በቻይና ውኃን ከተማ በታኅሣሥ 2012 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ መታየቱ የተነገረለት ኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ ኢትዮጵያ የገባው በቻይና ታየ ከተባለ ከሦስት ወራት በኋላ ነው፡፡ በዚህ መሀል ወረርሽኙ አውሮፓና አሜሪካን አጥለቅልቆ በሺዎች የሚቆጠሩትን ገድሎ ነበር፡፡

በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ዘግየት ብሎ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ እንደሠለጠነው ዓለም አገሮች በአሥርና በሃያሺዎች የሚቆጠር ሞት ባያስከትልም፣ ኢኮኖሚው፣ ፖለቲካውና ማኅበራዊ ዘርፉ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡

የዓለምን ኢኮኖሚ በእጅጉ የመታውና በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ከሥራ ያፈናቀለው ወረርሽኝ፣ ክትባት ተገኝቶለት በተለይ በሠለጠነው ዓለም ያሉ ሕዝቦች በከፊል እያገኙ ወደ አፍሪካና ሌሎች አኅጉሮችም በውስን ቁጥር እየገባ ቢሆንም ከአንድ ዓመት ወዲህ በዘለቀው ጉዞው በየአገሮች ላይ ያሳረፈውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀልበስ ዓመታት እንደሚፈጅ የዓለም ባንክ ትንበያ ያሳያል።

ወረርሽኙ የዓለምን ኢኮኖሚ በ2020 በ5.2 በመቶ፣ በ2021 በ4.2 በመቶ እንደሚቀንስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለከፋ ድኅነት እንደሚዳርግም በትንበያው ተቀምጧል፡፡ በዓለም ከ118 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አጥቅቶ ከ2.6 ሚሊዮን በላይ የገደለው ኮቪድ-19 በአፍሪካ እስከ መጋቢት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የ106712 ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል፡፡ በቫይረሱ የተያዙት ደግሞ 3,994,030 ደርሷል፡፡ በኢትዮጵያ ከ170 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲጠቁ፣ 2,466 ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

የሕይወት ማጣትና የጤና ማስተጓጎልን ያስከተለው ኮቪድ-19፣ በኢትዮጵያ የመጀመርያው ተጠቂ ተገኘ ከተባለ ቅዳሜ መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ዓመት ሆኖታል፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዘውግ ላይ በኢንዱስትሪ እንደበለጸጉ አገሮች ባይሆንም፣ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡

ቫይረሱ በኢትዮጵያ ከተከሰተ አንስቶ በመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት በኢኮኖሚው ላይ ያሳረፈውን ተፅዕኖ አስመልክቶ ዓለም ባንክ የለቀቀው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ ቫይረሱን በመከላከልና ኢኮኖሚው ላይ ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የተለያዩ ዕርምጃዎችን ብትወስድም፣ በተለይ በመጀመርያዎቹ ሁለትና ሦስት ወራት መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በከፊልና ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸው በተለይ በንግድ ላይ የተሰማሩ ትላልቅ ተቋማትን ጎድቷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተመዘገቡት 42 በመቶ የንግድ ተቋማት 37 በመቶው በመጋቢትና በሚያዝያ 2012 ዓ.ም. ምንም ዓይነት ገቢ እንዳልነበራቸው ገልጿል፡፡ ተቋማት ቀስ በቀስ እየተከፈቱ ቢሄዱም፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ቀድሞ ከነበረበት በአራት በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ተንብዩዋል፡፡

ኮቪድ-19 በቤተሰብ በተለይም በሥራ ላይ ያደረሰውን ተፅዕኖ አስመልክቶም፣ የቅጥር ሁኔታና የቤተሰብ ገቢ መቀነሱን ገልጿል፡፡ ቫይረሱ በኢትዮጵያ ከገባ በኋላ የነበሩት ሁለትና ሦስት ወራት ውስጥም ስምንት በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ሥራቸውን አጥተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 20 በመቶ በከተማ፣ ሦስት በመቶ ደግሞ በገጠር ሲሆን፣ በፆታ ሲታይም 13 በመቶ ሴቶችና ስድስት በመቶ ወንዶች ሥራቸውን ያጡበት ሆኗል፡፡ በተለይ ራሳቸውን የቀጠሩና በቀን ሥራ ተሰማርተው የነበሩ ለሥራ አጥነት ከተጋለጡት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡

ወረርሽኙ ራሳቸውን በቀጠሩ፣ ተቀጥረው በሚሠሩና በኢንተርፕሩነሮች ገቢ ላይ ባሳደረው ተፅዕኖ የቤተሰብ ገቢ መቀነሱ ታይቷል፡፡ በአዲስ አበባ ከፍተኛና ዝቅተኛ ክህሎት ያላቸው ሠራተኞች የ2012 ዓ.ም. ገቢ ከ2011 የሚያዝያ ገቢ ጋር ሲነፃፀር በ14 በመቶና በ3.7 በመቶ በተከታታይ ቀንሶ ነበር፡፡

በአሉላ ፓንክረስት (ዶ/ር) ዋና ዳይሬክተርነት የሚመራው ያንግ ላይቭ ኢትዮጵያ ያስጠናውና ባለፈው ሳምንት የተለቀቀው ጥናትም ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በትምህርት፣ በሥራ፣ በምግብ ዋስትናና በአዕምሮ ጤና ላይ ያሳደረውን ጤና አሳይቷል፡፡

ኮቪድ-19 በትምህርትና የወደፊት ሕይወትን በማሻሻል በኩል ታይቶ የነበረውን ለውጥ በተለይ ደሃና በጣም ለችግር ተጋላጭ የሆኑትን ወጣቶች ወደኋላ ጎትቷል፡፡ አሁን ላይ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች የሚገኙ ወጣቶች ወደ ትምህርት ወይም ወደ ሥራ ቢላኩም ለወራት ተስተጓጉሎ የነበረው ትምህርት፣ ሥራ በአግባቡ አለማግኘት፣ የምግብ እጥረትና የአዕምሮ መታወክ ቀድሞ የነበረውን የአኗኗር ልዩነት በጣም አስፍቶታል፡፡ የኑሮ ልዩነቱን በጣም አራርቆታል፡

እ.ኤ.አ. ከ2001 ጀምሮ 3,000 ልጆችን በመያዝ ተከታታይ ጥናቶችን እያከናወነ የሚገኘው ያንግ ላይብስ፣ በቅርቡ ባደረገው የስልክ ጥሪ ጥናት፣ ኮቪድ-19 መጀመርያ ኢትዮጵያ ሲገባ ከነበረው በተሻለ አሁን ላይ በርካታ ወጣቶች ወደቀደመ አኗኗራቸው መመለስ ጀምረዋል ሆኖም ውስብስብ ችግሮች ገጥሟቸዋል፡፡

ኮቪድ-19 በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ያሳደረውን ተፅዕኖ ዛሬ ላይ ትንሹ 19 ዓመት ትልቁ 26 ዓመት የሆናቸው 3,000 የተከታታይ ጥናቱ ተሳታፊ ወጣቶችን ለሦስተኛ ጊዜ የስልክ ጥሪ ዳሰሳ በማድረግ የተከናወነ ጥናት ነው፡፡ በኅዳርና በታኅሣሥ 2013 ዓ.ም. ሦስተኛው የስልክ ጥሪ ጥናት ከመከናወኑ በፊትም በሰኔና በሐምሌ 2012 ዓ.ም. እንዲሁም ከነሐሴ 2012 እስከ ጥቅምት 2013 ዓ.ም. በነበሩት ወራት የመጀመርያውና ሁለተኛው ስልክክ ጥሪ ቃለ መጠይቅ ተደርጓል፡፡

ትምህርት

የኮቪድ-19 መከሰት በዓለም 1.7 ቢሊዮን ተማሪዎች ከትምህርታቸው እንዲስተጓጎሉ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ 26 ሚሊዮን ያህል ተማሪዎች ለዘጠኝ ወራት ገደማ ትምህርታቸውን አቋርጠውም ነበር፡፡ ትምህርት ሲከፈት ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ አለመመለሳቸውን በመግለጽ የየክልል ትምህርት ቢሮዎች ንቅናቄ አድርገዋል፡፡

በዚህም የቀሩ ተማሪዎችን መመለስ ቢቻልም፣ በተለይ ግጭት ባሉባቸው አካባቢዎች ትምህርቱን ሙሉ ለሙሉ ለማስቀጠል አልተቻለም፡፡

የያንግ ላይቭስ ኢትዮጵያ ጥናት ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ የተቋረጠው ትምህርት ሲቀጥል የተመለሱ ተማሪዎች ቁጥር አበረታች ቢሆንም፣ ሁሉም ተማሪዎች ግን ሊመጡ አልቻሉም ብሏል፡፡ በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸው ቢመለሱም፣  ብዙ ትምህርቶች በበይነ መረብ የሚለቀቁ መሆናቸው ልዩነትን ፈጥሯል፡፡ የትምህርት ጥራቱ በዕኩል ደረጃ እየሄደም አይደለም፡፡

የኢንተርኔት አገልግሎት በማይደርስባቸውና ተማሪዎቹም በበይነ መረብ ትምህርቱን ለመከታተል የሚያስችል ፋሲሊቲ አለማግኘታቸው ዓመቱን የባከነ አድርጎታል፡፡ ይህ ደግሞ በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዳይመለሱ ያደርጋል፡፡ ጥናቱ በተደረገባቸው ጊዜያት 19 ዓመት ከሞላቸው ተማሪዎች 32 በመቶ ትምህርት እስኪከፈትላቸው የሚጠብቁም ነበሩ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ከድሃ ቤተሰብ የመጡ ሴት ተማሪዎች ከወንዶቹ በተለየ ትምህርት አቁመዋል፡፡

በኮቪድ ትምህርት መዘጋቱን ተከትሎም 19 ዓመት ከሞላቸው ሴት ተማሪዎች 39 በመቶው ምንም ዓይነት ትምህርት አላገኙም፡፡ ከእነዚህ ተማሪዎች አንድ ሦስተኛ ያህሉ በመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ሲገኙ፣ 15 በመቶው በሁለተኛ ደረጃ ገብተዋል፡፡

ትምህርት መዘጋቱ በተለይ ሴት ደሃ ተማሪዎችን ጎድቷል፡፡ በቤት ውስጥ ልጆች የመንከባከብና የቤት ውስጥ ሥራዎችን የመሸከም ጫናም አርፎባቸዋል፡፡

ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ መጀመሪያ ሲገባ ከነበረው በተሻለ በርካታ ወጣቶች ወደ ሥራ ተመልሰዋል፡፡ ነገር ግን ወረርሽኙ ከመከሰቱና ገደቦች ከመጣላቸው በፊት ከነበረው የመሥራት ዕድል ቀንሷል፣ መልሶ መቀጠሩም ዘገምተኛ ነው፡፡

26 ዓመት ከሞላቸው ሠራተኞች 57 በመቶ ያህሉ ወደ ሥራ የተመለሱ ሲሆን፣ ይህ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከመከሰቱ በፊት ከነበረው 63 በመቶ ቅጥር ሲነፃፀር የስድስት በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ከነበራቸው ሥራ ወደ ግብርናና ራስን ወደመቅጠር እንዲሁም ወደ ኢመደበኛ ሥራ መግባትም ጨምሯል፡፡

የምግብ ዋስትና

ደሃ ቤተሰቦች እንዲሁም በከተማ አካባቢ የሚኖሩ ችግረኞች በቂ ምግብ በማጣት ተርበዋል፡፡ በጥናቱ የተሳተፉ በርካታ ወጣቶችም አምና ላይ ቢያንስ አንዴ ምግብ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ በተለይ ደሃ ቤተሰቦች ክፉኛ ተጎድተዋል፡፡ በጥናቱ ከተሳተፉት የ19 ዓመት ወጣቶች እ.ኤ.አ. በ2016 የነበረው አምስት በመቶ የመራብ አጋጣሚ ከሦስት እጥፍ በላይ በመጨመር በ2020፣ 18 በመቶ ረሃብ ገጥሟቸዋል፡፡

የአዕምሮ ጤና

አገሮች ቤት የመቀመጥ ገደቦችን ሲያነሱ ሰዎች የተሻለ የአዕምሮ ጤንነት ታይቶባቸዋል፡፡ ሆኖም በአራት አገሮች የተደረገ ጥናት ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው አሳይቷል፡፡ በኢትዮጵያ ግን ከሴቶች ይልቅ ወንዶች ከፍተኛ ድባቴ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡

ዶ/ር አሉላ እንደሚሉት፣ የጥናቱ ውጤት ባጠቃላይ የሚያሳየው በጣም ደሃ የነበሩና ለችግር ለመጋለጥ ቅርብ የሆኑ ወጣቶች የኮሮና ወረርሽኝ ካሳደረባቸው ተፅዕኖ ለመውጣት እየታገሉ ነው፡፡ ነገር ግን የትምህርቱ፣ የምግብ እጥረቱና በየቤታቸው የተጣለባቸው የሥራ ጫና የአዕምሮ ጤናቸውን ሊያውከው ይችላል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *