በአስርት አመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲ ጉባኤዎችን፣ ክርክሮችን፣ ቅስቀሳዎችን ለተከታተለ አንድ ጎልቶ የሚንፀባረቅ ጉዳይ አለ።
የአንበሳ ድርሻውን የሚይዙት ወንዶች ከመሆናቸው በተጨማሪ በማዕከላዊ እና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነታቸው የሴቶች ቁጥር የተመናመነ ወይም በአንዳንድ ፓርቲዎች እንደሚታየው የሉም ማለት ይቻላል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ ቦርድ እውቅና ያገኙ ከ60 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖሩም ሁሉም በሚባል ሁኔታ አመራሮች ወንዶች መሆናቸው በአገሪቱ ውስጥ ግማሽ የህዝብ ቁጥር የሚወክሉት ሴቶች ለምን በነዚህ ፓርቲዎች ውስጥ የውሳኔ ሰጭነት ቦታ አላገኙም የሚለውን ጥያቄ ያጭራል።
በእነዚህ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በአመራር ደረጃ ቀርቶ ከወረዳ ጀምሮ ባለው መዋቅሮች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ይሄን ያህል እንዳልሆነ ተንታኞች ይናገራሉ።
በተለይም አገሪቱ ምርጫ በምታካሂድበት ወቅት የሚስተዋለው ክፍተት በከፍተኛ ሁኔታ ጎልቶ ይወጣል፤ ፓርቲዎቹ የሚያቀርቧቸው ዕጩ ተወዳዳሪ ሴቶች አናሳ መሆኑንም ማስተዋል ይቻላል።
የሴቶች ውክልና በምክር ቤት
እስቲ ወደኋላ 26 አመታትን ተመልሰን የ1987 ዓ.ም ምርጫን እንመልከት። በዚህ አመት በተደረገው አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ 536 ወንዶች የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫን ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን የሴቶች ቁጥር ደግሞ 10 ነበር።
በዚሁ ወቅት የነበረውን የክልል ምክር ቤቶችን አሸናፊዎች ስንመለከት ደግሞ 1 ሺህ 355 ወንዶች በዘጠኙ ክልለ ባሉ የክልል ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ማግኘት መቻላቸውን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። በዚሁ አመት በዘጠኙ ክልሎች መቀመጫ ያገኙ የሴቶች ቁጥር 77 ነው።
አስርት አመታትን ወደኋላ ሄደን በንጉሱ አገዛዝ ዘመን የነበረውን ቁጥር በምንመለከትበት ወቅት ከ240 የፓርላማ አባላት መካከል 2ቱ ሴቶች የነበሩ ሲሆን በደርግ ጊዜ ደግሞ ከ835 የሸንጎ አባላት መካከል 14 ሴቶች ይገኙበታል።
ከአስር አመታት በኋላ ወይም ኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ባደረገችው ምርጫ በምክር ቤቱ መቀመጫን ማሸነፍ ያገኙ ሴቶች ቁጥር ከፍተኛ መሻሻልን አሳይቷል።
በ2007 ወይም በአሁኑ ወቅት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ሴቶች ያላቸው ቁጥር 212 ወይም በመቶኛ ሲሰላ 38.8 በመቶ ነው።
የክልል ምክር ቤቶችን ስንመለከት ደግሞ በወቅቱ አገሪቷን ያስተዳድር የነበረው ኢህአዴግ እና የተለያዩ አጋር ድርጅቶች ሁሉንም መቀመጫዎችን ያገኙ ሲሆን ከነዚህም መካከል 800 ወይም በመቶኛ 40.3 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
ምንም እንኳን በምክር ቤቶች ያለው የሴቶች ውክልና ቁጥር መሻሻል ቢያሳይም በወሳኝ ቦታዎች አለመቀመጥ፣ የይስሙላ ተሳትፎና ቁጥር ማሟያ መሆናቸው የሚነሳ ጉዳይ ሆኗል።
በርካቶቹ የፓርቲዎቻቸውን ፕሮግራም ከማስፈፀም በዘለለ አጀንዳዎችን በመቅረፅም ሆነ ፖሊሲዎችን በማርቀቅ ደረጃ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላቸው ይናገራሉ።
በተለይም የስርዓተ ፆታ የኃይል ሚዛን ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት መዋቅራዊ የሆኑ የፖሊሲ ለውጦች ያስፈልጋሉ በሚባልበት ወቅት ሴቶች የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ፣ በራሳቸው መወሰን አልቻሉም ይባላል።
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ስድስተኛና አገር አቀፍ ብሔራዊ ምርጫን ለማድረግ በዝግጅት ላይ ናት፤ ምርጫው የተቆረጠበት ቀን ሊደርስም 13 ሳምንታት ያህል ቀርቶታል።
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረትም የፖለቲካ ፖርቲዎች እጩዎቻቸውን እያስመዘገቡ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎችም እስከ የካቲት 30፣ 2013 ዓ.ም እንደሚቀጥል ተገልጿል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባላቶቹ በታሰሩበት ሁኔታ፣ ቢሮዎቹ ተዘርፈውና ተዘግተው እንዲሁም የምርጫ መርሃ ግብሩ ባልተሻሻለበት በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አልሳተፍም ሲል አሳውቋል።
ከፓርቲው16 የስራ አስፈፃሚዎች መካከል ብቸኛ ሴት የሆኑት ዶ/ር በላይነሽ ይስሃቅም በዘንድሮው ምርጫ ለመወዳደር ፓርቲያቸውና መንግሥት እያደረገ የነበረውን ውይይት በመጠባበቅ ላይ ነበሩ።
ነገር ግን ፓርቲው ባሉት ሁኔታዎች “ተገፍቼ ወጥቻለሁ” ማለቱን ተከትሎ እርሳቸውም በዘንድሮው ምርጫ አይወዳደሩም። ሆኖም መለስ ብለን ከዚህ በፊት የተሳተፉባቸውን ምርጫዎች እንዲሁም የሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ተሳትፎ ማነስ ምክንያቶችን ቢቢሲ ጠይቋቸዋል።

የፎቶው ባለመብት,ANADOLU AGENCY
“ሴቶች በፖለቲካዊ ተሳትፏቸው ምክንያት ወሲባዊ ጥቃቶችንና የስም ማጥፋት ዘመቻን አስተናግደዋል”
ዶክተር በላይነሽ የፖለቲካ ህይወታቸው የሚጀምረው የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዲን)ን በተቀላቀሉበት በ1997 ዓ.ም ነበር። በዚያኑ አመት በትውልድ ቦታቸው በቄለም ወለጋ በምትገኘው አንፊሎ ወረዳን ወክለው ተወዳደሩ፤ ማሸነፍም ቻሉ።
ምንም እንኳን ምርጫውን ማሸነፍ ቢችሉም ለሴቶች ምርጫ ውድድር ውስጥ እጩ ሆኖ መቅረብ ሳይሆን ሴት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ይገጥማቸው የነበሩ ፈተናዎች “ተዘርዝረው አያልቁም” ይላሉ።
የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ይገጥማቸው የነበሩት ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታዎች ተደራርበው ይጨምራሉ ይላሉ።
በተለያዩ ምርጫዎች በተሳተፉበት ወቅት፣ በተለይም በቅስቀሳ ወቅት የሚያጋጥማቸው ከሆቴል መባረር እንደሆነም ያስታውሳሉ። በአንድ ወቅት አንድ ሆቴል ገንዘባቸውን መልሶላቸው ሌላ ማደሪያ ባለማግኘታቸው መኪና ውስጥ ለማደር መገደዳቸውንም ያስታውሱታል።
አንዳንድ ጊዜም ለምርጫ ቅስቀሳ ይዘዋቸው የሄዱት መኪኖችም በፍራቻ ባዶ ሜዳ ላይ ውረዱልን ብለዋቸው ያውቃሉ። ሆቴሎቹም ሆነ የትራንስፖርት መጓጓዣዎች በፍራቻ እንደሚያባርሩዋቸው በተደጋጋሚ ነግረዋቸዋል።
እርሳቸው ፓርቲውን በተቀላቀሉበት ወቅት በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ይሳተፉ የነበሩ የሴቶች ቁጥር በጣም አናሳ የነበረና ብዙ መስዋዕትነትም ስለሚያስከፍል በርካቶች መገፋታቸውን ይጠቅሳሉ።
“ተቃዋሚ መሆን በራሱ ከባድ ነው” የሚሉት ዶክተር በላይነሽ በተለይ ሴት ተቃዋሚ መሆን ደግሞ በርካቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋ እንዳስከፈላቸውም በአመታት ታዝበዋል።
በወንድ ተቃዋሚዎች ከሚደርሱት ማስፈራሪያ፣ ዛቻዎችና እስሮች በተጨማሪ ዘርዘር አድርገው ባይናገሩትም በፖለቲካ ተሳትፏቸው ምክንያት የመደፈር (ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው) መኖራቸውን ይጠቅሳሉ።
“ተቃዋሚ መሆን እንኳን ለሴት ለወንድ ከባድ ነው። እኔ የማልናገራቸው በርካታ ነገሮች የደረሰባቸው አሉ። ደረሰብን ብለው የሚናገሩት በጣም አስፈሪ ነው። ለሴት በጣም ፈታኝ ነው” ይላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ ከስራ መባረር፣ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች እንዲሁ በተቃዋሚ ፓርቲ ሴት አባላት ውስጥ የሚደርሱ በመሆናቸው በርካቶችን እንዲፈሩ ማድረጉንም ያስረዳሉ።
የእንስሳት ሃኪም የሆኑት ዶክተር በላይነሽ ራሳቸው በፖለቲካ ተሳትፏቸው ምክንያት ከስራ በመባረራቸው ኑሯቸውን በአንድ ወቅት ፈታኝ አድርጎት እንደነበር ያወሳሉ።
በተለይም ሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ላይ የሚደርሰው የሚከፋው በክፍለ ሀገር ከተሞች በመሆኑ በወረዳዎች ላይ የሚገኙ ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎም ሆነ በእጩ ተወዳዳሪነት ለመቅረብ ከፍተኛ ፍራቻ እንዳላቸውም ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት,ANADOLU AGENCY
የስርዓተ-ፆታ የኃይል ሚዛን መዛባት የፈጠረው ክፍተት
ከፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ በተጨማሪ የወንዶችንና የሴቶችን ግንኙነት ወይም ሴቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ሊኖራቸው የሚችለውን ቦታ አስመልክቶ በሚወስነው አባዊ ስርዓት (ፓትሪያርኪ) ምክንያት ሴቶች በፖለቲካው፣ በትምህርት እና በኢኮኖሚው ዘርፍ ተሳታፊነታቸውን ወደ ኋላ እንዲቀሩ አድርጓቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በሰፈነው ኢ-ፍትሃዊ የስርዓተ-ፆታ የኃይል ሚዛን ለተለያዩ መድልዎችና ፆታዊ ጥቃቶችም እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል።
የስርዓተ-ፆታ ሚዛን ኃይል አለመመጣጠን በተለይም የሚገለፅበት አንዱ ሁኔታ በሴቶች ላይ ያለው ተደራራቢ የስራ ጫና ሲሆን ይህም ሁኔታ ለሴቶች እፎይታ አግኝተው በሌሎች መድረኮች እንዳይሳተፉ አድርጓቸዋል።
በተለይም ዶክተር በላይነሽ እንደሚናገሩት በገጠሪቷ ክፍል የማገዶ እንጨት ለቀማ፣ ውሃ መቅዳት፣ ልጆች ማሳደግና ሌሎች ፋታ የማይሰጡ ስራዎች ወስኗቸው ይገኛሉ ይላሉ።
ከዚህ በተጨማሪ በከተሞች ዘንድም ቢሆን በፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ሴቶች ልጆችን ከመንከባበብ ጀምሮ የማይከፈልባቸው የቤት ውስጥ የስራ ጫናዎች ድርብር ኃላፊነትን ተሸክመው ይገኛሉ።
ምንም እንኳን ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ይህ ነው ባይባልም ፓርቲዎች በሚያደርጓቸው የድጋፍ ሰልፎች፣ የምረጡኝ ቅስቀሳም ሆነ ሌሎች ተሳትፎዎች ላይ የሚመዘገበው ቁጥር ከፍተኛ ነው።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንደ አንድ ትልቅ ምዕራፍ የሚታየውን የ1997 የመራጭ ሴቶች ቁጥር እንመልከት እስቲ-
ግንቦት 07 ቀን 1997 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ላይ 27 ሚሊዮን 372 ሺህ 888 ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ የሴቶች ቁጥር 13 ሚሊዮን 087 ሺህ 594 ነው።
ከተመዘገቡትም ውስጥ በአጠቃላይ 22 ሚሊዮን 610 ሺህ 690 መራጮች ድምፅ ሰጥተዋል፤ ከነዚህም ውስጥ 12 ሚሊዮን 058 ሺህ 511 ወንዶች ሲሆኑ የሴቶች ቁጥር ደግሞ 10 ሚሊዮን 552 ሺህ 179 መሆኑን ከምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
በአመታት ውስጥ መራጩ ህዝብ (ሴቶችም ይሁኑ ወንዶች) ሴት እጩ ተወዳዳሪዎች ካሉ ለመምረጥ ወደኋላ እንደማይሉም ወይዘሮ በላይነሽ በራሳቸው ልምድ አይተውታል።
ምንም እንኳን ሴት መራጮች በከፍተኛ ሁኔታ በአመታት ቢጨምሩም የሴት ፖለቲከኞችም ሆነ ተመራጮች ቁጥር አሁንም ይህን ያህል አልተራመደም። በቅርቡ የተመሰረቱት ፓርቲዎች ለዘመናት ወጣቶችን አግልሎ የነበረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተወሰነ መልኩ ቢቀይሩም የሴቶች ተሳትፎ ብዙ መራመድ እንዳልቻለም የፓርቲዎቹን የሴቶች ቁጥርና የስልጣን ተዋረድ በማየት መረዳት ይቻላል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) መስራች ከሆኑት መካከል የ29 አመቷ እመቤት ከበደ አንዷ ናት። በሙያዋ የፕሮጀክት አስተባባሪ የሆነችው እመቤት፣ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ስትገባ የመጀመሪያዋ ሲሆን ይህም በ2010 ዓ.ም ነው።
ፓርቲውን ስትመስርት ለእርሷ ዋነኛ ጉዳይ የነበረው “አማራ በባለፉት አስርት አመታት ተወካይ አላገኘም” የሚል እንደሆነ ትናገራለች።
ፓርቲያቸውም “የአማራ ውክልናን ማዕከል” አድርጎ ከመነሳቱ አንፃር እመቤት የስርዓተ ፆታ ጥያቄዎችም በዚያው ሊመለሱ እንደሚችሉ ትናገራለች።
ሆኖም በፓርቲያቸው ውስጥ ያሉ የሴቶች ቁጥር አነስተኛ መሆኑንም እሷም ቢሆን አትክደውም። ለምሳሌ ያህል ከ45 ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል ሴቶች ሶስት ብቻ ናቸው።
ከዘጠኝ ስራ አስፈፃሚዎች መካከል አንዲት ሴት የለችም። ሴቶች ተሳታፊ ብቻ ሳይሆን በፓርቲያቸው ውስጥ ውሳኔ ሰጭዎች እንዲሆኑ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያደርጉ ብትናገርም “ያን ያህል አጥጋቢ አይደለም” ትላለች።
ምንም እንኳን በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የሴቶች ቁጥር ዝቅተኛ ቢሆንም በወረዳዎች ደረጃ ባለው አወቃቀር ግን በርካታ ሴቶች ቁልፍ ሚናን እንደያዙም ትናገራለች።
እመቤት ለአንድ አመት ያህል የፓርቲው የባህርዳር ፅህፈት ቤት ኃላፊ የነበረች ሲሆን፣ ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ለመሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች ትሰጣለች።
በራሷ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ሴቶች ቁጥር ማሟያ ተደርገው መታየታቸውና (የይስሙላ ሴቶችን አሳትፈናል) ለማለት ብቻ የሚገቡ ሲሆን ሴቶች በወሳኝ ቦታዎች እንደማይቀመጡና አብዛኛውን ጊዜም የስራ ድርሻቸውም ይህን ያህል የረባ አለመሆኑንም ታዝባለች።
እንደ ዶክተር በላይነሽ እሷም ቢሆን “ለአመታት በአገሪቱ የሚገኙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተደጋጋሚ እስር፣ እንግልት፣ ዛቻና ማስፈራሪያዎች ሴቶችን በፓርቲዎች እንዳይሳተፉ አድርጓቸዋል” ትላለች። ከዚህም ጋር ተያይዞ “በፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፍም ሆነ የአመራር ቦታውን ይፈሩታል” ትላለች።
በተለይም ከፖለቲካ ምህዳሩ ጋር ተያይዞ ቤተሰቦች ስለሚሰጉ ሴቶች የቤተሰብ አባላትን በፖለቲካው እንዳይሳተፉ ተፅእኖ ማድረጋቸውን ትጠቅሳለች። “ለስብሰባዎች በምንሄድበት ወቅት ከፍተኛ ፍራቻ አለ። ሴቶች ራሳችንም እንፈራለን፤ እንዲሁም ቤተሰብም ስለሚሰጋ ከፍተኛ ተፅእኖ ያደርጋል። የተቃውሞ ፖለቲካ ከባድ ነው” ትላለች እመቤት
በአብን ፓርቲ ውስጥ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሴቶች ጉዳይ ዴስክ ኃላፊ የሆነችው እመቤት እሷም ቢሆን ቤተሰቦቿ መጀመሪያ አካባቢ ፍራቻ እንደነበራቸው አትደብቅም። ሆኖም በፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎዋ ቀጥላ ኢትዮጵያ በምታደርገው ስድስተኛ ብሔራዊ ምርጫ በባህርዳር ከተማ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆና ትቀርባለች።
እመቤትን ጨምሮ አብን በአገር ውስጥ ከሚያቀርባቸው እጩ ተወዳዳሪዎች መካከል 30 በመቶዎቹ ሴቶች እንደሆኑም ፓርቲዋን ወክላ ለቢቢሲ ተናግራለች።
የዘንድሮ የአገሪቱ ብሔራዊ ምርጫ ሲነሳ በከፍተኛ ደረጃ እየቀሰቀሱ ካሉትና የዜግነት ፖለቲካን አካሂዳለሁ ከሚለው ፓርቲዎች መካከል ኢዜማ ይገኝበታል። ኢዜማም በኢትዮጵያ ደረጃ ከሚያቀርባቸው እጩ ተወዳዳሪዎች መካከል 30 በመቶዎቹ ሴቶች መሆናቸውን የኢዜማ የወጣቶች ተጠሪ ፅዮን እንግዳዬ ለቢቢሲ ተናግራለች።
ፅዮን እሷን ጨምሮ ከ21 የስራ አስፈፃሚዎች መካከል ስድስቱ ሴቶች እንደሆኑ ትናገራለች። የፅዮን የፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎዋ በኢዜማ ቢጀምርም በአገሪቱ ውስጥ የሰፈነውን የስርዓተ-ፆታ ኃይል አለመመጣጠን እንዲሁም ያሉትን በሴቶች ላይ ጭቆና የሚያሳርፉ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ሌሎች መዋቅሮችን ለመቅረፍ የሚሰራው የሎው ሙቭመንት አካል ናት።
በምስረታው ወቅት ባየችው ተስፋ ሰጭ ነገርም ፖለቲካ ፓርቲው ይወክለኛል በሚል እንዳመነች ትናገራለች። ለዚህም እንደ ዋነኝነት የምታነሳው ለስርዓተ ፆታ ምላሽ ሰጭ ስርአት (Gender responsive system) በመዘርጋት በማህበራዊ ፍትህ የተቃኙ ፖሊሲዎች መኖራቸውን ትጠቅሳለች።
ፓርቲዋ በምጣኔ ኃብት፣ ትምህርት፣ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ያወጣቸው 42 ፖሊሲዎችም እንዲሁ በስርዓተ-ፆታ አይን እንዲታይና እንዲፈተሽ ማድረጉንም ታስረዳለች። ከዚህም ጋር ተያይዞ የስርዓተ-ፆታ የኃይል ሚዛን እንዲመጣጠን የምትሰራው ሴታዊት እንቅስቃሴን ማሳተፉ ያለውን ቦታ አሳይ እንደሆነም ትጠቁማለች።
ከዚህም በተጨማሪ ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ የሴቶች ጉዳይ ተጠሪዎች መኖሩ ፓርቲው የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማስፈን እየሰራ መሆኑ ማሳያ ነው ትላለች።

የፎቶው ባለመብት,ANADOLU AGENCY
በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ሴቶች እንደ ተቀጥላ መታየት
በኢትዮጵያ ታሪክ የተደራጀ ተቃውሞ ከሚነሱት መካከል የፊውዳላዊውን አገዛዝ ለመገርስስና የተቀሰቀው የተማሪዎች ጥያቄ ይጠቀሳል። ስር ነቀል ለውጥን በማቀንቀንና መሬት ለአራሹ በሚል እንቅስቃሴያቸው የአብዮቱ ጠባቂ (ጋርዲያን ኦፍ ዘ ሪቮሉሽን) የሚል ስያሜም ተሰጥቷቸዋል።
ተማሪዎቹ የኢትዮጵያ ትግል ለብቻው እንዳልሆነና በተለይም ከዓለም አቀፉ ፀረ-ኢምፔሪያሊዝም፣ ፀረ ቅኝ ግዛት እንዲሁም ዘረኝነትን ከመታገል ጋር ተያይዞ ትብብር ሊኖር እንደሚገባና ትንታኔም በዚያ መልክ ይሰጥ ነበር። በዚያን ወቅት ተሳትፏቸው የሚጠሩት ጥቂት ሴቶች ሲሆኑ በርካቶች የእንቅስቃሴዎቹ መሪዎችም አልነበሩም።
ቁጥራቸው ትንሽ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ጥቂቶቹም ቡና በማፍላት፣ የስብሰባ ቃለ ጉባኤ መያዝ፣ ወረቀት መበተን፣ መፈክር መያዝ የመሳሰሉ ሚናዎች እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ይዘክራሉ።
ቀስ እያሉ ሁኔታዎች የተቀየሩት የሴቶች መብትን እንደ ሰው መብት ወይም ደግሞ እንደ ፖለቲካዊ ጥያቄ ባዩ አንዳንድ የፖለቲካ ንቃተ ህሊናቸው ከፍ ባሉ አመራሮች ምክንያት እንደሆነም የታሪክ ተንታኞች ያስረዳሉ።
ከአስርት አመታት በኋላ ይኸው ሴቶችን ከቤት ስራዎች ድርሻ ጋር የመያያዙ ባህሉም ሆነ ልምዱ አልቀረም ። በርካታ የሴት ፖለቲከኞችም ሆነ ፅዮን የታዘበችው ቢኖር በተለያዩ ስብሰባዎች ሴቶች እንዲያስተናብሩ፣ ቡና እንዲያፈሉ፣ ቆሎ ማቀበል፣ አስተናግዱ እና ሌሎች ባለው የስራ ክፍፍል ውስጥ የሴቶች ተብለው የሚሰሩ ስራዎች እንዲያከናውኑ እንደሚጠየቁ ትናገራለች።
አንዳንድ ጊዜም የሴቶች ውጫዊ እይታቸውንም ከፖለቲካዊ ህይወታቸው ጋር በማስተሳሰር የሚሰጡ አስተያየቶችንም ሰምታለች “አንቺማ በመልክሽ ትመረጫለሽ” የሚል አስተያዬት እንዲሁም የፓርቲውን ፕሮግራሞች ለማስተዋወቅ “ቆንጆ ሴቶች ለምን አንመርጥም” የሚል ጉዳይ ሰምታለች።
የማህበረሰቡን አስተያየት ሙሉ በሙሉ መቅረፍ አስቸጋሪ ቢሆንም ፓርቲው መዋቅራዊ የሆነ መገለልን እንደማይቀበልና ይህንንም ለመፍታት ከደንብ በተጨማሪ የዲሲፒሊን ኮሚቴም አዋቅሯል ትላለች። ከዚህም በተጨማሪም የስርዓተ-ፆታንም በተመለከተ ስልጠናዎች እንደሚሰጡም ታስረዳለች።
በላይኛው አመራር ያሉ የፓርቲው አባላት በስርዓተ-ፆታ ጉዳይ ላይ ያላቸው እይታ መልካም ቢሆንም በወረዳ ደረጃ አንድም ሴት ሊቀ መንበር አለመኖሩ የሴቶችን ተሳትፎ ጥያቄ ገና ለመሆኑ ማሳያ ነው ትላለች።
ነገር ግን ኢዜማ በዘንድሮው ምርጫ ሴቶች በዕጩ ተወዳዳሪነት እንዲሳተፉ በዕጩ መመልመያ መስፈርት ውስጥ ከፍተኛ ማበረታቻ በማድረጋቸው ምክንያት በርካታ ሴት ዕጩዎችን ማግኘት መቻላቸውን ትናገራለች።
“ኢዜማ ስርዓተ ፆታ እኩልነትን ለማስፈን የሚሰራ ፓርቲ ነው” ብላ ፅዮን ሙሉ በሙሉ የምታምን ሲሆን ለዚህም በዋነኝነት “ሴቶች ራሳቸውን ወክለው ራሳቸው መጥተው የራሳቸውን ችግሮች የሚያነሱበትን መድረክ መፍጠር ችሏል” ትላለች።
የሴቶች ተሳትፎ ለምን? እንዴትስ ፍሬያማ ይሁን?
ኢትዮጵያ በነበሯት ህጎችም ሆነ የተለያዩ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊ መዋቅሮች ሴቶችን በልዩነትና በበታችነት ለዘመናት ስታይ ቆይታለች።
ለአመታትም የነበረው ሁኔታ ሲታይ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በመንግሥት ደረጃ የፖለቲካውን ስፍራ የተቆጣጠሩት ወንዶች ናቸው።
ማህበረሰቡን ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ሴቶችን የሚመለከቱ ህጎችን የሚያረቁትም ሆነ የሚያስፈፅሙት ወንዶች መሆናቸውም የህግ አውጭ ምክር ቤቱ በወንዶች ለመያዙ አስረጅ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ለምን አስፈለገ የሚለው የፍትህ ጥያቄ አንደሆነና ግማሹን የህብረተሰብ ክፍል እንደ መያዛቸው መጠን በውክልና ዲሞክራሲ ሴቶች በራሳቸው ለምን አይወከሉም የሚል ነው።
ሌላኛው ደግሞ የሴቶችና የወንዶች የህይወት ልምድ በተለይም ከታሪካዊ ፆታዊ ኢ-ፍትሀዊነት ጋር ተያይዞ መስተካከል ያለባቸው ህግጋትንና አፈፃፀማቸውን ከሴቶች በላይ የሚያውቅ ስለሌለ እንደሆነም ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሴቶችን በፖለቲካውም ሆነ በምርጫ እንዲሳተፉ ምርጫ ለማድረግ መዋቅራዊና ተቋማዊ ለውጦችን ማምጣት እንደሚያስፈልግ በርካቶች ይናገራሉ። የሴቶችን ድርብርቦሽ የስራ ጫና ከመቀነስ ጀምሮ፣ በማህበረሰቡ ላይ ግንዛቤን መፍጠር እንዲሁም ፓርቲዎች አቃፊ እንዲሆኑ ማስቻል ከሴት ፖለቲከኞች የሚነሱ ሃሳቦች ናቸው።