የሽረ ከተማ በየዕለቱ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ተፈናቃዮችን ታስተናግዳለች።
ከእነዚህም መካከል ከሽረ 50 ኪሎ ሜትር ርቃ ከምትገኘው አክሱም የመጣችው የስድስት ዓመቷ ቤተልሔም ተስፋዬ አንዷ ናት። ቤተልሔም በግጭቱ እናቷንና ሁለት እግሮቿን አጥታለች። አባቷ የቋጠረውን ጥሪትም ለእሷ ማሳከሚያ አውጥቶ ጨርሷል። አሁን ለቤተልሔም ሰው ሰራሽ እግር እንዲደረግላት የሚያስችለውን ገንዘብ ከየት እንደሚያገኝ ጨንቆታል። ሽረ እንደ ሌሎቹ የትግራይ ከተሞች ሁሉ የግፍ ግድያዎችና አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ሌሎችም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመውበታል በሚባለው ግጭት ሳቢያ ለተፈናቀሉ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች መጠለያ ሆናለች።
ነገር ግን በማዕከላዊ ትግራይ የምትገኘውና የ170,000 ሰዎች መኖሪያ የሆነችው ሽረ፤ ተፈናቃዮቹን ለማስተናገድ ከአቅም በላይ ሆኖባታል። ባለፉት አራት ወራት ምንም አይነት ዝግጅት ወዳላደረገችው ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ተሰዷል። በከተማዋ ያሉ ትምህርት ቤቶችና የዩኒቨርስቲ ግቢዎች የሰዎች ሰቆቃ የሚሰማባቸው ማዕከላት ሆነዋል።
የእርዳታ ድርጅቶች በከተማዋ ውስጥ ባሉት ጊዜያዊ መጠለያዎች በአሁኑ ጊዜ 200,000 ያህል ሰዎች እንደሚገኙ ይገምታሉ። ብዙዎቹም ሴቶችና ህጻናት ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ተፈናቃዮች የመጡት ጦርነቱ በተቀሰቀሰበት በኅዳር ወር ላይ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በግጭቱ ጅማሬ ላይ የውጊያ ማዕከል ከነበሩት ከደቡብ ምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች የመጡ ናቸው። ግጭቱ የተከሰተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን እስኪመጡ ድረስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የበላይ በነበረውና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በቆየው ህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ለረጅም ጊዜ ሲብላላ በቆየው አለመግባባት ሰበብ ነበር።
ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የአገሪቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ሲያዙ ግጭቱ በተለያዩ ግንባሮች የተለያዩ ኃይሎችን አሰልፎ ነበር የተቀሰቀሰው። በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ትግራይ በኩል የአጎራባች የአማራ ክልል ኃይሎች የፌደራል ሠራዊቱን በማገዝ ከህወሓት ኃይሎች ጋር በሚደረገው ውጊያ ውስጥ ተሳታፊ ሆኑ።
የ65 ዓመቷ ወ/ሮ አፀደ መብርሃቶም በእነዚያ ቀናት የተመለከቷቸውን አሰቃቂ ሁኔታዎችን ያስታውሳሉ። ወ/ሮ አፀደ በሁለት ሴት ልጆቻቸውና በቤተሰቦቻቸው እየተደገፉ ዳንሻ ውስጥ ይኖሩ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ወ/ሮ አፀደ፣ ልጆቻቸው፣ የልጆቻቸው ባሎች እና የልጅ ልጆቻቸው የሚኖሩት ሽረ ውስጥ ከሚገኙ መጠለያዎች በአንዱ ነው። ቤታቸውን ትተው ወዴት እንደሚሄዱ እንኳን ሳያውቁ ሲሸሹ በእጃቸው የነበራቸው በጣም ጥቂት ገንዘብ ነበር።
አስፈላጊ ሲሆን በእግራቸው እየተጓዙ፣ ሲችሉ እንደእነሱ የተፈናቀሉ ሰዎችን ከልክ በላይ ጭነው የሚጓዙ አውቶብሶችና የጭነት ተሽከርካሪዎችን ተጠቅመዋል።”ማረፍ እንኳን አልቻልንም” ይላሉ ወ/ሮ አፀደ። በጉዟቸው ላይ በረሃብና በውሃ ጥም ተሰቃይተዋል። “ቁራሽ ዳቦ ለምነን ለልጆቹ እንሰጣለን፤ ኩባያ ተውሰን ልጆቹን ውሃ እናጠጣለን።” ይላሉ። በመንገዳቸው ላይ ያልተቀበሩ አስከሬኖችን በየቦታው ወዳድቀው መመልከታቸውን ይናገራሉ። ይህንንም ለመርሳት አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል። ደስተኛ ባይሆኑም በህይወት መቆየታቸውን እንደ ትልቅ ነገር የሚያዩት ወ/ሮ አፀደ “ጊዜ ይመጣል ይሄዳል። እኛ ባለመሞታችን እድለኞች ነን” ይላሉ። በመጠለያ ካምፑ ውስጥ የተወሰነ እርዳታ የሚሰጥ ቢሆንም ቢቂ እንዳልሆነ ተፈናቃዮቹ ይናገራሉ።
ህወሓት ከሥልጣን ሲወገድ በፌደራል መንግሥቱ የተሾመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚለው ከትግራይ ክልል ነዋሪ ውስጥ ከግማሽ በላይ ወይም አራት ሚሊዮን ያህል ሰዎች የእርዳታ ድጋፍ ይፈልጋሉ። ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል። የአስተዳደሩ ቃልአቀባይ የሆኑት እቴነሽ ንጉሠ እንደሚሉት ለጋሾችና የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች በችግር ላይ ያለውን ሕዝብ ለመርዳት የሚያደርጉትን ጥረት የበለጠ ማጠናከር አለባቸው።
በክልሉ ውስጥ ያልተገደበ የእርዳታ አቅርቦት መንገድ እንዲመቻች ዓለም አቀፋዊ ጥሪ ሲደረግ መቆየቱ ይታወሳል። “አሁን የእርዳታ ድርጅቶች ገብተው ድጋፍ እንዲያደርጉ ተፈቅዶላቸዋል። ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው” ይላሉ እቴነሽ ቀደም ሲል የህወሓት መሪዎች መቀመጫ በነበረውና ከዕምነ በረድ ከተገነባው ህንጻ ፊት ለፊት ቆመው። “በመንግሥት ከሚቀርበው እርዳታ በተጨማሪ የእርዳታ ድርጅቶች ሕዝቡን ለመታደግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉልን እንጠብቃለን።” ብለዋል ቃል አቀባይዋ።
ለተብርሐን አሰፋ ሽረ 450 ኪሎ ሜትር ርቃ ከምትገኘውና ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከኤርትራ ጋር ከምትዋሰንባት ትንሽ ከተማ ሁመራ ነው የመጣችው። ግጭቱ ከመጀመሩ በፊት ልጇ በቀዶ ህክምና ወልዳ ተኝታ ነበር። መኖሪያቸውን ጥለው ሲሰደዱ እናት አራስ ልጇንና አዲስ የተወለደውን ጨቅላ መንከባከብ ነበረባት። ሽረ መጠለያ ውስጥ ከገቡ በኋላ ደህንነት ቢሰማቸውም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ግን እያገኙ እንዳልሆነ ትናገራለች።
በመጠለያው ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም አሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተጨናነቁ አውቶብሶች፣ የጭነት መኪኖችና በፈረስ ጋሪ እየተጓዙ ወደ ሽረ እየመጡ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ምንም እንኳን የፌደራል መንግሥቱ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ አብዛኛውን የትግራይ ክልል አካባቢዎችን መቆጣጠሩን ቢገልጽም፤ በአንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ውጊያዎች እንዳሉ ስለሚነገር የደኅንነት ሁኔታው አሁንም ድረስ ሙሉ ለሙሉ አስተማማኝ ባለመሆኑ ነው።
በክልሉ ላይ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሁንም ተግባራዊ ሲሆን፤ ከምሽት እስከ ንጋት የሚቆይ የሠዓት እላፊ ገደብ አለ። በመንገዶች ላይ በርካታ የፍተሻ ኬላዎችም ይገኛሉ። የተደረገው ወታደራዊ ግጭት የተቋጨ ቢመስልም ያስከተለው ቁስል ግን እስኪሽር ድረስ ዓመታትን ሊወስድ ይችላል።mለአንዳንዶች ደግሞ ጠባሳው እስከመጨረሻው አብሯቸው የሚኖር ይሆናል።
ምንጭ – ቢቢሲ