16 ሳምንታት አካባቢ በቀሩት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ፣ ምርጫውን በበላይነት የሚያስፈፅመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አንዳንድ ዝግቶቹን ማጠናቁን አስታውቋል።
የምርጫ ቦርዱ የምርጫው የጊዜ ሰሌዳን አስመልክቶ ባስቀመጠው መረጃ መሰረት ከታህሳስ 16-ጥር 16፣ 2013 ዓ.ም የምርጫ ክልል ቢሮዎችን መክፈት፣ እንዲሁም ከጥር 24- የካቲት 21 2013 ዓ.ም ለምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና ለመራጮች ምዝገባ የሚከናወን ይሆናል።
በዚህም የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የምርጫ ቢሮዎች ለመክፈት የሚያስፈልገው ትብብርን ማግኘት እንዳልቻለ ቅሬታውን አቅርቧል።
በአሁኑም ወቅት ለምርጫ ክልል እና ለዞን ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሊያገለግሉ የሚችሉ ቢሮዎችን አምስት ክልሎች ሙሉ በሙሉ ማሟላት አልተቻለም ብሏል። እነዚህም የተጠቀሱት ክልሎች አፋር፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፣ ሶማሌ ክልል ሲሆኑ እነዚህም ክልሎች የተጠየቁትን በሙሉ እስከ የካቲት 5፣ 2013 ዓ.ም ማጠናቀቅ አለባቸው ሲል አሳስቧል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ ጥር 10፣ 2013 ባወጣው መግለጫ ከክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች የሚያስፈልገው ትብብር ባለመሟላቱ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ለመክፈት ዝግጅት ማድረግ እንዳልቻለ ባስታወቀው መሰረት ከፍተኛ መሻሻሎች ታይተዋል ብሏል።
በዚህም መሰረት አዲስ አበባና ድሬዳዋ መስተዳድሮች፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ ሐረሪ ክልሎች ለምርጫ ክልልና ለዞን ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት የሚያስፈልጉትን ቢሮዎች በማዘጋጀት ለቦርዱ ማስታወቃቸው ተገልጿል።
በእነዚህ ቢሮዎችን ባሟሉ ቦታዎች የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው በሚያዘው መሰረት ከየካቲት 08-21፣ 2013 ዓ.ም የዕጩ ምዝገባ የሚካሄድ ሲሆን በቀሪዎቹ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ አሟልተው ሲያቀርቡ ምዝገባው እንደሚጀመር አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 28፣ 2013 ዓ.ም ለሚደረገው ምርጫ የመራጮች ትምህርት ለማስተማር ዕውቅና ለተሰጣቸው የሲቪል ማህበራት ሰርቲፊኬትና ተያያዥ ሰነዶችን መስጠት መጀመሩን አስታውቋል።
ምርጫ ቦርዱ የመራጮች ትምህርት ለሚያስተምሩ ሲቪል ማህበራት ዕውቅና ለመስጠት ባወጣው ጥሪ መሰረት መስፈርቱን የሚያሟሉ ሲቪል ማህበራትን በመገምገም ጥር 13፣ 2013 ዓ.ም ለ24 ሲቪል ማህበራት ዕውቅና መስጠቱን አስታውሷል።
ቦርዱ ከዚህም በተጨማሪ በሁለተኛው ዙር እንዲሁ ለተጨማሪ 47 ሲቪል ማህበራት እውቅና መስጠቱን አስታውቆ፣ ማህበራቱ ለ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ትምህርት ለማስተማር የሚያስፈልገውን ሰርቲፊኬትና ተያያዥ ሰነዶች እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል።
ከምርጫ ዝግጅት ጋር በተያያዘ የምርጫ ቦርዱ ለምርጫ ክልል ኃላፊዎች ለምርጫ ጣቢያ ሰራተኞችና በተለያየ ደረጃ ላሉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ለሁለት ቀናት ስልጠና መሰጠቱን እንዲሁ ገልጿል።
ስልጠናዎቹ ያካተቷቸው ርዕሶች የምርጫ የህግ ማዕቀፎች፣ የምርጫ ክልል ቢሮዎች ግዴታና ኃላፊነቶች፣ ለኮቪድ መከላከል ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎች፣ የምርጫ ቅሬታ አፈታቶች፣ የምርጫ ነክ ሎጂስቲክና ፀጥታ ሁኔታዎች ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ የስርዓተ ፆታና አካል ጉዳተኛ አካታችነት፣ የዕጩዎች ምዝገባ ሂደቶችን ጨምሮ ሌሎች ለምርጫው የሚያስፈልጉ አጀንዳዎች መካከል ናቸው።
ስልጠናው በቀጣይነት ለመሪ አሰልጣኞች የሚሰጥ መሆኑን አስታውሶ፣ እነዚህ መሪ አሰልጣኞች ደግሞ ወደተለያዩ ክልሎች በመሰማራት ምርጫ አስፈፃሚዎችን ያሰለጥናሉ ብሏል።
ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ መራጮች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታወቆ ነበር።
የኢትዮጵያ ምርጫ፡ ብርቱካን ሚደቅሳ ‘መንግሥት ምርጫውን እንዲታዘቡለት ለአውሮፓ ሕብረትና ለአሜሪካ ጥሪ አቅርቧል’
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በመጪው ምርጫ በርካታ ዓለም አቀፍና ሃገራዊ ታዛቢዎች ሊሳተፊ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ሰብሳቢዋ፤ መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ቻትሃም የተሰኘው ገለልተኛ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተቋም በመጪው የኢትዮጵያ ምርጫ ዙሪያ ባዘጋጀው የበይነ መረብ ውይይት ላይ ይህን ያሳወቁት።
በውይይቱ ላይ የቦርዱ ሰብሳቢን ጨምሮ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ [ዶ/ር]፣ የኢትዮጵያ ማሕበራዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር በየነ ጴጥሮስ [ፕ/ር] እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ ፓርቲ፤ ኢዜማ ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋ [ፕ/ር] ተሳትፈዋል።
ብርቱካን ታዛቢዎችን መጋበዝ የቦርዱ ሥራ ባይሆንም መንግሥት ግን ከኮቪድ-19 በፊት ሊካሄድ ታስቦ በነበረው ሃገራዊ ምርጫ ላይ በታዛቢነት እንዲሳተፉለት ለዩናይትድ ስቴትስና ለአውሮፓ ሕብረት ጥሪ አቅርቦ እንደነበር አሳውቀዋል።
በመጪው ግንቦት መገባደጃ ሊካሄድ በታሰበው ምርጫ ላይ በተሳታፊነት ለመሳተፍ ከ170 በላይ የሲቪክ ማሕበራት ማመልከቻ ማስገባታቸውንም ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል።
በቀጣዩ ወር የካቲት 8/2013 ቦርዱ ዕጩዎችን መመዝገብ እንደሚጀምር ያሳወቁት ብርቱካን፤ የመራጮች ምዝገባ የሚከናወን ፓርቲዎች ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት መሆኑን አክለዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች ‘ቅስቀሳና የመራጮች ምዝገባ እንድ ላይ መሆኑ አይጋጭም ወይ?’ ተብለው የተጠየቁት የቦርዱ ሰብሳቢ፤ “እንደውም ይህ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ምርጫዎች በተለየ መልኩ መራጮች የፓርቲዎችን ቅስቀሳ ታከው ለመመዝገብ እንዲበረታቱ ያደርጋል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ከውይይቱ አዘጋጆች ቀጣዩ ምርጫ ለፓርቲዎች እንዲሁም ለመገናኛ ብዙሃን የተስተካከለ መድረክ ይኖረዋል ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ብርቱካን “ይሄንን ለማሳካት የሁሉም አካላት [ፓርቲዎችና መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ] አብሮ መሥራት አስፈላጊነቱ ባያጠራጥርም ቦርዳችን ግን ይህን ለማሳካት እየጣረ ነው” ብለዋል።
“መጪው ምርጫ እስካሁን ከታዩት በላቀ ዴሞክራሲያዊ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ” ያሉት ደግሞ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ናቸው።
“ምንም እንኳ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሙን ብንጠብቅም ቀጣዩ ምርጫ እስካዛሬ ኢትዮጵያ ካከናወነቻቸው ምርጫዎች በተሻለ ፍትሐዊና ነፃ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ” ብለዋል።
ትግራይ ክልል
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጦርነት በተከሰተበት የትግራይ ክልል በግንቦት ወር የሚካሄደው ሃገር አቀፍ ምርጫ እንደማይካሄድ ማሳወቁ አይዘነጋም። ቦርዱ፤ ትግራይ ክልልን በተመለከተም የሁኔታዎች አመቺነት ታይቶ የጊዜ ሠሌዳ እንደሚወጣለት ማስታወቁ ይታወሳል።
ይህን በተመለከተ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ “በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት በመጪው ምርጫ ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል ብዬ አላስብም” ሲሉ መልሰዋል።
ዐቃቤ ሕጉ አክለውም “በሃገር አቀፍ ደረጃ ምርጫው ከተካሄደ በኋላ በትግራይ ክልል ምርጫው ጥቂት ወራት ዘግይቶ ቢካሄድ ችግር አይኖረውም” ብለዋል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በትግራይ ክልል ላይ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተነሳ በኋላ በክልሉ ምርጫ ሊካሄድ እንሚችል ጠቁመዋል።
በእሥር ላይ ያሉ ፖለቲከኞች
ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ከተሰነዘሩ ጥያቄዎች መካከል አንደኛው “ለውጡ በትክክለኛ ጎዳና ላይ ነው ብለው ያምናሉ ወይ?” የሚለው ነበር።
ዐቃቤ ሕግ ጌደዮን [ዶ/ር] “አዎ! ለውጡ አሁንም በትክክለኛ መንገድ ላይ ነው ብዬ አምናሉ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
አሁን በእሥር ላይ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በሚመለከት ከተሳታፊዎች ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ተሰንዝሯል። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጌድዮን [ዶ/ር] “በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እሥር ላይ አይደለም የሚገኙት። እንደውም ከዚህ በፊት ሕጋዊ አይደሉም ተብለው የተፈረጁ እንደ ኦነግ፣ ኦብነግ እና ግንቦት 7 የመሳሰሉ ፓርቲዎች ሃገር ቤት ገብተው እንዲሳተፉ ሆኗል” ብለዋል።
“ግጭት የሚያነሳሱ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በምርጫው ላይ እንዲሳተፉ በማለት ብቻ ከሕግ ጥላ ውጭ ይሁኑ ማለት ግን ለቀውስ በር መክፈት ነው” ሲሉ ዐቃቤ ሕጉ አክለዋል።
የውይይቱ እንግዶች
የውይይቱ ተጋባዥ እንግዶች ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት የኢትዮጵያ ማሕበራዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር በየነ ጴጥሮስ [ፕ/ር] የዘንድሮው ምርጫ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት በተነፃፃሪ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ነገር ግን የምርጫ ሕጉን በተመለከተ መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች እንዳሉ አንስተዋል።
ጉምቱው ፖለቲከኛ በየነ ጵጥሮስ [ፕ/ር] ሁሉን አሳታፊ የሆነ ሃገር አቀፍ የውይይት መድረከ እንዲዘጋጅ ጥሩ አቅርበዋል። ነገር ግን አሁን ላይ በቂ የሆኑ መድረኮች የሉም በማለት ምርጫውን ማራዘም እንደማይገባ ተናግረዋል።
አክለውም ሕገ-መንግሥቱ ማሻሻያ እንደሚያሻው ቢናገሩም ወደ ዝርዝር ከመግባት ተቆጥበዋል።
ፕሮፌሰር በየነ ቀጣዩ ምርጫ የተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ወደ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የሚገቡበት እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው አሳውቀው ከምርጫው በኋላ ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት [Government of National Unity] ሊመሠረት ይገባል የሚል ሐሳብ አቅርበዋል።
ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ ፓርቲ፤ ኢዜማ ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋ [ፕ/ር] ቀጣዩ ምርጫ ከፓርቲያቸው በላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ፓርቲያቸው ኢዜማ ነፃ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ የበኩሉን እንዲመወጣ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በቀጣይ ግንቦት ከሚካሄደው ምርጫ በላይ ለዘላቂ ብሔራዊ መግባባት ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
1997 በተደረገው ምርጫ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው የተመረጡት ኋላም ለ21 ወራት ያክል ለእሥር የተዳረጉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ‘ከ97ቱ ምርጫ ብዙ ሊማር ይገባል’ ሲሉ ተደምጠዋል።
አክለው ኢትዮጵያ ቀጣዩን ምርጫ በድል ካጠናቀቀች አንድምታው ከቀጣናው አልፎ በአህጉሪቱ ሊናኝ ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከውይይቱ አዘጋጆችና ተሳታፊዎች ለቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ የቀረቡ አንዳንድ ጥያቄዎች በግንኙነት መስመር ጥራት ምክንያት ምላሽ ሳያገኙ ቀርተዋል።
6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች እንዲሁም የትግራይ ክልል በቀር በመላ ሃገሪቱ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚደረግ ይጠበቃል።
የአዲስ አበባ እና የድሬደዋ ከተማ መስተዳደሮች ድምፅ መስጫ ቀን ሰኔ 05/2013 ዓ.ም እንደሆነ ቦርዱ ማሳወቁ አይዘነጋም።