አቶ ገብረእግዚአብሔር ኃይለሥላሴ ከ27 ዓመታት በፊት ሱዳን ከሚገኘው ኡም-ራቁባ የስደተኞች መጠለያ ወደ ኢትዮጵያ ሲሄዱ እንደ ስደተኛ ወደ መጠለያው እመለሳለሁ ብለው በጭራሽ አላሰቡም ነበር።

በ1977 ደርግ አገሪቱን በሚመራበት ወቅት እና ዕድሜያቸው 30ዎቹ አጋማሽ እያለ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት እና ረሃብ ሸሽተው በተሰደዱበት ወቅት የህይወታቸው አስከፊ ጊዜ በዚያ የሚያበቃ መስሏቸው ነበር።

ታሪካዊውን ረሃብና ጦርነት በመሸሽ ለቀናት በእግር ከተጓዙ በኋላ ድንበር አቋርጠው ሱዳን ከገቡ በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።

“መንገድ ላይ ብዙ ሰዎች ሞተዋል። በደርግ ዘመን በተፈፀሙ ግድያዎች ምክንያት በቤታችን መኖር ስላልቻልን በ1977 ከሰቆቃው መሸሽ ነበረብን” ሲሉ አቶ ገብረእግዚአብሔር ያስታውሳሉ።

ለአስር ዓመታት በስደተኞች መጠለያው ውስጥ ሲኖሩ ሁለት ልጆችን ወልደዋል። ደርግ ከወደቀ ከሦስት ዓመት በኋላ ሕይወታቸውን እንደ አዲስ ለመጀመር አቶ ገብረእግዚአብሔር በምዕራብ ትግራይ ወደምትገኘው ራውያን አቀኑ።

ራውያን ከደረሱ በኋላ ሌላ ሚስት አግብተው ተጨማሪ ልጆችን ወልደዋል። በግብርና ነበር የሚተዳደሩት።

በሚያሳዝን ሁኔታ ከ27 ዓመታት በኋላ በ70 ዓመታቸው ድንበሩን አቋርጠው ዳግመኛ እንደማያዩት ተስፋ ወዳደረጉበት የስደተኞች መጠለያ ለመመለስ ተገደዱ።

በትግራይ ክልል በተከሰተው ጦርነትን ምክንያት ወደ ጎረቤት ሱዳን ሸሽተው ከገቡ ከ60,000 በላይ ሰዎች መካከል አቶ ገብረእግዚአብሔር አንዱ ናቸው።

አንዳንዶቹ እንደ አቶ ገብረእግዚአብሔር ሁሉ 30 ዓመት ባልሞላ ጊዜ በድጋሚ ስደተኛ ሆነዋል።

ጦርነቱ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ነበር የተጀመረው። የህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኘውን የፌደራሉን ጦር ሠራዊት ካምፕ ጥቃት ሰንዝረው መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃ ወስዷል።

ግጭቱ በተነሳበት ወቅት አቶ ገብረእግዚአብሔር እና ቤተሰባቸው በእርሻ ቦታቸው ሰብላቸውን እየጠበቁ ነበሩ።

“ግጭቱ የተጀመረው በእርሻ ቦታችን እያለን በመሆኑ ሁለት ሌሊት እዚያው ማደር ነበረብን። ወደ ቤታችን ተመልሰን ደግሞ ሌላ ሌሊት አሳለፍን።”

ግጭቱ እየጠነከረ ሲሄድ እሳቸውም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ህይወታቸውን ለማዳን ወደ ሱዳን ተሰደዱ። ሌሎች ግን በሕይወት ለመትረፍ ዕድለኞች አልነበሩም ይላሉ የ70 ዓመቱ አዛውንት።

“ዓይነ ስውራን ተገድለዋል። የንሐሃ አባቴን ጨምሮ ቄሶችም ተገድለዋል” ሲሉ ከእንባቸው ጋር እየታገሉ ያስታውሳሉ።

ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች በጦርነቱ የሠላማዊ ሰዎች ህይወት አልፏል ቢሉም የሟቾችን ቁጥር ከገለልተኛ ወገን ለማጣራት ግን ከባድ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር 21/2013 ዓ.ም ለተሰበሰበው የአገሪቱ ፓርላማ የፌደራል መንግሥቱ ጦር “አንድም ሰላማዊ ሰው አልገደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

ሆኖም በዓይን ምስክሮች እና በዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ዘገባዎች መሠረት የኢትዮጵያ ፌዴራል ጦር፣ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ የአማራ ክልል ሚሊሻ አባላት እና የጎረቤት አገር የኤርትራ ወታደሮች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል።

‘በሕይወቴ እንደዚህ ያለ ነገር አላየሁም’

አቶ ገብረእግዚአብሔር የአሁኑን ግጭት የትግራይ አማጺያን ከደርግ ሥርዓት ጋር ለ17 ዓመታት ሲዋጉ ከነበረበት የእርስ በእርስ ጦርነት ጋር ያነጻጽሩታል።

የትግራይ ተወላጆች ብሔር ተኮር መገለል ያደርሳል በሚል ከሚከሱት የደርግ መንግሥት ጋር በተደረገው ትግል ህወሓትን ደግፈዋል።

“ከደርግ ሥርዓት ጋር ተዋግተናል። ደርግ ከእኛ ጋር ሲዋጋ በአመጹ ያልተሳተፉ ገበሬዎችን አልገደለም። ቤተ ክርስቲያናትን አልተቃጠለም።”

እንደ አቶ ገብረእግዚአብሔር ከሆነ በአብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች የማይወደደው የደርግ አገዛዝ ሰላማዊ ሰዎችን በመጠበቅ ረገድ ከአሁኑ መንግሥት የተሻለ ነው ብለው ያምናሉ።

“በጦርነት ምክንያት ከቤቴ ሦስት ጊዜ ተፈናቅያለሁ። ይኼኛው ከባድ ነው። በሕይወቴ እንደዚህ ያለ ነገር አልገጠመኝም። እዚህ ቀንና ሌሊት አለቅሳለሁ። የምንበላው ማሽላ እና የምንተኛበት ምንጣፍ ተሰጥቶናል። ሆኖም አገር ቤት የሚራቡ ሰዎችን አስባለሁ። እየተራቡ ነው። ማንም የሚረዳቸው የለም። የተወለድኩበትን ቀን እረግማለሁ” እያሉ በማልቀስ ይናገራሉ።

ወደተወለደበት የስደተኞች ካምፕ መለሰ

በትግራይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ለሁለተኛ ጊዜ ስደተኛ ለመሆን የተገደዱት አቶ ገብረእግዚአብሔር ብቻ አይደሉም።

ሙሉጌታ በርሔም እንዲሁ ለሁለተኛ ጊዜ ስደተኛ የመሆንን ታሪክ እና ስሜቱን ይጋራል።

የሙሉጌታን ታሪክ የበለጠ አስገራሚ የሚያደርገው ተወልዶ ወዳደገበት እና ሱዳን ወደሚገኘው ቱንያድባህ የስደተኞች መጠለያ መመለሱ ነው።

ሙሉጌታ እና አራት ልጆቹ በምሥራቅ ሱዳን ከምትገኘው ገዳሪፍ ከተማ በ136 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቱንያድባህ ውስጥ ከሚገኙት 13,000 ስደተኞች መካከል ናቸው።

ይህ የመጠለያ ጣቢያ በ1970ዎቹ በትግራይ ግዛት ከተከሰተው ግጭት የሸሹትን የሙሉጌታን ወላጆች ጨምሮ ሌሎችንም ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አስጠልሏል።

“እኔ የተወለድኩትም ያደግኩትም ስደተኛ ሆኜ ነው። ወደ ትግራይ ከመሄዴ በፊት እዚሁ ነው የተማርኩትና ያገባሁት” ሲል ሙልጌታ ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ከ 20 ዓመት በኋላ ከልጆቼ ጋር ወደ ተወለድኩበት እና ወዳደኩበት መጠለያ ተመልሼ መጣሁ።”

ልክ እንደ አብዛኛዎቹ በመጠለያው ውስጥ እንዳሉ ስደተኞች እርሱም ሆነ ሌሎች ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ያስገደዳቸው ግጭት ባልተጠበቀ ሁኔታ የመጣ ነበር። ግጭቱ ከተጀመረ በኋላም ቢሆን ችግሩ በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ ከአገሩ እንዲሰደድ እንደሚያሰገድደው አላሰበም ነበር።

“ዳግመኛ ስደተኛ እሆናለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። በሁመራ ከተማ ጥሩ ሕይወት ነበረኝ። አራት ልጆቼም እዚያ ነው የተወለዱት” ብሏል።

“ሱዳን ሁለተኛ ቤታችን ናት”

ሙሉጌታ ለመፈናቀሉ የኢትዮጵያ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋል። የኢትዮጵያ ኃይሎች ኅዳር ወር ላይ ጥቃት መሰንዘር ከጀመሩ በኋላ እሱ እና ቤተሰቦቹ በምዕራብ ትግራይ የምትገኘውን ሁመራን ለቀው ለመሰደድ መገደዳቸውን ይናገራል።

“ስደተኛ ሆኜ አድጌ ልጆቼም በዚሁ ህይወት ሲያልፉ ማየቴ ያሳዝነኛል። ልጆቼ በነበርኩበት ዓይነት አስቸጋሪ ሕይወት ውስጥ እያልፉ ነው ብዬ ማመን አልችልም” ይላል።

ሆኖም በፈታኝ ወቅት ገጥሞት ከለላ ሲያሻው “ሁለተኛ እናት አገር” ስላለው ያመሰግናል። “ሱዳን ሁለተኛ ቤታችን ናት ስል ማጋነኔ አይደለም” ይላል።

የፌደራል መንግሥት በኅዳር ወር መጨረሻ ዋና ዋናዎቹን የትግራይ ከተሞች ከተቆጣጠረ በኋላ ድል መቀዳጀቱን ቢገልጽም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እንደቀጠሉ ናቸው።

አቶ ገብረእግዚአብሔር እና ሙሉጌታን ጨምሮ በሺዎች ለሚቆጠሩ እና በሱዳን የሚገኙ ስደተኞች ወደ አገራቸው መቼ እንደሚመለሱና እና እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው የግጭት የመፈናቀል ስጋት ሳይኖር ህይወታቸው እንደገና እንደሚመሰርቱ ማንም አያውቅም።

 ምንጭ – ቢቢሲ      

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *