ግን በግልፅ ወጥተው ለግብፅና ሱዳን ያደላሉ የሚል እምነት የለኝም ይላሉ።

“ነገር ግን ለምሳሌ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ብንመለከት ከግብፅ ጋር ስምምነት ማድረግ ከጀመረች ቆይታለች። ምጣኔ ሃብታዊና የጦር ኃይል ድጋፍም ስታደርግ ነበር። እና በዲፕሎማሲ ወደ ሱዳንና ግብፅ ሊያዘነብሉ ይችላሉ። በጦርነቱ ግን ቀጥተኛ ተሳታፊ ይሆናሉ የሚል እሳቤ የለኝም።”

አቶ አብዱራህማን ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ከኢትዮጵያ ጋር መልከአ ምድራዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ስላላቸው ከኢትዮጵያ ጋር የሚስማማ አቋም ሊኖራቸው ይችላል ይላሉ።ቢሆንም እነ ኮንጎ ምናልባት ግብፅን የሚደግፉ አሊያም መሀል ላይ ሊሆኑ ይችላሉ ይላሉ አቶ አብዱራህማን።ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ባለፈ ሌሎች ኃያላን የዓለም አገራት በሦስቱ አገራት ጉዳይ ቀጥተኛ ያልሆነ ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል ምሁራኑ ይስማማሉ።

ግብፅ በሦስቱ አገራት ድርድር የአሜሪካ እጅ እንዲኖርበት ትሻለች። ኢትዮጵያ ደግሞ ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት አስማሚነት እንዲቀጥል እንደምትፈልግ በግልፅ አሳውቃለች።ከዚህ ባለፈው እንደ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ኳታር በዚህ ጉዳይ ጣልቃ ሊገቡ እንደሚችሉ እምነት አለ።

አደም (ዶ/ር) በአረብ ሊግ አገራት ለግብፅ ድጋፋቸውን ሲያሳዩ ቆይተዋል ይላሉ። እርግጥ ነው ቱርክ ከግብፅ ጋር ያላት ስምምነት ሰላማዊ ያልነበረ ቢሆንም አሁን ግን ረገብ ያለ ይመስላል ይላሉ። ስለዚህ ለግብፅ ሊያደሉ እንደሚችሉ እምነት አላቸው።ኢትዮጵያ በድርድሩ ላይ ያላትን ጫና ከፍ ለማድረግ መጀመሪያ አገር ውስጥ ያለውን አለመረጋጋት መቀልበስ እንዳለባት ያምናሉ። አለበለዚያ በድንበሩም ሆነ በግድቡ ዙሪያ የአቋም ለውጥ ሊመጣ እንደሚችል ይሰጋሉ። ይህ ደግሞ ዞሮ ዞሮ የአገር ቤት አለመረጋጋቱን ያሰፋዋል ባይ ናቸው- አደም።

ምሁሩ ለዚህ ነው ኢትዮጵያ ያላት አንዱ አማራጭ የአገር ውስጥ ፖለቲካውን ማረጋጋት ነው የሚሉት። የተረጋጋች ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲም ረገድ ለውጥ ልታመጣ ትችላለች በማለት ያጠናክራሉ።በሦስቱ አገራት መካከል ያለው የግድብ ድርድር አሁንም መፍትሄ አላገኘም። ምናልባት በሚቀጥሉት ድርድሮች አገራቱ ስምምነት ላይ ይደርሱ ይሆን? ገና ወደፊት የሚታይ ነው።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *