በአክሱም ከተማ በኤርትራ ወታደሮች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀል ወይም የጦር ወንጀል ሊሆን ይችላል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
ኮሚሽኑ በአክሱም ከተማ ውስጥ ስለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች ያካሄደው የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ ሪፖርቱ ላይ እንዳመለከተው የተፈጸሙት ድርጊቶች “ተራ ወንጀሎች ሳይሆኑ የዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችና መርሆዎችን የሚጥሱ ናቸው” በማለት በአጠቃላይ በክልሉ ውስጥ የተሟላ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ምርመራ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
በዚህም በኤርትራ ሠራዊት በአክሱም ከተማ ውስጥ የፈጸመው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት “ምናልባት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ወይም የጦር ወንጀል ሊሆን ስለሚችል” ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።
በከተማዋ በግጭቱ ተሳታፊ ያልነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሙን አመልክቶ በወታደራዊ ኢላማነት አስፈላጊነታቸው ሊገመገሙ የማይችሉ የሰላማዊ ሰዎች ንብረቶች፣ በሐይማኖት ተቋማትና በሆስፒታሎች ላይ ጭምር ሆን ተብሎ ዝርፊያና ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ሲያወጡ መቆየታቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎም የተለያዩ አገራት እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ጥሰቶቹ እጅጉን እንደሚያሳስባቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በምርመራው እንደደረሰበት በተለይ ከኅዳር 19 እስከ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም በነበሩት ሁለት ቀናት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደተፈጸሙ ጠቅሶ “ከአንድ መቶ በላይ ሰላማዊ ሰዎች በወቅቱ በአክሱም ከተማ በነበሩ የኤርትራ ወታደሮች መገደላቸውን” ገልጿል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው በዚህ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ላይ እንዳመለከተው ያነጋገራቸው የአክሱም ከተማዋ ነዋሪዎች፣ የተጎጂ ቤተሰቦችና የአይን እማኞች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች “ልጆቻቸው፣ ሚስቶቻቸውና እናቶቻቸው ፊት ጭምር በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉ አስረድተዋል” ብሏል።
በዚህ ጥቃት የተገደሉት የአክሱም ከተማ እና አከባቢው ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ጦርነት ሸሽተው በከተማዋ የተጠለሉ ተፈናቃዮች እንዲሁም የኅዳር ፅዮን ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓልን ለማክበር ከተለያየ ቦታዎች የመጡ ሰዎች ጭምር እንዳሉበት ሪፖርቱ አመልክቷል።
ኮሚሽኑ ጨምሮም በዚህ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ላይ የጠቀሳቸው አሃዞች በከተማው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር የሚያመላክት ሳይሆን በምርመራው ወቅት ለማረጋገጥ የቻለውን የሰላማዊ ሰዎች ጉዳት ብቻ የሚጠቁም መሆኑን ገልጿል።
ከየካቲት ወር አጋማሽ በኋላ የምርመራ ባለሞያዎቹን ወደ አክሱም ከተማ በማሰማራት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የዓይን ምስክሮችንና የሐይማኖት መሪዎችን በማነጋገር በከተማዋ ስለተፈጠረው ክስተት መረጃዎችን እንዳሰባሰበ ኢሰመኮ ገልጿል።
ሪፖርቱ ጨምሮም በክልሉ የተጣለውን የሰዓት እላፊ ገደብን ለማስከበርና በደኅንነት አጠባበቅ ምክንያት በመንግሥት ፀጥታ ኃይሎች የሚወሰደው የኃይል እርምጃ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ በሰዎች ላይ ሞትና የአካል ጉዳትን ማስከተሉን ጠቅሶ በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም በበኩሉ ተከሰቱ የተባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ በእራሱ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጾ የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት በምርመራው ውስጥ እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። ይህንንም የመንግሥት ውሳኔ “ትክክለኛ እርምጃ” ሲሉ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ገልጸውታል።
ጨምረውም “አብዛኛው የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በሕይወት መስዋዕትነት ጭምር አገራቸውንና ሕዝቡን የሚያገለግሉ ቢሆንም፤ በተወሰኑ የሠራዊቱ አባላት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ምርመራ ተገቢውን እገዛ ማድረግ ይገባል” ብለዋል።
ከኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በጥምረት የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እንዲመረምር ጥሪ የቀረበለት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በመርመራው ሂደት ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆኑንና ለዚህም እየተዘጋጀ መሆኑን ባለፈው ሳምንት አሳውቆ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መጋቢት 14/2013 ዓ.ም በአገሪቱ ምክር ቤት ቀርበው እንደተናገሩት ግጭቱ ከተጀመረ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በዚህ ወቅትም በትግራይ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ ገልጸው ነገር ግን እንዚህ ድርጊቶች መንግሥታቸው ችላ እንደማይላቸውና ምርመራ በማድረግ ጥፋተኞች ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
ከወራት በፊት በታሪካዊቷ የአክሱም ከተማ በኤርትራ ወታደሮች አማካይነት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች ከተለያዩ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በኩል መውጣቱ ይታወሳል።
የኤርትራ መንግሥት ግን ወታደሮቹ ፈጽመውታል በሚል ስለቀረቡ በይፋ የሰጠው ምላሽ ባይኖርም የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ የማነ ገብረ መስቀል ግን በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሯቸው መልዕክቶች ክሶቹን ማጣጣላቸው ይታወሳል።
የግጭቱ የተቀሰቀሰው በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የህወሓት ኃይሎች ጥቃት ከሰነዘሩ በኋላ ነበር። ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ አዘው የፌደራል ሠራዊቱ ወደተለያዩ የትግራይ ክልል አካባቢዎች መሰማራቱ ይታወሳል።
በዚህም ሠራዊቱ በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ዋና ዋና የትግራይ ከተሞችን በመቆጣጠር የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን ሲቆጣጠር ለ30 ዓመታት ያህል ትግራይን ሲያስተዳድር የቆየው ህወሓት ከስልጣኑ ተወግዶ ከአመራሮቹ መካከል የተወሰኑት ሲገደሉ ሌሎች ደግሞ የተያዙ ሲሆን የቀሩት የት እንዳሉ አይታወቅም።
ወታደራዊ ግጭቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ግድያን፣ ጾታዊ ጥቃትንና ዘረፋን ጨምሮ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች የወጡ ሲሆን በዚህ ድርጊት ውስጥም የኤርትራ ወታደሮች በስፋት ስማቸው ሲጠቀስ ቆይቷል።
ከተፈጸመው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በተጨማሪ በግጭቱ ሳቢያ በርካታ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ከ60 ሺህ በላይ ድንበር ተሻግረው ወደ ሱዳን ተሰደዱ መሆናቸውንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው በተለያዩ ቦታዎች እንደሚገኙ የእርዳታ ድርጅቶች ገልጸዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ