በኢትዮጵያ ያለው የኮሮናቫይረስ ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ገልጿል። በበሽታው የሚያዙ፣ በጽኑ የሚታመሙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሌላው ጊዜ በተለየ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።

የጥንቃቄ ጉድለት ብዙዎችን ለወረርሽኙ በማጋለጥ ዋጋ እያስከፈለ ነው። ከአሜሪካ ቤተሰብ ጥየቃ የመጡ ሁለት ግለሰቦችን ጨምሮ አስር የአንድ ቤተሰብ አባላት በጥንቃቄ ጉድለት ሳቢያ እንዴት ለበሽታው እንደተጋለጡ ታሪካቸውን ለቢቢሲ ነግረዋል።

አቶ ሰለሞን ድረስ በቅርቡ ነው ከሚኖሩበት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት። እንደማንኛውም ዓለም አቀፍ መንገደኛ ከበረራቸው ዕለት ቀደም ብሎ የኮሮናቫይረስ ምርመራ አድርገዋል። ውጤቱ ነጋቲቭ በመሆኑ ነው ጉዟቸውን ማድረግ የቻሉት። አዲስ አበባ በደረሱ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ዘመዶቻቸውን እና ጓኞቻቸውን አግኝተዋል። “ኮሮናቫይረስ የሌለባት የምትመስለው አዲስ አበባ ጥቂት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የሚያደርጉ ሰዎች ባይታዩ የተለመደው የኑሮ ሂደት የቀጠል ይመስላል” ይላሉ። የአቶ ሰለሞንም በሚኖሩበት አሜሪካ አስገዳጅ ስለሆነ የሚያደርጉትን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጥለው አገሬውን ለመምሰል ጊዜ አልፈጀባቸውም። በጥቂት ቀናት ውስጥ ግን ነገሮች በፍጥነት መቀያየር ጀመሩ።

“መጀመሪያ ላይ ከባድ ድካም ነበር ይሰማኝ የነበረው” ሲሉ የህመማቸውን ጅማሬ ይገልጻሉ። በመጀመሪያው ቀን ጉዞው እና ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ያደረጉት እንቅስቃሴ ያደከማቸው ቢመስላቸውም ሁለተኛው ቀን ላይ ድካሙ “ከሚገለጸው በላይ ሆነ። መጀመሪያ ከነበረኝ ድካም እጅግ የከበደ ነበር። ከአልጋ ወርጄ መጸዳጃ ቤት መሄድ ራሱ ፈታኝ ሆነብኝ” ሲሉ ሁኔታውን ይገለጻሉ። በተመሳሳይ ዘመድ ጥየቃ ከውጭ የመጡት አጎታቸውም “ከፍተኛ ድካም” ይሰማቸው ይጀምራል። ሁኔታው ስጋት ያሳደረባቸው አቶ ሰለሞን ከአጎታቸው ጋር በመሆን ወደ ህክምና ማዕከል በማቅናት ምርመራ ያደርጋሉ። ውጤቱ ግን ፍጹም ያልጠበቁት ነበር – ኮሮናቫይረስ ተገኘባቸው።

ህመምና ጭንቀት

“ከድካም በስተቀር ምንም የተለየ ምልክት ስላልነበረን ኮሮናቫይረስ ይሆናል የሚል ግምት አልነበረንም። ምርመራም ያደረግነውም በአጋጣሚ ነበር። ድካሙ እጅግ ከባድ ሲሆን ለተከታታይ ቀናትም የቀጠለ ነበር። አቶ ሰለሞንም ሆኑ አጎታቸው ራሳቸውን በመለየት የጤናቸውን ሁኔታ መከታተል ጀመሩ። ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ከእርሳቸው በላይ ያስጨነቃቸው የአጎታቸው ሁኔታ ነበር። የአጎታቸው ሁኔታ ያሳሰባቸው ከዕድሜያቸው እና ባለባቸው ተጓዳኝ ህመም ምክንያት ነው። “የተለያየ ክፍል በመሆናችን ያለኝን አቅም ሰብሰብ አድርጌ እሱ [አጎቴ] ያለበትን ሁኔታ እጠይቃለሁ።” ይላሉ።

ድካሙ እየጨመረ የሚወስዱት ምግብ እየቀነሰ ሄዶ ምግብም ሆነ ውሃ መውሰድ የማይችሉበት ደረጃ ደረሱ። ይህ ደግሞ ሌላ ችግር ሆነ። “የምንበላውም ሆነ የምንጠጣው ነገር በሙሉ ይወጣ ነበር” ሲሉ ሁኔታውን ያስታውሳሉ። “የምንወስደው ነገር በሙሉ ስለሚወጣ በሽታውን ለመቋቋም እንዲረዳን ምግብም ሆነ ማስታገሻ መድኃኒቶችን ለመውሰድ ባለመቻላችን ከቀን ወደ ቀን እየተዳከምን ሄድን” ይላሉ አቶ ሰለሞን።

“እኔም ሆንኩኝን አጎቴ ከመዳከማችን የተነሳ መቃዠት ጀምረን ነበር።. . . አንዳንዴ በእውን የማይመስሉ ነገሮችን እንመለከታለን። ከመተኛት ውጪ ምንም የማድረግ ጉልበት አልነበረንም።” ሲሉ ረዥሙን ሰዓት በእንቅልፍ ያሳልፉ እንደነበር ይናገራሉ። ከህክምና ባለሙያዎች በተነገራቸው መሠረት ቤት ውስጥ ሆነው በምግብ ምትክ ጉልኮስ እንዲሰጣቸው ተደረገ። በዚህ መልኩ ከቫይረሱ ጋር ትንቅንቁ ቀጠለ።

ተጨማሪ ታማሚዎች

ብዙም ሳይቆይ ግን ታናሽ ወንድማቸውም የማያቋርጥ ሳል እንዳለበት በማወቃቸው እንዲመረመር ይጠይቁታል። “ወንድሜን እኔም አጎታችንም ኮሮናቫይረስ እንዳለብን ከማወቃችን ከሁለት ቀናት በፊት አግኝተነው ነበር። ሳል ስለጀመረው ምርመራ እንዲያደርግ ብንመክረውም ‘ጉንፋ ነው’ የሚል ምላሽ በመስጠት ሳይመረመር ይቀራል።” የወንድማቸው ሳል ግን እንደዚህ ቀደሙ ቀላል የሚባል ባለመሆኑ እና የድካም ስሜት በማሳየቱ ምርመራ አደረገ። በውጤቱ ቫይረሱ ተገኘበት። በቀናት ልዩነት ሦስተኛው የቤተሰቡ አባል በኮሮናቫይረስ ተያዘ።

በዚህ ወቅት እነአቶ ሰለሞን ጤናቸው መሻሻል የጀመረበት እና “አሁን እንደማንሞት እርግጠኛ ሆንን” ያሉበት ጊዜ ነው። ምግብ በመጠኑም ቢሆን ይመገባሉ። ውሃ ይጠጣሉ። ማስታገሻ መድኃኒቶችንም መውሰድ ጀምረዋል። ከአምስት ቀናት በፊት አብዛኛዎቹ የቤተሰባቸው አባላት ተሰባስበው ስለነበር ሁሉም እንዲመረመሩ ይደረጋል። ቤተሰቡ በነበረው ስጋትና ንክኪ ምክንያት ሁሉም ቢመረመር ለጥንቃቄ እንደሚረዳ በማሰብ “ወደ ሃያ የሚጠጉ የቤተሰቦቼ አባላትና ከእኛ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች በሙሉ በተለያዩ ቀናት ተመረመሩ” ይላሉ አቶ ሰለሞን።

ነገር ግን ከአቶ ሰለሞን እና አጎታቸው ጋር ግንኙነት ኖሯቸው ለምርመራው ፈቃደኛ ያልሆኑም ነበሩ። “እስካላመመኝ ወይም ምልክት እስካላሳየሁ ለምን እመረመራለሁ?’ የሚል ነበር ምክንያታቸው” ሲሉ ይገልጻሉ። በዚህ መካከል የአንደኛዋ እህታቸው ውጤት ኮቪድ-19 እንዳለባት የሚያመለክት ሆነ። በዚህም ወረርሽኙ የተገኘባት አራተኛ የቤተሰቡ አባል ሆነች። “ምንም ምልክት ያላሳየች የመጀመሪያዋ የቤተሰባችን አባል ነች” ይላሉ።

እህታቸው ተጓዳኝ በሽታ ስላለባት ስጋት ቢፈጠርም ምንም ህመምም ሆነ ምልክት ሳታሳይ ቀጠለች። የተመረመሩት የቤተሰባቸው አባላት ቀስ በቀስ ሲመጣ ቫይረሱ ያልተገኘባቸው እንዳሉ ስንረዳ በትንሹም ቢሆን ጭንቀታችንን ቀለል አድርጎት ነበር። ከቀናት በኋላ ግን ያልተጠበቀ ውጤት መጣ። “እኔና አጎቴ ተመርምረን ውጤት ባወቅን በሳምንቱ ሌላኛው ወንድሜ በኮሮናቫይረስ መያዙ ተነገረው። ከወንድሜ በተጨማሪ ሚስቱ እና ልጆቹም መያዛቸው አስደንጋጭ ነበር” ይላሉ አቶ ሰለሞን። ይህም በቤተሰቡ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ወደ ዘጠኝ ከፍ አደረገው።

ውጤት ጥበቃ

አስደንጋጩ ነገር ናሙና ከሰጡ በኋላ ለአራት ቀናት ያህል ውጤት ባለመድረሱ የተለመደውን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር የሰነበቱት። “ውጤቱ ሲዘገይ የተለመደውን እንቅስቃሴዬን ቀጥዬ ነበር” ይላሉ የአቶ ሰለሞን ወንድም የሆኑት አቶ ሲሳይ። “ቤተሰቦቼን በተደጋጋሚ አግኝቻለሁ። ሥራ ቦታዬ ላይ ለአንድም ቀን ሳላዛንፍ ተገኝቻለሁ። ባለቤቴም እየሠራች ነበር። ሦስቱም ልጆቼ አንድም ቀን ከትምህርታቸው አልቀሩም ነበር” ብለዋል። በዚህ ምክንያትም የኮሮናቫይረስ ምርመራ ያደረጉ ቤተሰቦቻቸው በሦስት ቀን ልዩነት በድጋሚ ናሙና ለመስጠት ተገደዱ።

“የምርመራው ውጤት መዘግየት ቤተሰቡ ድጋሚ እንዲመረመር ከማስገደዱም በተጨማሪ አገርንም ዋጋ የሚያስከፍል ነው” ይላሉ አቶ ሲሳይ ሁኔታው ለቫይረሱ መስፋፋት ያለውን ሚና በመግለጽ። ውጤቱ ከታወቀ በኋላ የአቶ ሲሳይ ቤተሰብ አባላት ምንም ምልክትም ሆነ ህመም ሳይኖራቸው ራሳቸውን ለይተው ቆዩ። “የመጀመሪያዎቹ ቀናት አካባቢ ስጋት ነበረብን። ‘ልጆቼን ቢያማቸውስ? ባለቤቴስ ብትታመም?’ እያልኩ እጨነቅ ነበር። ከራሴ በላይ የእነሱ ሁኔታ ያሳስበን ነበር” ይላሉ። “የህክምና ባለሙያዎች በየጊዜው እየደወሉ ያለንበትን ሁኔታ ይጠይቁን ነበር። ለሁለት ሳምንት ራሳችንን ለይተን ከቆየን በኋላ ወደ መደበኛው ህይወታችን መመለስ እንደምንችል ተነገረን” ብለዋል።

መዘናጋት ያስከተለው ጥንቃቄ ጉድለት

ህይወት በተለመደው መንገድ ቢቀጥልም ኮሮናቫይረስ ኢትዮጵያ መግባቱ በተገለጸ በመጀመሪያዎቹ ወራት የነበረው ጥንቃቄ ቀርቶ ሁሉም በተለመደው አኗኗር መቀጠሉ ምክንያት እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል። እሳቸውም ሆኑ ዘመዶቻቸው ለወራት ያደረጉትን ጥንቃቄ በማላላት የተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ተገኝተዋል። “ከቤት ውጭ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ያደረገውም ያለደረገውም ቤት ሲደርስ አውልቆ ይቀላቀላል” ይህም ሲጠነቀቅ የዋለውን የቤተሰብ አባል ተጋላጭ እንደሚያደርግ በመጠቆም።

የአቶ ሲሳይ ቤተሰቦች ራሳቸውን ለይተው በቆዩበት ጊዜ ሌላ የቤተሰባቸው አባልም በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋገጠ። ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ አስረኛው የቤተሰቡ አባል ሆኑ። ‘መልካም’ የሚባለው ነገር ከአስሩ የቤተሰቡ አባላት መካከል ሰባቱ ምንም ምልክትም ሆነ ህመም ያልነበራቸው መሆናቸው ነበር። ሦስቱም ቢሆኑ መካከለኛ የሚባል ነበር ህመማቸው።

ወደ ጤና ተቋም የማያስኬድ እና ቤት ውስጥ የሚደረግ ጥንቃቄና እንክብካቤ ብቻ የሚያስፈልገው አይነት ነበር። ወደ ኢትዮጵያ ለሦስት ሳምንት የመጡት አቶ ሰለሞን እና አጎታቸው በኮሮናቫይረስ ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ክፍል ተለይተው እንዲቀመጡ ተገደዋል። “ቫይረሱ እንዴት ቤተሰቡ ውስጥ እንደገባ እና እንደተሰራጨ የምናውቀው ነገር የለም” የሚሉት አቶ ሰለሞን “የተለያየ ግምት ቢኖረንም እርግጠኞች ግን አይደለንም” ብለዋል። እርግጠኛ የሆኑት “ወረርሽኙ በሰዎች ቸልተኝነት እና የጥንቃቄ ጉድለት በፍጥነት እየተሰራጨ መሆኑን እና ብዙዎች ህይወታቸውን እስከማጣት መድረሳቸውን ነው።”

“ያለማስክ መንቀሳቀስ ተለምዷል። የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ትርፍ ጭነው ሲሄዱ እየተመለከትኩ ነው። የንግድ ቦታዎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው ተመልሰዋል። ተማሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አድርገው በፈረቃ እየተማሩ ቢሆንም ከትምህርት ቤት ውጭ ያለው ጥንቃቄ አነስተኛ ነው” ብለዋል። አንዳንዶችም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በአግባቡ ከመጠቀም “እጃቸው ላይ ሰክተው ሲንቀሳቀሱ ላየ ‘ቫይረሱ በምንድነው የሚተላለፈው?’ የሚል ጥያቄን ይጭራል” ሲሉ ትዝብታቸውን ያስቀምጣሉ።

ለሁለት ሳምንት ያህል በኮሮናቫይረስ ተይዘው የነበሩት የአቶ ሰለሞንና አስር የቤተሰባቸው አባላት አሁን አገግመው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል። አንዲት እህታቸው ግን አሁንም የጀመራት ‘ሳል’ አልፎ አልፎም ቢሆን ሄድ መለስ ይላል። አቶ ሰለሞን ዘመድ ለመጠየቅ፣ ላለባቸው የግል ጉዳይ እና ለእረፍት በሚል ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉት ጉዞ በቫይረሱ ምክንያት ብዙ መስተጓጎል ገጥሞታል።

“ከዕቅዴ ብስተጓጎልም የከፋ ጉዳት ሳይገጥመን ከቫይረሱ ነጻ በመሆናችን ዕድለኛነት ይሰማኛል። በየዕለቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ አሳሳቢ ሆኖብኛል። ሕዝቡ ጥንቃቄውን ትቶ ወደ መደበኛ ህይወቱ መመለሱ ይበልጥ ችግሩን ያስፋፋዋል። . . .ስለዚህ ሕዝቡ ቸልተኝነቱን ትቶ መጠንቀቅ አለበት” ይላሉ። በመጨረሻም አቶ ሰለሞን እና አጎታቸው እንዳመጣጣቸው ወደ አሜሪካ ለመመለስ የኮሮናቫይረስ ምርመራ አድርገው ውጤቱን ተቀብለዋል። ኔጋቲቭ።

ከ1,400 በላይ ሰዎች የኮቪድ-19 ክትባት ተከትበዋል

  • 35 ተከታቢዎች መጠነኛ የጎንዮሽ ጉዳት ደርሶባቸዋል
  • የህንድና የቻይና ተጨማሪ ክትባቶች ወደ ኢትዮጵያ ሊገቡ ነው

በመላ ኢትዮጵያ ከመጋቢት 4 ጀምሮ እስከ መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በተካሄደው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዘመቻ፣ ከ1,400 በላይ ሰዎች አስትራዜኔካ የተባለውን ክትባት ተከትበዋል፡፡

ከተከተቡት ውስጥ በ35 ያህሉ ላይ ከደም መርጋት ውጪ በጥናቱ የተለዩና የሚጠበቁ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንደተከሰተባቸው ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን የምርቶች ደኅንነት ዳይሬክተር ወ/ሮ አስናቀች ዓለሙ እንዳሉት፣ በተጠቀሱት ተከታቢዎች ላይ ከታዩባቸው የጎንዮሽ ጉዳቶች መካከል ክትባቱ በተሰጠበት የሰውነት አካል ላይ የመቅላት፣ የትኩሳትና የድካም ስሜቶች ይገኙባቸዋል፡፡

ማንኛውንም ዓይነት መድኃኒቶች ሲወሰዱ የየራሳቸው የሆኑና በሦስት ደረጃዎች የተከፈሉ የጎንዮሽ ጉዳዮች ሊያስከትሉ እንደሚችሉ፣ ከእነዚህም ጉዳቶች መካከል በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠው ዝቅተኛ እንደሚሆን፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ደረጃዎች የተያዙት ደግሞ እንደ ቅደም ተከተላቸው ጠጠር እንደሚሉ፣ በተከታቢዎች ላይ የተከሰቱት የጎንዮሽ ጉዳቶች ግን አነስተኛ እንደሆኑና የማይታወቁ የጎንዮሽ ጉዳቶች ግን እስካሁን ሪፖርት እንዳልተደረጉ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

ከወ/ሮ አስናቀች ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ያልተጠበቀና በጣም ከፍተኛ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት ቢመጣ ጉዳዩ በደኅንነት ክትትል ኮሚቴ በኩል በሚገባ ይጣራል፡፡ አግባብነት ያለው የምርመራ ሥራ ይከናወናል ብለው፣ በዚህም ሒደት ችግሩ ወይም ጉዳቱ ከክትባቱ ጋር የተያያዘ መሆኑን ከተረጋገጠ ተጎጂው እንዲካስ ይደረጋል ብለዋል፡፡

‹‹ክትባቱ መሰጠት የተጀመረው በተወሰኑ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች እንደነበር፣ በአሁኑ ጊዜ ግን እንቅስቃሴው እየሰፋ በመምጣቱ የክትባቱ ሥራ በጤና ተቋማት ጭምር እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ለዚህም ዕውን መሆኑ ተቋማቱ በሠለጠነ የሰው ኃይል እንዲጠናከሩና ግብዓት እንዲሟላላቸው ተደርጓል፡፡ በዚህም የተነሳ ከ600 በላይ የጤና ባለሙያዎች ሠልጥነው ወደ ክትባት ሥራ ገብተዋል፤›› ሲሉ ወ/ሮ አስናቀች አስረድተዋል፡፡

የባለሥልጣኑ የመድኃኒት ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክተር አቶ አብደላ ቃሶ፣ የኮሮና ወረርሽኝን በቁጥጥር ሥር ለመዋል የሚረዱና ተስፋ ሰጪ የሆኑ የጥናትና ምርምር ውጤቶች መታየት እንደ ጀመሩ፣ ከእነዚህም መካከል የመጀመርያውና ወሳኝ ምዕራፍ ተብለው የተወሰዱት የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

ክትባቶች በተለያዩ አገሮች ተቋማት ጥናትና ምርምር እየተደረገባቸው መሆኑን፣ በምርምር ሒደት ላይ እያሉ በተለያዩ የጤና ተቆጣጣሪዎችና በዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ/ድንገተኛ አጠቃቀም ፈቃድ አግኝተው ጥቅም ላይ የዋሉ እንደሆኑ  አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ፋይዘር፣ ሞዴርና፣ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ አስትራዜኔካ፣ ስፑትኒክ ፋይቭና ሳይኖ ቫክስ የተባሉ የኮቪድ-19 ክትባቶችን መጥቀስ ይቻላል ብለዋል፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ አጠቃቀም ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ከእነዚህ ክትባቶች መካከል የኦክስፎርድ ግኝት የሆነውና በደቡብ አፍሪካ ኤሴኬ ባዮሳይንስ፣ እንዲሁም በህንድ በሚገኝ ሴራም ኢንስቲትዩት የተመረቱ 2.2 ሚሊዮን አስትራዜኔካ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ከእነዚህም በተጨማሪ በቻይና የሚገኘው የሲኖፋርማ ምርት ለሆነው የኮቪድ-19 ክትባት የአስቸኳይ አጠቃቀም ፈቃድ ተሰጥቶት 18,000 ያህል ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል፡፡ ይህም ክትባት ኢትዮጵያ በሚገኘው የቻይና ኤምባሲ በኩል ለቻይና ዜጎች ብቻ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ አምራች ኩባንያ በቀጣይ በኢትዮጵያ መንግሥትና በቻይና መንግሥት መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት፣ ክትባቱ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ጥቅም ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ህንድ ከሚገኘው ባሃራት ባዮቴክ ከሚባል የኮቪድ-19 የክትባት አምራች ኩባንያ የአስቸኳይ አጠቃቀም ፈቃድ እንዲሰጠው ለምግብና መድኃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ጥያቄ እንዳቀረበ፣ ይህ ክትባት በህንድ አገር የአስቸኳይ አጠቃቀም ፈቃድ ተሰጥቶት ጥቅም ላይ በመዋል የሚገኝ ስለሆነ፣ በባለሥልጣኑ በኩል የመጀመርያ ግምገማ ተጨማሪ የምርምር ውጤትና ሳይንሳዊ ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎችን ለአምራች ኩባንያ ተልኮ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ እንደሆነ አቶ አብደላ አስረድተዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ጥቅም ላይ እንዲውሉ የአስቸኳይ አጠቃቀም ፈቃድ የተሰጣቸው ሁለቱ ክትባቶች የአፈጻጸም መመርያ መሥፈርት ያሟሉ ሲሆን፣ ክትባቶቹ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የተፈቀደው ዕድሜያቸው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ሰዎች ነው፤ይህም የሆነበት ዋና ምክንያት በሕክምና ሙከራ ተጠንቶ የቀረበው መረጃ የሚያሳየው ጥናቱ የተደረገው በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ጤናማና ዕድሜያቸው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ በሆኑ ግለሰቦች ላይ ሲሆን፣ የታወቁና ሊሆኑ የሚችሉ ጥቅሞች ከሚታወቁና ሊከሰቱ ከሚችሉ ጉዳቶች ጋር ሲነፃፀሩ ጥቅሙ ከጉዳቱ የሚበልጥ ሆኖ በመገኘቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የቀረበው የጥናትና ምርምር ውጤት እንደሚያሳየው ክትባቱ በሁለት ዙር የሚሰጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው ዙር የሚሰጠው ከስምንት እስከ 12 ሳምንታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ነው፡፡ በጥናትና ምርምር ወቅት በእነዚህ ክትባቶች ላይ የተመዘገበው የጎንዮሽ ጉዳቶች በክትባት በሚሰጠው የሰውነት ክፍል ላይ ድካም፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ ሕመም፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የመገጣጠሚያ ሕመምና ትኩሳት እንደሆነ፣ በሕክምና ሙከራ ውስጥ ከተሳተፉት ግለሰቦች ከላይ ከተዘረዘሩት የጎንዮሽ ጉዳቶች ውስጥ ቢያንስ ከአንድና ከሁለት በላይ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳጋጠሟቸው ነው ዳይሬክተሩ ያስረዱት፡፡

ከአቶ አብደላ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ክትባቱን የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎችና ክትባቱን የሚወስዱ ግለሰቦች ከሁለቱም የክትባት ዙሮች (የመጀመርያና ሁለተኛ) በኋላ አንዳንድ የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊኖሩ ይችላሉ ብለው መጠበቁ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በጥናቱ መሠረት በሁለተኛው ዙር የጎንዮሽ ጉዳት ከመጀመርያው ጠንከር እንደሚል ያሳያል፡፡ በመሆኑም መደንገጥ ሳያስፈልግ የሚታዩ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ሪፖርት ማድረግ በጣም አፈስፈላጊ ነው ተብሏል፡፡

ባለሥልጣኑ የክትባቶቹን ደኅንነት ለመከታተልና በሚፈለገው ፍጥነት አስፈላጊውን ዕርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት ከመዘርጋቱም በላይ በቁጥጥር፣ በመረጃ ቅበላና ትንተና፣ እንዲሁም  ክትባቱን በመስጠት ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉንና  የግንዛቤ  ማስጨበጫ ሥልጠናው አሁንም በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ ነው ከአቶ አብደላ ማብራሪያ ለመረዳት የተቻለው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *