1.9 ግጭትን ለመቆጣጠር እና ለመፍታት የሦስተኛ ወገን ሚና
የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ላይ የምናተኩርባቸው ሁለት ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው ሦስተኛ ወገኖች በግጭት ውስጥ የሚኖራቸውን የተለያዩ ሚናዎች ይበልጥ በተገነዘብን ቁጥር የውጭ ጣልቃ ገብነትን ያካተቱ ሰላማዊ ሒደቶችን የሚመለከት ውጤታማ ዘገባ እንድንሠራ ያስችለናል። ሁለተኛው ምክንያት እኛ እንደ ጋዜጠኛ የሚኖረንን አስተዋፅዖ ሦስተኛ ወገኖች ከሚጫወቱት ሚና ጋር ማነፃፀር እንድንችል ይረዳናል። ሸምጋይ አካላት ግጭቶችን ለመፍታት የሚኖራቸውን ሚና ከማየታችን በፊት ስለ የተለያዩ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ዓይነቶች እንወያያለን።
የግጭት ንድፈ ሐሳባውያን ሦስት ዓይነት የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ዓይነቶችን ለይተዋል። እነዚህም፦
- ሰላም አስከባሪነት
- ሰላም ፈጣሪነት
- ሰላም ገንቢነት ናቸው። ምንም እንኳን እነዚህ በጣም የተለያዩ ሒደቶች ቢኖሯቸውም እያንዳንዳቸው በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ወሳኝ ሚናዎች ይኖሯቸዋል።
ሰላም ማስከበር
ግጭቱ ተባብሶ ነውጥ የማስነሳት ደረጃ ላይ ከደረሰ ወይም ሁከት ተነስቶ ከሆነ፣ እንዲሁም ተሳታፊ ወገኖች ሰላማዊ ሥምምነቶችን ለማድረግ የማይተማመኑበት አስከፊ ደረጃ ላይ ከደረሱ ሰላም አስከባሪነት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። በአጠቃላይ የውጭ ታጣቂ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነትን ያካትታል፤ በተጨማሪም መሣሪያ ያልታጠቁ ታዛቢዎችን መኖርም ሊያካትት ይችላል።
የሰላም አስከባሪነት ዓላማ ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ተጨማሪ ጉዳት እንዳያደርሱ መከላከል፣ እንዲሁም ድርድር እና ውይይት የሚካሔድበት ሁኔታ መፍጠር ነው። ሰላም አስከባሪዎች ብዙውን ከመከላከያ ኃይል የተውጣጡ ሲሆኑ፥ አከባቢያዊ በሆኑ ግጭቶች ውስጥ የፖሊስ ኃይልም የሰላም አስከባሪነት ሚና ሊጫወት ይችላል።
ሰላም አስከባሪዎች ሁሉንም ወገኖች በእኩል ዓይን መመልከት እንዲሁም በተቻለ ፍጥነት ከተቀናቃኝ ወገኖች እና ከአከባቢው ማኅበረሰብ ተዓማኒነትን ማግኘታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ሰላም አስከባሪዎች ሁሌም ከተሳታፊ ወገኖች ተቀባይነት አያገኙም። በተለይም አንድ ወገን በወታደራዊ የበላይነት የሚመራ ሲሆን እና ሰላም አስከባሪዎች በኃይላቸው ሊያገኟቸው ከሚችሉት ተጨማሪ ጥቅሞች በሚታገዱበት ሁኔታዎች ተቀባይነት ያጣሉ።
ሰላም ማምጣት
ሰላም ማምጣት ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖችን መፍትሔ እንዲያገኙ የሚረዳ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትን ያካትታል። ይህ ሦስተኛ ወገን በብዛት በግጭቱ ተጠቂ ከሆነው ማኅበረሰብ ውጪ የሚመጣ ነው። የሰላም አምጪው ሚና በዋነኝነት በግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች መካከል ድልድይ እንዲፈጠር በማገዝ ፈጠራ የታከለበት መፍትሔ ፍለጋ እና የችግር አፈታት ሒደቶችን እንዲፈጠሩ ማስቻል ነው። በአብዛኛው የሰላም አስፋኞች ጣልቃ ገብነት ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ግጭቶችን ለመፍታት በሚተባበሩበት ዘላቂ ሒደት ውስጥ ቀዳሚ እርምጃዎች እንዲወስዱ ለመርዳት ነው። ሆኖም የሰላም አምጪው ሚና በዋናነኝነት ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት አስቸኳይ ለሆኑ ጉዳዮችን መፍትሔ እንዲፈልጉ ማድረግ ነው።
ሰላም ግንባታ
ይህ ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ወደፊት ሰላማቸው የተጠበቀ እንዲሆን የሚያስችላቸውን መንገድ እንዲያገኙ የሚያደርግ ረጅም ጊዜ የሚፈልግ አካሔድ ነው። የሰላም ግንባታ ዓላማ ወደፊት ግጭት ሊፈጠሩ የሚችሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ ነው። የሰላም ግንባታ በተለይ በድህነት የሚኖሩ ሰዎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻልን የሚመለከት ሲሆን እንዲሁም የረጅም ጊዜ ግንባታ እና ቅድመ ጥንቃቄዎችን ለማድረግ ታልሞ የሚታሰብ ነው። ሒደቱ በዋነኝነት የተገፉ እና የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች በፖለቲካ እና በኢኮኖሚ ውስጥ በንቃት መሳተፍ የሚችሉበትን ማኅበራዊ መዋቅሮችን ማሻሻል ላይ ያተኩራል።
የሰላም ግንባታ ሒደት በግጭቶቹ ምክንያት የሚከሰቱ የስሜት መቃወስ ሁኔታዎችን ለማስወገድ የተቋቋሙ ሐቅ እና ዕርቅ ኮሚሽኖችን ሊያካትት ይችላል። ለምሳሌ የኅብረተሰቡን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር ለመለወጥ ያለሙ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎች። የደቡብ አፍሪካው ሐቅ እና ዕርቅ ኮሚሽን በብዙዎች ትችት ቢሰነዘርበትም በአፓርታይድ ምክንያት ቀውስ ውስጥ የነበሩትን ሰዎች መፍትሔ በመስጠት ተጠቃሽ ምሳሌ ነው።
1.10 አሸማጋይነት
አሸማጋይነት በግጭት ውስጥ በጣም የተለመደ የሦስተኛ ወገን ጣልቃገብነት መገለጫ ስለሆነ፣ ጋዜጠኞች አሸማጋዮች የሚጫወቱትን ሚና ሊገነዘቡ እና ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት እልባት እንዲያገኙ በማድረግ ሒደት ውስጥ አካሔዳቸው ምን እንደሚመስል መረዳታቸው አስፈላጊ ነው። ሆኖም አሸማጋይነት ሲባል አንድ ዓይነት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። የሚኖራቸው የተለያዩ ሚናዎች እና ተግባራት ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ለመሥማማት ባላቸው የፈቃደኝነት ደረጃ ላይ የሚመሠረት ይሆናል። በአንድ በኩል በግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች መካከል የሚኖሩ ግንኙነቶችን ማመቻቸት ብቸኛ ዓላማቸው ያደረጉ ሸምጋዮች አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅማቸውን ተጠቅመው ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት የሚያቀርቡላቸውን መፍትሔዎች እንዲቀበሉ ጫና የማድረግ ዓላማ የያዙ አሉ።
ብዙ ጊዜ አሸማጋይነትዎች የሚከናወኑት በእነዚህ ሁለት ፅንፎች መካከል ሲሆን ከዚህ በታች በዝርዝር የምናየው ይሆናል።
የአሸማጋይነት ባለሙያ የሆነው ክሪስ ሞሪ ለአሸማጋይነት የሚከተለውን ትርጓሜ ይሰጣል:
አሸማጋይነት ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በመሐላቸው ያሉ ግጭቶችን በራሳቸው ለመፍታት በፍቃደኝነት ሥምምነት ላይ መድረስ እንዲችሉ ተቀባይነት ባለው እና ገለልተኛ ሦስተኛ ወገን የሚደረግ ጣልቃ ገብነት ነው።
ይህንን ትርጓሜ ከፋፍለን ስናየው በርካታ ነጥቦችን ማውጣት እንችላለን።
- በመጀመሪያ፣ አሸማጋይነት ተቀባይነት ባለው እና ገለልተኛ ሦስተኛ አካል መከናወን አለበት። በርካታ የፅንሰ ሐሳብ አሰላሳዮች ሁሉም ወገን እስከተሥማማባቸው ድረስ አሸማጋዮች በግጭቱ ተሳታፊ ከሆኑ ወገኖች መውጣት እንደሚችሉ በመጥቀስ ይከራከራሉ። ዋናው ነጥብ ተቀባይነት ማግኘት ነው። አሸማጋዮች የማንኛውንም ወገን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረግ አይችሉም፤ ነገር ግን የአንደኛው ወገን ተፅዕኖ እንዳለባቸው የሚቆጠሩ ቢሆን እንኳ በገለልተኛነት እርምጃ መውሰድ አለባቸው።
- ሁለተኛ፣ ሸምጋዮች ውሳኔ የመስጠት ምንም ዓይነት ሥልጣን የላቸውም። ሸምጋዮች ማንኛውንም ወገን የቀረቡ መፍትሔዎችን እንዲቀበሉ ለማስገደድ አቅም የላቸውም። ሸምጋዮች በሥምምነቱ ላይ መካተት ያለበትን እና የሌለበትን ጉዳይ መወሰን አይችሉም። ሸምጋዮች በአሸማጋይነቱ ሒደት የሚካተቱ ስርዓቶች ላይ የተወሰነ ቁጥጥር ሊኖራቸው ይችላል። አሸማጋዮችም ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖችን ወደ ሥምምነት ማምጣት አይችሉም፤ ነገር ግን ወገኖች ሥምምነት ላይ የሚደርሱባቸውን መንገዶች እንዲያገኙ ሊረዱ ይችላሉ።
- ሦስተኛ፣ የአሸማጋዮች ሚና ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በፈቃደኝነት የሚሥማሙበት የመፍትሔ ሐሳብ ላይ እንዲደርሱ መርዳት ነው። ግጭት ውስጥ ለገቡ ወገኖች ጥያቄ ምላሸ መስጠት የሸምጋዮቹ ሚና አይደለም፤ ይልቁን የራሳቸውን መፍትሔ እንዲያገኙ መርዳት አለባቸው። በብዙ ሁኔታዎች ውስጥ አሸማጋች ሚናቸውን በጥያቄ መጠየቅ ደረጃ ብቻ ይገድባሉ። በዚህ ረገድ ያለው ግንዛቤ ቡድኖቹ በራሳቸው የገነቡትን ሥምምነት ይቀበሉታልም፣ ይከራከሩለታልም የሚል ነው።
- በመጨረሻም፣ ተሳትፎው በፈቃደኝት ላይ የተመሠረተ መሆኑ አስፈላጊ ነው። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በአሸማጋይነት ሒደት ውስጥ ያለፈቃዳቸው እንዲሳተፉ ማስገደድ የሚያስገኘው ጥቅም አነስተኛ ነው። በአሸማጋይነትው ሒደት ተገደው እንዲገቡ የተደረጉ አካላት ሒደቱን ለማጓተት ሊሞክሩ ይችላሉ፤ የተደረሱባቸው ሥምምነቶችንም ላይጠብቁ ይችላሉ።
ሁለት ዋና ዋና የአሸማጋይ ዓይነቶች አሉ:
የውስጥ እና የውጪ አሸማጋዮች። ሁለቱም አካላት በተለያየ መልኩ ግጭት ውስጥ የገቡ አካላትን ለመርዳት ይችላሉ። የውጭ አሸማጋዮች ዕርዳታ እንዲያደርጉ ካልተጋበዙ በስተቀር ሙሉ በሙሉ ከግጭቱ የራቁ አካላት ናቸው። በአብዛኛው በአሸማጋይነት እና በግጭት ቁጥጥር የሠለጠኑ ናቸው። ከውጪ የመጡ በመሆናቸው በአጠቃላይ ገለልተኛ እንደሆኑ ተደርገው ይወሰዳሉ። ከማኅበረሰቡ የመጡ አለመሆናቸው ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ሁኔታዎችን በተለየ መንገድ እንዲመለከቱ የሚያግዝ አዲስ አስተሳሰብ እንዲያመጡ ይረዳቸዋል።
የውስጥ አካላት፤ በተቃራኒው ግጭቱ እየተፈጠረ ካለው ማኅበረሰብ የሚመጡ ናቸው። ብዙውን ጊዜ ከማኅበረሰቡ የወጡ የተከበሩ መሪዎች እና ሁሉም ወገኖች እምነት የሚጥሉባቸው ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሸምጋዮች ከውጭ አካላት ጋር ተመሳሳይ ሥልጠና ላይኖራቸው ይችላል፤ ነገር ግን ስለ ጉዳዩ የሚኖራቸው ጥልቅ ግንዛቤ ያካክስላቸዋል። ሆኖም ግን እነሱ ከኅብረተሰቡ ስለ መጡ እና ስለ ግጭቱ የተወሰነም ቢሆን አቋም ስለሚይዙ ገለልተኛ መሆናቸውን ለማሳመን የበለጠ ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ ሸምጋዮችን ከተለያዩ ቡድኖች ተውጣጥተው እንዲጣመሩ በማድረግ ከገለልተኝነት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ስጋትን ለማስወገድ ይቻላል። ለምሳሌ በሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች መካከል በሚነሳ ግጭት ከሁለቱም ሃይማኖቶች የሚወከሉ የእምነት አባቶችን ሽማግሌ አድርጎ መምረጥ ይቻላል።
የአሸማጋይነት ሒደት ዋና ዓላማ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ለግጭቶቻቸው መፍትሔ እንዲያገኙ ማገዝ ነው። እነዚህ መፍትሔዎች ቢያንስ ተቀባይነት ባለው ደረጃ የሁሉንም አካላት ፍላጎት እና ጥቅም ማሟላት አለባቸው። በመሠረታዊነት፣ ውጤቶቹ የሚተገበሩት በራስ ተነሳሽነት መሆን ይኖርበታል። እንዲሁም ውጤቱን ጠብቆ ለማቆየት የውጭ አካል ጣልቃ-ገብነት ማስፈለግ የለበትም።
ይህንን ዓላማ ለማሳካት ሸምጋዮች የሚከተሉትን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል:
- ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች የሦስተኛ ወገን ዕርዳታ ሳያስፈልጋቸው ድርድራቸውን ገንቢ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በራሳቸው መቀጠል የሚችሉበት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ መጣር።
- ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በግንኙነታቸው ውስጥ ውጥረት እንዲቀንሱ መርዳት። በብዙ አጋጣሚሚዎች፣ ይህ ሁኔታ ተጋላጭነት በሌለበት አካባቢ ውስጥ ሐሳባቸውን እና ስሜታቸውን በግልፅ ሳይጨናነቁ መናገር የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸትን ያካትታል። ይህ ሒደት ‘ማስተንፈስ’ በመባል የሚታወቅ ሲሆን ሒደቱ ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ስሜታቸውን እንዲገልጹ እና ሌሎች ወገኖች ስለእነሱ ምን እንደሚሰማቸው እንዲያውቁ ያስችላቸዋል። ከዚህ በኋላ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ዋና ዋና ጉዳዮችን መፍታት መጀመሩ ቀላል ይሆንላቸዋል።
- ቡድኖቹ ጉዳዮቻቸውን በግልጽ እንዲለዩ መርዳት። የአሸማጋይነት ሚና ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ለራሳቸውም ሆነ ለተቀናቃኝዎቻቸው በጣም አስፈላጊ ጉዳዮችን እንዲለዩ መርዳትን ያካትታል። ይህንን በማድረግ ሸምጋዩ ቅድሚያ መፍታት ያለባቸውን ጉዳዮች ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች መለየት እንዲችሉ ያግዛቸዋል። የነፍጥ ግጭት ባለበት ሁኔታ ውስጥ፣ ቡድኖቹ ወደ ሌላ እርምጃ ከመግባታቸው በፊት የተፈጠረውን የደኅንነት ስጋት መፍታት አለባቸው።
- የመፍትሔ ፍለጋዎችን ማስፋፋት። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በተወሰኑ ሐሳቦች ላይ ብቻ ስለሚወሰኑ ግጭቶችን ለመፍታት አማራጭ መንገዶችን ማየት አይችሉም። ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ግጭቱን ከተለየ አቅጣጫ እንዲያዩት በመርዳት እና በማበረታታት አንዳቸው የሌላውን ፍላጎት ሊያሟሉ የሚችሉባቸውን መንገዶች እንዲመለከቱ አሸማጋዮች ሊያግዙ ይችላሉ።
- ቡድኖቹ መካከል ያሉ ተግባቦቶችን እንዲሻሻሉ ማድረግ። በብዙ ድርድሮች ውስጥ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ወደ ክስ እና አፀፋዊ ምላሽ ወደ መስጠት ሁኔታ ውስጥ ይገባሉ። እጅግ ብዙ ዓይነት ድምፅ ይኖራል፤ የሚደመጠው ግን ጥቂቱ ነው። ቡድኖቹ የራሳቸውን ጉዳይ ለማሳመን በመሞከር ስለሚጠመዱ እርስ በርስ አይደማመጡም።
- ቡድኖቹ የተዛቡ አረዳዶችን ግልጽ እንዲያደርጉ መርዳት። በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች አንዳቸው ስለሌላቸው መጥፎ እሳቤ ስለሚኖራቸው የተዛቡ ግንዛቤዎች የተለመዱ ናቸው። በአንዱ ወገን የተወሰደ ማንኛውም እርምጃ በሌላው ወገን እንደ ስጋት ሊቆጠር ይችላል። አሸማጋዮች ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት የእያንዳንዳቸውን ድርጊትና ዓላማ እንዲገነዘቡ ይረዷቸዋል።
- ደካማ ወገኖችን ማጠናከር። በብዙ ግጭቶች ውስጥ በድሃ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ሰዎች ሀብት እና መረጃን የማግኘት አቅም ካላቸው ሰዎች ጋር መደራደር በጣም ይከብዳቸዋል። አሸማጋዮች ይህን የአቅም ልዩነት መገንዘብና ሰዎች በእኩልነት የሚደራደሩበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው።
- ከዚህ ቀደም ያልነበራቸውን መረጃን በመስጠት ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በተቻላቸው መጠን የተሻሉ ውሳኔዎችን እንዲወስኑ ችሎታቸውን ማሳደግ። ለምሳሌ፣ በደመወዝ ጭማሪ ክርክር ውስጥ ድርጅቱ በቀላሉ የሚከስር መሆኑን እንኳን ላያውቁ ይችላሉ። ይህንን መረጃ መስጠታቸው ድርጅቱ እንዲቀጥል ለማድረግ ከፍተኛ የደመወዝ ፍላጎቶችን ዝቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይችላል።
- ግጭት ውስጥ የገቡ አካላትን ከእርስ በርስ ጥቃት መጠበቅ።
አሸማጋዮች የሚጫወቱትን ሚና ከተመለከትን፣ ውጤታማ ለመሆን ከፈለጉ ሊያሳዩት የሚገባቸውን ባሕሪዎች በአጭሩ እናያለን። ሸምጋዮች ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ግጭት እንዲፈቱ በማገዝ ረገድ አዎንታዊ አስተዋፅዖ ማበርከት ከፈለጉ የሚከተሉትን ማድረግ አለባቸው፦
- ታማኝነት። በአሸማጋይነት ሒደት ውስጥ የገለልተኝነትን አስፈላጊነት ቀደም ሲል አንስተነዋል። ሁሉም የሚመለከታቸው አካላትን አመኔታ ካላገኙ፣ እንዲሁም ሁሉም ወገኖች በእኩልነት እንደሚታዩ ካልተሰማቸው ማንኛውም አሸማጋይነት እንደማይሳካ ግልጽ መሆን አለበት።
- የቡድኖቹን ፍላጎት ማገናዘብ። አሸማጋይነት ፍላጎቶቻቸውን እና ጥቅማቸውን የሚናገሩ ግለሰቦችን ከማዳመጥ የበለጠ ነገርን ያካትታል። ሸምጋዮች ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ያልጠቀሷቸውን ችግሮችን በማንሳት እነዚህን ጉዳዮች የድርድሩ አካል እንዲሆኑ ማስቻል አለባቸው።
- የተለያዩ ሁኔታዎች የተለያዩ ምላሾች እንደሚፈልጉ መረዳት።
- ለሰብኣዊ ስቃት ተቆርቋሪ መሆንን ማሳየት። አሸማጋዮች ስሜታዊ እንዲሆኑ ባይጠበቅባቸውም፣ ግጭት እንዴት የሰዎችን ስሜት እንደሚጎዳ ለማወቅ የሰዎችን ስሜት መረዳት መቻል አለባቸው።
- በግጭቱ ውስጥ ስላጋጠሙ ጉዳዮች ጥልቅ ግንዛቤ ማዳበር።
- ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች አንደኛው ስለሌላኛው የሚሰማቸውን ስሜት ለመረዳት መቻል። አሸማጋዮች ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ስሜታቸውን እንዲቆጣጠሩ መርዳት መቻል አለባቸው። ድርድሮች በጣም ሲጦፉ ማየት የተለመደ ነው። ሸምጋዮች ይህ የሒደቱ ተፈጥሯዊ አካል መሆኑን መገንዘብ እና ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ስለነዚህ ስሜቶች እንዲናገሩ መፍቀድ አለባቸው።