መገናኛ ብዙኃን በምርጫ ወቅትና ከድኅረ ምርጫ በኋላ የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች በአገራዊ ምርጫ ውጤት አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጥሩ ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡
ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከፈረንሣይ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ እንዴት መሆን እንዳለበት የሚገልጽ ሥልጠና፣ ሐሙስ መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ለተወጣጡ ጋዜጠኞች በሰጠበት ወቅት ነው፡፡ በሥልጠናው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ ሥራ አስፈጻሚ ሰብሳቢ አቶ አማረ አረጋዊ እንደገለጹት፣ መጪው አገራዊ ምርጫ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደመከናወኑ መጠን መገናኛ ብዙኃን ሚዛናዊ የምርጫ አዘጋገብን በመከተል በአገሪቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ትልቅ ሚና መጫወት አለባቸው፡፡
በሥልጠናው ላይ በአገራዊ ምርጫ የጋዜጠኞች የሥነ ምግባር ደንብ ይዘቶችን የገለጹት ከምርጫ ቦርድ ጋር በትብብር የሚሠራው አይኤፍሲ (IFC) የተባለው ተቋም የሕግ ጉዳዮች ከፍተኛ የፕሮግራም ባለሙያ አቶ ሰለሞን ግርማ፣ በምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ ሥነ ምግባር 1162/2011 የተባለ አዋጅ እንደተደነገገ አስታውቀዋል፡፡
ምርጫ ልዩ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው አገራዊ መርሐ ግብር እንደሆነ ያስታወቁት ባለሙያው፣ በተለይ መገናኛ ብዙኃን አገራዊ ምርጫ ከመከናወኑ በፊት፣ በሚከናወንበት ወቅትና እንዲሁም ከምርጫ በኋላ የሚያቀርቧቸው ዘገባዎች ሚዛናዊነት ከጎደላቸው በአገር ላይ የሚያደርሱት ችግር ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ጋዜጠኞች በምርጫ ወቅት የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የተጤኑ መሆን እንዳለባቸው ያስረዱት የሕግ ባለሙያው፣ በፓርቲዎችም ሆነ በዕጩዎች በጥቅም ለመደለል ከሚደረግ እንቅስቃሴ አንስቶ እስከ ቃላት አጠቃቀምና አገላለጽ ድረስ፣ ጋዜጠኞች በልዩ ትኩረት መሥራት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ታምራት ኃይሉ በበኩላቸው በሚዲያዎች የምርጫ አዘጋገብ ምክንያት ምርጫ ሰላማዊነቱ ሊረጋገጥና ላይረጋገጥ እንደሚችል አስታውቀው፣ መገናኛ ብዙኃን ዘገባቸው የተጣመመ ከሆነ ምርጫውም የተጣመመ ውጤት ይዞ እንደሚመጣ አስታውቀዋል፡፡ በተሰናከለ ዜና የሰዎች ሕይወት ሊጠፋ እንደሚችል ያስረዱት አቶ ታምራት፣ በመሆኑም መገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብን በአንክሮ ሊያዩት እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
በሥልጠናው ወቅት የማኅበራዊ ትስስር ገጾች የተዛቡ መረጃዎች አቀራረብ ለመጪው አገራዊ ምርጫ ሥጋት መሆን እንደ አንድ ርዕስ ተነስቷል፡፡ አቶ ሰለሞን የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን ለመምራት የሚያስችል ረቂቅ መመርያ የተዘጋጀ ቢሆንም፣ በበቂ ሁኔታ ውይይት እንዲደረግበት በመታመኑ፣ በዚህ ወቅት እንዳልፀደቀ ገልጸዋል፡፡ በአገራዊ ምርጫ ማኅበራዊ ሚዲያውን መቆጣጠር አለመቻል ሥጋት መሆኑ አይቀሬ እንደሆነ ያብራሩት አቶ ሰለሞን፣ ሆኖም በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡትን መከታተልና መቆጣጠር እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱ ‹‹በምርጫ ወቅት የጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙኃን ሚና ምን ሊሆን ይገባል?›› በሚል ርዕስ ተመሳሳይ ሥልጠናዎችን በክልሎችም ለማዘጋጀት መታቀዱን ያስታወቁት አቶ አማረ፣ ዋና ቢሮውን መስቀል አደባባይ አካባቢ በመክፈት በሥሩ ላቀፋቸው የሙያ ማኅበራት፣ የግልና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንና የክብር አባል የሆኑትን የጋዜጠኛ ትምህርት ተቋማት በማካተት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ለማከናወን መንቀሳቀሱን አስታውቀዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የሥነ ምግባርና አሠራር መመርያ፣ ማናቸውም በተመዘገቡበት አገር ሕግ ዕውቅና ተሰጥቷቸው የሚሠሩ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ የመገናኛ ብዙኃን በአገሪቱ ውስጥ የሚካሄዱ ምርጫዎችን በምርጫ ጣቢያ ውስጥ በመገኘት በሚወክሏቸው ጋዜጠኞች አማካይነት ለመከታተልና ለመዘገብ የዕውቅና ጥያቄ ለቦርዱ ማቅረብ እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር