1.2 የግጭት መንስዔዎችን መለየት

ጋዜጠኞች የግጭት ተሳታፊ ለሆኑ አካላት መፍትሔ እንዲያገኙ በማገዝ ረገድ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከፈለጉ በቅድሚያ ግጭቱ እንዴት እንደተጀመረ ማወቅ አለባቸው። የግጭቱን ትክክለኛ መንስዔ መለየት ባይችሉም እንኳን ግጭቱን የሚያስከትሉ የተለያዩ ምክንያቶችን ለማወቅ በመረጃ ላይ የተመሠረተ መላምቶችን ማዳበር ይችላሉ።  እነዚህ በመረጃ የተደገፉ መላምቶች ጋዜጠኞቹ የግጭቱን አመጣጥ በጥልቀት ለመመርመር የሚያስችሏቸውን ጥያቄዎች ለማንሳት ይጠቅሟቸዋል።  ይህም ምን እና ለምን እየተከሰተ እንዳለ አጠቃላይ ግንዛቤን እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። ጋዜጠኞች ግጭት ከአንድ በላይ መንስዔ ሊኖረው እንደሚችል ተገንዝበው ያልተረዱት ተጨማሪ እውነት እንደሚኖር በመገመት ሁኔታን በንቃት መከታተል አለባቸው። ግጭቶች ከአንድ በላይ መንስዔዎች በሚኖራቸው ጊዜ ዘላቂ መፍትሔ የሚገኝበትን አጋጣሚ ከባድ ያደርገዋል።

በግጭት ዙሪያ የሚጽፉ ባለሞያዎች አብዛኛዎቹ ግጭቶች መንስዔ ምክንያታቸውን መሠረት በማድረግ መከፋፈል እንደሚችሉ  ሥምምነት ላይ ደርሰዋል። እነዚህም፡

1 – ውስን ሀብቶች

አንድ ማኅበረሰብ ወይም አገር ለሁሉም ሰው ተገቢ የሆነ የኑሮ ደረጃን የሚያረጋግጥ ሀብት ከሌለው ውስን የሆኑ ሀብቶችን ለማግኝኝ በሚደረግ ፉክክር በቡድኖች እና ግለሰቦች መካከል ግጭት መቀስቀሱ እውን ነው።

እነዚህ ውስን ሀብቶች መሬት፣ የውሃ እና የጤና አገልግሎቶች፣ ወይም የሥራ እና የግል ብልፅግና የመሳሳሉ ቁሳዊ ሀብቶችን ያካትታሉ። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉት ግጭቶች የሚከሰቱት ተፎካካሪ ቡድኖቹ ሀብቱን በተለየ ሁኔታ መጠቀም በሚፈልጉበት ጊዜ ነው። የግጦሽ መሬት ፍለጋ ከቦታ ወደ ቦታ በሚዘዋወሩ አርብቶ አደሮችና እና መሬታቸው በአርብቶ አደሮች እንዳይነካባቸው በሚፈልጉ ማኅበረሰቦች መካከል የሚከሰት በግጭት የሚታወቁት ብዙ የአፍሪካ ገጠራማ አካባቢዎችን ለአብነት ያክል መጥቀስ እንችላለን። እነዚህ ግጭቶች በዋናነኝነት መንስዔያቸው ከመሬት ሀብት አጠቃቀም ጋር የተያያዘ ይሁን እንጂ የመሬት ባለቤቶቹ እና አርብቶ አደሮቹ ከተለያየ ጎሳ ስለሚሆኑ ግጭቱ የባሕል እና የጎሳ ፀብ መልክ የመያዝ አዝማሚያ ያሳያል።

በዓለም ላይ ከባድ ግጭቶችን የሚያስተናግዱ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በከፍተኛ የድህነት ደረጃ የሚታወቁ መሆናቸው የሚያስደንቅ ነገር አይደለም። በሀብት ምክንያት የሚነሱ ግጭቶች ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ደግሞ ግጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይባባሳል። ‘አንፃራዊ ድኅነት’ የተሰኘው ፅንሰ ሐሳብ ቡድኖች ፍትሐዊ የሃብት ድርሻ አላገኘንም ብለው የሚያስቡ ከሆነ ግጭት ይከሰታል የሚል አመለካከት አለው። በግጭቱ ተሳታፊ ወገኖች ከሌሎች ጋር “አላስፈላጊ ንፅፅር” ውስጥ ከገቡ ደግሞ ችግሩ የከፋ ይሆናል። ለምሳሌ የአንድ ፋብሪካ ሠራተኞች በሥራቸው እና በሚያገኙት ደሞዝ አንፃራዊ በሆነ መልኩ ደስተኛ ሆነው የሚሠሩት ሌላ ቦታ የሚገኝ ድርጅት ተመሳሳይ ሥራ እየሠሩ እነሱ ከሚያገኙት በጣም የተሻለ ደሞዝ እንደሚያገኙ መረጃውን እስኪያገኙ ድረስ ነው። ግጭቱ ይህ ልዩነት እስኪታወቅ ድረስ ታፍኖ ይቆይና በታወቀበት ወቅት ግጭቱ መታየት ይጀምራል። በማኅበረሰቡ እና በኢኮኖሚ ላይ የጎላ ለውጥ ሲከሰት ሰዎች ለዘመናት በተለምዶ እንደግል ሀብታቸው ወስደው ሲጠቀሙበት የነበሩትን ሁኔታ ስለሚቀይር በሀብት ላይ የተመሠረተ ግጭት ሊከሰት ይችላል። በነዳጅ ዘይት ሀብታቸው በታወቁ አገራት ዜጎች ነዳጅ ላይ ከፍተኛ ድጎማ ስለሚደረግላቸውና ይህንንም ድጎማ ለረጅም ጊዜ ስለለመዱት መንግሥታቸው ይህንን ድጎማ ማንሳቱን በሚገልጽበት ወቅት ከፍተኛ ግጭት ይቀሰቀሳል።

2 – ሰብኣዊ ፍላጎቶች

ብዙ የግጭት ንድፈ ሐሳብ አቅራቢዎች ሁሉም ሰዎች እና ቡድኖች ሊሟሉላቸው የሚፈልጉት የተለያዩ መሠረታዊ ሰብኣዊ ፍላጎቶች እንዳሏቸው ያምናሉ። እነዚህም እንደ ምግብ ፍላጎት፣ ልብስ እና መጠለያ፣ አካላዊ ደኅንነትን ለማስጠበቅ ከጥቃት መከለያ ያሉ አካላዊ ፍላጎቶችን ያጠቃልላሉ። በተጨማሪም ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለም እንዲሁም ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን ከሚጋሩ ሰዎች ጋር የመሰባሰብ፣ ያለስጋት ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትን የሚያካትተውን የማንነት ፍላጎቶች ይጨምራል። የግለሰብ ማንነት ብዙውን ጊዜ ከቡድን ማንነት ጋር የተቆራኘ ሲሆን ግለሰቦችም የቡድኑን መዋቅር፣ እምነቶች እና አመለካከቶች እንደራሳቸው የራሳቸው አካል አድርገው ይመለከታሉ። የሆነ ነገር ወይም አንድ ሰው የቡድኑን ማንነትን ስጋት ውስጥ የሚከት ከሆነ የዚያ ቡድን አባላት ስጋቱን በግለሰብ ደረጃ (በራሳቸው ላይ) የመጣ እንደሆነ አድርገው ይቆጥሩታል።

የቡድን ማንነት ፍላጎቶች መሪዎች የቡድን ማንነትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የሚያበላሹ ሰዎችን እንዲያደራጁ ስለሚያስችላቸው ግጭት አመላካች ናቸው። ሰዎችን በቡድን ማንነት ላይ ስጋት እንዳለ አድርገው አሳምነው ካደራጇቸው በኋላ፣ ሰዎቹን ለራሳቸውን አጀንዳ ማስፈፀሚያነት መጠቀሚያ ሲያደርጓቸው ማየት እንዲሁ የተለመደ ነው። የመቆጣጠር ፍላጎት (በራስ ሕይወት ላይ መወሰን መቻል) እና ዕውቅና የማግኘት ፍላጎት (ሌሎች የግለሰቦችን ወይም የቡድንን የሕይወት ምርጫዎች ዕውቅና እንደሚሰጡ መጠበቅ) ከሰብኣዊ ፍላጎቶች የሚካተቱ ናቸው።

ሰብአዊ ፍላጎቶችን ለማርካት ያለው ፍላጎት በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ቡድኖች መደበኛ እና የተለመዱ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ አካሔዶችን በመከተል ማሳካት ካልቻሉ አጨቃጫቂ ስልቶችን መጠቀም ይጀምራሉ። ይህን በሚያደርጉበት ወቅት መንግሥትን ችግር ውስጥ ሊያስገቡ፣ ሕጎችን ሊጥሱ፣ ነውጥ እና አንዳንድ ጊዜ በጣም ጭካኔ የተሞላባቸው ስልቶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ።

የእነዚህ ፍላጎቶች ዋነኛው ገጽታ ለግለሰቡ መሠረት ሆነው በተጨማሪ በቡድኖች ውስጥም ሥር የሰደዱ በመሆናቸው ለመደራደር የማይመቹ መሆናቸው ነው። እነዚህን ፍላጎቶች በተለያዩ መንገዶች ማስተናገድ ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን ፍላጎቶቹ ለድርድር የሚቀርቡ አይደሉም። በፍላጎት ላይ የተመሠረቱ ግጭቶችን ለመፍታት ፈጠራ የታከለበት ችግር የመፍታት አካሔዶችን በመከተል ያልተሟሉትን ፍላጎቶች መለየት እና እነዚህም እንዴት እንደሚስተናገዱ በዘዴ በማሰብ መፍታት ይጠይቃል።

3 – መዋቅራዊ አለመመጣጠን

ግጭት ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው የሀብት ቁጥጥር እና ክፍፍል ያልተመጣጠነ ሲሆን ወይም እንደሆነ በሚታሰብበት ጊዜ ነው። ይህ የሚከሰተው የበላይ የሆነው ቡድን ያለውን ኃይል ተጠቅሞ ተጠቃሚ የሚያደርገው  ቦታ  በመያዝ  ፍትሐዊ  ያልሆነ  ሀብት  ለማሰራጨት  ሲጠቀምበት  ነው።  ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ከ1994 በፊት በፖለቲካ ሒደቶች እና በመንግሥት ሥልጣን ላይ ነጮች በበላይነት መቆጣጠራቸው፣ አናሳ የሆኑ ነጮች አብዛኛውን የአገሪቱን ሀብት እንዲቆጣጠሩ አስችሏቸው ነበር።

በሌሎች አጋጣሚዎች የተወሰኑ ጎሳ አባላትን ወይም የሃይማኖት ተከታዮችን ለመጥቀም ሲባል ብቻ የፖለቲካ መዋቅሮች ይቋቋማሉ። የእነዚህ መዋቅሮች አሠራር አብዛኛውን ጊዜ  ሌሎች የማኅበረሰብ አከካላትን ይጎዳል። እንደዚህ ያሉ መዋቅራዊ አለመመጣጠን ብዙውን ጊዜ መነሻቸው በቅኝ ግዛት ዘመን ነው። በቅኝ ግዛት ጊዜ የጎሳ ማንነቶች መጠቀሚያ ሆነዋል ወይም በዘመናዊ አገር ግንባታ ወቅት ተረስተዋል። በድኅረ-ቅኝ ግዛት ወቅትም መንግሥት የአናሳ ቡድኖችን ፍላጎት ካላስተናገደ ግጭቶች ይከሰታሉ። አናሳው ቡድን የበላይ የሆነው ቡድን ቋንቋ እና ሃይማኖት እንደተጫነበት በሚረዳበት ጊዜ የሚፈጠሩት ችግሮች ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል።

ለመዋቅራዊ ግጭቶች መፍትሔ ማፈላለግ በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ፍላጎቶችን በተሻለ መንገድ ሊያስተናግድ የሚችል አዲስ የፖለቲካ ስርዓት መቀየር ሊያስፈልግ ይችላል። በቀደመው ስርዓት ተጠቃሚ የነበሩ ሰዎች ለውጡን ላለመቀበል ስለሚታገሉ፥ በፊት የተጨቆኑ፣ የተገለሉ እና ከሀብት ተደራሽነት ተገልለው የነበሩ ሰዎች ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊሟሉ በማይችሉ ተስፋዎች ስለሚሞሉ የለውጡ ሒደት አሰቃቂ ሊሆን ይችላል።

እንደዚህ ዓይነት ግጭቶችን መሻገር ማለት አስቸኳይ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ መንገዶች ታውቀዋል ማለት ነው። እንዲሁም ባለፈው ስርዓት የነበሩ መድሎዎች ሊስተካከሉ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ማቀድ ማለትም ነው። በተጨማሪም በፊት በነበረው ስርዓት ተጠቃሚ የነበሩ ቡድኖች ማኅበረሰቡ ከሚያገኛቸው ዕድሎች እንዳይገለሉ እና ሁሉም ዜጋ ለወደፊቱ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የሚስተናገድበት ስርዓት ተዘጋጅቷል ማለት ሊሆን ይችላል።

5 – መረጃ እና ተግባቦት

ብዙ ግጭቶች የሚከሰቱት በግጭቱ የሚሳተፉ ወገኖች በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችላቸው በቂ መረጃ ማግኛ መንገድ ሳይኖራቸው በሚቀርበት ሁኔታዎች ውስጥ ነው። አንዱ ሌላው የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ዓላማ አለመረዳት እና እርስ በርስ ውጤታማ በሆነ መንገድ መረጃ ለመቀያየር አቅም በማጣት ግጭት የሚከሰትበት አጋጣሚ አለ። በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ጥቅም ያስገኝልናል በሚል ተስፋ አንዳቸው ከሌላኛቸው መረጃ መደበቅ የተለመደ ነው። አነስተይ (2008) እንደሚለው ይህ መረጃን የመያዝ ስልት ለሁሉም ወገን ጎጂ ሊሆን ይችላል።

አነስተይ (2008) እንደሚለው:

“ የጋራ እና ሕጋዊ መረጃ እጥረት… የሥልጣን ትግል እንዲነሳ ያደርጋል፤ እንዲሁም በግንኙነቶች መሐል የአለመተማመን ደረጃ እንዲጨምር አስተዋፅዖ ያደርጋል። ከዚህም በላይ፣ አንዳቸው የሌላኛቸውን አቋም መረዳት የሚችሉበትን አቅም በመቀነስ፣ ተወቃቃሽነታቸው እንዲጨምር ያደርጋል…. በጋራ መግባቢያዎች ላይ በመሥራት ፈንታ፣ በግምት በደረሱባቸው አቋሞች እና መርሖዎች ግጭት ውስጥ እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል።

6 – የእርስ በርስ ግንኙነቶች

በቡድኖች መካከል የሚነሱ ግጭቶች አንዳንድ ጊዜ መንስዔያቸው የእርስ በርስ ግጭቶች ሊሆን ይችላል። በማኅበረሰቡ ውስጥ ተሰሚነት ያላቸው ግለሰቦች እርስ በርስ በሚጋጩበት ጊዜ ከተቀናቃኝያቸው ለመብለጥ በተደጋጋሚ ደጋፊዎቻቸውን ይቀሰቅሳሉ። በእንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች ደጋፊዎች ለመሪዎቻቸው ታማኝ ስለሆኑ በሚካሔደው ትግል ይሳተፋሉ። ምናልባትም ከመሪያቸው በሚያገኙት ድጋፍ ጥገኛ ሆነውም ይሆናል።

ግጭቶች በዚህ መንገድ በሚፈጠሩበት ወቅት የራሳቸውን ቅርፅ ስለሚይዙ አንዳንድ ጊዜ ከመሪዎቹ ቁጥጥር ውጪ ሊሆን ይችላል። በተለይም የዚህ ዓይነት ግጭቶች ወደ ሁከት የሚያመሩ ሲሆን በተጨማሪም የንብረት፣ የአካል ጉዳቶች እና የሰው ሕይወት ማጥፋት ይታከልባቸዋል።

ክሪስ ቺናካ ትላልቅ-ግጭቶች ለፀብ መንስኤ ቢሆኑ እንኳን እምብዛም ብቸኛ መንስዔ አይደሉም። ይልቁኑም ትክክለኛውን ጉዳይ የሚደብቅ እና ሰዎች ግጭትን በቀላሉ በሚረዱበትን መንገድ የሚያቀርብ “እጅግ አቃላይ” አቀራረብ የሚያመጣውን አደጋ ሰዎች መቃወም አለባቸው ሲል እንደሚከተለው ሐሳቡን ይገልጻል:

አፍሪካ ብዙ ጊዜ በኃያላን ግለሰቦች የምትገዛ በመሆኗ የዜና አውታሮች ግጭቶቹን አቃለው የማቅረብ ልምድ አላቸው። ነገር ግን ግጭቱ እነዚህ ኃያላን ከሥልጣን ከወረዱም በኋላ ደጋግሞ መከሰቱን ይቀጥላል… አንዳንዴ ብዙ ትኩረት የምናደርገው የተሳሳተ ቦታ ላይ ነው።

ቀደም ሲል ለሁኔታው ከነበረው ግንዛቤ ጋር እንዲጣጣም ለማድረግ ሲባል የሚታየው መረጃን የማዛባት ዝንባሌ ችግሮቹን ሊያባብሱት ይችላሉ። ሰዎች ከተቀናቃኝ ወገን የሚመጣውን ማንኛውንም አስከፊ ነገር ሊያምኑ ይችላሉ። እናም አስታራቂ የሆነ ሐሳብ ይዞ ለሚመጣ ሌላ ሰው ይህንን የሚረዳለት ሰው ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ይሆንበታል።

የአንድ ቡድን ለአዎንታዊ ለውጥ የሚደረግ ቀና ጥረት በሌላኛው ቡድን ግጭቶችን ለመፍታት ወይም በተፎካካሪ ወገኖች መካከል ድልድይ ለመገንባት እንደተደረገ ጥረት እንደሆነ ከመቁጠር ይልቅ፣ ወደፊት ጥቅም ለማግኘት ተብሎ የተወሰደ ስልታዊ እንቅስቃሴ ተደርጎ ሊተረጎም ይችላል። ከዚህ አስተሳሰብ እንደምናየው ጥረቱ ተቀባይነት ስለማያገኝ  በመጀመሪያ ግጭቱን ለማስቆም የፈለገው አካል በተራው የያዘውን አቋም አጥብቆ እንዲይዝ ያደርገዋል።

7- እርግጠኝነት ማጣት

ብዙውን ጊዜ አዲስ አሠራር በሚዘረጋበት እና ቡድኖች እርስ በእርስ ለመግባባት በሚሞክሩበት፣ በለውጥ፣ በአለመረጋጋት እና በሽግግር ወቅት ግጭቶች በተደጋጋሚ ይነሳሉ። ከጦርነት በኋላ በሚታዩ ሁኔታዎች ውስጥ እነዚህ አለመረጋጋቶች ግጭቶቹ እንደገና እንዲቀሰቀሱ ሊያደርጉ ይችላሉ። በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ልዩነቶች ተፈትተው ቢሆን እንኳን ከዚህ ቀደም በተቀናቃኝ ቡድኖች አባላት መካከል የነበረ ምሬት እና ጥላቻ ሊቀጥል ይችላል።

ዓላማቸውን ለማሳካት በትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ያለፉ ታጋዮች ለሲቪል ሕጎች ተገዥ በሚሆኑበት ጊዜ ግጭቶች ይፈጠራሉ። ለእነዚህ ሰዎች ፍላጎቶቻቸውን እንደማያገለግሉ ለሚያስቧቸው ዴሞክራሲያዊ ሒደቶች መገዛት በጣም ከባድ ሊሆን ይችላል። በጦር መሣሪያ መስፋፋት ምክንያት በነውጥ የመጡ የመንግሥት ለውጦች በተከሰቱባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖረውን አለመረጋጋት ለማስተካከል ያለው ፈተና በጣም ይጨምራል።

በተመሳሳይም አገሮች ቀደም ሲል የነበሩትን ግጭቶች ለመፍታት አዲስ ሕገ መንግሥት በሚያወጡበት ጊዜ አርቃቂው አካል አዲሱን የሕገ-መንግሥት መሥፈርቶች እና የሌሎች መብቶች እና ነጻነቶች ከሚጠበቁበት ሁኔታ ጋር ለመላመድ ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ። የመንግሥት የፀጥታ አካላት፣ ፖሊስ፣ የመረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት እና መከላከያ የፖለቲካ ምኅዳሩን በተቆጣጠሩባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ለሲቪል መንግሥት ራስን ተጠያቂ ማድረግ ይከብዳቸዋል።

8 – የዓላማ አለመጣጣም

የተለያዩ አካላት ግቦች ሳይጣጣሙ ይቀሩና ግጭት የሚከሰቱባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። የአንዲት መንደር ነዋሪዎች ያልታረሰ መሬት ላይ እህል ለማብቀል ሊፈልጉ ይችላሉ። በአንፃሩ የአየር ንብረት ተቆርቋሪዎች ደግሞ በመንደሩ የበቀለው ደን ተጠብቆ እንዲቆይ ይፈልጋሉ። አንድ ባለሀብት ባዶ በሚመስል መሬት ላይ ግንባታ ማካሔድ ይፈልጋል፤ የአካባቢው ማኅበረሰብ ደግሞ እዚያ መሬት ላይ የቀበሩትን ቀደምት ቤተሰቦች መቃብር ለማስጠበቅ ይፈልጋል። ሊከሰቱ የሚችሉ ግጭቶች ዝርዝር ማለቂያ የለውም፤ ፈታኙ ነገር የሁሉንም ወገኖች ፍላጎት በተወሰነ ደረጃ መሟላት የሚችሉባቸውን መንገዶች መፈለግ ነው። ዋናው ጉዳይ የተለያዩ ቡድኖች የያዙት ዓላማ አለመገጣጠም ሳይሆን ቡድኖቹ ዓላማቸው እንደማይጣጣም ማመናቸው ብቻ ግጭቱ እንዲፈጠር ለማድረቅ በቂ እንደሆነ ልብ ልንል ይገባል።

ሆኖም እነዚህ መደቦች የግጭት መንስዔዎችን መለየት የምንችልበትን ጠቃሚ መረጃ ቢያስጨብጡንም ወደ እውነታው ስንመጣ ግን ተለያይተው የሚከሰቱበት አጋጣሚ ጥቂት ነው። በብዛት አንደኛው ምክንያት ዋና ይሆንና ሌሎቹም መንስዔዎች ለግጭቱ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ። ለምሳሌ አንድ ብሔር ከሌሎቹ በበለጠ ተጠቃሚ በመሆኑ መዋቅራዊ መንስዔ ያለው ግጭት ይቀሰቀስና በተጨማሪም ተበድያለው የሚለው ቡድን የማንነት ፍላጎቶቹ ተረስተዋል የሚል ስሜት ስለሚኖረው የሰብኣዊ ፍላጎት ጉዳይም ሌላ የግጭት መንስዔ ይሆናል። በተመሳሳይ ሁኔታ ተጠቃሚ ያነበረው ቡድን ፍላጎቱን የሚያሟላበት አቅሙን ሊያሳጣው ስለሚችል የለውጡን ተፅዕኖን ይፈራል። በተፎካካሪ የፖለቲካ አንጃ መሪዎች መካከል የሚኖረው የግል ግንኙነት ለግጭት መነሳት አስተዋፅዖ ማድረጉ የተለመደ ነው።

በግጭት መንስዔዎች ላይ ባየነው ውይይት ውስጥ ብሔር ወይም ሃይማኖት የግጭት መንስዔዎች ሆነው አለመጠቀሳቸው ግልጽ ጉዳይ ነው። ምንም እንኳን ግጭቶች ብዙውን ጊዜ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በባሕል ወይም በብሔራዊ ልዩነቶች አንፃር ቢገለጹም፣ እነዚህ መጠሪያዎች በአጠቃላይ ሌላ ነገር ለመሸፈን የሚያገለግሉ መለያዎች ብቻ ናቸው ብለን እናምናለን። ሰዎች የተለያየ የጎሳ ወይም የሃይማኖት አባል መሆናቸው በራሱ የግጭት ምክንያት ሊሆን አይችልም።

ግጭቶች የጎሳ ወይም የሃይማኖት አንፃር ሊኖሯቸው ይችላል፤ ነገር ግን የእነዚህ ግጭቶች ዋና መንስዔ ሌላ ነው። ለምሳሌ ከላይ ባየናቸው ምድቦች ውስጥ ሊገኝ ይችላል። ሰዎች የተለያዩ በመሆናቸው ብቻ ነውጥ ውስጥ አይገቡም። በእኛ አስተያየት ኃይል ያላቸው አካላት ያላቸው ድጋፍ ለማሰባሰብ በጣም ስለሚቀላቸው ሰዎችን በዘር፣ በባሕል እና በሃይማኖት ማሰባሰብ ይቀናቸዋል። ባሕሎችን፣ እሴቶችን እና እምነቶችን የሚጋሩ ሰዎች ከማይሩ ሰዎች ይልቅ ለአንድ ዓላማ በጋራ የመቆም ዕድላቸው ከፍተኛ ቢሆንም፥ ልዩነቱ ለግጭት በቂ መንስዔ እንዳልሆነ ባለን እምነት እንፀናለን። ለግጭት መቀስቀስ መንስዔ የሆኑትን ምክንያቶችን አይተናል። የሚቀጥለው ክፍል ደግሞ ግጭቶች እየተባባሱ በሚሔዱበት ወቅት ምን ዓይነት ሁኔታ እንደሚከሰት ያብራራል።

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *