ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ተሳትፏቸው የጎላ እንዲሆን የፖሊሲ ክለሳ ለማድረግ ዕቅድ መኖሩ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው ዓርብ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የፖለቲካ አመራርና ሌሎች ተቋማት ተገኝተው በአያት ሬጀንሲ ሆቴል ባደረጉት ውይይት ላይ ነው፡፡
የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ወ/ሮ ፊልሰን አብዱላሂ እንደገለጹት፣ ሴቶች በሁሉም ቦታዎች ላይ እንዲሳተፉና ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ያለውን ፖሊሲ እንደ አዲስ ለመከለስ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው፡፡
ሴቶች በሁሉም ዘርፎች ላይ ተሳትፏቸው የላቀ እንዲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በተለያዩ ክልሎች ኮሚቴዎችን በማዋቀርና መዋቅሮችን በመዘርጋት፣ ያላቸውን አቅም እንዲጠቀሙ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ወ/ሮ ፊልሰን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ሲባል የፖሊሲ ክለሳ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሴቶች ጉዳይ ላይ እየተሠራ ያለው የሚበረታታ ቢሆንም፣ የሴት አመራሮችን ብቁ አድርጎ ወደ ተሻለ ደረጃ ከማድረስ አንፃር ግን ሰፊ የሆነ የቤት ሥራ የሚጠይቅ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በዘርፉ መንግሥትም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ያለባቸውን ኃላፊነት በመወጣት፣ ብቁ የሆኑ ዜጎችን ማፍራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ በየጊዜው በመገናኘት የመረጃ ልውውጦችን በማድረግ፣ እንዲሁም የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ከበፊት ጀምሮ ችግሩ የዱላ ቅብብል እየሆነ በመምጣቱ ምክንያት ሴቶች በፖለቲካ ጉዳዮችና በሌሎች ዘርፎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል ያሉት፣ የኢሕአፓ ሊቀመንበር ወ/ሮ ቆንጂት ብርሃን ናቸው፡፡
ይህም የሆነው ከመሠረቱ በሴቶች ላይ የወንዶች የበላይነት የሰፈነ በመሆኑ፣ አሁን ትልቅ ችግር ሊሆን እንደቻለ ወ/ሮ ቆንጂት አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግሥት እያደረገ ያለውን የሴቶች ተሳትፎ ንቅናቄ በመጠቀምና በማሳደግ፣ ሴቶች መራጭም ተመራጭም እንዲሆኑ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሴቶች በምርጫ እንዲሳተፉ፣ ፓርቲዎችም እንዲሳትፉ የሚያደርግ አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራሞቻቸውና የፆታ ፖሊሲዎቻቸው ላይ ጭምር መሥራት እንደሚያስፈልጋቸውም ተጠቁሟል፡፡