በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በተመለከተ ከመገናኛ ብዙሃን ወይም በዙሪያዎ ካሉ ሰዎች ሰምተው ይሆናል።

ነገር ግን ይህች ዕለት ለምን እንደምትከበር? መቼ እንደምትከበር? ዕለቷስ ክብረ በዓል ወይስ የአመፅ ቀን ? በተመሳሳይስ ዓለም አቀፍ የወንዶች ቀን አለ? በዚህ ዓመትስ ምን አይነት ዝግቶች ይኖራሉ?

ለአስርት ዓመታት ያህል በዓለማችን የሚገኙ ሕዝቦች ማርች 8ን ለሴቶች ለየት ያለች ቀን እንደሆነች አድርገው ይመለከቷታል። ለምን?

እንዴት ተጀመረ?
የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ታሪካዊ መነሻዋን ያደረገችው የሠራተኞች አንቅስቃሴን ሲሆን በአሁኑ ወቅት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና የተሰጣት ዓመታዊ በዓል ለመሆን በቅታለች።

የክብረ በዓሏ ጅማሮ በአውሮፓውያኑ 1908 ነው። በወቅቱ 15 ሺህ የሚሆኑ ሴቶች በኒውዮርክ ከተማ ላይ የሥራ ሰዓት መሻሻል (ማጠር)፣ የተሻለ ክፍያና ሴቶች በምርጫ መሳተፍ አለባቸው በሚል የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ።

ከአንድ ዓመት በኋላም የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቱ የመጀመሪያዋን ብሔራዊ የሴቶች ቀን አወጀ።

ቀኗን ዓለም አቀፍ የማድረግ ሃሳቡ የመጣው ክላራ ዜትኪን በምትባል ግለሰብ አማካኝነት ነው።

በዴንማርኳ ኮፐንሃገን በአውሮፓውያኑ 1910 የሴት ሠራተኞች ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ነበር ሃሳቡን ያነሳችው።

በወቅቱ ከ17 አገራት የተውጣጡ 100 ሴቶች ተሳትፈውበት የነበረ ሲሆን በሃሳቧም ሙሉ በሙሉ ነው የተስማሙት።

ለመጀመሪያ ጊዜም በኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመንና ስዊዘርላንድ በአውሮፓውያኑ 1911 ተከበረች።

በዚህ ዓመትም ዛሬ 110ኛዋ የዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን እየተከበረ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፋዊ ሆና መከበር የጀመረችው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ክብረ በዓሏን ማክበር በጀመረባት በአውሮፓውያኑ 1975 ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ “የኋላውን ማክበር፤ የወደፊቱን ማቀድ” በሚል በተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መሪ ቃል በ1996 ነበረ በዓለም አቀፍ ደረጃ በደመቀ ሁኔታ የተከበረችው።

ዓለም አቀፏ የሴቶች ቀን የምትዘክረው ሴቶች በማኅረበሰቡ የደረሰባቸውን ጭቆናን ተቋቁመው በፖለቲካውና በምጣኔ ሀብቱ ያገኙትን ትሩፋት ትዘክራለች።

ክብረ በዓሏ መሰረቷ ፓለቲካዊ ዓመፅ ሲሆን በአሁንም ወቅት በዓለም ላይ የሰፈነውን የተዛባ የሥርዓተ-ፆታ ኃይል ሚዛንን ለማስተካከል በተለያዩ ሰልፎችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ትዘከራለች።

መቼ ትከበራለች?

በየዓመቱ ማርች 8 ወይም በዘንድሮው በኢትዮጵያ አቆጣጠር የካቲት 29/2013 ዓ.ም ትከበራለች። ክላራ በዓሏ በዓለም አቀፍነት ደረጃ እንድትከበር ሃሳብ ስታመነጭ የቆረጠችው ቀን አልነበረም።

በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት አካባቢ የሩሲያ ሴቶች “ዳቦና ሰላም” በሚል ሰልፍ አደረጉ። በወቅቱ የነበረው ንጉሣዊ ሥርዓት ስልጣን የለቀቀ ሲሆን ጊዜያዊ አስተዳዳሪውም ሴቶች በምርጫ እንዲሳተፉ ፈቀደ።

እነዚህ ሴቶች ተቃውሞ ያነሱባት ቀን በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ማርች (መጋቢት) 8 ዕለት ናት።

ዓለም አቀፍ የወንዶች ቀን የሚባል አለ?

አዎ አለ! ቀኑም የሚከበረው ኖቬምበር (ኅዳር) 19 ነው።

ዕለቱ መከበር የጀመረው ከአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ በኋላ ቢሆንም ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕውቅና የለውም።

በዓለም ላይ ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ በ80 አገራት ይከበራል።

ዕለቱም ወንዶች በዓለም ላይ ያመጧቸውን አዎንታዊ እሴቶች፣ ለቤተሰባቸውና ለማኅበረሰቡ እያደረጉት ያለውን አስተዋፅኦ ይዘክራል።

ከዚህም በተጨማሪ አርዓያ የሚሆኑ ወንዶችን ማሳየትና በወንዶች ጤንነት ላይም ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ነው።

ባለፈው ዓመትም “የተሻለ ጤና ለወንዶች ” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።

በዚህ ዓመት የሴቶች ቀን እንዴት እየተከበረች ነው?

በሩሲያ ዕለቷ ሶስት አራት ቀናት ሲቀራት የአበቦች ሽያጭ በዕጥፍ ይጨምራል።

በቻይና የአገሪቷ ምክር ቤት በሰጠው ምክር መሰረት ሴቶች በዚያች ቀን ግማሽ ቀን ብቻ እንዲሰሩና ግማሽ ቀን እንዲያርፉ ቢደረግም በርካታ አሰሪዎች ይህንን ሁልጊዜም አይከተሉትም ተብሏል።

በጣልያን ላ ፌስታ ዴላ ዶና ተብላ የምትጠራው ይህች ዕለት ሚሞሳ ተብላ የምትጠራውን አበባ ስጦታ በመለዋወጥ ያከብሯታል።

ይህ ባህል መነሻው ባይታወቅም ምናልባት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በሮም እንደተጀመረ ይታመናል።

በአሜሪካ ሙሉ የማርች (የመጋቢት) ወር የሴቶች ታሪክ ወር የሚል ዕውቅና ተሰጥቷል። በአገሪቱ መሪዎች ዘንድ ዕውቅና በተሰጣት በዚች ወርም የአሜሪካ ሴቶች አስተዋፅኦ ይዘከራል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ባጠላበት በዘንድሮው ዓመት ክብረ በዓሏ የምትታወሰው በበይነ መረብ በሚዘጋጁ ዝግጅቶች ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም በዚሁ መልክ ይዘክራታል ተብሏል።

የዘንድሮው የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በምን መሪ ቃል ትታወሳለች?

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳሳወቀው የዘንድሮው መሪ ቃል “ሴቶች በአመራር ቦታ፡ በእኩልነት የተሞላ የኮቪድ-19 ዓለምን ማሳካት” በሚል ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ፉምዚሌ ምላምቦ ንጉካ እንዳሉት “በተለያዩ ባህላዊ ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ መዋቅሮች የሴቶች ውክልና አስፈላጊ ነው። ሴቶች ችሎታቸውንና ልዩነታቸውን በሚያሳይ መልኩ በተገቢ መልኩ ሊወከሉ ይገባል። በዚህም ሁኔታ ነው ሴቶችን በውሳኔ ቦታ በማካተትና ሁላችንም የሚጠቅም ትክክለኛ ማኅበራዊ ለውጥን ማምጣት የምንችለው” ብለዋል።

ነገር ግን በተለያዩ አካባቢዎች ሌሎች መሪ ቃሎችም እየተጠቀሱ ነው።

“ሴቶች አዎንታዊ ለውጦችን እንዲያመጡ መድረክ አመቻቻለሁ” የሚለው የዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን ድረ-ገፅ በበኩሉ የመረጠው መሪ ቃል “ለመገዳደር እንምረጥ” የሚል ሲሆን ሰዎች እጃቸውን አንስተው መበላለጥን ለማውገዝ ቃል እንዲገቡ ጥሪ አቅርቧል።

ቀኗ ለምን ታስፈልገናለች?

“በሚቀጥለው ክፍለ ዘመን እንኳን የሥርዓተ-ፆታ ኃይል መዛባትን ማስተካከል አንችልም” ያሉት የዓለም አቀፍ ሴቶች ቀን ዘመቻ አንቀሳቃሽ ሲሆኑ ይህንንም ያሉት ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚክ ፎረምን በመጥቀስ ነው።

“እዚህ ያለነው ሁላችንም አይደለም መጪዎቹ ልጆቻችን ኢ-ፍትሃዊ የሆነው የሥርዓተ-ፆታ ተስተካክሎ ሊያዩት አይችሉም” ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ተቋም (ዩኤን ውሜን) ባወጣው መረጃ መሰረት የኮሮናቫይረስ ወረረሽኝ ሥርዓተ-ፆታ ላይ የተሰሩትን ሥራዎች ወደ ኋላ 25 ዓመታት የሚጎትት ነው ብለውታል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሴቶች ተደራራቢ የቤት ውስጥ ሥራ ጫናዎች በርክተውባቸዋል።

ልጆች የማሳደግና ቤተሰብ የመንከባከብ ኃላፊነቱም በእነሱ ጀርባ ላይ ወድቋል። ይህም ማለት በሥራም ይሁን በትምህርት ሊያገኙዋቸው የሚችሉ እድሎች ላይ ተፅእኖ ያሳርፋል።

ምንም እንኳን የኮሮናቫይረስ ወርርሽኝ ስጋቶች ቢኖሩም የዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በማስመልከት በርካታ ሰልፎች በተለያዩ አገራት ተካሂደዋል።

ምንም እንኳን አብዛኞቹ ሰላማዊ ቢሆኑም በኪርጊዝታን መዲና ቢሽኬክ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ በርካታ የሴት መብት ተሟጋቾች በቁጥጥር ስር ውለዋል።


ሁኔታውም የተፈጠረውም ጭምብል ያጠለቁ ወንዶች ሰልፈኞቹ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ነው።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንደሚሉት የሴቶች መብት ሁኔታ በአገሪቷ ወደ ከፋ ሁኔታ እያመራ ነው ይላሉ።

በፓኪስታን የጥቃት ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች ቢደርስባቸውም በርካታ ሴቶች በመላው አገሪቷ ሰልፍ አካሂደዋል።

በሜክሲኮ እየጨመረ የመጣውን የሴቶችን ጥቃት በማስመልከት 80 ሺህ ሴቶች ወደ አደባባዮች የወጡ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 60ዎቹ ተጎድተዋል ተብሏል።

ምንም እንኳን ሰልፉ በሰላማዊ ሁኔታ ቢጀመርም ፖሊስ እንደሚለው አንዳንድ ቡድኖች የነዳጅ ቦምብ መወርወራቸውን ተከትሎ ፖሊሶች አስለቃሽ ጋዝ መርጨታቸው ተዘግቧል።

ነገር ግን ባለፉት ዓመታት በሴቶች እንቅስቃሴ ላይ መልካም ነገሮችም ተመዝግበዋል።

አሜሪካ ጥቁርና እስያዊቷን ካማላ ሃሪስ የመጀመሪያዋ ሴት ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጋ ሾማለች።

በአውሮፓውያኑ 2019 ፊንላንድ በአምስት ሴቶች የሚመራ የጥምር መንግሥት መስርታለች። በሰሜን አየርላንድ ፅንስ ማቋረጥ ፈቃድ አግኝቷል። በሱዳን ሴቶች ምን መልበስ እንዳለባቸው የሚያዘው ሕግ ተወግዷል።

በአውሮፓውያኑ 2017 የተነሳውን ‘ሚቱ’ (እኔም) የሚለው እንቅስቃሴ እንዴት ይረሳል። በዓለም ላይ መደፈርና ፆታዊ ጥቃቶችን ተቀባይነት እንደሌላቸውና እንዲወገዙ አድርጓል።

በአሁኑም ወቅት የቀጠለው ዓለም አቀፉ እንቅስቃሴ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ተገቢ ያልሆኑና ተቀባይነት የሌላቸውን ባህርያት እያጋለጠ ይገኛል። በዚህ እንቅስቃሴም በርካታ እውቅና ያላቸውን ግለሰቦችም ወደ ክስ ማቅረብ ተችሏል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *