በዛሬው ዕለት፣ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም ለስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በመላው አገሪቱ ይጀመራል።

ምርጫ ቦርድ ግንቦት 28 እና ሰኔ 5/2013 ዓ.ም ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ 50 ሚሊዮን መራጮች ይሳተፋሉ ብሎ እንደሚጠብቅ ከዚህ ቀደም አስታውቆ ነበር።

በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለመወዳደር 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ማስመዝገባቸውን ምርጫ ቦርድ ይፋ ያደረገ ሲሆን እንዲሁም 125 ግለሰቦች በግል ለመወዳደር ተመዝግበዋል። 10 ሳምንት ብቻ በቀረው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እስካሁን 8209 እጩዎችን ለክልል እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መመዝገባቸው ታውቋል።

በመራጭነት ለመመዝገብ ምን ያስፈልጋል?

እንደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ ከሆነ በምርጫ ሕጉ አንቀጽ 18 አዋጅ ቁ. 1162/2011 መሠረት አንድ ሰው በመራጭነት መመዝገብ የሚችለው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሆነ እና በምዝገባው ዕለት እድሜው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆነ ነው። በተጨማሪም ለምዝገባ በቀረበበት የምርጫ ክልል ቢያንስ ለ6 ወራት የኖረ መሆን ይኖርበታል።

ምርጫ ቦርድ በድረ ገፁ የመራጮች ምዝገባን በማስመልከት ባስቀመጠው መረጃ መሰረት በተለያየ ምክንያት ራሳቸውን ችለው መመዝገብ የማይችሉ ሰዎች በረዳቶቻቸው አማካኝነት በአካል ተገኝተው መመዝገብ እንደሚኖርባቸው አስታውቋል።

ለመራጭነት ለመመዝገብ ምን ምን ማሟላት ያስፈልጋል?

እንደ ምርጫ ቦርድ መረጃ ከሆን በመራጭነት ለመመዝገብ የሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ ወደ ምርጫ ጣቢያው ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ ይዞ በአካል መቅረብ ይኖርበታል። የቀበሌ መታወቂያ ካርድ የሌለው ግለሰብ ደግሞ ያልታደሰም ቢሆን ፓስፖርት ይዞ መቅረብ እንደሚችል ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው መረጃ ላይ ተገልጿል።

የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ማቅረብ ያልቻሉ ተመዝጋቢዎች በቅርቡ ፎቶግራፍ ተደርጎበት የተሰጠ የመንጃ ፈቃድ፣ የመኖሪያ የምስክር ወረቀት፣ ከውትድርና የተገለሉበት ሰነድ፣ የትምህርት ቤት መታወቂያና የመሳሰሉ የመለያ ማስረጃዎች ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች በማይኖሩበት ወቅት መዝጋቢዎች የምርጫ ጣቢያው ለረዥም ጊዜ መኖራቸው የተረጋገጠ ሦስት ነዋሪዎች በሚሰጡት ምስክርነት ማስረጃ አልባውን ተመዝጋቢ ለመለየት ከተቻለ ቃለ ጉባኤ ተይዞ ምዝገባ ይከናወናል። በገጠር አካባቢ በባህላዊና ልማዳዊ ዘዴ ተመዝጋቢውን ለመለየት የሚቻልበት ሁኔታ ካለ እንዲሁ ቃለ ጉባኤ በመያዝ ምዝገባው መከናወን እንደሚቻል ምርጫ ቦርድ አመልክቷል።

ማን ለመራጭነት ሊመዘገብ አይችልም?

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዕምሮ ህመም ምክንያት የመወሰን አቅም የሌለው መሆኑ ስልጣን ባለው አካል ወይም በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠበት ሰው ለመራጭነት መመዝገብ እንደማይችል በሕግ ተደንግጓል። እንዲሁም የመምረጥ መብቱ በሕግ ወይም አግባብ ባለው ሕግ መሠረት በፍርድ ቤት ውሳኔ የተገደበባቸው ሰዎች በመራጭነት ሊመዘገብ አይችሉም።

ለመራጭነት የት መመዝገብ ይቻላል?

አንድ መራጭ መመዝገብ የሚችለው በአንድ የምርጫ ጣቢያ ላይ ብቻ ነው። ይህም በሚኖርበት ቀበሌ ላይ በተሰየመ የምርጫ ጣቢያ ላይ መሆኑ በምርጫ ቦርድ ተገልጿል።

ከዚያ ባሻገር በአርብቶ አደር አካባቢዎች የምርጫ ጣቢያ ሊኖር የማይችልባቸው አጋጣሚዎች ሲኖሩ እንደ አስፈላጊነቱ አዳዲስ የምርጫ ጣቢያዎች በማቋቋም የመራጮች ምዝገባ ሊከናወን እንደሚችል ምርጫ ቦርድ ይገልጻል።

በዚህ ምርጫ በመላው አገሪቱ ድምጽ የሚሰጡባቸው ከ50 ሺህ በላይ የምርጫ ጣቢያዎች፣ ከ152 ሺህ በላይ የመራጮች ምዝገባን የሚያከናውኑ ባለሙያዎችና ከ254 ሺህ በላይ ምርጫ አስፈጻሚዎ እንደሚሰማሩ ተነግሯል።ዛሬ የተጀመረውና ለአንድ ወር ያህል የሚቆው የመራጮች ምዝገባ የሚጠናቀቀው ሚያዚያ 15/2013 ዓ.ም መሆኑን የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ ያሳያል።

ምርጫ 2013

ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ወደዚህ ዓመት ከተሸጋገረ በኋላ፤ በመጪው ግንቦት ማብቂያና በሠኔ ወር መጀመሪያ ላይ ለማካሄድ የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶለት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ዝግጅት እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ከትግራይ ክልል በስተቀር በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ይካሄዳል በተባለው በዚህ ምርጫ 50 ሚሊዮን መራጮች ማለትም ከአገሪቱ ሕዝብ ወደ ግማሽ የሚጠጋው ድምጽ በመስጠት ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምርጫ ቦርድ ገልጿል።

በምርጫው ከሚሳተፉት 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዕጩዎች በማቅረብ በኩል ገዢው ፓርቲ ብልጽግና 2432 ዕጩዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚው መሆኑ በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።

ከዚህ አንጻር ከብልጽግና በመከተል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ዕጩዎች በማስመዝገብ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 1385 ዕጩዎችን እንዲሁም እናት ፓርቲ ደግሞ 573 ዕጩዎችን አስመዝግበዋል።ሦስቱን ፓርቲዎች ጨምሮ በምርጫው ለመወዳደር በፓርቲና በግል ለመወዳደር ከስምንት ሺህ ሁለት መቶ በላይ ዕጩዎች መመዝገባቸውን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *