1.3 የግጭት የእድገት ደረጃዎች

ይህ ክፍል ግጭቶች እየተባባሱ ሲሔዱ የሚያልፉባቸው የተለያዩ ደረጃዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን የግጭቱ ተሳታፊ አካላት ግጭቱን በተግባራዊ ሁኔታ ለመፍታት እንዲችሉ ጋዜጠኞች መጫወት ስለሚችሏቸው የተለያዩ ሚናዎች ያነሳል።

1 – እምቅ ግጭት

እምቅ ግጭት አለ የሚባለው ግጭት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ሁኔታዎች ሲኖሩ ነገር ግን እነዛ ሁኔታዎች በተሳታፊ ወገኖች ሳይደረስበት ሲቀር ነው።

አንድ ቡድን ዓላማው ከሌላው ቡድን ዓላማ ጋር እንደማይጣጣም ሳያገናዝብ በዓላማው ፀንቶ ሲቀጥል እምቅ ግጭት ይኖራል። የሚከተሉት ምሳሌዎች ለእምቅ ግጭት በተወሰነ መልኩ ማሳያ ይሆኑናል።

  • የተወሰኑ ገበሬዎች በጎቻቸውን የሚሰርቁባቸውን አዳኝ አውሬዎችን ለማጥመድ ይወስናሉ። በእነሱ አስተሳሰብ ኑሯቸውን ስጋት ውስጥ በመክተታቸው አውሬዎቹ አደገኛ ናቸው። ገበሬዎቹ ወጥመዱን ቢጠቀሙ ከአየር ንብረት እና የእንስሳት መብት ተቆርቋሪዎች ጋር ግጭት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ አላወቁም።
  • በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ለዘመናት በአለባበሳቸው ወግ አጥባቂ ነበሩ። ሁል ጊዜ ረጅም ሙሉ ቀሚስ ብቻ ነበር የሚለብሱት። በጊዜ ኺደት የተወሰኑት ሴቶች ዘመናዊ አለባበስን ለመከተል በመወሰን ጉርድ ቀሚስ፣ አጭር ቀሚስ እና ሱሪ ይለብሱ ጀመር። ይህን በማድረጋቸው ባሕላዊ እሴቶችን ከሚያጠብቁ ወንዶች ጋር ግጭት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ።
  • በአንድ አገር ውስጥ የሚገኝ የአናሳዎች ቡድን በሌላ ቡድን አባላት በበላይነት በሚያስተዳድርበት የአገሪቱ ክፍል ለመቆየት እንደማይፈልግ ይወስናል። ሰዎቹ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ እስኪጀምሩ ድረስ ግጭቱ ስውር ሆኖ ይቆያል። አናሳ ቡድኑ የግዛት መካለል ጥያቄ ማቅረብ በሚጀምርበት ሰዓት ግጭት መቀስቀስ ይጀምራል።
  • በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ለብዙ ዓመታት የሚሰጣቸውን ደካማ አገልግሎት ታግሰው ቢቆዩም፣ ሌሎች ማኅበረሰቦች ከሚያገኙት አገልግሎት አንፃር ወደ ኋላ መቅረታቸውን በሚረዱበት ወቅት ብስጭት ውስጥ ይገባሉ።
  • ከኅብረተሰቡ መዋቅር አደረጃጀት የሚነሳ አጠቃላይ የገቢ አለመመጣጠን አለ። በመደበኛ መንገድ ለውጥ ለማምጣት የሚደረጉ ምርጫዎች እና የፖለቲካ ሒደቶች ሙከራዎች ተስፋ አስቆራጭ ሆነዋል። በገቢ አለመመጣጠን ላይ የሚነሳው ቅሬታ ይጨምራል እንዲሁም ሰዎች ለውጥ ለማምጣት መንቀሳቀስ ይጀምራሉ።

ግጭት ተደብቆ እስከቆየ ድረስ ሰላም ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ይኖራሉ። ግጭት የሚያስነሱ ሁኔታዎች እንዳሉ ግንዛቤው ቢኖራቸውም ሰላም እንዲቀጥል ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ሁኔታዎቹን ንቀው ቢያልፏቸው ይመርጣሉ። በዚህ ሁኔታ ችግሮች በጭራሽ መፍትሔ አያገኙም። አንድ ነገር ካልተፈጠረ በቀር የሁሉም ወገኖች ጉዳይ ምላሽ ሊያገኝ አይችልም። ግጭት ሳይከሰት በፊት ሰዎች በሌሎች ሰዎች ብስጩ እና ትእግስት የለሽ መሆናቸው ይጨምራል። አንዳንድ ጊዜ እምቅ ግጭቶችን ችግር መፍታት እንዲቻል ግጭቶቹን መለየት እና ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል።

2 – አፍላ ግጭት

አፍላ ግጭት የሚጀምረው ቡድኖች እርስ በርስ የማይጣጣሙ ግቦች እንዳሏቸው ሲገነዘቡ ነው።

የተበደለ ቡድን ሁኔታዎች ፍትሐዊ አይደሉም ብሎ ሲያስብ እና አሁን ያለውን ሁኔታ ከዚህ በኋላ ለመሸከም ዝግጁ ሳይሆን ሲቀር ግጭት ብቅ ማለት ሊጀምር ይችላል። በብዙ ሁኔታዎች ቡድኖች ረዘም ላለ ጊዜ የበላይ በሆኑ ቡድኖች ሲተዳደሩ ተቀብለው ይኖራሉ።

ነገር ግን እነዚህ ማኅበረሰቦች ስለሚደርስባቸውን በደል የበለጠ እየተረዱ ሲመጡ የለውጥን አስፈላጊነት ይገነዘባሉ። በዚህ ደረጃ ሁሉም አካላት የግጭቱን መኖር ይቀበላሉ እንዲሁም ተቀናቃኞቻቸውን በትክክል ለይተው ሊያውቁ ይችላሉ። ወደ ድርድር ውስጥ በመግባት ለውጥ መምጣቱ አስፈላጊ እንደሆነ ይጠቁማሉ። በአንፃሩ ሌሎች ቡድኖች ደግሞ ለውጡን እንደሚቃወሙ በግልጽ ያስቀምጣሉ።

3 – ነውጥ አልባ ግጭት

ነውጥ አልባ ግጭት የሚከሰተው ቡድኖች ለውጥ ለማምጣት ኃይላቸውን ማሰባሰብ ሲጀምሩ ሌሎች ቡድኖች ደግሞ ለመመመከት ሲዘጋጁ ነው።

ይህ የግጭት ደረጃ አብዛኛውን ጊዜ ግጭት ውስጥ ያሉት አካላት ግጭቱን በሌላው ወገን ዕይታ እንዲመለከቱት እና አቋማቸውን እንዲቀይሩ ለማሳመን ማስፈራሪያ እና ሙከራዎችን በማካሔድ ባሕሪው ይታወቃል። በተመሳሳይ በተቻለ መጠን ብዙ ድጋፍ ለማሰባሰብ ይሞክራሉ።

ይህን በማድረጋቸው ጠንካራ እንደሆኑ፣  ሌላውን ወገን የማሸነፍ አቅም እንዳላቸው እና ማንኛውንም የጥቃት ሙከራ መቃወም እንደሚችሉ ያሳያሉ። በተጨማሪም የውጭ ግፊት ተቀናቃኝዎች አቋማቸውን እንዲተዉ ያስገድዷቸዋል ብለው ተስፋ በማድረግ በውጭ ያሉ አካላትን ጥያቄያቸው አግባብ እንደሆነ ለማሳመን ይሞክራሉ።

ይህ የግጭት ደረጃ የቡድኑ ፍላጎቶች በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት አንዲያገኝ ለማሳመን የሚደረጉ አንፃራዊ ቀና ሙከራዎችን ሊያካትት ይችላል። ሆኖም ሌሎቹ  ወገኖች ሙከራውን ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆኑ፤ መጀመሪያ ተነሳሽነቱን የወሰደው ወገን ተግባራቱ ከማሳመን ወደ ማስፈራራት ሊሸጋገር ይችላል።

4 – ነውጥ አዘል ግጭት

ነውጥ አዘል ግጭት ትክክለኛው የነውጥ ግጭት የሚጀምረው የግጭቱ አካላት አንዱ በሌላው ላይ ጉልበት መጠቀም ሲጀምሩ ነው።

ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በግጭቱ ውስጥ አዳዲስ ለውጦችን ያካተተ እጅግ አደገኛ የሆነ ደረጃ ውስጥ መገባቱን ያመላክታል። በመጨረሻም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ለችግሩ መንስዔ ለሆነው ጉዳይ መፍትሔ መስጠት ብቻ ሳይሆን በግጭቱ የሚወዱትን ቤተሰብ ሕይወት ያጡ ሰዎች እና ማኅበረሰቦች የሚካሱበትን መንገድ ይፈልጋሉ።

እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን አስፈላጊ ነጥብ ግጭት ከአንድ ደረጃ ወደ ቀጣዩ ደረጃ በሚያድግበት ወቅት ግጭት ውስጥ የገቡት ወገኖች ግጭቱን እንዲያባብሱ የሚገፋፋ አጋጣሚ ይከሰታል። አንዴ ግጭቶች ብቅ ማለት ከጀመሩ በኋላ  የግጭት አዙሪት ውስጥ መገባቱ አይቀርም። ግጭት ቀስቃሽ ሁኔታዎች ብዙ ዓይነት ቅርፅ ሊይዙ ስለሚችሉ ምናልባትም ከግጭቱ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት ልል ይሆናል። ለምሳሌ ከሕግ ውጪ መንደር መሥርተው በሚኖሩ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድን ተከታዮች መካከል ውጥረት በሚኖርበት ጊዜ በአንድ የተሰረቀ ዶሮ ምክንያት የሚፈጠር አለመግባባት ሰበብ ይሆንና በመካከላቸው ከፍተኛ ግጭት ሊፈጥር ይችላል። ለተቃወውሞ የወጡ ሰልፈኞችን ለመቆጣጠር ወይም ለመከላከል ፖሊስ የሚወስደው መጠን ያለፈ የኃይል እርምጃ በብዛት ኅብረተሰቡ ከአገልግሎት መሻሻል ጋር በተያያዘ ጥያቄ ሲያነሱ ሁከት ቀስቃሽ ምክንያት ይሆናል። ዓለም ዐቀፍ ፈተናዎችን ያስከተለው የግጭት ቀስቃሽ ተምኔታዊ ምሳሌ የፍራፍሬ አዟሪው መሐመድ ቡአዚዚ ዲሴምበር 17 ቀን 2010 እራሱን በእሳት ለኩሶ መግደል ነው። ቦአዚዚ የማዘጋጃ ቤት ኃላፊዎች ንብረቱን በመውረሳቸው እና ያደረሱበትን ሰብኣዊ ክብር የሚነካ ትንኮሳ እና ውርደት ለመቃወም የመወሰደው እርምጃ በቱኒዚያ አብዮት አስነሳ። ይህም ግብፅ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ባሕሬን፣ አልጄሪያ፣ ኢራቅ፣ ጆርዳን፣ ኩዌት እና ሞሮኮን ጨምሮ ወደ ሌሎች የአረብ ሃገራትን ያጥለቀለቀው የአረብ ፀደይ ተብሎ የሚታወቀው የተቃውሞ አብዮት መነሻ ምክንያት ሆኗል።

የተቃውሞዎቹ ምክንያት በአምባገነኖች አመራር ሰፊ የሆነ በደል፣ ድህነት፣ ሥራ አጥነት፣ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶች እና ሙስና እንደሆኑ ይታመናል። በቦአዚዝ ተቃውሞ የተነሳ አራት መንግሥታት ተገልብጠዋል። በርከት ያሉ አመራሮች ደግሞ የሥልጣን ዘመናቸው ሲያበቃ ከሥልጣናቸው ለመነሳት ያላቸውን ፍላጎት አስታውቀዋል።

የግጭት ዘገባዎችን ስናይ ግን ጋዜጠኞች ግጭቱ የሚባባስባቸውን የመጨረሻዎቹ ሁለት ደረጃዎች ላይ በማተኮር በእምቅ እና በውጥን ደረጃ ስለነበረው ግጭት በተደጋጋሚ ሳይጠቅሱ ያልፋሉ። ይህ በአጠቃላይ ሒደቱ ላይ ሳይሆን በሚታዩ እርምጃዎች ላይ ያተኮረ አካሔድ ብዙ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ሊያስከትል ይችላል። ለተደራሾቻቸው ስለ ሁኔታው የተዛባ ግንዛቤን እንዲኖራቸው ያደርጋል። ተደራሾች የተለያዩ ችግሮች ከጊዜ በኋላ ግጭቱን ለመቀስቀስ ምክንያት እንደሆነ መገንዘብ ሲኖርባቸው ግጭቱ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ወይም ምልክት በድንገት እንደመጣ ሊያስቡ ይችላሉ። በእነዚህ አጋጣሚዎች ሰዎች  የ ከዚህ  ቀደም  ሙከራዎችን ሳይረዱ ሀይለኛ ሚመስለውን ቡድን ይወቅሳሉ። ማለት ጋዜጠኞች ስለሚጠበቁ ግጭቶች ቅድመ ማስጠንቀቂዎችን በተመለከተ ቀድመው መረጃ የሚያሰሙበትን ዕድሎች አሳልፈዋል ማለት ነው። ስለዚህ ግጭቶች አውዳሚ ከመሆናቸው በፊት የመፍታት አጋጣሚዎችን ያጣሉ።

ጋዜጠኞች በእምቅ እና በውጥን ደረጃ ያሉ ግጭቶችን መለየት የሚችሉት ከማኅበረሰቡ ጋር ጊዜ በማሳለፍ አሳሳቢ ጉዳዮችን ለማወቅ ጊዜ የሚወስዱ ከሆነ ብቻ ነው። በዜና ክፍላቸው ቁጭ ብለው ሁኔታዎችን የሚከታተሉ ጋዜጠኞች ስለግጭት መዘገብ የሚጀምሩት ወደ ሁከት ከተቀየረ በኋላ ነው።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *