ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በቅርበት ሆነው ማየት ያልቻሉትን ነገር ከውጭ ያለ ሰው ይመለከተዋል… ሰዎች ከእርስዎ ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ላይሆኑ ይችላሉ ብለው ያስቡ ይሆናል፣ ነገር ግን ከልምዴ እንዳየሁት አዎ ፈቃደኛ ይሆናሉ፤ ምክንያቱም ሰዎች ስለ ግጭቱ እና ምን እየተከሰተ እንደሆነ ለማብራራት ይፈልጋሉ። ሁል ጊዜ ከአዳዲስ የግጭት ተሳታፊ ወገኖች በምትነጋገሩበት ጊዜ ግጭቱ መልኩን ይቀይራል፤ በአዲስ ዕይታ ታዩታላችሁ፣ አሁንም ሌላ ዕይታ፣ አሁንም እንደገና ሌላ ዕይታ። እና ብዙውን ጊዜ እርስ በርስ ስለማይነጋገሩ ሸምጋዩ ወገን ከእነሱ እጅግ የተሻለ አጠቃላይ ዕይታን ያገኛል።
ይህ የሰላም ጥናቶች አባት እንደሆኑ በብዙዎች ዘንድ የሚታመንላቸው ፕሮፌሰር ዮሃን ጋልቱንግ ሐሳብ በግጭት ሁኔታዎች ውስጥ የውጪ ሸምጋዮች ጣልቃ መግባትን ጥቅም ያሳያሉ። ጋዜጠኞች ብዙዎቹን እነዚህን ጥቅሞች ይጋራሉ ብለን እናምናለን። ከግጭቱ በተወሰነ ደረጃ ሙያዊ ርቀትን መጠበቃቸው ጋዜጠኞች ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ውስጥ የማይገኝ የግጭቱን አንፃር እንዲገነዘቡ ያስችላቸዋል። በአጠቃላይ ጋዜጠኞች (ሁል ጊዜም ባይሆን) ከሁሉም ወገኖች ካሉ ሰዎች ጋር የሚነጋገሩ ሲሆን፥ ሰዎች አቋማቸውን ለዘጋቢዎች ለማብራራትና ብዙ ጊዜ ለመስጠት ፈቃደኞች ናቸው። ሁሉንም ወገን ማናገር መቻል ማለት ጋዜጠኞች ግጭቱን ከተለያየ አቅጣጫ እንዲገነዘቡና የተለያዩ ወገኖች ያላቸውን አመለካከት እንዲያዩ በመርዳት ሚና ይጫወታሉ ማለት ነው።
ክፍል ሁለት ጋዜጠኞች የግጭት ዘገባ በሚሠሩበት ወቅት የሚኖሯቸውን የተለያዩ ሚናዎች ላይ ትኩረት ያደርጋል። እነዚህ ሚናዎች ጋዜጠኞች ዕለት ተዕለት የሚሠሯቸውን ሥራዎች ከሸምጋዮች በግጭት ዙሪያ ከሚኖራቸው ሚና ጋር በማነፃፀር የተገኙ ናቸው። ንፅፅሮቹ ጠቃሚ ቢሆኑም ጋዜጠኞች ሆን ብለው ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖችን ለመሸምገል መፈለግ አለባቸው እያልን እንዳልሆነ ልብ ማለት አስፈላጊ ነው። እያልን ያለነው ጋዜጠኞች እና የሚሠሩላቸው የሚዲያ ተቋሞች በኅብረተሰቡ ውስጥ የሽምግልና ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ግጭቱን በላቀ የትብብር መንፈስ ለመመርመር እንዲችሉ የሚያደርግ “የሽምግልና ሜዳ” እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ።
ከዚህ በታች የሚብራሩት ሁሉም ሚናዎች በተለምዶ ከምናውቀው የመልካም ጋዜጠኝነት ዕሳቤ ጋር ይጣጣማሉ። ባርቤ ዜሊዜር መልካም ጋዜጠኝነት “የተወሳሰቡ፣ ግልጽ ያልሆኑ እና ብዙውን ጊዜ ቀጥተኛ የሚመስሉ ነገር ግን ድብቅ የሆኑ ክስተቶችን” መፍታት እንዳለበት ይገልጻሉ። እነዚህ ሚናዎች ጋዜጠኞችን ከግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ጋር እንዲወግኑ ሳይሆን ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት ሥራቸው ምን ያህል አስተዋፅዖ እንደሚያደርግ እንዲገነዘቡ ይጠይቃሉ። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ምን ዓይነት ባሕሪ ሊያንፀባርቁ እንደሚገባ ጋዜጠኞች ሊጠይቋቸው አይገባም፤ ነገር ግን ጋዜጠኞቻቸው ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ለሚያሳዩት ባሕሪ ተጠያቂነት እንዲሆኑ ማድረግ መቻል አለባቸው። ጋዜጠኞች አንድ መፍትሔን ብቻ በመደገፍ እንዲያበረታቱ አይጠበቅም፤ ነገር ግን ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች የወሰኑት ውሳኔ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ከግምት እንዲያስገቡ መጠየቅ አለባቸው። ጋዜጠኞችን የፍትሐዊነት እና ትክክለኝነትን ዓላማዎች እንዲተዉ አይጠይቁም፤ ነገር ግን ጋዜጠኞች ከተለመዱ የዘገባ አሠራሮች በላይ እንዲሔዱ ይፈለጋል። ጋዜጠኞች ፊት ለፊት የሚነገረውን ብቻ መቀበል የለባቸውም። ከዚያ ባሻገር የግጭቶችን ትክክለኛ መንስዔዎችን እና ከግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ዓላማ በስተጀርባ ያለውን ትክክለኛ መንስዔ ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በተጨማሪም ጋዜጠኞች ከተለመደው ምንጮች በዘለለ እንዲሔዱ ይጠበቃል። ብዙውን ጊዜ ተንቀው የሚተዉ አካላት የሚናገሩት ጠቃሚ ታሪኮች አላቸው።
የዚህ ክፍል ቀሪው አካል ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ውጤታማ በሆነ መንገድ ግጭቱን እንዲፈቱ እና መፍትሔ እንዲያገኙ ጋዜጠኞች እንዴት ልዩነት ማምጣት ይችላሉ በሚለው ላይ ትኩረት ያደርጋል። እነዚህን ሚናዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት በሁሉም ታሪኮች ውስጥ ሁሉንም በአንድ ጊዜ መጠቀም እንደሚከብድ መገንዘብ ይኖርብናል። ነገር ግን የእነዚህ የተለያዩ ሚናዎች ልምድ ተፅዕኖዎች ከጊዜ በኋላ ልዩነት ሊፈጥሩ ይችላሉ ተብሎ ተስፋ ይደረጋል። በቀጣይ ገጽ ጋዜጠኞች ሊኖሯቸው የሚችሏቸውን ሚናዎች እንመልከት።
ጋዜጠኞች በግጭቶች ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ መግባት ይችላሉ?
ጋዜጠኞቹ በግጭት ሁኔታዎች ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ መግባት አለባቸው ወይ የሚለው ጥያቄ በአዘጋጅ ክፍል አባላት መካከል የጦፈ ክርክር አስነስቷል። ጋዜጠኞች ራሳቸውን እንደ ሸምጋዮች ማየት እንደሌለባቸው ሁሉም ተስማምተው፣ ነገር ግን ጉዳዩ ቀላል እንዳልሆነም ተገንዝበዋል። ባርባራ አሞንግ “በመጡበት ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ እና የሚሠሩ ጋዜጠኞች በጣም ጥሩ ሸምጋዮች ሊሆኑ ይችላሉ” ሲሉ አስረድተዋል፤ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ የሚከሰቱትን ክስተቶች እንደ ጋዜጠኝነት ለመሸፈን በጣም ስሜታዊ በሆነ መልኩ ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል። በግልጽ የሸምግልና ሚናን መጫወት ፈልገው ሳይሆን፣ የተማሩ ስለሆኑ፣ የሕግ እና የፖለቲካ ሒደቶችን ስለሚረዱ እና ታዋቂ ስለሆኑ ሰዎች ብዙ ጊዜ ወደነሱ ያማትራሉ። በእንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ጋዜጠኞች በብዛት ማኅበረሰባቸውን መርዳት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል።
ጋዜጠኞች እንዴት ግጭቶችን እየዘገቡ በመሸምገሉም ሒደት መሳተፍ ይችላሉ? ወይም፣ በሽምግልና መሳተፉን እና መርዳታቸውን ትተው ግጭቱ በራሱ እንዲሔድ ማድረግ አለባቸው? እነዚህ መሐል የሆነ አስታራቂ ሐሳብ አለ? በሚሉት ጥያቄዎች ላይ የክፍሉ አባላት ተከራክረው ነበር። ለችግሮቹ በቀጣዩ ገፅ የተቀመጡትን የሚከተሉት ሦስት መፍትሔዎች ተሰጥተዋል።
መፍትሔዎቹ፥
- ጋዜጠኛች ግጭት ውስጥ የገቡትን አካላት መርዳት እና ማደራደር ይችላሉ። ነገር ግን ሁኔታውን በሚዘግቡበት ወቅት ሚናቸው ግልጽ መሆን አለበት። ጋዜጠኞቹ በታሪኩ ውስጥ፣ ይህ ለየት ያለ ሁኔታ መሆኑን እና በተለምዶ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር አለመሆኑን በግልጽ ማሳየት አለባቸው።
- ጋዜጠኞቹ በቀጥታ በሽምግልና ሒደት ውስጥ ለመሳተፍ ባይሥማሙም እንኳ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖችን ስለ መብቶቻቸው በማስተማርና ስጋታቸውን ለመቅረፍ ሊከተሏቸው የሚችሏቸውን መንገዶች ለሰዎች በመግለጽ የምክር ሰጪ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። በብዛት በግጭቱ ውስጥ በተሳተፉ ባለድርሻ አካላት መካከል የመጀመሪያ ግንኙነቶችን ለማመቻቸት ይጠቅማሉ።
- ጋዜጠኞች ጉልህ ሚናን ለመውሰድ ላይፈልጉ ይችላሉ፤ ነገር ግን በዘገባው አማካይነት ወገኖች በራሳቸው መፍትሔ ለማግኘት የሚረዳቸውን አስፈላጊ ጥያቄዎች ሊያቀርቡ ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉት ጥያቄዎች የግለሰቦችን እና የቡድን መብቶችን፣ የአገልግሎት ሰጭዎችን እና ኩባንያዎችን ግዴታ እንዲሁም በተወሰኑ ሁኔታዎች ውስጥ የሚሠሩ መፍትሔዎች ላይ ትኩረት ለማድረግ ይጠቅማሉ።
የሚከተለው ከደቡብ አፍሪካ የተገኘ እውነተኛ ታሪክ አንዲት ጋዜጠኛ በዘገባዋ ባለማወቅ ባለፀጋ ጎረቤታሞች መካከል ራሷን ስትሸመግል እንዳገኘች ለማሳየት ይጠቅማል። ግጭቱ የተጀመረው አንደኛው ሰው የመዋኛ ገንዳው በግቢው ወሰን ላይ እንዳረፈ እና ድንበሩን እንደጣሰ በተሰማው ጊዜ ነበር። መዋኛ ገንዳው እንዲነሳ በመፈለግ ጎረቤቱን ለመክሰስ በዝግጅት ላይ ነበር። የአንዱን ዕድል ሊያሳጣ የሚችል ሕጋዊ ፍልሚያ ላይ ቀርበዋል። ጋዜጠኛዋ በመጀመሪያ ከሳሹን በጣም የተበሳጨበት ጉዳይ ምን እንደሆነ ለማወቅ ቃለ መጠይቅ አደረገችለት። በዚህ ቃለ ምልልስ ሰውየውን ከዋና ገንዳው በተጨማሪ የሚያበሳጨው ሌሎች ጉዳዮች መኖራቸውን ተገነዘበች። ከነዚህ ውስጥ የጎረቤቱ ድምፃቸው የሚረብሹ ፓርቲዎችን የማስተናገድ ዝንባሌን እና የውሻውን ኃይለኛ ጩኸት መቆጣጠር አለመቻልን ያካትታሉ። ከሌላኛው ጎረቤት አስተያየት ለመጠየቅ እና ለቀረበበት ክስ ምላሽ እንዲሰጥ በጠየቀች ጊዜ ክሱ ከዋና ገንዳው ጋር ብዙም ግንኙነት እንደሌለው እና በዋነኝነት በሁለቱ ሰዎች መካከል ካለው ግንኙነት ጋር እንደሚያያዝ ግልጽ ሆነ። ታሪኩ የሚያልቀው ጎረቤታሞቹ በጋራ ቁጭ ብለው ተሥማምተው የሚኖሩበትን ሁኔታ ሊመክሩ ሲወስኑ ነው። በመጨረሻም ከወሰኑ አልፎ የታየው የዋና ገንዳው አካል በሁለቱ ክልል መኸል ባለ የማዘጋጃ መሬት ላይ መሆኑን አወቁ። በዚህ ጊዜ የድንበር ግጭቱ ጉዳይ ችግር መሆኑ ቀርቶ ጎረቤታሞቹ ያለምንም ግጭት በጋራ መኖር ቀጠሉ።
2.1 ጋዜጠኞች በተለያዩ ወገኖች መካከል የተግባቦት መንገድ መፍጠር ይችላሉ
ጋዜጠኞች በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች እርስ በርሳቸው ብቻ ሳይሆን በግጭት ውስጥ በቀጥታ ተሳታፊ ካልሆኑ አካላትም ጋር እንዲነጋገሩ ሁል ጊዜም ዕድል ይሰጣሉ። የዝግጅት ክፍላችን ቡድን አባል የሆኑት ጄምስ ምፋንዴ እንደተናገሩት በሁሉም ወገን ስላሉ ሰዎች በመናገር “ሰዎች እርስ በርስ እንዲነጋገሩ” የሚያደርግ “ድልድይ” መሆን ይቻላል። ይህ ማለት ፊት ለፊት አንድ ላይ ማገናኘት ማለት አይደለም፤ ይልቁንም “ሁለቱንም ጎራዎች እንዲደርሳቸው ሐሳቦቻቸውን የሚያጋሩበት መድረክ ትሰጧቸዋላችሁ”። ጄምስ እንደሚሉት ይህን በማድረግ ጋዜጠኞች “አንዳቸው የሌላውን አቋም እንዲረዱ ሊያግዙ ይችላሉ”።
ባርባራ ሞንግ ሐሳቡን በመደገፍ እንዲህ ይላሉ:
ስለ ግጭቱ አንድ ሰው የሆነ ነገር ይላል፣ ከዚያም እኔ እንደ ጋዜጠኛ ሌላኛውን ሰው መልስ እጠይቀዋለሁ። ሌላኛው ሰውም ለመጀመሪያው ሰው ንግግር ምላሽ ይሰጣል። ታሪኩ ሚዛኑን ይጠብቃል። የሁለቱንም ወገኖች በዘገባዬ አካትታለው።
ሆኖም በብዙ አጋጣሚዎች ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ዓላማቸውን ለማሳወቅ እና በተቀናቃኞቻቸው ላይ ጫና ለማሳደር ሚዲያውን ለመጠቀም ይሞክራሉ። ምንም እንኳን ይህ በግልጽ የግንኙነት ዓይነት ቢሆንም ጠቃሚ ግን አይደለም። ቡድኖቹ ሚዲያውን እርስ በርስ የሚወነጃጀሉበት ሜዳ አድርገው እንዲጠቀሙ የምንፈቅድላቸው ከሆነ በማኅበረሰባችን ውስጥ ለሚካሔድ ሰላማዊ ግንባታ አስተዋፅዖ እያበረከትን አይደለም። ፍትሐዊ፣ ሚዛናዊ እና ትክክለኛ ሽፋን ማቅረብ አልቻልንም ማለት ነው። ወደ ግጭቱ እየገባን እንዲሁም ሳናውቅ እና ፈቃደኛ ሳንሆን ለሌላ አካል ዕቅድ ማስፈፀሚያ መሣሪያ እንሆናለን።
አንዳቸው ሌላኛው ላይ የስድብ ናዳ እንዲያወርዱና እና የሐሰት ክስ እንዲያቀርቡ በሚያደርግ መልኩ ግጭት ውስጥ የገቡ ቡድኖች ጎልተው ሚታዩበት መድረክ ማቅረብ የእኛ ሥራ አይደለም። የኛ ሥራ በዓለማችን ዙሪያ ምን እየተካሔደ እንዳለ ማሳየት ነው። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ፍላጎቶቻቸውን፣ እሴቶቻቸውን እና ጥቅማቸውን እንዲያብራሩ የሚያግዙ ጥያቄዎችን መጠየቅ አለብን። ስለ ስሜቶቻቸው እና ስጋቶቻቸው እንዲናገሩ ማድረግ አለብን። በግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች የተሰጠ መግለጫ መውሰድ እና በዜና ዘገባ ውስጥ ማካተት ብቻ በቂ አይደለም። ከዚህ በመሻገር ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች፣ ሚዲያዎች ሰዎች እርስ በእርሱ እንዲተዋወቁ፣ ልዩነቶችን እንዲመረምሩ እና መፍትሔዎችን እንዲፈልጉ ስለሚያስችሉ ለእውነተኛ ተግባቦት እንዲጠቀሙበት ማበረታታት ያስፈልገናል። ይህ ማለት ከወሬ እና የቃላት ውንጀላዎች ባሻገር መሔድ ማለት ነው።
ጋዜጠኞች በሰላም ማስፈን ሒደት ላይ በቀጥታ ተሳትፎ ያላቸው ልኂቃንን፣ ማለትም ፖለቲከኞች፣ የችሎት ኃላፊዎች፣ ሸምጋዮች እንዲሁም ሌሎች አስተያየት ላይ የሚያተኩሩበት ጊዜ አለ። ጋዜጠኞች አስታራቂ ሜዳውን ለማስፋት የሚፈልጉ ከሆነ መረጃ የሚያገኙባቸውን ምንጮች ማስፋት መቻል አለባቸው።
ለባርባራ ይህ ማለት፡
…. የዋና ዋና ተሳታፊዎች ድምፅ ብቻ ሳይሆን የተጠቂዎችም ድምፅ በእኛ ታሪኮች ውስጥ መሰማት አለባቸው። ልኂቃኑ በሚወስዷቸው እርምጃዎች የተጠቁ ሰዎች መሰማት አለባቸው። ለሰዎችን በመገናኛ ብዙኃን በኩል ስጋቶችን ስናመላክት፣ መገናኛ ብዙኀኑ ለሁሉም ለተጠቁት ግለሰቦች ክፍት መሆን ይኖርባቸዋል። ይህም ሰዎች በጉዳዩ እንዲሳተፉ እና ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲወስዱት ያደርጋል። መገናኛ ብዙኀን የንግግር ሱቅ ብቻ ሳይሆኑ መፍትሔ አፈላላጊም መሆን አለበት።
ግጭት የበለጠ የቡድን ትብብርን የሚያበረታታ ቢሆንም፥ ይህ ማለት ግን የተወሰኑ ቡድኖች አባላት ሁሌም አንድ አስተሳሰብ አላቸው ማለት አይደለም። በተፎካካሪ ቡድኖች ውስጥ ያሉ የተለያዩ ንዑስ ቡድኖች የጋራ ጉዳዮችን እና ጥቅሞችን ምናልባት ሊጋሩ ይችላሉ። አንዳንዴ እነዚህን የጋራ የሚያደርጓቸውን ጉዳዮች በመገናኛ ብዙኀን ሊያካፍሉ ይችላሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ጋዜጠኞች ለእውነተኛ ንግግር መድረኩን ሊያመቻቹ ይገባል።