የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ፣ በኅብረተሰቡና በትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎች የተዘነጋውን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል ታሳቢ በማድረግ፣ የሕዝብ ትራንስፖርትና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ለመወሰን የተዘጋጀውን መመርያ የማስታወስና የማስፈጸም ሥራ እንደሚያከናውን አስታወቀ፡፡
የትራንስፖርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አረጋዊ ማሩ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኮሮና ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ መመርያ በማዘጋጀት በከተማው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ እንዲተገበር የተደረገበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በመመርያው ለውጥ ማምጣት ተችሎ እንደነበር፣ ሆኖም ከተወነ ጊዜ በኋላ ከፍተኛ መዘናጋት በመስተዋሉ የወረርሽኙ ሥርጭት መጨመሩን፣ ለዚህም ሲባል አስገዳጅ የትራንስፖርት መመርያውን የማስታወስና የማስፈጸም ሥራ ቢሮው እንደሚያከናውን አስታውቀዋል፡፡
ወረርሽኙ ከሚተላለፍባቸው መንገዶች መካከል ትራንስፖርት ዋነኛው እንደሆነ የገጹት ኃላፊው፣ በተለይ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በኮሮና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር አምና ወደ አገር ቤት ሲገባ ከነበረው ቁጥር ያሻቀበ እንደሆነ በመግለጽ፣ የሥርጭቱ ከፍተኛ መሆንና የኅብረተሰቡን መዘናጋት ከግምት ውስጥ በመክተት፣ ቀደም ሲል የወጡትን የኮቪድ ፕሮቶኮሎች በድጋሚ የማስተወስ ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎትና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ለመወሰን የተዘጋጀው መመርያ የተሻረ እንዳልሆነ ያስታወቀው ቢሮው፣ ቀደም ሲል ይደረግ እንደነበረው በታክሲ ማኅበራትና በተራ አስከባሪዎች የጥንቃቄ መመርያዎች የማስተግበር ሥራ በድጋሚ እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡ በዚህም በታክሲ ተራም ሆነ በሥምሪት መስመር ላይ ተሳፋሪዎች የፊት መሸፈኛ (ጭምብል) አድርገው እንዲሳፈሩ፣ የፊት መሸፈኛ ሳያደርጉ ለመገልገል የሚመጡ ተሳፋሪዎች አገልግሎቱን እንዳያገኙ የማድረግ ሥራ በቅንጅት የሚከናወን እንደሆነ ታውቋል፡፡
የቅስቀሳ ዘመቻዎችን ማድረግ አንገብጋቢው ነገር እንደሆነ ያስረዱት አቶ አረጋዊ፣ የትራንስፖርት ማኅበረሰቡን በተለይም አሽከርካሪዎችን የንቅናቄ መመርያው ማዕከል በማድረግ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል፡፡
የትራንስፖርት መመርያው አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ተሳፋሪዎችን የመጫን ገደብ እንዳስቀመጠ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህም የሚኒባስ ታክሲ የተፈቀደ የተሳፋሪ ቁጥር ወይም የመጫን አቅም በተሽከርካሪው ወንበር ልክ፣ የሀይገርና የቅጥቅጥ አውቶቡስ የተፈቀደ የትራንስፖርት ተሳፋሪ ቁጥር ወይም የመጫን አቅም በተሽከርካሪው ወንበር ልክና ተጨማሪ አምስት ሰው ነው፡፡
ማንኛውም የከተማው የትራንስፖርት ተጠቃሚ፣ አሽከርካሪና ረዳት የፊት መሸፈኛ ማድረግ እንዳለበትና የፊት መሸፈኛ ያላደረገ ተሳፋሪ ማሳፈር እንደሌለበት መመርያው ቢያስቀምጥም፣ ሪፖርተር በተለያዩ የከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ባደረገው ቅኝት ተሳፋሪዎች፣ የታክሲ ረዳትና ሹፌሮች ያለ የፊት መሸፈኛ እንደሚንቀሳቀሱ፣ እንዲሁም ድጋፍ ሰጪ የብዙኃን ትራንስፖርት አቅራቢዎችና ታክሲዎች በመመርያው ከተደነገገው የሰው ጭነት ልክ እንደሚያጓጉዙ ለመረዳት ችሏል፡፡
ማንኛውም መመርያውን ተላልፎ የተገኘ ሚኒባስ ታክሲ፣ ሃይገር፣ ቅጥቅጥ፣ አውቶቡስ፣ አንበሳና ሸገር አውቶቡስ፣ እንዲሁም፣ የባለአራትና ባለሦስት እግር ተሽከርካሪና የሞተር ብስክሌት የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ በመጣሉና ከመጫን ልክ በላይ ካሳፈረ ከ1,000 አስከ 500 ብር፣ ጥንቃቄ ያላደረገ ተሳፋሪ በሚጭንበት ጊዜ 500 ብር እንደሚቀጣ ያስታወሱት አቶ አረጋዊ፣ ሆኖም መመርያውን በዚህ ወቅት የተዘነጋበትና የማይተገበርበት ሁኔታ እየተስተዋለ መምጣቱን አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮቪድ-19 ሥርጭት ለመግታት በቀጣይ የፕሮቶሉን አስገዳጅነት በማስታወስ እንዲተገበር መመርያዎችን እንዳስተላለፈ ያስረዱት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው፣ በታክሲ መጫኛና ማውረጃ ሥፍራዎች የቅስቀሳ መልዕክቶችን የማስተላለፍ እንቅስቃሴን ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር ዓባይ የተጀመረው በከተማዋ የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመግታት፣ በትራንስፖርት ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ንቅናቄ ባለፈው ሳምንት እንደተጀመረ አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ መገኘቱ ከታወቀ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ገለጸ።
ትናንት ሐሙስ በተደረገ ምርመራ በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ከፍተኛው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች አሃዝ ተመዝግቧል። በዚህም ምርመራ ከተደረገላቸው 8,055 ሰዎች መካከል በሽታው በ2,057 ሰዎች ላይ መገኘቱን ኢኒስቲቲዩቱ ያወጣው መረጃ አመልክቷል። ይህ ማለት ከተመረመሩት 100 ግለሰቦች ውስጥ 26 ወይም 25.5 በመቶው የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል በማለት “በማኅበረሰብ አቀፍ የምርመራ ዘመቻ ወቅት እንኳን ይህን ያህል ከፍተኛ ቁጥር አልተመዘገበም” ብሏል።
ከሰሞኑ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ “በአስደንጋጭ ሁኔታ” እየጨመረ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የሰጧቸው መግለጫዎች ያመለክታሉ። ቢሆንም ግን ወረርሽኙ እየፈጠረ ያለውን ከባድ አደጋ ከግንዛቤ በማስገባት ተገቢውን የመከላከያ ጥንቃቄ “ከማድረግ ይልቅ መዘናጋት በሰፊው እንደሚታይ” ቢቢሲ ያናገራቸው የሕክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ የተሳተፈባቸው የተለያዩ ስብሰባዎችና ዝግጅቶችን የታዘቡት የጤና ባለሙያዎች ችግሩ ሕብረተሰቡ ጋር ብቻ ሳይሆን መንግሥት የጤና ሚኒስቴር የሚያስቀምጣቸውን የኮሮናቫይረስ መከላከያ መመሪያዎች “ለማስፈፀም ተነሳሽነት ይጎድለዋል” አስብሏቸዋል።
ይህንንም ተከትሎ ከጊዜ ወደ ጊዜ የበሽታው መስፋፋት እጨመረ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ በወረርሽኙ የሚያዙ፣ በጽኑ የሚታመሙና ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከመድረሱ ባሻገር የጤና ተቋማት ህሙማንን ለማስተናገድ ፈተና እየገጠማቸው ነው። በዚህም ሳቢያ በመላው አገሪቱ በጽኑ ለታመሙ ሰዎች አጅጉን አስፈላጊ የሆኑት የኦክስጅንና የሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ (ቬንትሌተር) እጥረት በመከሰቱ በርካታ የኮቪድ-19 ታማሚዎች ህይታቸውን እንዲያጡ ሊያደርግ እንደሚችል ስጋት ፈጥሯል።
“በአንድ ጊዜ በርካታ ኦክስጅን የሚፈልጉ ህሙማን ወደ ህክምና ተቋማት ይመጣሉ” የሚሉት ዶ/ር ብሩክ አለማየሁ ኦክስጂን ባለመኖሩ ብቻ ህሙማን ወደ ቤታቸው ለመመለስ የሚገደዱበት ጊዜ ላይ መደረሱን ይናገራል። “በርካታ ሰዎች በግላቸው የኦክስጂን ሲሊንደር እየገዙ ወደ ቤታቸው እየገቡ ነው” በማለት፣ ሆስፒታል አልጋ ይዘው የሚታከሙም ቢሆኑ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ ለማግኘት ረዥም ወረፋ እንደሚጠብቁ ይገልጻሉ። በኮቪድ-19 ተይዘው በቤታቸው ውስጥ እራሳቸውን ለይተው እንዲቆዩ ከሚደረጉት ባሻገር ወደ ህክምና ተቋማት የሚመጡ ህሙማንን የመቀበል አቅማቸው እየተሟጠጠ መሆኑንም አልሸሸጉም።
በኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል የጽኑ ህክምና ክፍል ኃላፊ ዶክተር ህሩይ አርዓያ ለፋና እንደተናገሩት ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ወደ ማዕከሉ የሚመጡ የቫይረሱ ታማሚዎች ቁጥር እንዲሁም ወደ ጽኑ ህክምና ክፍል የሚገቡ ታካሚዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው ብለዋል። የሚሊኒየም ኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ውለታው ጫኔ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ወደ ማዕከላቸው ከሚመጡ ሕሙማን መካከል ከ75 በመቶ በላይ ኦክስጅን የሚፈልጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በማዕከሉ የመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር መበርከቱን ገልፀው “በመካኒካል ቬንትሌተር እጥረት ምክንያት የማንቀበላቸው ህሙማን ይኖራሉ” ብለዋል። ዶ/ር ውለታው ጨምረውም የኦክስጅን እጥረት ስለገጠማቸው ድጋፉን ፈልገው የሚመጡ ሁሉንም ጽኑ ህሙማን ማስተናገድ አለመቻላቸውን ገልፀዋል።
የጽኑ ህሙማን ቁጥር እየጨመረ ነው
ዶ/ር ብሩክ ዓለማየሁ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ መጨመር እያሳየ መምጣቱን እነዳስተዋሉ የጠቆሙ ሲሆን፤ ዶ/ር ውለታው ጫኔም በበኩላቸው በተለይ ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት በኮቪድ-19 በጠና ታምመው ወደ ማዕከላቸው የሚመጡ ሰዎች በመርከቱን ተናግረዋል። በየተቋማቱ ለህሙማን አልጋ በመጥፋቱ አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩን የሚናገሩት ዶ/ር ብሩክ፣ ይህም በህክምና ባለሙያዎች ላይ ጫና መፍጠሩን አስረድተዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት ኮቪድ-19 የተያዙ ሕሙማን እየበዙ በመምጣታቸው በሌላ የሕክምና ክፍል ያሉ አልጋዎችን እስከ መሻማት ተደርሷል። ዶ/ር ብሩክ በሚሰሩበት ህክምና ተቋም ከዚህ በፊት አንድ ታካሚ በኮቪድ-19 ተይዞ ኦክስጂን ባያስፈልገው እንኳን ተኝቶ ህክምና እንዲያገኝ ይደረግ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን አስተኝቶ ለማከም ህሙማኑ ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው መሆን አለመሆኑ ይወስነዋል ይላሉ።
“አሁን የምናስተኛቸው ታካሚዎች በሙሉ ኦክስጂን ፈላጊዎች ናቸው።” እንደ ዶ/ር ብሩክ ከሆነ ሁሉም ተኝተው የሚታከሙ ሰዎች ኦክስጂን የሚፈልጉ መሆናቸውን ገልጸው፤ በአሁኑ ጊዜም የኦክስጂን ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል ብለዋል። ይህንን ሲያብራሩም በአሁኑ ጊዜ ተኝተው የሚታከሙ ህሙማን በሙሉ ኦክስጅን ፈላጊ ሲሆኑ የሚፈልጉት የኦክስጅን መጠን ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
“ከአምስት እና ከአስር ሊትር በላይ መጠን ያለው ኦክስጂን፣ የመተንፈሻ መሳሪያ ድጋፍ የሚፈልጉ ህሙማን ቁጥር ጨምሯል።” ይህ የግብአት እጥረት በተወሰኑ ተቋማት ላይ ብቻ የታየ ሳይሆን ዶ/ር ብሩክ እንደሚሉት የኮቪድ-19 ህሙማንን በተለይ በሚያክሙት በሚሌኒየም እና ኤካ ኮተቤ ሆስፒታሎች ጭምር እንደሚስተዋል ከባልደረቦቻቸው ተረድተዋል። በተጨማሪም በግል ሆስፒታሎች የረር፣ ቤተዛታ፣ ሃሌሉያ የሚሰሩ ባለሙያዎችም ተመሳሳይ ነገሮችን ማስተዋላቸውን እንደነገሯቸው ይጠቅሳሉ።
ዶ/ር ብሩክ እርሳቸው የሚሰሩበት ተቋም ከፍተኛ የኦክስጂን ተጠቃሚ ህሙማንን መቀበል የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱንም ይናገራሉ። ይህ የኦክስጂን እጥረት በአዲስ አበባ እና በክልል በሚገኙ ሆስፒታሎች እንደሚስተዋል የሚናገሩት ዶ/ር ብሩክ፣ ችግሩን ለመቅረፍ የጤና ሚኒስቴር የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንቅስቀሴ እያደረገ መሆኑን እንደሚያውቁ አስረድተዋል። ዶ/ር ብሩክ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቀነስ ከተቀመጡ መመሪያዎች ሁሉ ቢያንስ ቢያንስ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጠቃቀምን መጨመር በወረርሽኙ ስርጭት ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ ይመክራሉ።
የበሽታው መስፋፋት ከዚህም በላይ እንዳይጨምር በግለሰብ ደረጃ የመከላከያ እርምጃዎችን ከመውሰድ ባሻገር በርካታ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸውን ዝግጅቶችና ሥነ ሥርዓቶችን በተመለከተ የተቀመጡ መመሪያዎችን አጠናክሮ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲሉ አሳስበዋል።
አዲስ የኮቪድ-19 ዝርያ ተከስቶ ይሆን?
ዶ/ር ብሩክ በሚሰሩበት እና በሌሎች የኮቪድ-19 ህክምና በሚሰጥባቸው ተቋማት የሚሰሩ ባልደረቦቹ ለኮሮናቫይረስ ታማሚዎች መጨመር አንዱ ምክንያት የጥንቃቄ ጉድለትና መዘናጋት ነው ይላሉ። በዚህ ወቅት እንዲህ በሽታው እንዲንሰራፋ ያደረገው ሌላም ምክንያት ሊኖር እንደሚችል ጥርጣሬ አላቸው። “ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ ውስጥ እንደተደረገው በቫይረሱ ላይ ጥናት ቢደረግ አዲስ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ሊኖር ይችላል” ሲሉ ይሰጋሉ።
ይህንንም ሲያስረዱ መጀመሪያ ላይ በኮቪድ-19 ተይዘው እና ታመው ወደ ህክምና ተቋማት ከሚመጣ ሰዎች መካከል ህመሙ የሚጠናባቸው በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው እንደነበሩ ይጠቅሳሉ። በተጨማሪም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ አንድ ሰው ታሞ ሌሎች የቤተሰብ አባላት ሳይታመሙ ይገኙ እንደነበርም አስታውሰው፤ ምልክት የማያሳዩ ህሙማን ቁጥርም በርካታ እንደነበሩ ጠቅሰዋል። አሁን ግን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መታመማቸው፣ በእድሜም ሲታይ በርካታ ወጣቶች በበሽታው መያዛቸውና ወደ ህክምና ተቋማት መጥተው አልጋ መያዛቸውን ማስተዋላቸውን ይናገራሉ።
ከዚህ በፊት በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቢኖሩም በሚሰጣቸው ህክምና በፍጥነት የማገገም ይታይባቸው እንደነበር የገለጹት ዶ/ር ብሩክ፣ በዚያን ወቅት አልጋ ይዘው የሚቆዩ ሰዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነበር ይላሉ። በአሁኑ ጊዜ የቫይረሱ የመተላለፍ አቅም እና የመግደል አቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው “በእርግጥ ጥናት ያስፈልገዋል፤ በእኔ እይታ አዲስ ዓይነት የቫይረስ ዝርያ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት አለኝ” ብለዋል።
ጨምረውም በዚህ ወቅት ከአንድ ቤተሰብ ሁለት ሦስት ሰው የሚታመምበት እና አልጋ የሚይዝበት አጋጣሚ ተደጋጋሚ መሆኑን ዶ/ር ብሩክ ዓለማየሁ ይናገራሉ። ለበሽታው እንዲህ በአሳሳቢ ሆኔታ መስፋፋት ሁሉም ሰው ማድረግ ያለበት የመከላከያ ጥንቃቄን አለመተግበር መሆኑን ዶ/ር ውለታው ጫኔ እና ዶ/ር ብሩክ ዓለማየሁ የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። በአዲስ የወረርሽኙ ዝርያ ተከስቶ ሊሆን ይችላል የሚለው የዶ/ር ብሩክ ጥርጣሬ እነዳለ ሆኖ፤ ሁለቱም የህክምና ባለሙያዎች እዚህ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ተገቢው ምርመራ መደረግ እንዳለበት ይናገራሉ።