በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ በተደጋጋሚ እያጋጠመ ያለው ዘር ተኮር የንጹሃን ሞትና ሰቆቃ እንዲያበቃ፣ መንግስት ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ፓርቲዎች አሳሰቡ።
በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ሻንቡ ጃርቴ ወረዳ ዴቢስ በተባለ ቀበሌ እንዲሁም በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ በፅንፈኛ ብሔርተኞች፣ የንፁሃን ህይወት በየጊዜው መቀጠፉ በእጅጉ እንዳሳዘነው የገለጸው ኢዜማ፤ “የፌደራልና የክልል መንግስታት የዜጎችን ሞት ማስቆም ባለመቻላቸው ከፍተኛ የደህንነት ስጋት በሀገር እና በህዝብ ላይ ተፈጥሯል” ብሏል።

“የዜጎችን ህይወት መጠበቅ ያልቻሉ መሪዎች በሃላፊነት የሚጠየቁበት ጊዜ እንዲመጣ፣ አጥፊዎች ተቀጥተው የተጎጂዎች እንባ እንዲታበስ፣ ኢትዮጵያውያን በሃገራችን በፈቀድነው ቦታ በነፃነት መኖር እንድንችል መንግስት፤ ሃገር የመምራት  የዜጎችን የመኖር መብት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቀርባለሁ” ብሏል ኢዜማ በመግለጫው።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በበኩሉ፤ በወለጋ እየተፈፀመ ያለው የዘር ማጥፋት ድርጊት ነው ብሎ እንደሚያምን ጠቁሞ፤ ከሰሞኑ በተፈጸመ ጥቃትም ከ60 በላይ ንፁሃን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን አስታውቋል። ለዚህ ጥቃትም ኦነግን ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ያደረገው የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስትና በመንግስታዊ መዋቅሩ ውስጥ ያሉ አካላት  ከተጠያቂነት አያመልጡም ያለው ባልደራስ፤  ጥቃቱ በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል ብሏል።

የመላ ኢትዮጵያውያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጥቃቱን በፅኑ አውግዞ፤ በአማራ ተወላጆች ላይ በየጊዜው የሚፈፀመው መሰል ጭፍጨፋ መቼ ነው የሚያቆመው?” ሲል ጠይቋል- መንግስት ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ በማቅረብ።  የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን በበኩሉ “ኦሮሚያ ክልል ወለጋ በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል የኦሮሚያ ብልፅግና አመራሮች የአደባባይ ፍረጃ ውጤት ነው”በአካባቢው በአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት ሊፈጽም እንደሚችል በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ መስጠቱን በመግለጫው ያመለከተው አብን መንግስት ለማሳሰቢያው ትኩረት ባመስጠቱ ከየካቲት 27 ቀን 2013  ጀምሮ በአካባቢው በተፈፀመ ጥቃት ከ60 በላይ ወገኖቹ በጭካኔ ተገድለዋል ብሏል።

በዚህም የክልሉ መንግስት መዋቅር ተሳታፊ ነበር ሲል አብን የክልሉን መንግስትም በግድያው ቀጥተኛ ተጠያቂ አድርጓል። በጥቃቱም ዋነኛ ምክንያት አማራ ጠል የፅንፈኛ ፖለቲካ እና የፍረጃ ቅስቀሳዎች ናቸው ብሏል አብን በመግለጫው። የካቲት 27 ቀን 2013 ጀምሮ እስካአሁን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ  በተፈጸሙ ዘር ተኮር  ጥቃቶች 42 ሰዎች  በብሔር ተለይተው በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የክልሉ ፖሊስ አስታውቋል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *