ኤርትራ በትግራይ ክልል ውስጥ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ያስገባቻቸውን ወታደሮቿን ለማስወጣት ከስምምነት መደረሱን የኢትዮጵያ መንግሥት ገለጸ።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ፣ አርብ ጠዋት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሐሙስ ዕለት አሥመራ የገቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባደረጉት ውይይት ኤርትራ ሠራዊቷን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት ተስማማታለች።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የድንበር አካባቢዎቹን ተረክቦ ጥበቃውን ወዲያውኑ እንደሚጀምር ሁለቱ መሪዎች ከስምምነት ደርሰዋል። በተጨማሪም ሁለቱ አገራት በመተማመንና በመልካም ጉርብትና ላይ በተመሰረተ መንፈስ የጀመሩትን የሁለትዮሽ ግንኙነትና ምጣኔ ሃብታዊ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።

በተለይም በትግራይ ክልል ውስጥ ባለው ሕዝብና ከድንበር ባሻገር ኤርትራ ውስጥ በሚገኘው ሕዝብ መካከል መተማመንን መሰረተ ባደረገው መልኩ ግንኙነቱ እንዲሻሻሻል ማድረግ አስፈላጊ ነው ብሏል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትግራይ ከተከሰተው ወታደራዊ ግጭት ጋር ተያይዞ የኤርትራ መንግሥትና ሕዝብ ሠራዊታቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በገባበት ጊዜ ላደረገለት ድጋፍ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ሲያመሰግኑ ቆይተዋል።

ማክሰኞ ዕለት ከአገሪቱ ምክር ቤት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስና ማብራሪያ ወቅት ይህንኑ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።ጥቅምት መጨረሻ ላይ የህወሓት ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በሠሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ የኤርትራ ሠራዊት በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ እንደሆነ በተለያዩ ወገኖች ሲገለጽ ቆይቷል።

ነገር ግን ሁለቱ አገራት የኤርትራን ሚና ሲያስተባብሉ ቆይተው ከቀናት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በድንበር አካባቢ ባሉ ቦታዎች ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሠራዊት ከጀርባው ጥቃት እየተፈጸመበት የድንበር አካባቢውን መጠበቅ አስቸጋሪ ስለሆነበት የኤርትራ ጦር ድንበር አልፎ መግባቱን በማብራሪያቸው ላይ ተናግረዋል።

አክለውም ሠራዊቱ የህወሓት ኃይሎችን ለመዋጋት ወደ ሌሎች የትግራይ አካባቢዎች በመንቀሳቀሱ ክፍተት እንደተፈጠረና የኤርትራ መንግሥትም በዚህ ክፍተት ጥቃት እንዳይፈጸምበት በመስጋቱ ወደ ስፍራዎቹ መግባቱን ገልጸዋል። ቢሆንም ግን የኢትዮጵያ ሠራዊት ሌላውን ተልዕኮ ሲያጠናቅቅና አካባቢዎቹን መቆጣጠር ሲችል የኤርትራ ኃይሎች ከስፍራው እንደሚወጡ ተናግረው ነበር።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾችና ድርጅቶች በተደጋጋሚ ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ክልል ውስጥ ከድንበር አካባቢዎች ባሻገር በሚገኙ ስፍራዎች ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ግድያና ዘረፋዎችን መፈጸሙ ሲገለጽ የቆየ ሲሆን ኤርትራ ግን ይህንን ክስ ውድቅ አድርጋዋለች።

የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ውስጥ ተፈጸሙ ከተባሉ ግድያዎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ አሜሪካንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሠራዊቱ ከክልሉ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ቆይተዋል።ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው የሚያደርሱትን ጥፋቶች መንግሥታቸው ፈጽሞ እንደማይቀበለው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሠራዊት መቀለን ተቆጣጥሮ የህወሓት አመራሮችን ከሥልጣናቸው ከማስወገዱ በፊት የህወሓት ኃይሎች በአሥመራና በሌሎች የኤርትራ ከተሞች ላይ የሮኬት ጥቃቶች ማድረሳቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም በከተሞቹ ነዋሪዎችና በዲፕሎማቶች ቢረጋገጥም በወቅቱ ከኤርትራ ባለሥልጣናት በኩል የተሰጠ ምላሽ አልነበረም።

የጠቅላይ ሚኒስትር የአስመራ ጉብኝት

ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉዞ በትግራይ ክልል ውስጥ ወታደራዊ ግጭት ከተከሰተ በኋላ ሁለተኛው ነው።የመጀመሪያ ግጭቱ በተጀመረበት ወቅት ጥቃት ተሰንዝሮበት ወደ ኤርትራ የተሻገረውን የኢትዮጵያን ሠራዊት ለመጎብኘትና መልሶ ለማደራጀት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጦር ጄነራሎቻቸው ጋር ወደ ኤርትራ የተጓዙበት ነበረ።

ይህ ይፋዊ ያልበረ ጉዞ በወቅቱ ያልተነገረ ሲሆን የፌደራሉ ሠራዊት ከሦስት ሳምንታት ዘመቻ በኋላ የክልሉን ዋና ከተማ ከተቆጣጠረ በኋላ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገሪቱ ምክር ቤት ስለግጭቱ አጠቃላይ ሁኔታ ማብራሪያ በሰጡበት ጊዜ መግለጻቸው ይታወሳል። የአሁኑ ጉብኝት ግን የኤርትራ ስም በተደጋጋሚ የተነሳበት ትግራይ ውስጥ የተካሄደው ወታደራዊ ግጭት ከተከሰተ በኋላ የተደረገ ይፋዊ ጉዞ ነው።

የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገፃቸው እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና አብሯቸው የተጓዘው ልዑክ አሥመራ ሲደርስ የአገሪቱ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ኤርትራ ያመሩት ከመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቀንዓ ያደታ እንዲሁም ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይ ጋር መሆኑ ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ እና በቀጠናው ልማት ዙሪያ እንደሚነጋገሩ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ የማነ ገልጸዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ ለሁለት አስርት ዓመታት የቆየውን ፍጥጫቸውን ፈትተው ሠላም ካወረዱ በኋላ የሁለቱ አገራት መሪዎች ከዚህ በፊት ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን አድርገዋል።

በትግራይ ውስጥ የተከሰተው ግጭት ከመቀስቀሱ ጥቂት ጊዜ ቀደም ብሎ የመጨረሻውን ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሲሆኑ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል የተለያዩ ቦታዎችን ጎብኝተው እንደነበር ይታወሳል።በትግራይ ውስጥ ጥቅምት መጨረሻ ላይ በትግራይ ውስጥ በተከሰተው ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ህይወት ማለፉ ሲነገር፤ ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች ድንበር ተሻግረው ወደ ሱዳን ሸሽተዋል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት ደግሞ ግጭቱን በመሸሽ ተፈናቅለው በክልሉ ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *