1.6 የመባባስ ስጋቶች
የግጭት መባባስ ዋነኛ ችግር ከላይ የግጭት አዙሪት ብለን ከጠቀስነው ጉዳይ ጋር መመሳሰሉ ነው። ግጭቶች እየቀጠሉ ሲሔዱ ይበልጥ ውስብስብ እና ከግጭቶች ጋር ተያይዘው ከሚከሰቱ ጉዳቶች ጋር ተደምረው ከባድ ይሆናሉ። የነውጥ ድርጊት የበቀል እርምጃን ያስከትላል፣ በተራው ደግሞ ተጨማሪ በቀል ይጠራል። ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ከቀጠሉ ድርጊቱ በራሱ ዑደት የሚቀጥል ይሆናል። አንዱ ሌላኛው ላይ የሚያደርሰው ጉዳት በጨመረ ቁጥር፥ ሁኔታው ተረጋግቶ እና ወደ ነበረበት ከመመለሱ በፊት መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮችም ይጨምራሉ።
ከዚህ በታች የሰላም ሒደቱን የሚያወሳስቡ የተወሰኑ የግጭት መባባስ የሚያስከትላቸው መዘዞች ይቀርባሉ፥
- ቡድኖች መዋረድ ይፈራሉ። ግጭት እየተባባሰ ሲመጣ መሪዎች ሳይዋረዱ ወይም ደካማ ሆነው ሳይታዩ ስለድርድር ማውራት መቻል ከባድ ነው። በግጭት ወቅት መሪዎች የደጋፊዎቻቸውን እና የተቀናቃኞቻቸውን ቀልብ ለመግዛት ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ። ይህም ደካማ ሳይመስሉ ከያዙት አቋም ወደ ኋላ ለመመለስ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። ይህ ደግሞ መገናኛ ብዙኃን የጉዳዩ መሪዎችን የሚያፋጥጥ ጥያቄ ካቀረቡ እና ብርጭቆው ግማሽ ሙሉ ወይስ ግማሽ ጎዶሎ? የእከሌ ወገን በማሻሻል ሥም ያደረገው ብዙ ነገር አሳልፎ ሰጠ ወይስ ተስፋ ቆርጧል? ነው ወይስ ሽንፈቱን ተቀብሏል? የመሳሰሉ ቋንቋዎችን ከተጠቀሙ ደግሞ ይበልጥ እየከበዳቸው ይመጣል።
- ቡድኖች ጠባብ ራዕይ ያዳብራሉ። ግጭቶች እየተባባሱ ሲመጡ ቡድኖች የራሳቸውን አቋም በማስተዋወቅ እና በመከላከል ስለሚገደቡ ከሌሎች የሚነሱ አስተያየቶችን ለመቀበል ይከብዳቸዋል። በብዛት ጠባብ ራዕይ ላይ ብቻ በማተኮር ጊዜያቸውን ስለሚያሳልፉ ግጭትን ፈጠራ በታከለበት መንገድ መመልከት ወይም የሌሎች አካላትን ፍላጎት እና ጥቅም መገንዘብ አይችሉም።
- ቡድኖች የበለጠ ሊቀናጁ ይችላሉ። ግጭቶች እየተባባሱ ሲመጡ የቡድኖች ቅንጅት እየጠነከረ ይመጣል። ቡድኖች የግጭቱን አካሔድ አባላቶቻቸው እንዲቀበሉ ጫና ያሳድሩባቸዋል። ግጭቱን በተመለከተ በምክንያት የታገዘ አቋም ወይም ምክንያታዊ አካሔድ ሊያስወግዝ እና እንደ ከዳተኛ መታየትን፣ አንዳንዴ ደግሞ ሕይወት እስከማጣት ሊያስከትል ይችላል።
- ቡድኖች በቀልን ይፈልጋሉ። ቡድኖቹ የሚደርሰው ጉዳት በሁለቱም ወገኖች ላይ መሆኑን ለመገንዘብ እምብዛም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው እና በግጭት ምክንያት የደረሰባቸው መከራ ብቻ እያሰቡ ተቀናቃኛቸው ሲቀጣ ለማየት ከፍተኛ ፍላጎት ያሳድርባቸዋል። በሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተሳተፉ ቡድኖች ግጭቱ ካለቀ በኋላ ሌላኛው ወገን በቀል ሊፈፅም እንደሚችል በመስጋት ጦርነትን መቀጠሉ የተሻለ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ግጭቶችን ለመፍታት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ እነዚህ ጉዳዮች እንዴት ይታያሉ የሚለው ሐሳብ እንቅፋት ይሆናል።
- ግጭቶች በጣም እየተወሳሰቡ መሄዳቸው ቡድኖቹ ከየት መጀመር እንዳለባቸው ግራ ሊያጋባቸው ይችላል።
1.7 ነውጥ ሊከሰት የሚችልበትን ሁኔታ ማወቅ
ለጋዜጠኞች ትክክለኛ መንስዔዎቹን በማጤን ግጭት ወደ ነውጥ የሚቀየርበት ደረጃ ላይ መድረሱን መለየት መቻል አስፈላጊ ነው። ምልክቶችን በመገንዘብ ግጭቶች እየተባባሱ ከሔዱ የሚያስከትሉትን አደጋ በተመለከተ ያለው ግንዛቤ ከፍ እንዲል የሚያስችሉ ጥያቄዎችን ማንሳት እንችላለን። ይህም ግጭቱ ወደ ነውጥ ከማምራቱ በፊት የመዳኘት ሥራ እንዲጀመር ያበረታታል። ቀጥሎ ምን ሊከሰት እንደሚችል መተንበይ መቻል ጋዜጠኛው ነውጥ ሲነሳ ከመደንገጥ ይልቅ ግጭትን ውጤታማ በሆነ መልኩ መከታተል መቻሉ የተሻለ ቦታ ያሰጠዋል።
የሚከተሉትን አዝማሚያዎች በጥንቃቄ ተመልከቱ፥
- በአንዱ ቡድን ውስጥ ወይም በሁሉም ቡድኖች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ተስፋ መቁረጥ እና መከፋት
- አንድ ወይም ከዚያ በላይ ግጭት ውስጥ ያሉ አካላት በሌላ አካል ጥያቄ ወይም በሚመጣው ለውጥ ስጋት ሲያድርባቸው
- ድርድር ለማካሔድ የታመኑ መድረኮች፣ አሠራሮች እና የገለልተኛ ወገን አለመኖር እንዲሁም አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አካላት ግጭቶችን ለመቆጣጠር የሚረዱት ስርዓቶች ያጭበረብራሉ ወይም ፍትሐዊ አይደሉም ብለው ሲያምኑ
- ማኅበራዊ የቁጥጥር ስርዓቶች ተዓማኒነት ማጣት። ለምሳሌ ፖሊስ
- ግጭት ውስጥ ያሉት ወገኖች ከነውጥ ውጪ ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅላቸው አማራጭ ማየት ሳይችሉ ሲቀር
- ግጭት ውስጥ ያሉት ወገኖች ነውጥ በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ተቀባይነት ያለው እንደ ሁኔታው ደግሞ ተቀባይነት ያለው እንደሆነ ሲያምኑ
- ግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ነውጥ ውስጥ ገብተው የሚያውቁበት ታሪክ ካላቸው
- ሰዎች ልዩነቶችን ወይም ለውጥን ለመቋቋም አዳዲስ መንገዶችን ለማግኘት ሲታገሉ የማኅበራዊ ልማዶች እየተሻሩ ከሆነ
- ግለሰቦች በቡድናቸው ውስጥ የሚከሰት ነውጥ ለመከላል ኃላፊነት እንዳለባቸው የማይቆጥሩ ከሆነ
- የቡድን አባላቱ የመተዛዘን ችሎታቸውን እንዳጡ የሚያሳዩ ሁኔታዎች ካሉ
- ከፍተኛ ግርግሮች ያለመታወቅ እና ኃላፊነት የመቀነስ ስሜት ሲፈጥሩ
- በግጭቱ ውስጥ ያሉ የግንኙነት መንገዶች ደካማ በመሆናቸው ሊከሰቱ የሚችሉ ጥቃቶች እና ነውጥ አሉባልታዎችን በማውራት ሰዎች ስለሁኔታ የተሳሳተ አረዳድ እንዲኖራቸው ከተደረገ ጋዜጠኞች ነውጥ እንደሚቀሰቀስ ለመተንበይ እና ይህንንም በዘገባቸው ለማሳየት ከፈለጉ በግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች መካከል ስላለው የግንኙነት ታሪክ ጠንቅቀንው ማወቅ ይኖርባቸዋል። ይህን ለማድረግም ጥልቅ ምርምር ማካሔድ ሊኖርባቸው ይችላል። ወይም በቀላሉ ግጭት ውስጥ ከገቡ አካላት ጋር ጊዜ በማሳለፍ፣ ስለታሪካቸው እንዲያወሩ በማድረግ እና ግንኙነታቸውን ለመረዳት የሚጠቅሙ ጥያቄዎች በማንሳት መረዳት ይቻላል።
1.8 ግጭትን የሚመለከቱ አቀራረቦች
ቀደም ሲል ያየነው የግጭት መባባስ ሞዴል ግጭት ውስጥ በገቡ አካላት መካከል የፀበኛ ግንኙነት እንዳለ ቢጠቁምም ይህ ግን መከሰት እንደሌለበት ልንገነዘብ ይገባል። ወገኖች በግልፅ ፀብ ውስጥ እንዲሳተፉ ከማያደርጓቸው የተለያዩ አማራጮችን መውሰድ ይችላሉ። የተወሰኑት አማራጮች ለሁሉም አካላት በጣም ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፤ የተቀሩት አማራጮች በአጭር ጊዜ የተወሰኑትን አካላት በረጅም ጊዜ ውስጥ ሁሉንም አካላት የመጉዳት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ጋዜጠኞች በእነዚህ የተለያዩ አቀራረቦች የተካተቱትን ተግዳሮቶችና ጥቅሞች ከተገነዘቡ ግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች የሚጠቀሙት ስልት እና የሚያስተላልፉት ውሳኔዎች ሊያስከትሉ የሚችሉትን ጉዳት የሚያመላክቱ ተገቢ ጥያቄዎችን ለማንሳት ብቁ ይሆናሉ።
የሚከተሉት አቀራረቦች በግጭቶች ተሳታፊ አካላት ግባቸውን ለማሳካት በመደበኛነት የሚጠቀሙባቸው ናቸው። ግጭት የፉክክር ሒደት እንደሆነ በመቁጠር የአሸናፊ እና የተሸናፊ መኖር ግዴታ እንደሆነ በሚቆጥረው አቀራረብ እንጀምራለን። ይህ አቀራረብ የአንዱ ቡድን መጠቀም የሌላውን መጎዳት ያመላክታል የሚል ዕሳቤ አለው። ፉክክርን ከግምት የሚያስገባው አቀራረብ የሚያስከትለውን ጉዳት ካየን በኋላ ግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ቢጠቀሙት አለመግባባቶችን ለመቆጣጠር እና ለመፍታት የሚጠቅማቸውን የትብብር አቀራረብ እንመረምራለን።
የበላይነት ወይም ሙሉ ድል
ቡድኖቹ ኃይላቸውን በመጠቀም ሌላውን ወገን ለማሸነፍ እና እንዲቀበላቸው ለማስገደድ ሙከራ ያደርጋሉ። እንዲህ ያሉት ሙከራዎች አካላዊ አካላዊ ኃይልን መጠቀም፣ የተለያዩ ማዕቀቦችን ማዘጋጀት፣ ሕዝባዊ ሰልፎችን ማካሔድ እና ሕጋዊ መግቶችን ሊያካትቱ ይችላሉ።
የዚህ ዓይነት አቀራረብ የሚያስከትለው ውጤት የሚከተሉትን ይጨምራል፦
- ቡድኖቹ ብዙ ኃይል ማደራጀት የቻለው አካል የሚፈልገውን ማግኘት ይችላል ብለው ያምናሉ። ይህ ነገር በተደጋገመ ቁጥር የመተግሩ እና ቡድኖቹም ግባቸውን ለማሳካት በኃይላቸው የመተማመናቸው ሁኔታ ይጨምራል።
- በግጭት ተሳታፊ አካላት ስለሌላው ወገን ለማወቅ እና ራሳቸውን ለማሻሻል ዕድል የላቸውም።
- ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ድል ለመቀዳጀት በተቻላቸው ሁሉ ኃይላቸውን ያደራጃሉ። ነገር ግን ይህንን ስጋት ለመመከት ተቃራኒ ወገን ለመልስ ምት እንዲዘጋጅ መንገድ ይከፍታል። ሁለቱም ወገኖች የበለጠ ሀብት እንዲያፈስሱ ይገደዳሉ፤ በዚህም ሁለቱም ዘንድ የግጭት አዙሪቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።
- ቡድኖቹ ከግጭቱ በስተጀርባ ያለውን ትክክለኛ ምክንያት ለመቅረፍ አይሞክሩም።
- ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ወደፊት የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማቃለል ከሚረዷቸው አካላት ጋር ግንኙነቶችን የሚያዳብሩ አጋጣሚዎችን አይጠቀሙበትም።
- የተሸነፉ ወገኖች በውጤቱ ደስተኛ ስለማይሆኑ ግጭቱ ዳግም የመቀስቀስ ዕድሉ ሰፊ ነው፤ ምናልባትም የበለጠ አስከፊ ጉዳቶችን ያስከትላል።
ሽሽት ወይስ ማቀፍ
በግጭት ውስጥ መሳተፍ ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍለን ይችላል ብለው የሚፈሩ ወገኖች ብዙውን ጊዜ ችግሩን በመሸሽ ችላ ለማለት ወይም ተቀናቃኞቻቸውን ለመቻል ይሞክራሉ። አንድ ምሳሌ ብናነሳ፣ አንድ የበላይ የሆነ ቡድን ወቅታዊ ሁኔታውን ያናጋል በሚል ስጋት የአንድን አናሳ ቡድን ጥቅም እና ፍላጎቶችን ለመቀበል ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። አንድ ደካማ ፓርቲ ጠንካራ የሆነ ፓርቲን ኃይል በመፍራት ወሳኝ የሆነ ሥምምነት ላይ መድረሱም ሌላ ምሳሌ ይሆነናል። ውጤቶቹ የሚከተሉትን ያካትታል፡-
- በአጠቃላይ ሽሽት ሁኔታውን ከማዘግየት ውጪ ጥቅም የለውም። በመጨረሻ ግጭት ውስጥ የገቡት ቡድኖች ግጭቱን ሊያስከትሉ የሚችሉ ጉዳዮችን ለመጋፈጥ ይገደዳሉ።
- ቡድኖቹ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ስለማይጥሩ ለውጥ የሚያመጡበትን ዕድል ሳይጠቀሙበት ያልፋል።
- ቡድኖቹ አንዳቸው የሌላቸውን ፍላጎት እና ጥቅም ለማወቅ ፍላጎት ያጣሉ።
- ቡድኖቹ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለማጥራት አይሞክሩም፤ ወይም የራሳቸውን ጭፍን አመለካከት ጥያቄ ውስጥ አያስገቡም።
- ጥያቄያቸው ያልተመለሰላቸው ቡድኖች ከፍተኛ ምሬት ውስጥ ስለሚገቡ ከቆይታ በኋላ ግጭቱን መፍታት አስቸጋሪ ይሆናል።
- እውነተኛ ጥያቄዎቹን ለማደፋፈን የሚደረጉ ትናንሽ ማስተካከያዎችን ሌላውን ወገን የማያስደስቱ ሲሆን እንዲያውም ተጨማሪ ጥያቄዎች እና ፍላጎቶች እንዲነሱ ያደርጋል።
የችኮላ መፍትሔዎች
ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ከግጭቱ ጀርባ ላሉ ዋና ጉዳዮች መፍትሔ ለመስጠት ሳይሞክሩ ለችግሮቹ ቀላል እና ጊዜያዊ መፍትሔዎችን ለመስጠት ይሞክራሉ። ሥምምነት ላይ ለመድረስ መጣደፍ መጀመሪያ ላይ ሁሉንም ሰው ሊያስደስት ይችላል፤ ግን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ዋና ፍላጎቶች እንዲሟሉ በጥንቃቄ ካልታየ በስተቀር ችግሮች የመቀስቀስ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው። ውጤቶቹ የሚከተሉትን ይጨምራል፦
- ችግሩ መፍትሔ እንዳገኘ የሚያስመስል ብዥታ ይፈጠራል።
- የተሰጠው መፍትሔ ዋናውን ጉዳይ የማይነካ ከሆነ መፍትሔው ጊዜያዊ ከመሆን አያልፍም።
- የሥምምነት ሙከራዎች ካልተሳኩ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በጋራ መሥራት ላይ የነበራቸውን እምነት ያጣሉ።
- መፍትሔ መስጠት የሚጠበቅበት አካል ምንም እንኳን ያቀረበው መፍትሔ ጊዜያዊ ቢሆንም ያልተገባ ዕውቅና ሊያገኝበት ይችላል።
ድርድር
ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ሰጥቶ መቀበል ሒደት ውስጥ ይገባሉ። ሁሉም ወገኖች የተወሰነ መሻሻል እያሳዩ ከተቃራኒ ወገኖች የሚፈልጉትን በተቻላቸው አቅም ለማግኘት ጥረታቸውን ይቀጥላሉ።
ውጤቱ የሚከተሉትን ይጨምራል:
- ግጭት ውስጥ የገቡ ቡድኖች የግጭቱ ዋና ዋና መንስዔዎች መፍትሔዎችን ከመፈለግ ይልቅ ከፊት ለፊት በሚታዩዋቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። ለሁሉም አካላት የሚያዋጣ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ትንሸ ማሻሻያ ማድረግ የሚችሉበትን ሁኔታ በማሰላሰል ጊዜያቸውን ያባክናሉ።
- የአንድ ወገን ኃይል የሚገለጸው ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ሌላኛውን ወገን ይበልጥ ሁኔታዎችን እንዲያሻሽል በሚያደርጉበት አቅም ይሆናል።
- ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በግጭት ውስጥ አሸናፊ እና ተሸናፊ ወገን የሚኖርበት የዜሮ ድምር ጉዳይ እነደሆነ ያስባሉ።
- ተሸናፊዎች በውጤቱ የመከፋት ስሜት ውስጥ ስለሚገቡ ግጭቱ የመጨመሩ ዕድል ከፍተኛ ይሆናል።
- ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ለእነሱ አስፈላጊ የሆነ ነገርን እንዲተዉ ሊገደዱ ይችላሉ።
- በመሐከላቸው ያሉ ግንኙነቶች ሊበላሹ ወይም ሊቆሙ ይችላሉ።
- ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ብዙ ጊዜያቸውን እና ሀብታቸውን ስላፈሰሱ እናም በተለያዩ ምክንያቶች በአቋማቸው እንደፀኑ ስለሚቆዩ ለመቀየርም ፈቃደኛ ስለማይሆኑ ሒደቱ በጣም ጊዜ ይወስዳል።
ከላይ ያየናቸው አራቱ አቀራረቦች ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ላይ በረጅም እና በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ አሉታዊ ተፅዕኖዎች እንደሚከተለው ሊጠቃለሉ ይችላሉ።
- የዜሮ ድምር ውጤቶችን የመፍጠር ሁኔታ ይታይባቸዋል። አንደኛው ወገን ያገኘውን ውጤት ሌላኛው ማጣት አለበት።
- የወደፊት አለመግባባቶችን መፍታት እንዲችሉ የሚረዳቸውን የሥራ ግንኙነቶች ከማዳበር ይልቅ፥ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች አንዳቸው ሌላኛቸውን የሚቃወም ሥራ ይሠራሉ። ወደፊት ግጭቶች በቀላሉ እንዲነሱ የሚያደርጉ ከፍተኛ ቅሬታዎች እና ዘላቂ ጥላቻዎች የመፍጠር ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
- በብዛት ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች የሚያቀርቧቸው መፍትሔዎች የአጭር ጊዜ ይሆናሉ። አንድ ወገን ሽንፈቱን እንዲቀበል ተገዷል ማለት ወደፊት በርካታ ቅሬታዎቹን ይዞ አይነሳም ማለት አይደለም። ብዙ ጊዜ የተሸነፉ ቡድኖች ዓላማቸውን ለማሳካት ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ እርምጃዎች ይወስዳሉ።
- ግጭቱ በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ፍላጎቶችን ለማርካት አለመቻሉ ግጭቱ በተለየ መልክ እና በተሻለ አቅም ዳግም እንዲቀሰቀስ ያደርጋል። ቅሬታዎቸ እና ብስጭቶች ለወትሮው ሁከትን ለመከላከል የሚጠቅሙ መንገዶችን አቅም ዝቅ ሊያደርጉ ይችላሉ።
የትብብር አቀራረብ
የትብብር አቀራረብ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በሌላው ወገን ጉዳት የራስን ግብ ማሳካት ለግጭቱ መፍትሔ እንደማያመጣ እንዲገነዘቡ ስለሚረዳ እነዚህን አሉታዊ ተፅዕኖዎች ማለፍ ያስችላል።
አንዳቸው ለሌላኛቸው ውድቀት ከመሥራት ይልቅ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በጋራ ሆነው የሁሉንም ጥቅም ተቀባይት ባለው ደረጃ የሚያስጠብቅ መፍትሔ ለማምጣት ይሠራሉ። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ወዲያውኑ የትብብር አቀራረብን ላይቀበሉት ይችላሉ።
በፉክክር ሒደት ውስጥ የበላይነትን ለማግኘት በሚሞክሩበት ወቅት አጣብቂኝ ውስጥ ከገቡ በኋላ በእንደዚህ ያሉ ሒደቶች ለመሳተፍ ይሥማማሉ። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በሚተባበሩበት ጊዜ ራሳቸውን በጣም ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን ሁኔታ ቢፈልጉም፥ የመጨረሻ መፍትሔው ሌሎችንም የሚጠቅም ካሆነ ውጤቱ ጥቅማቸውን ያስጠበቀ እንዳልሆነ ሊገነዘቡ ይገባል።
የትብብር አቀራረብ ባሕርያቱ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ውጤቶችን ያስገኛል:
- በመጨረሻ ሁሉም ወገኖች ተጠቃሚ እንደሆኑ የሚሰማቸውን አዎንታዊ-ድምር ውጤት ያመጣል
- ግጭት ውስጥ የገቡ ቡድኖች ሁሉንም ወገኖች የሚያሥማሙ ውጤቶች ላይ በጋራ ሥምምነት ላይ ለመድረስ በጋራ ይሠራሉ
- ከመደራደሪያ ሐሳቦች ይልቅ ሁሉም ወገኖች በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀሙበት ፈጠራ የታከለባቸው መፍትሔዎች ይቀርባሉ
- በግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች መካከል በጣም የዳበሩ ግንኙነቶች ይኖራሉ። በትብብር ደረጃ ግጭቶችን መፍታት እንዲችሉ በመካከላቸው ጠንካራ የግንኙነት መሥመሮችን መዘርጋት አለባቸው። እነዚህ የግንኙነት መሥመሮች ወደ ፊት ግጭቶችን በሰላም ለመቆጣጠር መንገዱን
- በግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች መካከል ከፍተኛ የመተማመን ደረጃ እና የዳበሩ ግንኙነቶች ይኖራሉ። አንዳቸው የሌላኛቸውን እሴቶች፣ ስጋቶች እና ፍላጎቶች በተመለከተ የበለጠ ግንዛቤን ማዳበር ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ይህ ወደፊት ለሚከሰቱ ግጭቶች የበለጠ ሰላማዊ አቀራረቦች እንዲኖሩ ይረዳል።
የትብብር አቀራራብ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንዲሁም ወደፊት ግጭትን በሰላማዊ መንገድ ለመቆጣጠር የሚረዱ ግንኙነቶችን እና ሒደቶችን ለመዘርጋት የሚያስችል ሥምምነት ላይ የሚያደርስ ጥሩ አማራጮችን የሚያቀርብ እንደሆነ ማሰብ የተለመደ ነገር ነው። ሆኖም ያን ያክል ቀላል አይደለም። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች በግጭት ዙሪያ መተባበር የሚችሉበት ደረጃ ለመድረስ ረጅም ጊዜ እና የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ሊያስፈልግ ይችላል። እነዚህ ጣልቃ ገብነቶች እንዴት ጠቃሚ እንደሚሆኑ በቀጣዩ ክፍል አጠር አድርገን እናየዋለን።