ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ ለማካሄድ ለግንቦት 28 እና ሰኔ 5 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ይዛለች። ለዚህም ፓርቲያቸውን ወክለው የሚወዳደሩ የተለያዩ ዕጩዎች ምዝገባም በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በቤኒሻንጉል፣ በሃረሪ፣ በጋምቤላ እና ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልሎች ከየካቲት 08 ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
በእነዚህ አካባቢዎች የእጩዎች ምዝገባ የሚጠናቀቀው የካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም መሆኑንም በምርጫ ቦርድ ተገልጿል።
በአፋር፣ አማራ፣ ሲዳማ ፣ ደቡብ ሕዝቦች እና ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥቶች ደግሞ ከየካቲት 15 እስከ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. የዕጩዎች ምዝገባ የሚከናወንበት ጊዜ እንደሚሆን ቦርዱ አሳውቋል።
በምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የመራጮች ምዝገባ የሚካሄደው ከዛሬ ሰኞ የካቲት 22/2013 ዓ.ም ጀምሮ ይሆናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ እና ኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ አመራሮች አባላቶቻቸውና መሪዎቻቸው መታሰራቸውን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ቢሮዎቻቸው መዘጋታቸውን በመግለጽ ይህም በምርጫ ተሳትፏቸው ላይ ጥላ ማጥላቱን ገልፀዋል።
አባላቶቻቸው ፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸውን አክብሮላቸው እንኳ አለመፈታታቸውን በመግለጽም ተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ለሚመለከታቸው አካላት አቅርበዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባት ያሳስበናል ሲሉ ተናግረዋል።
ከቀደሙት ምርጫዎች የተለየ ምርጫ ሊሆን ይችላል?
በማክስ ፕላንክ ተቋም የፖስት ዶክቶራል ፌሎ የሆኑት ዶ/ር በሪሁን አዱኛ በሕገመንግሥታዊ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥናቶችን ሰርተዋል።
ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ኢትዮጵያ ካካሄደቻቸው ካለፉት አምስት ምርጫዎች ልዩ የሚያደርገው አገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ መሆኑን በመግለጽ ይጀምራሉ።
በርካቶች ይህንን ምርጫ እንደ ከዚህ ቀደሙ የዲሞክራሲ፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱ ያለችበትን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቅራኔዎች ይፈታል ብለው መጠበቃቸው፤ አገራዊ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልጋል የሚለው ላይ የጋራ መግባባት መኖሩም ለየት እንደሚያደርገው ይናገራሉ።
ዶ/ር በሪሁን ይህ ምርጫ መሠረታዊ ምርጫ መሆኑን መንግሥት ማሰብ ይኖርበታል ሲሉም ይመክራሉ።
ይህ ምርጫ እንደከዚህ ቀደሞቹ ዓይነት ምርጫ ካልሆነ እና መሠረታዊ ምርጫ ከሆነ ደግሞ “ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አብሮ መሥራት አለበት፤ ብቻውን ሊያደርገው የሚችለው ነገር አይደለም” ሲሉ አክለዋል።
የባለፉት አምስት ምርጫዎች ኢህአዴግ በሚባል ፓርቲ ማዕቀፍ ውስጥ የተደረገ ነው በማለት ይሄኛው ስድስተኛ አገራዊ ምርጫ ግን በአዲስ ብልጽግና በሚባል ፓርቲ መዋቅር ስር የሚደረግ መሆኑን በራሱ ልዩ እንደሚያደርገው ያስረዳሉ።
ሌላው ለዶ/ር በሪሁን ይህ ምርጫ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ምርጫዎች በመላው አገሪቱ የሚካሄድ አለመሆኑም ለየት ያደርገዋል።
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ መደፍረስ ይህንን ምርጫ ስጋትና ተስፋ ይዞ እንዲካሄድ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱ መሆኑንም ይናገራሉ።
የፖለቲካ ለውጥ እና የፖለቲካ ሽግግር ወሬ በሚሰማበት ወቅት የሚደረግ ምርጫ መሆኑ ደግሞ ይህንን ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለየት እንደሚያደርገው ይስታውሳሉ።
ሆኖም ግን ይላሉ ዶ/ር በሪሁን ይህንን ምርጫ ከዚህ በፊት ከነበሩት ምርጫዎች የተለየ ነው ወይንም አይደለም የሚለውን የሚወስነው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡት ሃሳብ ነው ይላሉ።
ከዘንድሮው ምርጫ ምን ይጠበቃል?
እንደከዚህ ቀደሙ የዲሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን ብቻ ይዞ እነርሱን ለመፍታት የሚደረግ የምርጫ ውድድር ከሆነ ካለፉት በብዙ ላይለይ ይችላል ሲሉ ይገልጻሉ።
ነገር ግን አሁን አገሪቱ ላይ ያሉትን የማኅበራዊ እና የፖለቲካዊ ችግሮችን በመሰረታዊ መልኩ ለመፍታት የሚደረግ እና በዚያ እሳቤ ለመፍታት የሚካሄድ ምርጫ ከሆነ ደግሞ ካለፉት ምርጫዎች የተለየ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
በተደጋጋሚ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የመንግሥትን እርምጃዎች በመተቸት የሚታወቁት አቶ እያስፔድ ተስፋዬ በበኩላቸው ይህ አገራዊ ምርጫ ከዚህ በፊት ሲካሄዱ ከነበሩ አምስት ተከታታይ ምርጫዎች የተለየ ይሆናል ብለው አያስቡም።
ይህንን ሃሳቡን ሲያብራሩም ኢህአዴግ ከዚህ በፊት በአውራ ፓርቲነት ከመራቸውና ከተሳተፈባቸው አምስት ተከታታይ ምርጫዎች የተለየ የፖለቲካ ባህል በዚህኛው ምርጫ አለማስተዋላቸውን ይጠቅሳሉ።
ከዚህ ቀደም የተካሄዱት ምርጫዎች ከምርጫ በፊት፣ በኋላ እና በምርጫ ወቅት የተለያዩ ጉድለቶች እንደሚስተዋልባቸው የሚጠቅሱት አቶ እያስፔድ፤ ለዚህም ማሳያዎች ፓርቲዎች እንዳይንቀሰቅሱ ማድረግ፣ አባላቶቻቸውን ማሰር፣ ቢሯቸውን መዝጋት መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት ቀጣዩ ምርጫ ከዚህ በፊት ከተደረጉት አምስት ምርጫዎች ሁሉ የተለየ ይሆናል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው የገለፁት አቶ እያስፔድ፤ ይህ ግን በሂደት መጥፋቱን ይናገራል።
በወቅቱ ተስፋ አድርገው የነበሩበትንም ምክንያት ሲያስረዱ፣ የፖለቲካ ምሕዳሩ ከዚህ በፊት ከነበረው ጊዜ ሁሉ የተሻለ መስፋቱን እና በእስር ቤት የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች መፈታታቸው መሆኑን ያስታውሳሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን እንደ ልባቸው ተንቀሳቅሰው ያሻቸውን ያለ ተጽዕኖ የሚሰሩበት እድል ተመቻችቶ እንደነበርም አልዘነጉም።
ከምርጫ እና ዲሞክራሲ ጋር ተያይዞ ያሉ ተቋማትን የሚመሩ ሰዎችንም በሚመለከት በሕዝቡም ሆነ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዘንድ ከሞላ ጎደል እምነት የሚጣልባቸውን ግለሰቦች ወደ አመራርነት ማምጣት መቻሉን በማንሳት ቀጣዩ ምርጫ ተስፋ አለው ብለው እንደነበር ለቢቢሲ ገልፀዋል።
“ግን እነዚህ ነገሮች እንዳለ ተቀልብሰው ወደ ነበርንበት ተመልሰናል” የሚሉት አቶ እያስፔድ የፖለቲካ ምሕዳሩ መጥበብ ብቻ ሳይሆን በርካቶች እስር ቤት እንደሚገኙም ይጠቅሳሉ።
ዛሬም ፍርድ ቤት ንፁህ መሆናቸውን ገልጾ የታሰሩ መኖራቸውን በተለያዩ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሪፖርቶች ላይ መገለፁን የሚያነሱት አቶ እያስፔድ፤ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸውን አክብሮላቸው ነገር ግን ፖሊስ ከመልቀቅ ይልቅ አሁንም ከተማ እና ፍርድ ቤት እየቀያየረ የተለያየ ክስ የሚመሰርትባቸው መኖራቸውን ይገልጻሉ።
የባልደራስ አባላት እንዲሁም የተለያዩ የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መታሰር ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የምርጫ ቦርድ ግቢ ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ መታገታቸውን ራሱ የምርጫ ቦርድ የገለፀው መሆኑን በማንሳት በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የፖለቲካ ምሕዳሩ ጠብቦ “ፍትሃዊና የተለየ ምርጫ ይደረጋል ብሎ ማሰብ የማይታሰብ ነው” ይላሉ።
ጋዜጠኞችን በሚመለከትም ሲናገሩ ሲፒጄ ዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን በመጡበት ወቅት አንድም ጋዜጠኛ ያልታሰረባት አገር ያላት ኢትዮጵያ፣ በአሁኑ ሰዓት ግን ከቤላሩስ በመቀጠል በፍጥነት ጋዜጠኞችን በማሰር ሁለተኛዋ አገር በሚል እንደፈረጃት ይጠቅሳሉ።
ዶ/ር በሪሁን በበኩላቸው ፖለቲከኞች እስር ቤት ውስጥ ሆነው የሚካሄድ ምርጫ የቅርብ እና የሩቅ ጊዜ ተጽዕኖ እንዳለው ይናገራሉ።
በቅርብ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ አለመቻል ሲሆን፣ አርቆ ሲመለከቱት ደግሞ ከምርጫ በኋላ ለሚመጣው የፖለቲካ ሥርዓት አሉታዊ ተጽዕኖ አለው ሲሉም ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
ፓርቲዎች ይደርስብናል ያሏቸው ችግሮች ከአሁኑ መፍታት አለመቻል በኋላ ላይ ምርጫውን ለማከናወን የሰላም እና የደኅንነት ችግር ሊፈጥር ይችላል ሲሉም አክለዋል።
ምርጫውም ካለፈ በኋላ ምርጫውን ያሸነፈው ፓርቲ የተለያዩ ፖሊሲዎችና ሕጎችን ቢያወጣ፣ የሕገመንግሥት ማሻሻያ ማድረግ ቢፈልግ የሚወሰነው ፓርላማ ባሉ ፓርቲዎች እና ሰዎች በመሆኑ፣ ከዚህ ውጪ የሆኑ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎችን በአጠቃላይ ትርጉም ባለው መልኩ የማያሳትፍ ይሆናል ሲሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
የምርጫው ነጻና ፍትሃዊነት
ዶ/ር በሪሁን በምርጫ ቦርድ አካባቢ የማይካዱ የአስተዳደር እና የሕግ ለውጦች መካሄዳቸውን ይገልጻሉ። የምርጫ ቦርድ አመራሮች ቀጣዩን ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ለማድረግ ቁርጠኝነቱ እንዳላቸው “እንደ ግለሰብ ግምት አለኝ” የሚሉት ዶ/ር በሪሁን አጠቃላይ ሁኔታው ሲታይ ግን ያለው ችግር ከእነርሱ በላይ ነው ይላሉ።
ምርጫ ቦርድ በራሱ ብቻ ማስፈፀም የሚችለው ነገር የለም በማለትም መንግሥት፣ ፍርድ ቤቶች፣ የፀጥታና ደኅንነት አካላት ሁሉም የየራሳቸው ድርሻ አላቸው ብለዋል።
አሁን ያለው ጉዳዩ ከምርጫ ቦርድ በላይ ነው የሚሉት ዶ/ር በሪሁን፣ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊ ለማድረግ “ዝም ብሎ በምርጫ ቦርድ ላይ ብቻ የምንንጠለጠል አይሆንም” ይላሉ።
መንግሥት፣ ተቃዋሚዎች፣ ሕዝቡ፣ የፍትህ አካላት ሁሉም በትብብር ካልሰሩ አንዱ ተቋም ብቻ ይህንን ምርጫ በሥነ ሥርዓት ማድረግ ይችላል ማለት ከባድ ነው ሲሉ ያክላሉ።
ዶ/ር በሪሁን ይህንን ሁሉ ከግንዛቤ አስገብተው ምርጫ ቦርድ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ይችላል ለሚለው ጥያቄ “መልሴ አይችሉም ነው” ይላሉ።
አቶ እያስፔድ የምርጫ ቦርድ ፍትሃዊነት ላይ ያላቸው እምነት እየተሸረሸረ መምጣቱን ገልፀው የኦነግ እና ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ቢሮዎች በተለያዩ አካባቢዎች ተዘግተው፣ ፓርቲዎቹ ምርጫ ላይ እንዴት መሳተፍ ይችላሉ በማለት፣ ምርጫ ቦርድ ይህንን የፓርቲዎቹን ችግር እንኳ ለመፍታት ቁርጠኝነት እንዳልታየበት ያስረዳሉ።
እርሳቸው እና ሌሎች ግለሰቦች በጋራ በመሆን ባካሄዱት የማኅበራዊ ድረ ገጽ ዘመቻ የኦነግና ኦፌኮ ቢሮዎች የት የት ቦታ እንደተዘጉ አቅማቸው በፈቀደ በአካል በመሄድ፣ ሌሎቹን ደግሞ ከፓርቲው መረጃ በመሰብሰብ በፌስቡክና ትዊተር ላይ ማስፈራቸውን ያስታውሳሉ።
ፓርቲዎቹም ቢሆኑ ይህንኑ ጉዳይ ለቦርዱ በደብዳቤ በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን አቶ እያስፔድ አክለዋል።
ምርጫ ቦርድ ግን “ኦነግም ሆነ ኦፌኮ ቢሮዎቻቸው የት የት ቦታ እንደተዘጉባቸው በትክክል ስላላቀረቡላቸው መቸገራቸውን” ሲናገር መስማታቸውን ይጠቅሳሉ።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ከፓርቲዎች የሚቀርቡለትን ቅሬታዎችና አቤቱታዎችን በመቀበል ምላሽና መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ጥረት እንደሚያደርግ በተለያዩ ጊዜያት መግለጹ ይታወሳል።
ምርጫውን የሚያሸንፍ ፓርቲ መሠረታዊ የፖለቲካ ለውጥ ማምጣት የሚፈልግ ከሆነ አሁን ከምርጫ በፊት ቁጭ ብሎ “በተለይ ኦሮሚያ ውስጥ ካሉ እና ሌሎችም ፓርቲዎች ጋር መነጋገር፤ በተለይ መንግሥትን ለሚያስተዳድረው፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በይበልጥ ፓርቲ ለብልጽግና ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ” ይላሉ።
ስጋቶች እና ተስፋዎች
ኢትዮጵያ ይህንን ምርጫ የምታካሄደው በተለያዩ የደኅንነት እና የፀጥታ ስጋቶች ውስጥ ሆና ነው። የሕዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳይ፣ ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ፣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የፀጥታ ችግሮች ቢኖሩም አገሪቱ ያለችባቸውን የተለያዩ ችግሮች ለመፍታት “ቢዘገይም ምርጫ ማካሄድ አማራጭ የሌለው ነገር ነው” ዶ/ር በሪሁን ይላሉ።
መንግሥት የሕዝቡን ይሁንታ ማግኘት እንዲችል የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች እና ሕጎች ተቀባይነትና ተፈጻሚነት እንዲያገኙ ምርጫ ማድረጉ አማራጭ የለውም ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ከዶ/ር በሪሁን ጋር ተመሳሳይ አስተያየት ያላቸው አቶ እያስፔድ ይህንን ቀጣይ አገራዊ ምርጫ እስር ቤት ካሉ የፖለቲካ አመራሮች ጋር እውነተኛ የሆነ ድርድር ሳያካሄዱ ማከናወን ከዚህ ቀደም “አገሪቱ የሄደችበትን መንገድ መድገም” ይሆናል ሲሉ ይናገራሉ።
አምስተኛው አገራዊ ምርጫ ኢህአዴግ መቶ በመቶ ማሸነፉን ያስታወሱት አቶ እያስፔድ፣ አሁን የተወሰኑ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊ ሁኔታ እንዳይንቀሳቀሱ እድሎችን መዝጋት ወደሌላ አማራጭ ሊያመራ እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ውይይትና ድርድር እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት አቶ እያስፔድ የመራጮች ምዝገባ እየተጠናቀቀ መሆኑ ግን ይህንን ተስፋቸውን እያመነመነው መሆኑን ተናግረዋል።
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል የሚሉት አቶ እያስፔድ፣ ሕዝቦች በተለያየ ምክንያት ተወካዮቻቸው ባልተሳተፉበት እና በሌሉበት ምክር ቤት ለሚወጡ ሕጎች ተገዢ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ ከባድ መሆኑን ከዚህ ቀደም የተደረጉ ተቃውሞዎችን በማስረጃነት በመጥቀስ ይናገራሉ።
ዶ/ር በሪሁን ምርጫ ማለት አገሪቱን ለቀጣይ አምስት ዓመት ማን ያስተዳድራት በሚል የሚከናወን መሆኑን በማንሳት አሁን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ፣ የሕግ እና ሌሎች በርካታ ልዩነቶች ያሉበት መሆኑን ጠቅሰው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለየት እንደሚል ተናግረዋል።
አሁን ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው ፓርቲም ሆነ የሚመረጠው ፓርቲ አገሪቱ ያለችበትን ችግሮች ሁሉ ብቻውን የሚፈታቸው አይደሉም የሚሉት ዶ/ር በሪሁን፣ ከምርጫውም በፊት ሆነ በኋላ መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል።
ስለምርጫውና ከምርጫው በኋላ ምን ማድረግ እንችላለን፣ የቆዩ መሠረታዊ ጥያቄዎችንና ልዩነቶችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ማሰብ፣ አገሪቱ የምትፈልገውን መሠረታዊ ለውጥ ታሳቢ ያደረገ ውይይት ያስፈልጋል ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ዶ/ር በሪሁን ላለፉት ሁለት ዓመታት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የእንነጋገር ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር ገልፀው አሁንም ግን ጊዜ መኖሩን ይናገራሉ። ለዚህም ረዥም ርቀት መሄድ ያለበት መንግሥት መሆኑን ይናገራሉ።
ምርጫው በተለያዩ ልዩነት መንፈሶች ውስጥ የሚካሄድ መሆኑንም በማንሳት፣ ውይይቶች እና ንግግሮች ከምርጫው በፊትም ሆነ በኋላ መደረግ እንዳለባቸው ያሰረዳሉ።
አለበለዚያ ግን ከሰኔው ምርጫ በኋላ መንግሥት ችግሮችን ካልፈታ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከምርጫ በኋላ ቀውስ ላለመከተሉ ማረጋገጫ የለም ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ኢሕአዴግ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ሙሉ በሙሉ አሸንፌያለሁ ባለ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ፀረ መንግሥት አመፆች ተቀሰቀሱ።
ይህም ከግዜ ወደ ግዜ እየተጋጋለ ግንባሩ ከውጪም ከውስጥም ከፍተኛ ጫና ውስጥ እንዲወድቅ እና ሊቀመንበሩ እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በገዛ ፍቃዳቸው ስልጣናቸውን እንዲለቁ ምክንያት ሆነ።
የሕዝባዊ አመፁን፤ ብሎም በገዢው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረውን የመከፋፈል ምዕራፍ ይዘጋል ተብሎ በተጠበቀው ለውጥ፣ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መጋቢት 18/ 2010 የፓርቲው ሊቀ መንበር ሆነው ተመረጡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፣ በበዓለ ሲመታቸው አስተዳደራቸው ሊያከናውናቸው ያሰባቸውን ዋና ዋና ተግባራት ያካተተውን ንግግራቸውን አሰሙ። ታዲያ በንግግራቸው ላይ፤ መንግሥት ‘ከተፎካካሪ’ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የነበረውን ግንኙነት ማሻሻል እንዲሁም ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስፈን የተጠቀሰ ጉዳይ ነበር።
በምርጫ ዙሪያ አስተዳደራቸው ያለውን ቁርጠኝነት በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብበራሪያ በሰጡበት ሌላኛው የምክር ቤት ንግግራቸው ላይም ‹‹ላለፉት ሶስት አመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ ጫፍ አካሄዳችን መቀየር አለበት፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ ናፍቆናል ብሎ ከውጪም ከውስጥም ባደረገው ጥረት ለኢትዮጵያ የህልውና ጥያቄ የሆነውን እውነተኛ ዴሞክራሲ ለመገንባት የሚቀጥለው ምርጫ እንደ አንድ ዋና መመዘኛ ተወስዷል›› ሲሉም ተደመጡ።
ታዲያ ከዚህ ለውጥ ማግስት የሚካሄደው ምርጫ ምን የተለየ ያደረገዋል?
ብርቱካን ሚደቅሳ
‹‹መንግሥት ለራሱ ቅርበት ያላቸውን ሰዎች በምርጫ፣ ለቦርድ አመራርነት ያስመርጣል የሚውን ክስ ከግምት ውስጥ ያስገባ›› በማለት የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ስማቸው የሚታወቀውን ብርቱካን ሚደቅሳን እጩ ማድረጋቸውን አስረዱ።
የቀድሞዋ ዳኛ፣ ፖለቲከኛ እና ምርጫ ቦርድ ፍትሃዊ አልሆነም ሲሉ ከስ የመሰረቱት፤ ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ምርጫውን ለማስፈጸም በዝግጅት ላይ መሆናቸው መጪውን ምርጫ በጉጉት እንዲጠበቅ ከሚያደርጉ ጉዳዮች አንዱ ነው።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ሹመትን ተከትሎ ነበር ብርቱካን ሚደቅሳ በስደት ከሚኖሩበት ሰሜን አሜሪካ ለኃላፊነት ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልለው የመጡት።
ቦርዱ ከእርሳቸው በፊት ሶስት ሰብሳቢዎች ኖረውት ያውቃል። ሕገ መንግስቱ ከፀደቀ በኋላ የመጀመሪያው የቦርዱ ሰብሳቢ የነበሩት ከማል በድሪ ከ1986-1997 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል። ቀጥሎም መርጋ በቃና ከ1999-2009 ዓ.ም እንዲሁም ሳሚያ ዘካሪያ ከ2010-2011 ቦርዱን መርተዋል።
ብርቱካን ከሌሎቹ በምን ይለያሉ?
ብርቱካን በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው ሶስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ቅንጅትን ወክለው ተወዳደረዋል። ምርጫውን ተከትሎም መንግሥት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን እና አመራሮችን የማሰር እርምጃ ሲወስድ የዚህ ገፈት ቀማሽ ነበሩ።
በፖለቲካ ተሳትፏቸው ዓመታትን በእስር ያሳለፉት ብርቱካን በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከተመራጭነት ይልቅ ምርጫውን የሚያስፈጽመውን ተቋም ይመራሉ።
‹‹ዛሬ የማቀርባቸው እጩ ለመንግሥትም ቢሆን በተሳሳተ መንገድ እጅ የማይሰጡ፣ ለሕግ እና ስርዓት ጽኑ እምነት ያላቸው፣ እምነት ብቻ ሳይሆን፤ ለዚያ ዋጋ ለመክፈልም ዝግጁ መሆናቸውን በተግባር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስመሰከሩ ናቸው›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምክር ቤት ስለ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
አዲሷ ሰብሳቢ ከመጡ ቦርዱ የተቋሙን ሕጋዊ እና ተቋማዊ ቅርፅ በተለያ መልኩ ቀይሯል።
ቦርዱ ከዚህ ቀደም ዘጠኝ አባላት የነበሩት ሲሆን፤ በአዲሱ የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ወደ አምስት ዝቅ ተደርጓል። ኢትዮጵያ ምርጫን የምታስተዳድርባቸው ሶስት ሕጎች ወደ አንድ ተጨምቀው እና የተለያዩ ማሻሻያዎች ተደርገውበት ሥራ ላይ ውሏል።
ቦርዱ ከዚህ ቀደም ሲጠቀምባቸው የነበሩ ቁሳቁሶችን በመቀየር አዳዲስ ቁሳቁሶችን ማስተዋወቅ ከጀመረም ሰነባብቷል።
ብርቱካን በ1996 ዳኛ ከነበሩበት ግዜ ጀምሮ በሚይዙት ጠንካራ አቋም ስማቸው ይነሳል። በስደት በቆዩበት አሜሪካም ተጨማሪ ትምህርት፤ በተለይም ከዴሞክራሲ ጋር የተያያዙ ልምዶችን ማግኘታቸው ተደምሮ መጪውን ምርጫ የሚያስፈጽመውን ቦርድ መምራታቸው፣ የምርጫው ተዓማኒነት የራሱ ሚና ይኖረዋል የሚሉ አስተያየቶች ተደጋግመው ተሰምተዋል።
በሕገ-መንግሥት እና ምርጫ ጉዳዮች ላይ ጥናቶችን ያደረጉት የሕግ ባለሞያው አደም ካሴ፤ የቦርዱ ሰብሳቢ ጥንካሬ የቦርዱ ጥንካሬ ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ተጽእኖ እንዳለው ቢስማሙም፤ ከግለሰብም በላይ ሌሎች የቦርዱ አባላት ገለልተኛነት ብሎም የተቋሙ ጥንካሬ ይወስናል ሲሉ ያስረዳሉ።
ነፃ ምርጫ ለማካሄድ ምርጫ ቦርድ ጠንካራ ዳኛ መሆኑ ወሳኝ ቢሆንም ይህ ያለ መንግሥት ትብብር ውጤታማ ምርጫ ለማካሄድ ያስችላል ማለት እንዳልሆነም አደም ይገልፃሉ።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቦርዱ ገዢው ፓርቲ የመንግሥት መዋቅርን ተጠቅሞ ከሚያደርስብን በደል አልተከላከለንም ሲሉ በተደጋጋሚ ገልፀዋል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲዎች በቀጣዩ ምርጫ የመሳተፍ አቋም ላይ አንገኝም ሲሉ ቆይተዋል።
ኦፌኮ እና ኦነግ አባላቶቻችን ሲታሰሩ እና ጽህፈት ቤቶቻችን ሲዘጉ ምርጫ ቦርድ በዝምታ አልፎናል ሲሉም በተደጋጋሚ ተደምጠዋል።
‹‹ምርጫ ቦርድ እንደተቋም ራሱን በማጠንከር ስራዎች ላይ ተጠምዶ መቆየቱ በተለይም የተወዳዳሪ ቡድኖችን መብቶች መጠበቅ ላይ ክፍተቶች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን ይሄም ለቦርዱ በቀረበው በማስረጃ ላይ የተመሰረተ አቤቱታ ላይ ይመሰረታል›› ሲሉ አደም ለቢቢሲ ገልፀዋል። ለዚህም ቦርዱ በቅርቡ ገዢው ፓርቲ በሕዝባዊ ሰልፍ ላይ ስም አጥፍቷል ተብሎ ለቀረበለት አቤቱታ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ እንደማስረጃነት ይጠቅሳሉ።
ነገር ግን ምርጫው እየተቃረበ ሲሄድ እና የፖለቲካ ግለቱ ሲጨምር እንዲህ ያሉ ወቀሳዎች ይጨምራሉ፤ ቦርዱም እየተፈተነ ይሄዳል ሲሉ ያስረዳሉ።
“አሸባሪ” ተብለው ተፈርጀው የነበሩ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት መሆኑ
መጪውን አገራዊ ምርጫ ልዩ ከሚያደርጉት ጉዳዮች ሌላኛው፤ ነፍጥ አንግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ፓርቲዎች በዘንድሮ ምርጫ ስልጣን ለመያዝ መወዳደራቸው ነው።
በአንድ ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‘አሸባሪ’ ተብለው ተፈርጀው የነበሩት፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር እና አርበኞች ግንቦት 7 (ከስሞ ኢዜማ ሆኖ) ወደ አገር ቤት ተመልሰው በምርጫው ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ ናቸው።
በመጀመሪያው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ ከመሳተፍም ባሻገር የክልሉን ምርጫ አሸንፎ የነበረው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) በመጪው ምርጫ ላይ ለመወዳደር እጩዎቹን እያዘጋጀ ይገኛል።
ግንባሩ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር ሜዳ የገባው፣ የካቲት 01/2011 ዓ.ም 1740 ታጣቂዎቹን ትጥቅ በማስፈታት በሶማሌ ክልል በሚገኙ የሲቪል እና የፀጥታ መዋቅር ውስጥ ለመመለስ ከክልሉ መንግሥት ጋር ተስማምቶ ነበር።
ምንም እንኳን የፓርቲው መሪዎች እርስ በእርስ ብሎም ከክልሉ መንግሥት ጋር የተለያዩ ፖለቲካዊ ያለመግባባቶች ውስጥ ገብተው የነበረ ቢሆንም አንድም የግንባሩ አባል ወደ ትጥቅ ትግል አለመመለሱን ፓርቲው ለቢቢሲ ገልጿል።
የፓርቲው ሊቀ መንበር አብዲራሂም መሃዲ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የተገባላቸው አብዛኛው ቃል ባይፈፀምም ፓርቲያቸው በሰላማዊ ትግል ተስፋ እንዳልቆረጠ እና በክልሉ ያለውን ሰላም እንደ ስኬት እንደሚቆጥረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
‹‹ሕዝባችን ከዚህ በኋላ ወደ ጦርት እንዲገባ አንፈልግም፣ ለዚህም ነው ልዩነት ወደ ግጭት እንዳያመራ የራሳቸንን ድርሻ እየተወጣን ያለነው። መጪው ምርጫም ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ምርጫ ቦርድ እና የፌደራል መንግሥት ምን እንደሚያደርጉ ባናውቅም የክልሉ መንግሥት ግን ወደ አገር ከገባንበት ቀን ጀምሮ የሚያደርስብን ጫና አሳሳቢ ነው›› ሲሉም አብዲራሂም ገልፀዋል።
መሠረቱን በኦሮሚያ ክልል ያደረገውን እና የጠቅላይ ሚንሰትሩን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ወደ አገር የተመለሰው ኦነግ፤ በአገሪቱ ሕግ መሠረት ዓላማዬን ‘በሠላማዊ ለማሳካት እየተንቀሳቀስኩ እገኛለሁ’ ይላል።
ከ400 በላይ የምርጫ ወረዳ ጽህፈት ቤቶችን ከፍቶ ለቀጣዩ ምርጫ ዝግጅት እያደረገ የሚገኘው ኢዜማ፣ 6 ፓርቲዎች ከስመው የመሰረቱት ነው። ከእነዚህ ውስጥ ነፍጥ አንግቦ ሲታገል የነበረው አርበኞች ግንቦት 7 ተጠቃሽ ነው።
ኢዜማ “ዜግነትን መሠረት ያደረገ” ፖለቲካን በማራመድ፤ በኢትዮጵያ ማህበራዊ ፍትህን ማረጋገጥ ቀዳሚ ግቤ ብሎ ለምርጫው ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
የሕገ-መንግሥት እና ምርጫ ጉዳዮች ባለሙያው አደም ካሴ፤ ከዚህ ቀደም በነበረው አፈና ምክንያት የተቃውሞ ፖለቲካ መሰረቱ በአብዛኛው በውጪ አገራት ነበር ይላሉ። አደም የእነዚህ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት መመለስ ከፍተኛ ተስፋ እንዲሁም ጫና እና ጭንቀት ይዞ የመጣ ነው ብለዋል።
‹‹አንዳንዶቹ እንግልት አለብን፣ ቢሮ ከፍተን መንቀሳቀስ አልቻልንም እያሉ ነው፤ ሌሎቹ ደግሞ በእስር ላይ ናቸው። በተለይ ከፍተኛ ፉክክር የሚያደርጉት ፓርቲዎች ከዚህ አንጻር ያኔ ሲመጡ የነበረውን የሚያክል ተስፋ አሁን ባይኖርም፤ ተስፋው ሙሉ በሙሉ ተሟጥጧል የሚል ግምት የለኝም፣ ይህም በቀጣይ ወራት የሚኖረው መሻሻል ላይ ይመሰረታል›› ሲሉ ባለሙያው ያስረዳሉ።
በርካታ ፖለቲከኞች እስር ላይ ሆነው መካሄዱ
በኢትዮጵያ በተለይም ከሶስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በኋላ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና አባላቶች በእስር ላይ ሆነው ምርጫ ማካሄድ እንግዳ ነገር አይደለም።
በየትኛውም መለኪያ ቢሆን ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በተለይም በ2002 እና 2007 ከተካሄዱት ምርጫዎች የተሻለ ሆኖ ይካሄዳል የሚሉት አደም፤ ከሁለቱ ምርጫዎች የማይሻል ምርጫ ማካሄድ አይቻልም ሲሉ ያነፃፅራሉ። ነገር ግን መለኪያው መሆን ያለበት ሕገ መንግሥታዊ ስርአቱ እና ሕጎች የሚጠይቁት መመዘኛዎች መሟላታቸው ነው፤ ከዚህ አንፃር ዘርፈ ብዙ ጎዶሎች አሉ ይላሉ።
በአሁኑ ወቅት የኦነግ፣ የኦፌኮ እና የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በአዲስ አበባ ያለውን ዋና ጽህፈት ቤቱን ጨምሮ 103 ጽህፈት ቤቶቹ መዘጋታቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል። በዲስትሪክት ደረጃ 989 አባላቶቼ ታስረው ይገኛሉ ያለው ኦነግ 145 መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም 32 ከፍተኛ አመራሮቼ በእስር ላይ ናቸው ሲል ለቢቢሲ ገልጿል።
የኦፌኮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እስር ላይ መሆናቸውን በማስታወስ “አሁን በምርጫ አንሳተፍም አንልም። ይሁን እንጂ ምርጫ መሳተፍ የማያስችል ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው” ይላሉ።
በተመሳሳይ ግንቦት 28 ለሚካሄደው ምርጫ፤ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ቢሮ ኃላፊ አቶ ገለታው ዘለቀ፤ “የምንሄደው ምርጫ ውስጥ እንገባም የሚል እምነት የለንም። ነገር ግን እንደ አገር የምንገባበት ምርጫ አሁን ያለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ያሳስበናል” ሲሉ ለቢቢሲ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተናግረዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የቀድሞ ሊቀ መንበር ደሳለኝ ጫኔ ፓርቲው የታሰረበት አባል ወይም አመራር ባይኖርም፣ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ወደ 20 የሚቆጠሩ ጽህፈት ቤቶቹ መዘጋታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። አቶ ደሳለኝ እንደሚሉት በኦሮሚያ ክልል ፓርቲያቸው እጩዎቹን ያስመዘግባል፤ ነገር ግን ቅስቀሳን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን እንዴት ያካሂዳል የሚለው ያሳስበናል ብለዋል።
አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች መደበኛ ስብሰባ እንኳን እንደልባቸው ለማካሄድ የማይፈቀድላቸው ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የሚጠቅሱት አደም፤ ገዢው ፓርቲ ግን የኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር የወጡ ደንቦችን እንኳን የማያከብሩ ሰልፎችን ሲያካሂድ መመልከት በራሱ አሁንም ለገዢው ፓርቲ የሚያደላ ስርአት እንዳለ ያሳያል ሲሉ ያብራራሉ።
‹‹መንግሥት አሁንም የፖለቲካ ችግሮችን እንደ ፀጥታ ችግር አድርጎ የማየት አባዜው ስላለ በተለይም ምርጫው እየቀረበ ሲሄድ እና ሙቀቱም ከፍ እያለ ሲመጣ በተቃዋሚዎች ላይ ጫና ሊጨምር ይችላል›› ሲሉ ባለሞያው ያስረዳሉ። በዚህ የሚቀጥል ከሆነም ውድድር የማይፈቀድበት ምርጫ ሊሆን ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
ህወሃትን የማያሳትፈው ምርጫ
ሕዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት) ከፍተኛ ተፅእኖ ፈጣሪ በነበረባቸው ያለፉት አምስት አገር አቀፍ ምርጫዎች የተለያዩ ወቀሳዎችን ሲያስተናግድ ቆይቶ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫን በተመለከተ ግን ከማዕከላዊ መንግሥት ሙሉ በሙሉ የተገለለው ፓርቲው ወቀሳዎችን ሲያቀርብ ነበር። በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ መከሰትን ተከትሎ ምርጫ እንዲራዘም ሲወሰንም ህወሃት በክልሉ ምርጫ ማካሄዱ ብሎም ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ፓርቲው ከጥቂት ወራት በኋላ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ የተሰረዘ ሲሆን፣ የፓርቲው አመራሮች በክልሉ ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር ተያይዞ የተወሰኑት ህይወታቸው አልፏል፣ ሌሎቹ በትጥቅ ትግል በበረሃ የሚገኙ ሲሆን የተወሰኑት በሕግ ጥላ ስር ይገኛሉ።
ሴቶችና ወጣቶች የራቁት የተቃውሞ ፖለቲካ
እናም ህወሃት ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ ጀምሮ እንደ ፓርቲ ተሰርዞ የሚካሄድ የመጀመሪያው አገር አቀፍ ምርጫ ይሆናል። በክልሉ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል የሚካሄደው ምርጫ ከሌላው የአገሪቱ ክፍል ዘግይቶ እንደሚደረግ ምርጫ ቦርድ ገልጿል። አደም እደሚያስረዱት ህወሃት በትግራይ ክልል ብቻ የሚወዳደር ፓርቲ እንደመሆኑ የፓርቲው ያለመኖር በቀጥታ ከቀጣዩ ምርጫ ጋር ግንኙነት ባይኖረውም በሂደት የሚታዩ ውጤቶች ግን መኖራቸው አይቀሬ ነው ይላሉ።
እንደ አደም ገለፃ ፓርቲው እንደ አንድ ነባር ፓርቲ ያካበተው የራሱ ልምድ፣ አቅም እና ሃብቶች የነበሩት መሆኑ እና አሁን ያ ሙሉ ለሙሉ መጥፋቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የራሱ ጉድለት ይኖረዋል። በህወሃት የሚደገፉ ፓርቲዎች ከዚህ በኋላ ያንን ያለማግኘታቸው የፓርቲው መጥፋት ከክልሉ ያለፈ ሚና ይኖረዋል ሲሉም ያስረዳሉ።
ምርጫው ኢትዮጵያ ለገባችባቸው ችግሮች መፍትሄ ያመጣ ይሆን?
በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በክልሉ የታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰፍቶ በመተከል ዞን ላይ ተተግብሯል። ኢትዮጵያ እና ሱዳንም አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ በሚል ግጭት ውስጥ ገብተዋል። በአገሪቱ የተለያዩ የፖለቲካ ልዩነቶች ተካረው እንዲሁም ልሂቃኑ በሚመሩት የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ መገኘቷን ብዙዎች ደጋግመው ያነሳሉ። በአገር ውስጥ በተነሱ ግጭቶች አያሌ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡበት እና እስከ አሁንም ድረስ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ይገኛሉ። ብሔርን፣ ሃይማኖትን ብሎም ሌሎች ማንነቶችን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን መስማትም የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
የአብን የቀድሞ ሊቀ መንበር ደሳለኝ ጫኔ መጪው ምርጫ ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀውስ ማውጣቱ ወይም መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ለአዲስ ቀውስ ይጋብዛል ብለው ይሰጋሉ። ፓርቲያቸው ከምርጫ በፊት አገራዊ ንግግር ያስፈልግ ነበር ብሎ ቢጎተጉትም ተቀባይነት አላገኘም ሲሉ ያስረዳሉ። ምርጫውን ተከትለው የሚኖሩ ውጤቶች ወደ ሌላ ቀውስ ሊያስገቡ ይችላሉ ብለው ቢያምኑም፣ ምርጫው መደረጉ ስላልቀረ ግን ጠንክረው ለመወዳደር ተዘጋጅተዋል።
በደሳለኝ ሃሳብ የሚስማሙት አደም ምርጫ እንኳን እንዲህ በተለያዩ ቀውሶች ውስጥ በሰላማዊ ሁኔታ ውስጥም ብዙ ግዜ ውጥረት ይፈጥራል ይላሉ። የምርጫ ውጤት ለአምስት አመት ስለሚዘልቅ የተሸነፈው ቡድን ገዢው ፓርቲም ይሁን ተፎካካሪዎቹ በቀላሉ በፀጋ አይቀበሉትም።
‹‹ መሰረታዊ የፖለቲካ ልዩነቶች እያሉ ያለንግግር በሚደረግ ምርጫ ብቻ ካለው ችግር መውጣት አይቻልም። ተቃዋሚዎች የሕዝብ ቅቡልነት እንዳላቸው እና የሚወክሉት እና የሚደግፋቸው የሕዝብ ክፍል እንዳለ አምኖ ለንግግር መቀመጥ ያስፈልጋል›› የሚሉት አደም ‹‹ያለ ንግግር ምርጫን ማካሄድ እንደ ህመም ማስታገሻ ለተወሰነ ግዜ ቅቡልነት ያመጣ ይሆን እንጂ ዘላቂ ውጤት አያመጣም›› ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከ 2007 ምርጫ መማር ያለባትም ይህንኑ እንደሆነ የገለፁት የሕግ ባለሞያው ከምርጫው በኋላ ለጥቂት ወራት ሰላም ቢሆንም ችግሮቹ ከመሰረታቸው ካልተፈቱ ለውጥ አይመጣም ይላሉ። ይህም በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነት የፖለሲ ሳይሆን በመሰረቱ በአገረ መንግስቱ ላይ ገና መስማማት ሳይደርስ የተመረጠው ፓርቲ ቅቡልት አለኝ ብሎ መሰረታዊ የፖለቲካ ለውጦችን፣ ካስፈለገም ሕገ መንግስቱን እቀይራለሁ የሚል ከሆነ ወደ ባሰ ቀውስ ሊከት ይችላል ሲሉ ይከራከራሉ።
ነገር ግን መንግስት ከምርጫው በኋላ በሚመረጡ እና ቅቡል በሚሆኑ ፓርቲዎች አማካኝነት ንግግሩ ይካሄደል ያለውን የሚተገብር ከሆነ ምርጫው ምን አልባት አገሪቷ ካጋጠሟች ችግሮች የሚያወጡ መፍትሄዎችን ሊያመጣ ይችላል ሲሉም ተስፋቸውን ያስቀምጣሉ።