ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በትግራይ ውስጥ ስለተከሰተው ቀውስና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር እንዲወያዩ መልዕከተኛ ወደ ኢትዮጵያ ሊልኩ ነው።

በተጨማሪም አሜሪካ ለእርዳታ የሚውል 52 ሚሊዮን ዶላር በትግራይ ግጭት የሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የሚውል ድጋፍ እንደምትሰጥ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ በኩል አስታውቃለች።

የባይደን መልዕክተኛ የአሜሪካ ምክር ቤት አባል የሆኑት ክሪስ ኩንስ በትግራይ ክልል ስለተከሰተው ቀውስ፣ ስለሰብአዊ መብት ጥሰቶችና በሱዳንና ኢትዯጵያ መካከከል ያለው የድንበር አካባቢ አለመረጋጋት የፕሬዝዳንቱን ስጋት አንስተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር እንደሚነጋገሩ መረጃዎች ጠቁመዋል።

መልዕክተኛው ሴናተር ክሪስ ኩንስ ወደ ኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉዞ ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተጨማሪ ከአፍሪካ ሕብረት ኃላፊዎችም ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ለአገሪቱ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ኢትዮጵያን በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ ላይ በትግራይ ክልል “የዘር ማጽዳት” ድርጊት ተፈጽሟል ብለው መናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ይህንን ክስ “ተጨባጭነት የሌለውና ሐሰተኛ” በማለት የብሊንከንን ንግግር አጥብቆ ተቃውሞታል።

በተያያዘ ዜና የአሜሪካ መንግሥት በትግራይ ክልል ለሚከናወን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት የሚውል 52 ሚሊዮን ዶላር ማቅረቡን አስታውቋል።

የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መረጃ መሠረት ይህ እርዳታ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ አጋሮች በትግራይ ውስጥ የሚገኙትንና ወደ ሱዳን የተሰደዱ ድጋፍ ለሚሹ ሰዎች የሚሆን እርዳታ ለማቅረብ ያስችላቸዋል ብለዋል።

የአሜሪካ መንግሥት የሚሰጠው ይህ የገንዘብ ድጋፍ ለተረጂዎች ህይወት አድን አገልግሎቶችን፣ መጠለያ፣ መሠረታዊ የጤና አገልግሎት፣ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ፣ ውሃና የንጽህና አቅርቦቶች የሚውል ይሆናል ተብሏል።

አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ሁኔታዎችን በማመቻቸት በኩል ያሳያውን ቁርጠኝነትና መሻሻል እንደምታደንቅ ገልጾ፤ “ትግራይ ውስጥ እየተባባሰ ያለው ሰብአዊ ቀውስ በእጅጉ እንደሚያሳስበው” አመልክቷል።

ጨምሮም አስቸኳይ፣ የተሟላና ገደብ የሌለበት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መንገዶች ለእርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና ሠራተኞች መመቻቸት በግጭቱ ለችግር የተጋለጡ ሰዎች ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ ወቅታዊ ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስችል ጠቅሷል።

“ፖለቲካዊ መፍትሔ አስካልተገኘ ድረስ የሰብአዊ ቀውሱ ሁኔታ እየተባባሰ ይቀጥላል” ያለው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ከዚህ በፊት እንዳለው አሁንም ደግሞ፤ ግጭቶች እንዲቆሙ፣ የኤርትራና የአማራ ክልላዊ ኃይሎች በአስቸኳይ ከትግራይ ክልል እንዲወጡ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለዚህ ሰጥቶ በነበረው ምላሽ ላይ በግዛቱ ውስጥ ሕግን ለማስከበር በሚወስደው እርምጃ ውስጥ ስለሚያሰማራው የጸጥታ ኃይልን በተመለከተ በአሜሪካ በኩል የተጠቀሰው ነገር “በሉአላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት ነው” ሲል መቃወሙ የሚታወስ ነው።

የአሜሪካ መንግሥት በተጨማሪም በትግራይ ውስጥ ተፈጽመዋል ከተባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ግድያዎች ጋር በተያያዘ በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ ከሆኑ ከሁሉም ኃይሎች በኩል ያሉ አጥፊዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአህጉራዊና ከዓለማ አቀፋዊ ተቋማት ጋር በመሆን ምርመራ እንዲካሄድ በጠየቀው መሰረት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን በመርመራው ውስጥ ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆኑን መግለጹ ይታወቃል።

በፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልልን ያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ለረጅም ጊዜ ሲብላላ የቆየው አለመግባባት በጥቅምት ወር መጨረሻ የአገሪቱ ሠራዊት አንድ ክፍል በሆነው በሠሜን ዕዝ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ሳቢያ ወደ ሙሉ ወታደራዊ ግጭት መሸጋገሩ ይታወሳል።

በዚህም ሳቢያ አስካሁን የሞቱ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ባይታወቅም በሺዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ሲገምት በመቶሺዎች ደግሞ በክልሉ ውስጥ ተፈናቅለው እርዳታና ድጋፍ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ከ60 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ደግሞ ግጭቱን በመሸሽ ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን የእርዳታ ድርጅቶች ይገልጻሉ።

ምንጭ – ቢቢሲ
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *