1.11 ከአሸማጋይነት ባሻገር
በግጭት ውስጥ ባሉ የቡድን መሪዎች መካከል አሸማጋይነት ግጭትን ወደ ሰላማዊ መፍትሔ ለማሸጋገር ውጤታማ መንገድ ሊሆን ቢችልም እንደነዚህ ያሉት ሒደቶች በራሳቸው ብቻ በቂ አይሆኑም። ግጭቶችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት በተለያዩ ደረጃዎች እና በሁሉም የኅብረተሰብ ደረጃዎች ባሉ ሰዎች መካከል መከሰት አለበት። ለዚህም አንዳንድ ምክንያቶች ከዚህ በታች ቀርበዋል።
- መሪዎች በራሳቸው ብቻ አይንቀሳቀሱም። ቢያንስ ከተከታዮቻቸው ይሁንታ ሳያገኙ በግልጽ ድርድር ውስጥ መግባት ወይም በአሸማጋይነት ሒደት ውስጥ መሳተፍ አይችሉም። በተመሳሳይ ተከታዮች እና ደጋፊዎች ፍላጎቶቻቸውን እና ጥቅሞቻቸውን የማያስጠብቁ የሰላም ሥምምነቶችን ያከብራሉ ብለው አይጠብቁም። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ጉዳዮቻቸውን ሸምጋይ አካላት በበቂ ሁኔታ እንደተረዷቸው እና መፍትሔ እንዳገኙ ማወቅ አለባቸው።
- ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ለግጭቱ መንስዔ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ሊደርሱ ይችላሉ፣ ነገር ግን ግጭቱ እየተባባሰ በሔደ ወቅት በግንኙነታቸው ላይ ያደረሰውን ጉዳት መፍትሔ መስጠት ሊቸግራቸው ይችላል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ በቡድኖች መካከል ዕርቅን ለማምጣት ታቅደው በተዘጋጁ ሒደቶች ላይ መሳተፍ ያስፈልጋቸው ይሆናል። በብዙ ማኅበረሰቦች ውስጥ ልዩ የዕርቅ ሠነ ስርዓቶች ቂምን በማስወገድ እና ዕርቅ በመፍጠር ረገድ ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።
- በአንዳንድ ሁኔታዎች መሪዎች ከአንዳንድ ተከታዮቻቸው በጣም የተለየ ፍላጎቶች ሊኖራቸው ይችላል። ተቀባይነት ያላቸው ቡድኖች ከሌላው ቡድን አባላት ጋር መገናኘት ሳይኖርባቸው በራሳቸው አጥር ተከልለው መኖር ይችላሉ። ነገር ግን በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላሉ ሰዎች ይህ አይሠራም። እነዚህ ሰዎች ግጭቱ እንደገና ይነሳል የሚል ፍራቻ ሳይኖራቸው አብረው መሥራት፣ የንግድ ልውውጥ ማድረግ እና ትምህርት ቤቶችን መከታተል መቻል አለባቸው።
በሰላምና በግጭት ጥናቶች መስክ ግንባር ቀደም ምሁራን መካከል አንዱ የሆነው ጂን ፖል ሊደራች እንደሚለው ሥር በሰደደ ማኅበራዊ ግጭት ውስጥ ያለፉ ማኅበረሰቦች ውስጥ፥ በሁሉም በማኅበራዊ እና በፖለቲካዊ መስኮች የተሰማሩ ሰዎች በመፍትሔ ማፈላለጉ ሒደት ውስጥ የሚሳተፉበት መንገድ መመቻቸት እንዳለበት እንደሚከተለው ይገልጻል:
ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና ማኅበረሰቦች ግኝኙነታቸውን ነውጥ ከሞላው የግጭት አዙሪት ወደ ሰላማዊ ስልቶችን የተከተሉ ግንኙነቶች የሚቀይሩበት ዘላቂ [የሰላም] ሒደቶችን መገንባት በጥንቃቄ የተሞላ የማኅበራዊ አሸማጋይነት አቅምን ማዳበር ይጠይቃል።
ሊደራች ማኅበራዊ ግጭት የሚከሰተው ከግንኙነቶች መረብ እንደሆነ እና ማንኛውም ማኅበራዊ ግንኙነት በግጭት ወቅት በሚከሰቱ ክፍተቶች እንደሚፈጠር ከግምት ማስገባት አለብን የሚል ሐሳብ ያቀርባል። በኅብረተሰቡ ውስጥ በአንድ ወቅት ጎረቤት የነበሩ፣ የንግድ ሥራ የሚሠሩ፣ በአንድ ላይ የሚያመልኩ፣ ወይም አንድ ላይ ስፖርት የተጫወቱ ሰዎች በግጭት ምክንያት ሊለያዩ እና እንደ ጠላት መተያየት ሊጀምሩ ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች በመደበኛ የአሸማጋይነት ሒደቶች ውስጥ መሳተፍ የማይችሉ ቢሆኑም በግጭቱ ምክንያት የተፈጠረውን ስሜታዊ እና አካላዊ ጉዳት በተመለካተ በራሳቸው እንዲወጡት ይተዋሉ። በጣም የተባባሰ ግጭት በነበረበት ወቅት የቤተሰብ አባሎቻቸውን፣ ንብረታቸውን እና መሬታቸውን አጥተውም ይሆናል።
አንድ ማኅበረሰብ ከግጭት ባሻገር እንዲንቀሳቀስ የእነዚህ ሰዎች አሳሳቢ ጉዳዮችም መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል።በእንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች ውስጥ ግጭቶችን ለመፍታት ከላይ ወደታች የሚወርዱ አቀራረቦች መፍትሔ የሚሆኑት ለተወሰኑ ችግሮች ብቻ ነው። ከታች ያሉ ሰዎች እርስ በርስ እንዲተባበሩና እና እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሏቸውን መንገዶች ለመፈለግ እንዲችሉ ዕድሎች መፈጠር አለባቸው። ልሒቃኖች ባሳለፉት የድርድር ሒደት ዜጎችም በተመሳሳይ ሒደት ውስጥ መሳተፍ ያለባቸው ሲሆን ሒደቱ በማኅበራዊ ደረጃ መሆን ይጠበቅበታል። ስለ ሌሎች ቡድኖች ፍላጎቶች እና ጥቅሞች የበለጠ ማወቅ የሚፈልጉ መሪዎች ብቻ አይደሉም። እርስ በርስ የሚጣጣሙበትን መንገዶችን መመርመር የሚኖርባቸው መሪዎች ብቻ አይደሉም። እርስ በርስ መግባባትን ማወቅ የሚያስፈልጋቸው መሪዎች ብቻ አይደሉም። እነዚህ ሒደቶች በተቻለ መጠን በጉዳዩ ላይ ፍላጎት ያላቸውን አካላት በሙሉ በማካተት በኅብረተሰቡ ውስጥ መከናወን አለባቸው። ለውጥ በኅብረተሰቡ ውስጥ መከሰት አለበት እናም እያንዳንዱ ሰው በሰላም ሒደት ውስጥ እንዲሳተፍ ዕድል ሊያገኝ ይገባል።
ጋዜጠኞች የግጭት ዘገባን በሚሠሩበት ወቅት ስለ ሚኖራቸው ሚና የሚያተኩረው ክፍል ሁለት ላይ ለምናነሳቸው ነጥቦች የአሸማጋይነት ሜዳ የሚለው ፅንሰ ሐሳብ በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ ክፍል ጋዜጠኞች ሸምጋዮች ከሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ትምህርት መቅሰም እንደሚችሉ እንዲሁም ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በአሸማጋይነት ሜዳ የሚገናኙበትን ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋፆ ማበርከት እንደሚችሉ እናያለን። ሆኖም ጋዜጠኞች ራሳቸውን እንደ ሸምጋዮች አድርገው እንዲያስቡ አይመከርም። ነገር ግን በኅብረተሰቡ ውስጥ የአሸማጋይነት ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ መገንዘብ አለባቸው።