የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት አስከትሏል የተባለውን የመብቶች ጥሰት በጋራ ለመመርመር በኢትዮጵያ በኩል የቀረበውን ጥሪ መቀበሉን ገለጸ።

በሚሼል ባሽሌት የሚመራው ኮሚሽኑ “ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኩል የጋራ ምርመራ ለማካሄድ የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ ሰኞ ዕለት አውንታዊ መልስ ሰጥቷል” ሲሉ ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቃል አቀባይ የሆኑት ጆናታን ፎውለር ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የተቀሰቀሰውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በትግራይ ክልል ውስጥ ከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትና የንበረት ውድመት መፈጸሙን የሚገልጹ ሪፖርቶችን አውጥተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ሚሼል ባሽሌት ከሳምንት በፊት ባወጡት መግለጫ በትግራይ ግጭት የተሳተፉ አካላት “የጦር እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ፈጽመው ሊሆን እንደሚችል” ገልጸው ነበር።

ሚሸል ባሽሌት “የሚረብሹ” ያሏቸው የመደፈር፣ የዘፈቀደ ግድያ፣ መጠነ ሰፊ የንብረት ውድመትና ዘረፋ መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እየወጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግልጽና ነፃ ምርመራ ካልተካሄደና ጥሰቱን የፈፀሙትን አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ካልተቻለ እነዚህ ጥቃቶች ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።

ኮሚሽነሯ ከትግራይ የሚወጡ ተያያዢነት ያላቸውና ተአማኒ ያሏቸውን ሪፖርቶች ጠቅሰው በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ የተለያዩ ወገኖች የተፈፀሙ ከባድ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊ እርዳታ ሕጎች ጥሰት መፈጸማቸውን እንደሚያመለክቱ ተናግረዋል።

በዚህም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉትንና እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ሪፖርት የተደረጉ የጅምላ ግድያዎችን፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ወሲባዊ ጥቃቶችን ለመመርመር እንዲችል ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ በእነዚህ ድርጊቶች ውስጥ ሳይሳተፉ አይቀሩም በሚል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን፣ ህወሓትን፣ የኤርትራ ወታደሮችን፣ የአማራ ክልል ኃይሎችን ጠቅሶ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ተፈጽመዋል ስለተባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ግድያዎችን በሚመለከት ከተለያዩ ወገኖች በኩል የሚወጡትን መረጃዎች መሠረት በማድረግ የአገሪቱን የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን፣ ዐቃቤ ሕግን፣ የትግራይ ገዜያዊ አስተዳደርንና የፌደራል ፖሊስን ያካተተ ቡድን አቋቁሞ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት እየተደረገ ባለው ምርመራ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ በማድረግ ቀረቡትን ክሶች ለማጣራት ፈቃደኝነቱን አሳይቷል።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ የህወሓት ኃይሎች የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ በተቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ የጠፋው ህይወት ምን ያህል እንደሆነ በትክክል የማይታወቅ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሳይሞቱ እንዳልቀሩ የእርዳታ ድርጅቶች ይገምታሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ግጭቱን በመሸሽ ከ60 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ድንበር ተሻግረው ወደ ሱዳን የገቡ ሲሆን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት ደግሞ እዚያው በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል።

ምንጭ – ቢቢሲ 

                                                                                                                                                                                                            

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *