“ቤተሰቦቼ እኔን ለማግባት ለሚቀርብ የትዳር ጥያቄ እምቢ እንዳልል ነገሩኝ፤ ምክንያቱም ሊያገባኝ የሚፈልገው ግለሰብ ከሀብታም ቤተሰብ የተገኘ ስለሆነ” ትላለች የ14 ዓመቷ አበባ።

ከጥቂት ወራት በፊት እናቷ እና ወንድም እህቶቿ የትዳር ጥያቄውን እንድትቀበል ከፍተኛ ጫና ያደርሱባት የነበረ ሲሆን፤ ቶሎ አግብታ በኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የገንዘብ እጥረት ያጋጠመውን ቤተሰብ እንድትረዳ ይፈልጉ ነበር።

አበባ ዶክተር መሆን ትፈልጋለች። ነገር ግን በትውልድ ከተማዋ ደቡብ ጎንደር የመማር ተስፋዋ የመነመነ ነው።

ራቢ ደግሞ የ16 ዓመት ታዳጊ ስትሆን ናይጄሪያ በሚገኘው ጋሳዉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቷን እየተከታተለች ነው። ነገር ግን በጣም የምትቀርባቸው አራት ጓደኞቿ በኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ትዳር መስርተዋል። እናቷ ደግሞ እሷም ማግባት እንዳለባት ታስባለች።

“ሁለት የጎረቤቶቻችን ታዳጊ ሴቶች በሚቀጥለው ሳምንት ያገባሉ፤ እንደ ፈጣሪ ፈቃድ። የእኔም ተራ እንዲህ በቶሎ ይደርሳል ብዬ አልጠበኩም ነበር” ትላለች ራቢ ስጋት ውስጥ ሆና።

ይህን መሰል በቤተሰብ ግፊት የሚፈጸሙ ጋብቻዎች የተለመዱ ነገሮች ናቸው።

በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ተጨማሪ 10 ሚሊየን ታዳጊ ሴቶች ሊዳሩ እንደሚችሉና የኮሮረናቫይረስ ወረርሽኝ ደግሞ ነገሮችን ሊያባብስ እንደሚችል ዩኒሴፍ በቅርቡ የሰራው ጥናት ያሳያል።

ዩኒሴፍ እንደሚለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት እንኳን በሚቀጥሉት አስር ዓመታት 100 ሚሊየን ታዳጊ ሴቶች ወደ ትዳር ተገደው ሊገቡ እንደሚችሉ ተገምቷል።

ነገር ግን አሁን ይህ ቁጥር ጨምሯል። ከተገመተው በላይ ሆነ 10 በመቶ ጭማሪም አሳይቷል።

በመላው ዓለም ወረርሽኙን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በመስተጓጎላቸውና የበርካታ ቤተሰቦች የገቢ ምንጭ በመጎዳቱ ምክንያት ተጨማሪ 10 ሚሊየን ታዳጊ ሴቶች ለአቅመ ሄዋን ሳይደርሱ እስከ 2030 ድረስ ተገደው ትዳር ይመሰርታሉ ይላል የዩኒሴፍ ጥናት።

“ይህ መረጃ የሚያሳየው ዓለማችን ምን ያክል ለታዳጊ ሴቶች አስቸጋሪ እየሆነች መምጣቷን ነው” ይላሉ የዩኒሴፍ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መከላከል አማካሪ የሆኑት ናንካሊ ማስኩድ።

“ወላጆች ትዳር ከማሰባቸው በፊት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ነው ያለባቸው” ትላለች አበባ።

ይህች ታዳጊ ኢትዮጵያዊት ከተዘጋጀላት የትዳር መንገድ ማምለጥ ችላለች። ምክንያቱ ደግሞ አባቷን ማሳመን በመቻሏ ነበር። “እናቴና ወንድሞቼ እንዳገባ በጣም ይገፋፉኝ ነበር። መጨረሻ ላይ የአካባቢው ኃላፊዎች ምክር ከሰጧቸው በኋላ ሃሳባቸውን ቀየሩ።”

ለራቢ ግን [ትክክለኛ ስሟ አይደለም፤ ምስሏም እንዲታይ አትፈልግም] አደጋው አሁንም እንዳለ ነው። በግብርና በሚታወቅ ጋምባ በሚባል አካባቢ ነው የምትኖረው። በዚህ አካባቢ ታዳጊ ሴቶች ቶሎ እንዲያገቡ ይደረጋል።

“ሁሉም ነገር የጀመረው በወረርሽኙ ምክንያት እንቅስቃሴ ሲገሰደብ ነው። ታናናሽ ወንድሞቼ ቃላትን የመጻፍ ጨዋታ ሲጫወቱ አብሬያቸው መጫወት ጀመርኩኝ” ትላለች የ16 ዓመቷ ራቢ።

“ጨዋታው ትንሽ ከበደኝ። እናቴ ደግሞ በጣም ተበሳጨች። ይሄን ሁሉ ጊዜ ትምሀርት ቤት ስትሄጂ ጊዜሽን ዝም ብለሽ ነው ያባከንሽው። ታናናሽ ወንድሞችሽ ከአንቺ የተሻሉ ናቸው” አለችኝ። እናቷ በዚህ አላበቁም ነበር።

“እስካሁን የአብረውሽ የሚማሩት ሴቶች በሙሉ አግብተዋል። ለሻፊዩ (ራቢን ሊያገባ የሚፈልገው ግለሰብ) ሊያገባሽ እንደሚፈልግ በይፋ በቤተሰቦቹ በኩል ለትዳር መጠየቅ አለበት” አለች።

ጓደኞቿ ሀቢባ፣ ማንሱራ፣ አስማው እና ራሊያ ባለፉት ወራት ውስጥ ሁሉም ትዳር መስርተዋል። ዋነኛ ምክንያታቸው ደግሞ በወረርሸኙ ምክንያት ጫና የደረሰበትን ቤተሰባቸውን ለመርዳት ነው።

አንዲት የራቢ እናት ጎረቤት ለምን ታዳጊ ሴቶች ቶሎ ማግባት እንደማይፈልጉ አይገባኝም ትላለች። “ወላጆች ምንድነው የሚጠብቁት? ለልጆቼ በሙሉ የትምህርት ወጪ መክፈል አልችልም። ትዳር ደግሞ የተረጋጋ ህይወት ለመምራት ወሳኝ ነው። በተጨማሪ ደግሞ ሴቶቹ አግብተው ሲወጡ በቤተ ውስጥ ትንሽ ሰው ይኖራል” ትላለች።

ከአውሮፓውያኑ 2011 ጀምሮ ያለእድሜያቸውና ያለፍላጎታቸው የሚያገቡ ታዳጊ ሴቶች ቁጥር 15 በመቶ መቀነስ አሳይቶ የነበረ ሲሆን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ግን ይህን መሻሻል ወደኋላ እንዳይመልሰው ስጋት አለኝ ብሏል ዩኒሴፍ።

“በዓለም አቀፍ ደረጃ የታዳጊዎች ትዳርን በተመለከተ ብዙ መሻሻሎችን እያየን ነው። ከነጭራሹ ለማጥፋት ካስመጥነው እቅድ አንጻር ብዙ ቢቀረንም በትክክለኛው መንገድ ላይ እንዳለን ግን እናምናለን” ይላሉ ናንካሊ ማስኩድ።

“ነገር ግን ኮቪድ-19 ነገሮችን በሙሉ አበለሻሽቶብናል። በመላው ዓለም የሚኖሩ ታዳጊ ሴቶች በሙሉ ህይወታቸው ከባድ ሆኗል።”

በዩኒሴፍ ሪፖርት ላይ በጎ የሚባሉ ነገሮችም ተስተውለዋል። ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው ሰዎች ጣልቃ የሚገቡ ከሆነ የታዳጊ ሴቶችን ወደ ትዳር መግባት በከፍተኛ ሁኔታ መከላከልና መቀነስ ይቻላል።

ምንም እንኳን ያለእድሜ ጋብቻ በአንዳንድ የዓለማችን አካባቢዎች በጣም የተለመደ ነገር ቢሆንም ትክክለኛው እርምጃ በሚወሰድባቸው ቦታዎች ግን ክስተቱ በጣም የቀነሰ ነው።

“ዘጠኝ የትዳር ጥያቄዎች ቀርበውልኛል”

“ከ14 ዓመቴ ጀምሮ በተለይ ከወረርሽኙ በኋላ ዘጠኝ የእናግባሽ ጥያቄዎች ቀርበውልኝ ነበር” ትላለች ማራም። ከጥቂት ዓመታት በፊት ከሶሪያ ተሰዳ ወደ ዮርዳኖስ የመጣች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በዛታሪ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ነው የምትኖረው።

”ከማኅበረሰቡ ከፍተኛ ጫና የነበረ ቢሆንም እናትና አባቴ ግን ሁሌም ከጎኔ ናቸው” ትላለች።

“እናቴ በጣም ነው የምትደግፈኝ፤ ሁሌም ቢሆን ገና ልጅ እንደሆንኩኝና ስለትዳር ምንም የማውቀው ነገር እንደሌለ ነው የምትነግረኝ።”

ማራም ትምህርት ቤት ሄዳ ለመማርና ኳስ ለመጫወት ችላለች።

“ካገቡ በኋላ ትምህርታቸውን ያቋረጡ በርካታ ሴቶችን አውቃለው። ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ከባሎቻቸው ጋር ይሄዳሉ። እነዚህ ታዳጊ ሴቶች እንዲህ አይነት ትልቅ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ገና ልጆች ናቸው።”

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት በትክክለኛው ጊዜ ማኅበራዊ ግንዛቤ መፍጠር ከተቻለ ያለእድሜ ጋብቻን መቆጣጠር ይቻላል።

“ለዚህ ትልቅ ምሳሌ መሆን የምትችለው ሕንድ ነች። ባለፉት 30 ዓመታት የሕንድ መንግሥት በርካታ ቤተሰቦች የገንዘብ ክፍያ ፕሮግራም ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ አድርጓል” ይላሉ ናንካሊ ማክሱድ።

በዚህ ምክንያት የሕንድ መንግሥት ለበርካታ ቤተሰቦች ታዳጊ ሴት ልጆቻቸውን እንዳይድሩ ለማድረግ ማበረታቻ ክፍያ ፈጽሟል። በተጨማሪም ጋብቻውን ማስቀረት ካልተቻለ ደግሞ ቢያንስ ለማራዘም ይሞከራል።

“ይሄ በጣም ወሳኝ ነገር ነው። ሌላው ቢቀር ታዳጊ ሴቶች ትምህርታቸውን የመጨረስ እድል ይኖራቸዋል። በተጨማሪም ሌሎች እውቀቶችን አዳብረውና በራስ መተማመናቸው ጨምሮ ነው ወደ ትዳር የሚገቡት።”

የዩኒሴፍ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አማካሪ የሆኑት ናንካሊ ማክሱድ እንደሚሉት በኮቪድ-19 ምክንያት እየጨመረ የመጣውን የታዳጊዎች ወደ ትዳር መግባት ለመቀነስ ሦስት ወሳኝ ነገሮች አሉ።

“በመጀመሪያ ሴቶቹ ደኅንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ማድረግ አልያም እንደ ንግድና የእጅ ጥበብ ሥራዎች አይነት ክህሎታዎችን እንዲያዳብሩ ማድረግ ወሳኝ ነው።”

“በተጨማሪ ደግሞ በወረርሽኙ ምክንያት በደሀ ቤተሰቦች ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ የተለያዩ ፕሮግራሞችን መቅረጽ። ይህ ሲሆን ቤተሰቦች ለገንዘብ ብለው ልጆቻቸውን መዳር ያቆማሉ” ብለዋል።

አክለውም በአስራዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ታዳጊዎች ማርገዝ በራሱ በቶሎ ወደ ትዳር እንዲገቡ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል አንደኛው ነው ይላሉ።

“የማኅበረሰብ ጤና እና የሥነ ተዋልዶ ትምህርት ለታዳጊ ሴቶች በአግባቡ ሊሰጣቸው ይገባል። ትክክለኛው ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ሁሉም መረጃ ሊቀርብላቸው ይገባል።”

ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ አበባ ጓደኞቿ በሙሉ ከትዳር በፊት ትምህርታቸውን ጨርሰው እንደሚመረቁ ተስፋ ታደርጋለች። ሌላኛዋ መቅደስ ደግሞ ወደፊት ኢንጂነር የመሆን ሕልም አላት።

“የእንቅስቃሴ ገደቡ ታውጆ በቤት ውስጥ እያጠናን እያለ ወላጆቼ ለአንድ ሰው እኔን ስለመዳር ሲያወሩ ሰማኋለቸው። ልጁን ከነጭራሹ አላውቀውም” ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች።

“ማግባት እንደማልፈልግና ትምህርቴን መጨረስ እንደምፈልግ ስነግራቸው ሊሰሙኝ ፈቃደኝ አልነበሩም።”

“ትምህርት ቤታችን እስከሚከፈት ድረስ ጠበኩቅና ለትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ነገርኩት” ትላለች መቅደስ። “ወዲያው አካባቢውን ኃላፊዎች አሳወቀ፤ እነሱም መጥተው ከቤተሰቦቼ ጋር ተነጋገሩ።”

አሁን ላይ ቤተሰቦቿ ከ18 ዓመቷ በፊት እንደማይድሯት ቃል ገብተዋል።

“የምክር አገልግሎቱ በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ በጣም እየጠቀመን ነው። ሌላው ቀርቶ ወላጆች እምቢ ብለው ልጆቻቸውን ለመዳር የሚያስቡ ከሆነ ጉዳዩ በፖሊስ በኩል እንዲያዝ ይደረጋል።”

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *