ዘገባ የሠሩለትን የመጨረሻ ታሪክ ያስቡ። በታሪኩ ውስጥ አንዳንድ የግጭት ዓይነቶች የመካተታቸው ዕድል ሰፊ ነው። ለምን? ምክንያቱም ግጭት በማንኛውም ሁኔታ ስለሚገኝ። ግጭት ሁሉንም ዓይነት ማኅበራዊ ሕልውና ይነካል። እንዲሁም ግጭት ሁልጊዜም ለውጥን የመፈለግ ጉዳይ ነው። ግጭት ያልተሟላ ፍላጎታቸውን ለማሟላት የሚሞክሩ፣ ተፅዕኗቸው የጎላ እንዲሆን የሚፈልጉ፣ ለማንነታቸው የሚሟገቱ፣ የሀብት ተጠቃሚነታቸው እንዲጨምር እና ኢ-እኩልነት እና ኢ-ፍትሐዊነት እንዲቀንስ የሚፈልጉ ሰዎች የሚገቡበት ጉዳይ ነው። እንዲሁም ለውጥን የሚቃወሙ እና ጥቅማቸውን ለማስቀጠል የሚታገሉ ሰዎችም ጉዳይ ነው። ግጭት ለለውጥ አስፈላጊ መሪ ኃይል ሲሆን፥ ለውጥ ደግሞ የሁሉም ዓይነት ዘገባዎች እስትንፋስ ነው። ለውጥ ዜናን ዜና የሚያሰኘው ጉዳይ ነው።

ጋዜጠኝነት ማለት ለውጥ በሰዎች፣ በማኅበረሰቦች፣ በቡድኖች እና በብሔረሰቦች፣ በፖለቲካ መዋቅሮች፣ በኢኮኖሚ እና በተፈጥሯዊ አየር ንብረት ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ማሳየት ነው።

ሰዎች ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ አካባቢዎችን እንደሁኔታው መቀየር ይችሉ ዘንድ በዙሪያቸው ከሚገኘው ዓለም ጋር በማስተዋወቅ የሚረዷቸው ጋዜጠኞች ላይ እምነታቸውን ይጥላሉ። በተጨማሪም ሰዎች ከጋዜጠኞች የሚያገኙትን መረጃ በመተማመን ለግጭት እንዴት ምላሽ እንደሚሰጡ፣ በግጭቱ ውስጥ ስላሉት ሌሎች ሰዎች ምን ዓይነት ግምት ሊኖራቸው እንደሚገባ እና በነሱ ላይ ምን ዓይነት ባሕሪ ማንፀባረቅ እንዳለባቸው ለመወሰን ይጠቀሙበታል።

ግጭት በዚህ ደረጃ የምንዘግባቸው ዜናዎች እና ታሪኮች ዋና ክፍል ከሆነ፥ ስለ መንስዔው፣ ስለ ተለዋዋጭነቱ እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች በተመለከተ ይበልጥ በተረዳን ቁጥር ዘገባችንም የተሻለ እንደሚሆን ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። ግጭት ሁልጊዜም ከምንገምተው በላይ የተወሳሰበ በመሆኑ ከሰላም እና የግጭት ጥናት ትምህርት ዘርፍ የምናገኛቸውን ተግባራዊ መመሪያዎች በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው በግጭት ወቅት ምን እና ለምን እየሆነ እንዳለ ያለንን ግንዛቤ ለማሳደግ ይረዳናል። እነዚህ ተግባራዊ መመሪያዎች አለመግባባቶች እና ግጭቶች ውስጥ ከተሳተፉ ቡድኖች ትርክት ውጪ ያለውን ሁኔታ እንድናይ እና የግጭቱን ዋና መንስዔ ለመመርመር እንድንችል ይረዱናል። እንዲሁም በግጭቱ የተሳተፉ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ሊያስደስት የሚችል የመፍትሔ ሃሳብ እንድናፈልቅ ይጠቅሙናል።

ጋዜጠኛ እንደመሆናችን መጠን ግጭቱን አቅልለን በማየት እና ጥላቻን የሚያስፋፋ ከባድ ቋንቋ በመጠቀም ግጭቶችን እንዲባባሱ ልናደርግ የምንችልበት ሁኔታ ውስጥ ልንገባ እንችላላን። መመሪያው እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መሆናችንን እንድንረዳ ያግዘናል።

የሚቀጥሉት ጥቂት ልጥፎች (posts) በሚከተሉት ጉዳዮች ዙሪያ ሊረዱን የሚችሉ በርካታ ጠቃሚ ፅንሰ ሐሳቦችን፣ ንድፈ ሐሳቦችን እና ተግባራዊ መመሪያዎችን ያስተዋውቃሉ።

1     ስለግጭት ያለንን ግንዛቤ ማሳደግ

2     የግጭቶችን ውስብስብነት ማስረዳት የሚችሉ ታሪኮችን ለመንገር ብቁ እንድንሆን ማዘጋጀት፣

3     የራሳችን ዘገባ በግጭት ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ከግምት ማስገባት ናቸው።

እነዚህን ፅንሰ ሐሳቦች በበርካታ እና የተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ሊተገበሩ የመቻላቸው ነገር አስፈላጊ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ከትንሽ ቡድን የእርስ በርስ ግጭት ወቅት ያገኘነው ትምህርት በአገር ዐቀፍ ወይም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ያሉ ግጭቶችን በምንመለከትበት ጊዜ ጠቃሚ ግብዓት ሆኖ ሊገኝ ይችላል። የተለያዩ የግጭት ገጽታዎች እርስ በርስ እንዴት እንደሚገናኙ በዝርዝር ከማየታችን በፊት የግጭትን የተለመደ ትርጓሜ በመመርመር ይህንን ክፍል እንጀምራለን።

1.1 ግጭት ምንድን ነው?

አንዳንድ ጋዜጠኞች የዚህ ክፍል መግቢያ ግራ ያጋባቸዋል። በአጠቃላይ በዘገባቸው የሚካተቱ ታሪኮች ለውጥን እንደሚያካትቱ ይስማማሉ፤ ነገር ግን ታሪኮቹ የግጭት ናቸው የሚለው አገላለጽ ላይ ይከራከራሉ ወይም አይሥማሙም። ጥቂት (እሱም ካለ) የሚሆኑት ታሪኮች ብቻ ነውጥ የሚስተዋልባቸው፣ አብዛኛዎቹ ግን የቁጣ ንግግር እንኳን ያልያዙ መሆናቸውን በመጥቀስ ይከራከራሉ። እንዴት የሚታይ ግጭት በሌለበት ሁኔታ ስለ ግጭት ማውራት ይቻላል? ሲሉ ይጠይቃሉ። ብዙ ሰዎች ስለግጭት የሚያስቡበትን መንገድ የሚያብራራ ወሳኝ ጥያቄ ነው።

በጥያቄው ላይ ግልጽ ግንዛቤ ለማዳበር በመጀመሪያ ነውጥ እና ግጭት ተመሳሳይ አለመሆናቸውን መገንዘብ አለብን። ነውጥ የግጭት መገለጫ ሲሆን በአንድ ጊዜ ለተለያዩ ተግባሮች ጥቅም ላይ መዋል ይችላል። ለምሳሌ ያህል ኢመደበኛ ሰፈራ ውስጥ የሚኖሩ እና ዝቅተኛ አገልግሎት እያገኙ ያሉ ነዋሪዎች ሰልፍ ወጥተው በፖሊስ መኪናዎች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ በአንዴ ብዙ ነገር እያደረጉ ነው። ከነዚህም ውስጥ:

  • በአካባቢያቸው በሚስተዋለው የልማት እጥረት ሳቢያ ተስፋ በመቁረጣቸው የመጣ ብስጭታቸውን መወጣት፣
  • ለመንግሥት ባለሥልጣናት መከፋታቸውን ማሳወቅ (ፖሊስ መንግሥትን በመወከል ነው የሚመጣው)፣
  • የሚዲያ ትኩረት በመሳብ ባለሥልጣናትን የሆነ ነገር እንዲያደርጉ ጫና ማሳደር፣
  • አቅም/ኃይል የሌላቸው እንዳልሆኑ ማሳየት፣ እና/ወይም
  • ባለሥልጣናትን ከዚህ ከፍ ያለ ነውጥ ይከሰታል የሚል ስጋት ውስጥ መክተት የሚሉት ናቸው።

ነውጥ አንደኛው ወገን ሌላውን ለመጉዳት ሆን ብሎ እርምጃ መውሰድን ያካትታል። የሚወሰደው እርምጃ ግዴታ አካላዊ ኃይልን መጠቀምን ማካተት የለበትም። እንዲሁም ነውጥ ቁሳዊ ዕቃዎችን የመያዝ ወይም የማገት ሁኔታን ሊጨምር ይችላል። ለስደተኞች የሚሔድ ምግብ እንዳይደርሳቸው አግቶ ማቆየት ከፍተኛ ስቃይ ያስከትላል፤ እንዲሁም ድርጊቱ ነውጥ እንደ ሆነ ልንገነዘብ ይገባል። በተመሳሳይ፣ እንደ ሰብአዊ መብቶችን መጣስ ወይም የፖለቲካ መብትን መከልከል ያሉ የሰዎችን ግለሰባዊ የማንነት ስሜትን የሚያጣጥል ማንኛውም እርምጃ እንደ ነውጥ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ከዚህ ዕሳቤ ስንነሳ የምርጫ ድምፅ መስጫ ሳጥኖችን በኸሰተኛ ካርዶች የመሙላት ተግባር ከማጭበርበር በላይ መሆኑን እንረዳለን። ድምፅ በሚሰጠው ሕዝብ ላይ የተፈፀመ የነውጥ ዓይነት ነው። ከዚህ ጋር አብሮ የሚሔደው የተሳዳቢው ዓላማ በሌላው ላይ ጉዳት ማድረስ በመሆኑ በቃላት መልክ የሚሰነዘሩ ስድቦች እንደ ነውጥ ድርጊት መታየት ይኖርባቸዋል። ግጭት ሁል ጊዜ ባይሆንም ተሳታፊዎቹ አካላት ወደ ነውጥ ሊገቡ የሚችሉበት የበለጠ የተወሳሰበ ሁኔታን ያካትታል። ለዚህ ውይይት እንዲረዳን በደቡብ አፍሪካ ግጭት ባለሙያ የሆኑት ማርክ አንስቴይ ያስቀመጡትን የሚከተለውን የግጭት ትርጓሜ እንጠቀምበታለን።

የተለያዩ ወገኖች ፍላጎታቸውን በተመሳሳይ ጊዜ ማሳካት እንደማይችሉ በሚያምኑበት ጊዜ፣ ወይም እሴቶቻቸው፣ ፍላጎቶቻቸው ወይም (የታቀቡ) ጥቅሞቻቸው መካከል ልዩነቱ እየሰፋ መሆኑ ከተሰማቸው እና ራሳቸውን ለመጠበቅ ወይም ጥቅሞቻቸውን ለማሳደግ በማሰብ በሚኖራቸው ግንኙነት (ግጭትን ጨምሮ) ሆነ ብለው ኃይላቸን በማንቀሳቀስ አንዳቸው ሌላኛቸውን ለማጥፋት፣ ለማምከን ወይም ለመለወጥ ሲሞክሩ ግጭት ይኖራል።

ግጭት በግንኙነቶች መካከል የሚከሰት ሲሆን የግንኙነቶቹ ዓይነት በግጭቱ ሒደት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ግልጽ ነው። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች የከረመ የጥላቻ እና የቅራኔ ታሪክ ያላቸው ከሆኑ ፀብ ውስጥ ሳይገቡ ሁለቱንም ወገኖች የሚያስደስት ውጤት ላይ የመድረስ ተስፋ ይቀንሳል። በታሪካቸው አከራካሪ ጉዳዮችን ገንቢ በሆነ መንገድ ያከናወኑበት አጋጣሚ ካለ ደግሞ ሰላማዊ ውጤት ላይ የመድረሱ ዕድል ከፍተኛ ይሆናል።

  • በተለያየ ወገን የሚገኙ ቡድኖች የሚኖራቸው እምነቶች እና አስተሳሰቦች ግጭቶች በምን ዓይነት መልኩ እንደሚነሱ አቅጣጫ በማስያዝ ረገድ እጅግ በጣም አስፈላጊ ሚና ይጫወታል። አንድ ወገን የሆነ ነገር እውነት ነው ብሎ የሚያምን መሆኑ ያ እምነት ምክንያታዊ መሆኑን ወይም ያለመሆኑን ያክል አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ አንድ ቡድን በ‘አያቶች መሬት’ ላይ የይገባኛል ጥያቄ እንዳለው ሲያምን ሌላኛው ደግሞ ታሪካዊ የይገባኛል ጥያቄውን የማይቀበል ከሆነ ግጭት ሊኖር ይችላል። በተመሳሳይም አንደኛው ቡድን ላይ ሌላኛው ሆን ብሎ በማስፈራራት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ካመነ፣ ማስፈራሪያው ሆን ተብሎ የታሰበ መሆኑና ያለመሆኑ እውነታ ጉዳይ ጥቅም የለውም። የቡድኑ ባሕሪ እውነት ነው ብሎ በሚያምነው ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ነው።
  • ግጭት ሁል ጊዜ የተሳታፊ ቡድኖችን ወይም አካላትን ፍላጎቶች፣ እሴቶች እና ጥቅሞችን ያካትታል። (ይህ ነጥብ ወደፊት በስፋት የሚዳሰስ ይሆናል።)
  • ግጭት አንደኛው ወገን ሁኔታውን የሚቀይር እርምጃ መውሰድ እስከሚጀምር ድረስ ታፍኖ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል። ሰዎችን ለችግር የሚያጋልጥ አንድ ነገር ተከስቶ እስኪያነቃቸው ድረስ ብዙውን ጊዜ የግጭት አደጋ መኖሩን ላይገነዘቡ ይችላሉ። ማኅበረሰቦች በመሬታቸው ላይ የማዕድን ሀብት እስከሚገኝ ድረስ መሬቱን ለግጦሽ በጋራ እየተጠቀሙ በደስታ ይኖራሉ። በኋላ በመካከላቸው ውጥረቶች መታየት ሊጀምሩ ይችላሉ። በተመሳሳይም አንድ ሰው የተመሳሳይ ፆታ ካህናትን የመሾም ጥያቄን እንስከሚያነሳበት ዕለት ድረስ የአንድ ትልቅ ቤተ-ክርስቲያን አባላት ለዓመታት በደስታ ሲያመልኩ ሊኖሩ ይችላሉ። ሰዎች ስለ ችግሩ መረጃው የሌላቸው ወይም ከግጭቱ ለማምለጥ ተስፋ በማድረግ ከጉዳዩ መራቅን ይመርጡ ይሆናል። ሆኖም ጥያቄው በአግባቡ አጀንዳ ሆኖ በሚቀርብበት ጊዜ ግጭቱ ግልጽ መውጣት ይጀምራል።

ግጭት መታየት የሚጀምረው ተሳታፊ ወገኖች የሚከተለውን ሲያደርጉ ነው:

  • ያላቸውን ኃይል ሆን ብለው ሲያነቃንቁ። ይህ ኃይል ብዙ ዓይነት መገለጫዎች ሊኖሩት የሚችል ሲሆን በመንግሥት ወይም በነውጠኞች የአገር መከላከያ ኃይልን መጠቀም፣ የሥራ ማቆም አድማዎች በማኅበራት እና በድርጅቶች፣ የእስረኞች የረሃብ አድማ እና የተበደሉ ዜጎች የሚያደርጓቸው የተቃውሞ ሰልፎችን ያካትታል። እንዲሁም የሕዝብ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር የታሰበ ማስታወቂያ ወጪ በመሸፈን፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ድጋፍ ለማግኘት ስልታዊ አጠቃቀምን በመከተል፣ በጋራ የሚወሰዱ እርምጃዎችን በማስተዋወቅ፣ የሸማቾች ማዕቀብ የሚያደርጉ አና ተሰባስቦ አንድ ቦታ ቁጭ የማለት አድማ ላይ የሚሳተፉትን ይጨምራል። ብዙ ጊዜ የመሰባሰብ ስጋት ፍራቻ ብቻ ለውጥ ለማምጣት በቂ ይሆናል። የሚያደርሰውን ተፅዕኖ የፈሩ ቡድኖች ማሻሻያዎች ሊያደርጉ ይችላሉ። ሆኖም፣ ማስፈራሪያዎች ሌላው ወገን አቋሙን አጥብቆ እንዲይዝ ሊያባብሱ እና ለመደራደር ወይም ለውጦችን ለማድረግ ፈቃደኛ የማይሆንበትን ሁኔታ የሚፈጥሩበት ጊዜ ይኖራል።በአንዳንድ ሁኔታዎች ተሳታፊ ወገኖች በጣም አሳማኝ የሆኑ ክርክርዎችን በመያዝ እና ሌሎች አካላትን በማሳመን ተቀባይነትን እንዲያገኝ ወይም የቀረበው ቅሬታ እንዲነሳ በማድረግ ግጭቶችን የሚፈቱበት አጋጣሚ አለ።

ምንም እንኳን ግጭት አብዛኛውን ጊዜ ወደ ነውጥ የሚያመራ ቢሆንም ከላይ እንዳየነው ግጭት ሁሉ ሁከትን እንደማያስከትል ግልጽ መሆን አለበት። ግጭቶች ወደ ነውጥ ሳያመሩ መፍትሔ የሚያገኙባቸው ብዙ ሁኔታዎች አሉ።

ይህ ዓይነት ሁኔታ የሚያጋጥመው የዳበረ የግጭት አፈታት መንገድ በሚኖርበት ወቅት ሲሆን ፍርድ ቤቶች፣ ወጎች እና ረዥም ጌዜ የቆዩ ባሕሎች ግጭቶች ወደ ነውጥ ሳይቀየሩ የሚፈቱበት ልማዶች ወይም አሠራሮች ውስጥ ይካተታሉ። እንዲሁም በግጭቱ የተሳተፉ ወገኖች በግጭቱ ሒደት ወቅት አንዳቸው የሌላውን የይገባኛል ጥያቄ ትክክለኛነት ተገንዝበው የመፍትሔ ሐሳቦችን በሰላማዊ መንገድ የሚያስተናግዱበት መንገድ ሲያገኙም ሊከሰት ይችላል።

በተጨማሪም በተቀናቃኝ ወገን የሚወሰዱት እርምጃዎች በፍርሐት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን መገንዘብ ምላሽ የሚሰጡበት መንገድ ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል። በግጭት ላይ የምንሠራቸው ዘገባዎች ልዩነት እንዲያመጣ ከፈለግን ስለ ጉዳዩ በጥልቀት ማሰብ አስፈላጊ ነው። ግጭት ሁከት ከመፍጠር አልፎ አሸናፊ እና ተሸናፊ በመለየት ሊጠናቀቅ ይችላል። እንዲሁም ሁሉንም ጎራዎች የሚያስደስት መፍትሔ ሊገኝ እና ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ ሊቆም ይችላል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *