ምናልባት ጋዜጠኞች ግጭትን ሪፖርት በሚያደርጉበት ወቅት ሊሠሩት የሚችሉት በጣም አስፈላጊው ነገር እየተካሔዱ ባሉ ወሳኝ ኩነቶች ውስጥ መሳተፍ ነው። እኛ በግጭቶች ላይ ዘገባ በምናደርግበት ጊዜ የራሳችንን እምነት እና አመለካከት ተፅዕኖ እንዳያሳድርብን መጠንቀቅ አለብን። በሐቀኝነት ከሳሰላሰልነው በኋላ ነው ሴትሳቢል ሲቢሲ ጋዜጠኞች ማድረግ አለባቸው ያለችውን የሚከተለውን ምክር መተግበር የሚገባን:

በንፁሕ አእምሮ ወደ ታሪኩ ይሒዱ። ማንኛውንም ዓይነት ግምታዊ አስተሳሰቦች ያፅዱ እና ሁሉም የተሳተፉ ሰዎች ምን እንደሚሉ ለመስማት ፈቃደኛ ይሁኑ… ለየትኛውም ወገን ሳይደግፉ መረጃውን ያቅርቡ። አዳዲስ ሁኔታዎችን በተመለከተ መረጃ እንደሚያገኙ ያረጋግጡ።

በግጭቱ ላይ ሪፖርት በምናደርግበት ጊዜ የሚዲያው ተቋማዊ እሴቶች የሚያሳድሩብንን ተፅዕኖ ከግምት ማስገባት አለብን። የምንሠራበት የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ግጭት እንዲባባሱ የሚያደርጉ አጀንዳዎችን የሚፈልጉ ከሆነ፣ ውሳኔ ለሚሰጡት አካላት ያሉትን አደጋዎች በመጥቀስ እንዲሁም የግጭት አጋናዛቢ ዘገባን ጥቅም ለማሳመን የምንችላቸውን ሁሉ ማድረግ አለብን። ክሪስ ቺናካ  የግጭት ዘገባ የሚሠሩ ጋዜጠኞች ለራሳቸው በጣም ከፍተኛ መሥፈርቶችን ማውጣት እንዳለባቸው ይናገራል። ምክንያቱም፦

… ግጭትን በተመለከተ በሚከታተሉበት ጊዜ በጣም ስሜታዊ ጉዳዮችንም ይከታተላሉ፤ ምናልባትም የሞትና የሕይወት ሁኔታዎችን የሚያካትት፣ የሰላም እና አስተዳደር አንዲሁም ከፍትሕ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች። ከሌሎቹ የጋዜጠኝነት ዘርፎች የበለጠ ትልቅ ኃላፊነት አለብን። ትልቅ ኃላፊነት ነው።

ወደድንም ጠላንም የግጭት ዘገባ ስናቀርብ የግጭቱ ዐውድ አካል እንደምንሆን ልብ ልንል ግድ ይላል። ራሳችንን እንደ ገለልተኛ ታዛቢ መቁጠር የለብንም። ምንም እንኳን ብዙ ጊዜ እርግጠኛ ሆነን ተፅዕኖው ምን እንደሆነ መተንበይ ባንችልም ሥራችን ሁልጊዜ በግጭቱ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። ባርባራ አሞንግ እንደምትለው፣ “የግጭቱን ዘገባ በሠራንበት መንገድ ብቻ ጦርነቱን ማባባስ ወይም ሁኔታውን ማረጋጋት ወይም ሁኔታውን መቆጣጠር ይችላሉ”። ታሪኮችን የምንናገርበት አቀራረብ ሰዎች ጉዳዩን የሚረዱበትን መንገድ እና እርስ በርስ እንዴት እንደሚተያዩ ግንዛቤ ይሰጣል። ኪዮኮ ኪቫንዲም በዚህ ይሥማማሉ። በኬኒያ በ2007/2008 ምርጫ ማግሥት ስለ ነበረው ነውጥ ሲገልጽ እንዲህ ይላሉ፦

… እኛ ኃላፊነት አለብን… እንደ መገናኛ ብዙኃን ተቋምም ሆነ እንደ ጋዜጠኛ ዘገባ ለመሥራት ብለን ብቻ አንዘግብም። እዚህ ያለነው ማኅበረሰባችንን ለማስቀጠል ነው። እነዚህ ማኅበረሰቦች ከጠፉ እኛም ቦታ የለንም። የምንጫወትበት ሜዳ አይኖረንም።

ግጭት ውስጥ የገቡ ቡድኖች ከሚዲያ የተወሰኑ እርምጃዎችን ብቻ የሚከተል ሽፋን የሚጠብቁ በመሆናቸው፣ በግጭቱ ወቅት ምን ዓይነት ባሕሪ ሊያሳዩ እንደሚገባ ከሚዲያ ሊማሩ ይችላሉ። ስለ ሰላም እና ጋዜጠኝነት የብዙ ጠቃሚ መማሪያ መጽሐፍት ደራሲ የሆኑት ጄክ ሊንሽ እና አናቤል ማክጎድሪክ በግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ሚዲያዎች ለሚሰጡት ሽፋን በሚሰጡት ግምት እና አድማጮች ለዚያ ሽፋን ምላሽ የመስጠት አቅማቸው ላይ በመመርኮዝ መግለጫዎቻቸውን እና ተግባሮቻቸውን የሚያስተካክሉበትን ይህንን ሁኔታ የግብረመልስ አዙሪት ሲሉ ይገልፁታል።

የምናስተላልፈው ወይም የምናትመው እያንዳንዱ ታሪክ ሰላምን በማስፈን ረገድ ትንሽ አስተዋፅዖ የማድረግ አቅም አለው። በተመሳሳይ ግጭትን የማባባስ አቅምም ይኖረዋል። የሚከተሉት ጥያቄዎች ግጭት-ነክ የሆኑ ታሪኮችን በምንሠራበት ወቅት መጠየቅ ያለብን ናቸው። በምኅፃረ ቃል ፍተኃት ይባላል (ፍትሐዊነቱ? ተፅዕኖው? ኃላፊነቱ? ትክክለኛነቱ?)።

3.1 ታሪኩ ፍትሐዊ ነው?

ራስዎን ይጠይቁ፣ ታሪኩ ለሁሉም ወገኖች ሚዛናዊ ነው? ሁሉም በግጭቱ የተሳተፉ አካላት የራሳቸውን ወገን ታሪክ እንዲያስረዱ ዕድሉ ተሰጥቷቸዋል? የተዘነጋ በግጭቱ ድርሻ የነበረው አካል አለ?

ሚዛናዊ መሆን ማለት አንዳንድ ወገኖች ተመሳሳይ ሀብቶች እና መሠረተ ልማት አቅርቦት እንደሌላቸው እና ከዜና አውታሮች ጋር እንዴት መሥራት እንዳለባቸው አለማወቅንም እንደሚጨምር መገንዘብን ይጨምራል። አነስተኛ ማኅበረሰብን መሠረት ያደረጉ ቡድኖች በአካባቢያቸው የሠለጠኑ የሚዲያ ግንኙነት ባለሙያዎች እና ሐኪሞች የመኖራቸው ዕድል አነስተኛ ነው። ይህ ማለት እነሱን ችላ ማለት አለብን ማለት አይደለም። ይልቁኑም ጋዜጠኞች የእነዚህ ሰዎች ድምፅ መሰማቱን ለማረጋገጥ ልዩ ጥረት ማድረግ አለባቸው።

ለተደራሾቻችን ሚዛናዊ ሆነን እናውቃለን? ስለሚሆነው ነገር የተገናዘበ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችሉ መረጃዎች ሁሉ ተሰጥቷቸዋል? ተደራሾቻችን ብዙውን ጊዜ በግጭቱ ውስጥ በቀጥታ እንደሚሳተፉ እና በዘገባችን የምናካትታቸው ጉዳዮች የነሱም ጉዳዮች መሆናቸውን ማወቃችን አስፈላጊ ነው። በግጭቱ ውስጥ በተነሱት ጉዳዮች ላይ የራሳችንን አቋም ጠንቅቀን ማወቅ ይኖርብናል። እንዲሁም ምርጫዎቻችን እና ጭፍን ጥላቻዎቻችን የምንጠይቃቸውን ጥያቄዎች፣ የምንመርጣቸውን ምንጮች እና የምንጠቀመው ቋንቋ ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ያለማቋረጥ መመርመር አለብን። ይህ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ምክንያቱም እኛ ሳይታወቀን አድልዎ ልንፈፅም እንችላለን። ተጨባጭ አቋም መያዝ ያንን አድልዎ አያስወግድም። ስለ ለግጭቱ በምንሰጣቸው ምላሾች ላይ ዘወትር ማሰላሰል እና ይህም ዘገባችንን እንዴት እንደሚያስተካክል መጠየቅ አለብን። ጀምስ ምፋንዴ ይህ ጉዳይ ለጋዜጠኞች በተለይም በቅርባቸው ያለ ግጭትን ለሚዘግቡ አስፈላጊ መሆኑን እንደሚከተለው ይገልጻል:

ብዙ ኃላፊነቶች ይጠበቅብዎታል ምክንያቱም ይህ ነገር (ግጭቱ) በራስዎ ወይም የተወሰኑ የቤተሰብ አባላት ወይም ራቅ ያሉ ቤተሰቦችን በተወሰነ መልኩ ጫና የማሳደር ዕድሉ ከፍተኛ ነው… ዘገባዎም ጫና ሊደርስበት ይችላል።

በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ ጋዜጠኞች ግጭቱ በራሳቸው ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ የማሳደር አቅም ሊገነዘቡ ይገባል። እንዲሁም ግጭቱ ግጭት ውስጥ የገቡ አካላትን በሚዛናዊነት የሚመለከቱበትን ሁኔታ በምን መልኩ ጫና እንደሚያሳድር በጥንቃቄ ማሰብ አለባቸው። ባርባራ እንደሚከተለው ትዝብቷን ትገልጻለች፡-

እንደ ጋዜጠኞች ማኅበረሰቡን በጥሩ እና በክፉ አጋጣሚዎች ውስጥ እናየዋለን። እዛው ነው ያለነው እናም በሁለቱም ሁኔታዎች እናገኛቸዋለን፤ በጥሩውም በክፉውም። እንደ ጋዜጠኛ በነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ሲሆኑ በተቻለ መጠን ሙያዊነትዎን ጠብቀው እንዴት መቆየት ይችላሉ?

ጋዜጠኞች ወገንተኛ ሆነው ከታዩ ልዩነት የመፍጠር አቅማቸውን በከፍተኛ ደረጃ ሊቀንሰው እንደሚችል ማወቅ አለባቸው። ጋዜጠኛው በግጭቱ ውስጥ በተሳተፉ አካላት ተዓማኒነት ካላገኘ በመጨረሻው ክፍል ከተወያየንባቸው ሚናዎች ውስጥ አንዱን እንኳን በተሳካ ሁኔታ ማሟላት አይችልም።

ማስታወሻ

ጋዜጠኞቹ አመራሩ ስለ ጉዳዩ ምን እንዳለ ሪፖርት ያደርጋሉ፤ ግን ብዙውን ጊዜ በግጭቶች ውስጥ የተወጠሩ የዜጎችን እና ማኅበረሰቦችን ዕይታ ችላ ይላሉ። እነዚህ ዜጎች ድምፃቸው እንዲሰማ ዕድል ተሰጥቷቸዋል? የተለያዩ አካላት በእነሱ ላይ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተወክለዋል? በታሪኩ ውስጥ የተካተተ አንድ አካል በተሳሳተ መንገድ እንደተጠቀሰ ሆኖ ይሰማዋል? የተለያዩ አካላትን አቋማቸውን፣ ፍላጎቶቻቸውን እና ጥቅማቸውን ለመግለጽ ምን ዓይነት ቋንቋ ተጠቅመን ነበር? እነዚህ ሁሉ ነገሮች አንድ ታሪክ ሚዛናዊ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *