በትግራይ ክልል ያለው ውጥረት አሁንም አልረገበም። የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክሶች እየተዘገቡ ነው። አለመረጋጋቱ ሊቀጥል እንደሚችልም ስጋት አለ።
የፕሮፓጋንዳ ጦርነት በማኅበራዊ ድር አምባዎች እየተካሄደ ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ሐሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎችን በማሰራጨት ተጠምደዋል።
ቢቢሲ እየተሰራጩ የሚገኙ ሐሰተኛ መረጃዎችን አጣርቷል።
ሐሰተኛው ዲፕሎማት
ኦፊሴላዊው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ቀደም ሲል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ዲፕሎማት የነበሩ ግለሰብ የኢትዮጵያን ዓላማ በመደገፍ በትዊተር ገጻቸው ጽፈው እንደነበር ዘግቧል።
ድርጅቱ በፌስቡክ ገጹ ጆርጅ ቦልተን (George Bolton) የተባሉ እና በትዊተር ገጻቸው @GboltonUN የሚል መለያ ያላቸው ግለሰብ ያሰፈሩትን ጽሑፍ አጋርቷል።
የፖለቲካ ተንታኝ እና የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን እንደሆኑ የሚገልፁት “ጆርጅ ቦልተን” የትግራይን አመራር “ጨካኝ” ሲሉ የሚገልጹ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል። በተጨማሪም አሜሪካ ግጭቱን በመመለከተ ጣልቃ መግባት የለባትም ብለዋል፡፡
ይኸው ተመሳሳይ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የአማርኛ እና የትግርኛ የፌስቡክ ገጾች ላይ ሰፍሯል፡፡
የእነዚህ ጽሑፎች ችግር “ጆርጅ ቦልተን” የሚባሉ ሰው አለመኖራቸው ብቻ አይደለም። ቢቢሲ ስለ ግለሰቡ የሕይወት ታሪክ የተጻፈ ምንም አይነት መረጃ በድረ ገጽ ላይ አላገኘም። ቀደም ሲል በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ሲሠሩ መቆየታቸውን የሚያሳይ ማስረጃም አላገኘንም፡፡
ጥቅም ላይ የዋለው ፎቶም እንዲሁ የውሸት ነው። ፋይናንሻል ታይምስ ባደረገው ምርመራ በሰው ሠራሽ ክህሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) የተፈጠረ የሰዎች ምስል ውስጥ ተመሳሳይ ፎቶ አግኝቷል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከዚህ የትዊተር መለያ ጋር የሚገናኙትን መረጃዎች በሙሉ ከገጹ አንስቷል፡፡
ከቀናት በኋላ ይኸው የትዊተር መለያ ፎቶውን ወደ የአሁኑ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ቀይሮታል፡፡
አሳሳቹ የፈረሰ ቤተክርስቲያንምስል
በትግራይ የተፈጠረው ግጭት አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ በርካታ ሕንፃዎች እንዲወድሙ ምክንያት ሆኗል፡፡
በፈረሰ ህንፃ አጠገብ ሲጸልዩ የሚታዩ ሁለት እናቶች ምስል በማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ በስፋት የተሰራጨ ሲሆን፤ ፎቶው በእነዚህ ዘገባዎች ላይ እንደተጠቀሰው ከትግራይ የተገኘ አይደለም፡፡
ምስሉን ላይ በተደረገ ምርመራ (reverse image search) መሠረት ይህ ፎቶ በጎርጎሮሳዊያኑ ሐምሌ 2018 ፌስቡክ ላይ የተለጠፈ ሲሆን፤ ይህም ከወቅቱ የትግራይ ግጭት ቀድሞ ብሎ መሆኑ ነው፡፡
ምስሉ በትራቭል ኖትስ ድረ ገጽ ላይ የሚገኝ ሲሆን ፎቶው ከኤርትራ፣ አዲ ኬህ ከተማ የተገኘ መሆኑን ያትታል፡፡
ከ20 ዓመታት በፊት በጎርጎሮሳዊያኑ 1999 በኢትዮጵያ ኃይሎች በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት ቤተ ክርስቲያን የወደመበት ቦታ ነው፡፡
ከዚያ ጥቃት በኋላ የተነሱት ምስሎችን ያገኘን ሲሆን፤ በፎቶው ላይ ከሚታየው ጋር የሚመሳሰል የተጎዳ ህንፃ በግልፅ ይታያል።
የተጠሙት ልጆች
ሁለት ወንዶች ልጆች ከጨቀየ መሬት ውሃ ሲጠጡ የሚያሳይ ፎቶ በድረ ገጽ ላይ በስፋት ተሰራጭቷል። ስለ ጉዳዩ የተሰጡ አስተያየቶች ምስሉ በትግራይ እጅግ አስከፊ የሆነውን ሰብዓዊ ቀውስ ያሳያል ይላሉ፡፡
አንደኛው ጽሑፍ “በትግራይ ስለተራቡት ሰዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚሆን ምስል” ይላል።
ፎቶው ግን ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል እንጂ ከትግራይ የተገኘ አይደለም፡፡
ፎቶውን ፌስቡክ ላይ የለጠፈውን ሰው ወደ ኋላ ተመልሰን ስናጣራ ሰይድ አብዲራምን ሆኖ አገኘነው። ሰይድ ለቢቢሲ እንደተናገረው ፎቶውን ያነሳው አውል በሚባል መንደር ውስጥ ነው፡፡
የአሜሪካ ቡድን ስለ ጭፍጨፋምርመራ አላደረገም
በታሪካዊቷ አክሱም ከተማ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ኃይሎች የደረሰውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በጎርጎሮሳዊያኑ 2020 ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ክሱን “ሐሰተኛ” ሲል አጣጥሏል።
በመቀጠልም አንድ የሄራልድ ጋዜጣ ዘገባ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት (ዩኤስኤይድ) የላከው የምርመራ ቡድን አክሱምን መጎብኘቱን ገልጿል። ተጨፈጨፉ የተባሉ ሰዎችን በተመለከተ “አንድም የቀብር ስፍራ ያላገኘ ሲሆን ከዘመዶቻቸውም ጋር መገናኘት አልቻለም” ይላል ዘገባው።
ነገር ግን ዩኤስአይዲ በጭራሽ የምርመራ ቡድን ወደ አክሱም አልላኩም ብሏል፡፡
“ዩኤስኤይድ በአክሱም ስለተፈጸሙ ድርጊቶች ምርመራ አላደረገም። የምርመራ ቡድንም ወደ አካባቢው አልላከም” ሲል በትዊተር ገጹ ባስተላለፈው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ምንጭ – ቢቢሲ