በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተደራጀ ተቃውሞ በሚነሳበት ወቅት የፊውዳላዊውን አገዛዝ ለመገርሰስ አስተዋፅኦ ያደረገው በጊዜው የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ የአብዮቱ አንቀሳቃሽ ሞተር ተደርጎ ይታያል።
በአገሪቷ ውስጥ የነበሩ የባሌና የጎጃም ገበሬዎች አመፅ፣ የመምህራን ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴ እንዲሁም በአጠቃላይ ማህበረሰቡ በተለይም ሴተኛ አዳሪዎች በሰላማዊ ሰልፎች ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ቢኖራቸውም ታሪካቸው በተገቢው ሁኔታ አልሰፈረም።
በዲላ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆነችው መስከረም አበራ በዚህ ላይ እንደ ምክንያት የምታያቸው የተወሰኑ ፅንሰ-ሀሳቦች አሏት።
መስከረም እንደምትለው ብዙ ፅሁፎች የሚፃፉት በወንዶች ስለሆነ የሴቶችን ሚና ያለማጉላት ጉዳይ አለ።
ከዚህም በተጨማሪ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይ የሴቶች ተሳትፏቸውም የተወሰነ ነበር።
በተለይም በተማሩት መካከል የመሬት ለአራሹ እና የመደብ ጥያቄዎች በጠነከሩበት ወቅት ምንም እንኳን ሴቶች ቢኖሩበትም መስከረም እንደምትለው የእንቅስቃሴው መሪዎች አልነበሩም። የተወሰኑትም ተሳትፎ የነበራቸው የወንድ ጓደኞቻቸውን በመከተል እንደሆነ ትናገራለች።
ፌሚኒዝም አገራዊ በሆነ መልኩ ውይይቶች እንዲፈጠሩና፤ የፆታ እኩልነት እንዲሰፍን የሚታገለው የሴታዊት እንቅስቃሴ አንደኛዋ መስራች የሆነችው ዶክተር ስሂን ተፈራ የሴቶች ቁጥር በሚያስደነግጥ ሁኔታ ከማነሱ በተጨማሪ በፖለቲካው ላይ የነበራቸው ተሳትፎ “በሚያሳፍር ሁኔታ” ቡና ማፍላት፣ የስብሰባ ቃለጉባኤ መያዝ፣ ወረቀት መበተን፣ መፈክር መያዝን የመሳሰሉ ሚናዎች ይሰጣቸው እንደነበር ትናገራለች።
ከዚህም በተጨማሪ በወቅቱ ተሳታፊ የነበሩት ሴቶች እንደሚናገሩት ይቀልዱባቸው እንደነበር ስሂን ትናገራለች። ይህ ሁኔታ እየተለወጠ የመጣውም የፖለቲካ ንቃተ-ህሊናቸው ከፍ ባሉት እነዋለልኝ መኮንን የመሳሰሉት የሴቶች መብትንና እንቅስቃሴውን ስለተቀበሉት ነው።
ከአስርት ዓመታትም በኋላ ብዙ ለውጥ እንደሌለ የምትናገረው መስከረም በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ የሴቶች ቁጥር አነስተኛ ነው፤ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሴቶችም በጣም ጥቂት ናቸው።
ጎልተው ከወጡት መካከል ብቅ ብላ የጠፋችውና የቅንጅት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር የነበረችውና ብርቱካን ሚደቅሳ ተጠቃሽ ናት። ከእርሷ በኋላም ሆነ ከሷ በፊት የነበሩት ሴቶች በስም ማጥፋት ዘመቻ ከፖለቲካው ምህዳርም ተገለዋል።
በፖለቲካ ላይ ለምን መሳተፍ አስፈለገ?
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በመንግሥት ደረጃ የፖለቲካውን ስፍራ የተቆጣጠሩት ወንዶች ናቸው። ማህበረሰቡን ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ሴቶችን የሚመለከቱ ህጎችን የሚያረቁትም ሆነ የሚያስፈፅሙት ወንዶች ናቸው።
አቶ ሺመልስ ካሳ “ቻለንጅስ ኤንድ ኦፖርቱኒቲስ ኦፍ ዉሜን ፖለቲካል ፓርቲሲፔሽን ኢን ኢትዮጵያ” በሚለው ፅሁፋቸው የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለምን አስፈለገ ለሚለው ጥያቄ እንደ ዋነኛ መልስ የሚያነሱትም የፍትህ ጥያቄን ነው።
ግማሹን የህብረተሰቡን ክፍል እንደ መያዛቸው መጠን በውክልና ዲሞክራሲ ሴቶች በራሳቸው ለምን አይወከሉም የሚል ነው።
ሌላኛው ደግሞ የሴቶችና የወንዶች የህይወት ልምድ በተለይም ከታሪካዊ ፆታዊ ኢ-ፍትሀዊነት ጋር ተያይዞ መስተካከል ያለባቸው ህግጋትንና አፈፃፀማቸውን ከሴቶች በላይ የሚያውቅ ስለሌለ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ሴቶችና ወንዶች በእኩልነት መወከል አለባቸው የሚሉ ሐሳቦችንም ያነሳሉ።

መሰናክሎቹ ምንድን ናቸው?
መስከረምም ሆነ ስሂን እንደ ምክንያትነት የሚጠቅሱት “አባታዊ ሥርዓት'” (ፓትሪያርኪ) ወንዶችን የበላይ በማድረግ ሴቶችን የደጋፊነት ሚና ሰጥቷቸዋል። በዚህም የፆታ የሥራ ክፍፍልና የሴቶችን ሚና በማዕድ ቤት ሥራዎች፣ ልጅ መውለድና መንከባከብ ነው።
ሴቶች ወደ አደባባይ መውጣታቸው እንደ ነውርና ሥርዓቱን እንደ መጣስ ተደርጎ ነው የሚታየውም ትላለች መስከረም።
ይህንን ሥርዓት ተላልፈው በፖለቲካው ላይ ተሳትፎ ያደርጉ የነበሩ ሴቶች ዘለፋ፣ ስድብ እንዲሁም “እዩኝ ባይ” የሚል ስም እንደሚያተርፉም ትናገራለች።
በተለይም መሪ መሆን የወንድነት ሥራ ተደርጎ የሚታይ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የእምነት ተቋማት ሴቶች በብዙ መንገድ ከወንድ እንደሚያንሱ መስበካቸውም አስተዋፅኦ አድርጓል። የሀይማኖት ድርጅቶቹ የሴቶችን ቦታ ግልፅ አድርገው እንዳስቀመጡ አቶ ሽመልስ ይናገራሉ።
ከሴቶች አለባባበሰ ጀምሮ፤ በምን መንገድ ወንዶችን መታዘዝ እንዳለባቸው እንዲሁም ከእምነት ቦታዎች አመራርም የተገለሉ መሆናቸው አስተዋፅኦ አድርጓል በማለት አቶ ሽመልስ በፅሁፋቸው አስፍረዋል።
በተለይም የቤተሰብ መዋቅር ሲነሳ ይላሉ አቶ ሽመልስ “አባታዊ” በሆነ መንገድ የሚመራ ሲሆን የመንግሥት ሥርዓትም የቤተሰብ መዋቅርን ከመከተሉ አንፃር በቤት ውስጥ ያለውም የወንዶች የውሳኔም ይሁን የሌሎች ጉዳዮች የበላይነት በመንግሥት መዋቅሮች፤ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ወይም በቀን ተቀን ኑሮ ውስጥ ይንፀባረቃል።
ብዙ ሴቶች ቢማሩም አሁንም ያለው “ያረጀ ያፈጀ” የሥራ ክፍፍል ሴቶች ቤት ውስጥ እንዲሰሩ ያስገድዳቸዋል። በሚገርም ሁኔታ ሁለቱም ተመሳሳይ ሥራ ሰርተው የገንዘብ አመንጪ ቢሆኑም ሴቷ የቤቱን ሥራ እንድትከውን ይጠበቅባታል።
ይህም ሁኔታ ለመስከረም ጊዜያቸውን በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዳያተኩሩ እንደሚያደርጋቸው ትናገራለች።
በተለያዩ መፅሄቶች የአገሪቷን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ትንታኔ በመፃፍ የምትታወቀው መስከረም ለወንዶች ተብለው የተተዉ እንደ “ፓርላማ” መመልከት የእሷ ቦታ እንዳልሆነ የሚነግሯት አይታጡም።
በተለይም ይህ “አባታዊ”ን ሥርዓት ምንም እንኳን ወንዶችን ቢጠቅምም ማህበረሰቡ እንደ ሥርዓት የተቀበለው በመሆኑና ሴቶችም ስለተቀበሉት ሥርዓቱን ለማፍረስ ውስብስብ ያደርገዋል።
“ወንዶች የራሳቸው የሆነ የሚሰባሰቡበትና የሚወያዩበት ሴቶችን ያገለለ ቡድን አላቸው” የምትለው መስከረም ከዚህም ጋር ተያይዞ ሴቶች በፖለቲካው ወጣ ወጣ ሲሉ “ኩም” እንደሚደረጉ ትናገራለች።
በአንድ መፅሄት ስትፅፍ በተመሳሳይ ዘርፍ ይፅፍ ከነበረ ወንድ በአራት እጥፍ ያነሰ ክፍያ እንዲሁም ፅሁፏን አውቀው እንዳላነበቡ የሚነግሯት ወንዶችም አልታጡም።
” ጎበዝ ካለችና እነሱን የምትፈታተን ከመሰላቸው በተለያዩ ነገር ሊመቷት ይፈልጋሉ፤ የማሸማቀቅ ፖለቲካ የሰፈነበትና በአይን የሚታዩና የማይታዩ ጋሬጣዎች የተሞሉበት ነው” ትላለች።

የፎቶው ባለመብት,BBC
የፆታዊ ጥያቄዎችና መደራጀት
በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም ቦታው ግን አሁንም የአንድ ፓርቲን ሥራ ለማስፈፀም ካልሆነ ትክክለኛ ተሳትፎ አይደለም የሚሉት የህወሓት የቀድሞ ታጋይ የውብማር አስፋው ናቸው።
የውብማር እንደሚናገሩት በንጉሡ አገዛዝ ዘመን ከ240 የፓርላማ አባለት 2 ሴቶች፤ በደርግ ጊዜ ከ835 የሸንጎ አባላት14 ሴቶች ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት የሴት ፓርላማ አባላት 30 በመቶውን ይይዛሉ።
ቁጥር መጨመሩን እንደ መልካም ነገር የሚያዩት ስሂንና የውብማር፤ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ የፓርቲውን ፕሮግራም ከማስፈፀም የዘለለ ባለመሆኑ ተሳትፎውን ሙሉ አያደርገውም ይላሉ።
“በአሁኑ ወቅት ተሳትፏቸውን እንደ መሳሪያና የሴቶች ጥያቄ እንደተመለሰ ተደርጎ ነው እየተነገረ ያለው፤ ይሄ ግን ከወረቀት እየዘለለ አይደለም። ዋናው ጥያቄ ግን ነፃነት አላቸው ወይ? ምን ያህልስ የሀገሪቱን ፖሊሲ መቀየር ይችላሉ? ምንስ ያህል ተፅእኖ ፈጥረዋል” ብለው ወ/ሮ የውብማር ይጠይቃሉ ።
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘም በኋላ የነበሩት ሴቶች በአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መዋቅሮች ፖሊሲዎችን በማርቀቅና ህጎችን በማውጣት ተሳትፎ አልነበራቸውም።
“ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት ትግል ቢሆንም፤ የመጣው ለውጥ ግን ዲሞክራሲያዊ ሳይሆን አፋኝና ሰብአዊ መብቶችን የሚጥስ ድርጅት ነው” ይላሉ የውብማር።
እነዚህ መሰናክሎች እያሉ በተደራጀ መልኩ የሴቶች እንቅስቃሴ ጎልቶ መውጣት ቢከብድም የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርን የመሰለ ጠንካራ ድርጅትም መምጣት ችሏል።
ከመንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ህግና ገቢ ከማግኘት ጋር ተያይዞ የድርጅቱ ሚና ቢቀንስም በሀገሪቱ ውስጥ የፆታ ግንኙነት ላይ ውይይቶችንና አከራካሪ ጉዳዮችን በመድረኩ ላይ በማምጣት አብዮት መፍጠር ችለዋል።
የተነሱትንም ጥያቄዎች በማስቀጠልም፤ ብዙ ያልተደፈሩ አከራካሪ ጉዳዮችን በማንሳት ሴታዊት እንቅስቃሴ እንዲቀጥል ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው።
እስካሁን ድረስ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይሁኑ የነፃነት እንቅስቃሴዎች የሥርዓተ-ፆታን ጥያቄ እንደ ፖለቲካ ጥያቄ አድርገው ይዘው መነሳት አልቻሉም። “ኃላፊነቱ የማን ነው? ማንነው ማንሳት ያለበት፤ ሴቶች ናቸው። የማንን ጥያቄ ማን ነው የሚያነሳው?” በማለት ስሂን ትጠይቃለች።
“ፊኒክሷ ሞታም ትነሳለች፡ ያልተቋጨው የትግራይ ሴቶች ገድል” በሚል ርዕስ መፅሀፍ የፃፉት የውብማር በትግሉ ውስጥ የነበረው ሁኔታ ማህበረሰቡ ለሴቶች ዝቅተኛ ቦታ ያለው ነፀብራቅም ነው ይላሉ።
በመጀመሪያው ዓመታት ሴቶች ፓርቲውን እንዲቀላቀሉ ያልተፈቀደ ሲሆን ከ1968 በኋላ ብዙ ሴቶች በሰራዊቱ እንዲሁም በሌሎች የትግሉ ዘርፍ ተሳታፊ ሆነዋል።
የውብማር እንደሚናገሩት መጀመሪያ ላይ ከባድ መሳሪያዎችን ሴቶች መሸከም አይችሉም በማለት እኩልነትን ከጉልበት ጋር ማዛመድ፤ እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ የፆታዊ ግንኙነት ስለማይፈቀድ ሴቶችን እንደ ”አሳሳች” ማየት፤ ይባስ ሲልም ፆታዊ ትንኮሳዎችም ነበሩ።
ለችግሩም ምንጭ ወንዶችን ተጠያቂ የማያደርጉት የውብማር “ችግሩ የሰፈነው ሥርዓቱ ወንዶችን የበላይ ሲያደርግ ሴቶችን ተገዢና የበታች አድርጎ የሚያስቀምጡ ነው” በማለት ይናገራሉ።
“በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚው አቅምን አደራጅቶ መታገል እንጂ ማንም መብታችንን ሊሰጠን አይችልም። ሴቶች ማንንም ሳይጠብቁ በራሳቸው መታገል አለባቸው፤ ስለሴቶች ጉዳይ ወንዶች እንዲታገሉ መማፀንም መጠበቅም የለብንም” በማለት ጨምረው ይናገራሉ።
ለዚህ ግን የፖለቲካው ምህዳር መጥበብ የሰላማዊ ሰልፍን፣ የመናገር ነፃነትን መገደቡ ሴቶች ሊያደርጉት ከሚፈልጉት እንቅስቃሴ መገደብንም አምጥቷል ብለው ወ/ሮ የውብማር ያምናሉ።