በየመኗ ዋና ከተማ ሰንዓ በርካታ ኢትዮጵያውያን በነበሩበት አንድ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በተነሳ እሳት በርካቶች መሞታቸው ተነገረ።

በርካታ ከአፍሪካ ቀንድ በተለይም ከኢትዮጵያ የሄዱ ስደተኞች በተጠለሉበት በዚህ ስፍራ የተነሳው እሳት 30 ሰዎችን ሲገድል 170 ሰዎች ደግሞ ተጎድተዋል ሲል ዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም (አይኦኤም} ገልጿል።

የእሳት አደጋው የተነሳው የሁቲ ታጣቂዎች በሚሳዔልና ድሮን ሳዑዲ አራቢያ ውስጥ ያለ የነዳጅ ማከማቻ መምታቸውን ተከትሎ ሳዑዲ መራሹ ኃይል በሰንዓ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ነው።

የእሳት አደጋው ከመድረሱ በፊት መጠለያ ጣቢያው በጦርነቱ ሳቢያ ምስቅልቅሉ ወጥቶ እንደነበር ተነግሯል።

ከስደተኞቹ በተጨማሪ የመጠለያው ጠባቂዎችም በአደጋው ከሞቱ መካከል ናቸው።

የአይኦኤም የመካከለኛው ምሥራቅና ሠሜን አሜሪካ ተወካይ የሆኑት ካርሜላ ጎዴ የድርጅቱ ሠራተኞች ከ170 በላይ ለሆኑ በእሣት አደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች እርዳታ እያደረጉ እንደሆነ በትዊተር ገፃቸው አሳውቀዋል።

አደጋ ከደረሰባቸው 170 ሰዎች መካከል 90 ያክሉ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ካርሜላ ጽፈዋል።

የእሳት አደጋው መንስዔ እስካሁን ባይታወቅም የሳዑዲ መራሹ ኃይል ያደረሰው ጥቃት በአካባቢው ባሉ ሕንፃዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ ከተነገረ በኋላ መሆኑ ተገልጿል።

የእሳት አደጋውን በተመለከ የሁቲ ታጣቂዎች ባወጡት መግለጫ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅትና የተባበሩት መንግሥታት ለስደተኞቹ መኖሪያ ባለማቅረብ እና ከየመን እንዲወጡ ለማድረግ ባለመተባበራቸው ለደረሰው አደጋ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል።

ትናንት እሁድ በስደተኞቹ መጠለያ ውስጥ በደረሰው የእሳት አደጋ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ተሰግተወል።

አይኦኤም እንደሚገምተው በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተጣለውን የመንቀሳቀስ ገደብ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች የመን ውስጥ ወደየትም መሄድ ሳይችሉ እየተጉላሉ ነው።

ምንም እንኳ የመን ማብቂያ ባላገኘ ጦርነት ውስጥ ብትሆንም በተለይ ደግሞ መነሻቸው ከአፍሪካ ቀንድ የሆኑ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ድንበሯን እያቋረጡ ወደ ጎረቤት አገር ሳዑዲ አራቢያ ለመግባት በመፍለስ ላይ ናቸው።

የመን ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ ድንበሯን በመዝጋቷ አብዛኞቹ ስደተኞች በጦርነት፣ በረሃብና በበሽታ እየተሰቃዩ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይገኛሉ።

የመን ውስጥ በሳዑዲ መራሹ ኃይልና በኢራን በሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች መካከል ስድስት ዓመት የሆነውና አሁንም እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከስደተኞቹ በተጨማሪ የአገሪቱን ዜጎች ህይወት አመሰቃቅሎታል።

የመን ውስጥ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል 80 በመቶ ያህሉ እርዳታ ላይ ጥገኛ ሲሆኑ፤ በርካቶች አገራቸውን እየለቀቁ ጦርነቱን ሽሽት ይሰደዳሉ።

ምንድን ነው የተከሰተው?

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና በየመን ሰንዓ የእሳት አደጋ በደረሰበት ማቆያ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ስለእሳት አደጋው መንሰኤ ሲናገሩ “የተወረወረ የእጅ ቦንብ” ነው ይላሉ።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት [አይኦኤም] የየመን ቢሮ እንዳለው ለበርካታ ሰዎች ምክንያት የሆነው ቃጠሎ የደረሰበት ማዕከል በአገሪቱ መንግሥት የሚተዳደር ማቆያ ሲሆን አደጋው በደረሰበት ወቅት 700 ያህል ስደተኞች በውስጡ ነበሩ።

በወቅት በማቆያ ውስጥ የነበረ አንድ ስደተኛ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ እንዳለው ከእሳት አደጋው ቀደም ብሎ በማቆያው ጠባቂዎችና በስደተኞች መካከል አለመግባባት ነበር።

አለመግባባቱ ተባብሶ ስደተኞቹ ወደ አገራችን መልሱን ማለታቸውንና ካልሆነ ግን ምግብ እበላም በማለ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ይናገራል።

ይህ አለመግባበት ተካርሮ “ጠባቂዎቹ የማቆያውን በር ዘግተው ከውጪ የእጅ ቦንብ በመወርወር” አደጋው መፈጠሩን ለቢቢሲ አስረድቷል።

አደጋው በደረሰበት ወቅት በአካባቢው የነበረ ሌላ ኢትዮጵያዊ ስደተኛም ለደረሰው አደጋ ምክንያቱ “የተወረወረ የእጅ ቦንብ ነው” ብሏል።

ጨምሮም አደጋው ከደረሰበት ስፍራ የሟቾችን አስከሬን ካነሱ ሰዎች አረጋገጥኩ በማለት እንደተናገረው “እስከ ትናንት እኩለ ለሊት ድረስ 182 ሰዎች መሞታቸውን” ገልጿል።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ስደተኞች ሰንዓ ውስጥ ወዳሉ ትልልቅ የመንግሥት ሆስፒታሎች በአምቡላንስ መወሰዳቸውንም ጨምሮ ገልጿል።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በየመን እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ በችግር ላይ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ።

ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው ተገልጿል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እንዳለው ባለሥልጣናት ቢያንስ 14 ሺህ 500 የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን መሰረታዊ የጤና እና የንፁህ ውሃ አገልግሎት በማያገኙበት ሁኔታ እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ በከፋ ችግር ላይ እንዲወድቁ አድርገዋቸዋል።

አገሪቷ በወረርሽኙ ሳቢያ ድንበሮቿን በመዝጋቷ ስደተኞቹ ያለ ፈቃዳቸው ወደ አደን ፣ ማሪብ፣ ላህጅ እና ሳኣዳ እንዲሄዱ መገደዳቸውንና በእነዚህ ቦታዎች በአስከፊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ድርጅቱ አትቷል።
ስደተኞቹ ቫይረሱ እንዳለባቸው በማሰብም መገለልና እና ጥቃት እንደደረሰባቸው ድርጅቱ ገልጿል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በየመን የሚገኙ ስደተኞች የቃል እና አካላዊ ጥቃቶች እየደረሰባቸው፣ የእስር ጊዜያቸው እየጨመረ፣ የእንቅስቃሴ ገደብ እንዲሁም ያለፈቃዳቸው መሰረት ልማት በሌለባቸው አካባቢዎች እንዲሄዱ እየተገደዱ ነው።

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመጓዝ የመንን ያቋርጣሉ። በዚህ ዓመት ግን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር የተጣሉ ገደቦች ችግሩን የከፋ አድርጎታል።

ባለፈው ዓመት ከአፍሪካ ቀንድ አገራት፤ አብዛኞቹ ከኢትዮጵያ የሆኑ 138 ሺህ ስደተኞች ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለመግባት በማለም የመን መግባታቸውን ድርጅቱ አስታውሷል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *