በትግራይ ግጭት የተሳተፉ አካላት “የጦር እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ፈጽመው ሊሆን እንደሚችል” የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሸል ባሽሌት ገለጹ።

ኮሚሽነሯ ከትግራይ የሚወጡ ተያያዢነት ያላቸውና ተአማኒ ሪፖርቶች በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ የተለያዩ ወገኖች የተፈፀሙ ከባድ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊ እርዳታ ሕጎች ጥሰት ማመልከታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉትንና እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ሪፖርት የተደረጉ የጅምላ ግድያዎችን፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ወሲባዊ ጥቃቶችን ለመመርመር እንዲችል ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ሚሸል ባሽሌት የተፈፀሙት የመብት ጥሰቶች እንደ ጦር እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ሊቆጠሩ እንደሚችሉ ገልፀው በዚህም ውስጥ የተለያዩ አካላት ተሳታፊ ሳይሆኑ እንዳልቀረ ጠቁመዋል።

በተጠቀሱት ድርጊቶች ውስጥ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይችላል ያሏቸውን አካላት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ህወሓት፣ የኤርትራ ወታደሮች፣ የአማራ ክልል ኃይሎችና ግንኙነት ያላቸው ታጣቂ ሚሊሻዎች ናቸው ብለዋል።

“በግጭቱ ላይ በርካታ አካላት መሳተፋቸውን ጨምሮ፤ ጥሰቶቹን መካድ እንዲሁም ጣት መጠቆም ይታያል። የጥሰቶቹን ሪፖርት በተመለከተ ግልፅ፣ ነፃ የሆነ ግምገማና ምርመራ ያስፈልጋል። የጥቃቱ ሰለባና ተራፊዎች የእውነትና የፍትህ ጥያቄያቸው ሊካድ አይገባም” ብለዋል ኮሚሽነሯ።

አክለውም “የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ቢሮና ሌሎች ነፃ መርማሪዎች ወደ ትግራይ ገብተው ያለውን ሁኔታ እንዲገመግሙና እንዲመረምሩ ፍቃድ እንዲሰጠን እንጠይቃለን። የትኛውም አካል ይፈፅመው እውነታው መታወቅ አለበት፤ ፈጻሚዎቹም ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚሽነሯ ሚሸል ባሽሌት በአሁኑ ወቅት “የሚረብሹ” ያሏቸው የመደፈር፣ የዘፈቀደ ግድያ፣ መጠነ ሰፊ የንብረት ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እየደረሳቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

“በክልሉ ተዓማኒ የሚባሉ ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት የሚጥሱ ሪፖርቶች በግጭቱ ተሳታፊ በሆኑ አካላት በሙሉ መፈፀማቸውን የሚገልጽ መረጃ ደርሶናል” ብለዋል።

አክለውም “ግልጽና ነፃ ምርመራ ካልተካሄደና ጥሰቱን የፈፀሙትን አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ካልተቻለ እነዚህ ጥቃቶች ሊቀጥሉ እንደሚችሉ እፈራለሁ። ሁኔታውም ባልተረጋጋ መልኩ ለዓመታት ሊቀጥል ይችላል” ብለዋል።

ኮሚሽነሯ ከአስተማማኝ ምንጭ ነው ያገኘሁት ባሉት መረጃ መሰረት በአዲግራት፣ በመቀለ፣ በሽረና በውቅሮ በተነሳው ተቃውሞ ስምንት ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል ብለዋል።

በተጨማሪም በትግራይ ምሥራቃዊ ክፍል በሚገኙት በመቀለ፣ በአይደር፣ በአዲግራትና በውቅሮ በአንድ ወር ብቻ 136 ወሲባዊ ጥቃቶች ሪፖርት መደረጋቸውን ገልፀው፣ ይህም ከዚህ በላይ በርካታ ጥቃቶች መድረሳቸውን ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ እነዚህ ጥቃቶች መድረሳቸውን አረጋግጦ ምርመራ ከፍቻለሁ ማለቱ የሚታወስ ነው።

በተጨማሪም በቅርቡ ሂውማን ራይትስ ዋች፣ በትግራይ ከተሞች በኅዳር ወር በዘፈቀደ የከባድ መሣሪያ ድብደባ ደርሷል ያለውን መረጃ እንዳገኙና ማረጋገጥ መቻላቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአክሱም፣ ደንገላትና በማዕከላዊ ትግራይ በኤርትራ ጦር የተፈፀሙ ግድያዎችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተም እንዲሁ ማረጋገጣቸውን አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ ታስረው የተፈቱትን የቢቢሲ ጋዜጠኛን ጨምሮ ሌሎች ዘጋቢዎችና ተርጓሚዎችን በተመለከተ ያላቸውን ስጋትም ገልጸዋል።

ምንም እንኳን ጋዜጠኞቹ በአሁኑ ሰዓት ያለ ክስ ቢለቀቁም አንድ የመንግሥት ባለስልጣን “ዓለም አቀፉን ሚዲያ የሚያሳስቱ ግለሰቦችን ተጠያቂ ይሆናሉ” ማለታቸው እንዳሳሰባቸውም ገልፀዋል።

“የሰብዓዊ መብት ጥቃት ሰለባዎችና የዓይን እማኞች ጉዳት ሊደርስብን ይችላል በሚል ፍራቻ ሊገደቡ አይገባም” ብለዋል ከፍተኛ ኮሚሽነሯ።

ባሽሌት በዛሬው መግለጫቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብዓዊ ረድዔት ድርጅቶች የሰጠውን ፈቃድ እንዲሁም አንዳንድ እርምጃዎቹን በመልካም ጎን አነንስተዋል።

በተጨማሪም ባለስልጣናቱ የገቡትን ቃል ወደ ተግባር እንዲለወጡ ጠይቀዋል።

የእራሳቸው ቢሮም በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚደረጉ ምርመራዎችን ይደግፋል ብለዋል።

በትናንትናው ዕለትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከትግራይ ክልል ግጭት ጋር በተያያዘ የተነሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ግድያዎችን በተመለከተም መንግሥት ከፌደራል ፖሊስ፣ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ከሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመጣመር ይመረምራል ብለዋል።

ጨምረውም የእነዚህን አካላት ምርመራ መሰረት በማድረግም መንግሥታቸው በድረጊቱ ውስጥ እጃቸው ያለበትን አካላት ወደ ፍትህ እንደሚያቀርብ አፅንኦት ሰጥተው፤ በምርመራው ላይ ተጨማሪ እርዳታ ካስፈለገ መንግሥት የውጭ አካል ሊጋብዝ እንደሚችል ጠቆም አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናትና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሚያደርጉት ምርመራ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም ሕዝብ በወቅቱ እንደሚያሳውቁ ጨምረው ቃለ አቀባዩ ገልፀዋል።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት በመፈፀሙ መንግሥት “ሕግ የማስከበር” ወታደራዊ ዘመቻን ማካሄዱን ገልጿል።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን ቢገልጽም በአንዳንድ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ወታደራዊ ግጭቶች እንዳሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ከፍተኛ ኮሚሽነሯም በአሁኑ ወቅት በማዕከላዊ ትግራይ ጦርነቱ መቀጠሉንም መረጃ እንደደረሳቸው አስታውቀዋል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *