የዕጩዎች ምዝገባ እስከ የካቲት 30 ቀን ድረስ ተራዝሟል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስድስተኛውን አገራዊ ምርጫን ደኅንነት ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረጋቸው ውይይቶችና ንግግሮች መሠረት አብዛኛዎቹ የምርጫ ክልሎች ጥበቃ ሊሟላላቸው መቻሉን ጠቁሞ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሱማሌና በደቡብ ክልሎች 98 የምርጫ ክልሎች ጥበቃ ስላልተመደበላቸው በአስቸኳይ እንዲያሟሉላቸው አሳሰበ፡፡
ቦርዱ የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ጥበቃ ያልተመደበላቸው የምርጫ ክልል ቢሮዎች በኦሮሚያ ክልል 21 የምርጫ ክልሎች፣ በሶማሌ ክልል 31 የምርጫ ክልሎች፣ በአማራ ክልል 40 የምርጫ ክልሎችና በደቡብ ክልል ስድስት የምርጫ ክልሎች ጥበቃ አልተመደበላቸውም፡፡ በመሆኑም በአስቸኳይ ጥበቃ እንዲመደብላቸው አሳስቧል፡፡
ምርጫ ቦርድ ለስድስተኛው አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ 673 የምርጫ ክልሎችን በመክፈት የዕጩዎች ምዝገባን እያከናወነ መሆኑን አስታውሶ፣ የምርጫ ክልሎችን ደኅንነታቸውን የማስጠበቅ ኃላፊነት የክልልና የከተማ መስተዳድሮች መሆኑን አስታውቋል።
ቦርዱ በተለያዩ ጊዜያት የምርጫውን ደኅንነት ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይቶችና ንግግሮችን እያደረገ የቆየ መሆኑን፣ በዚህም መሠረት አብዛኞቹ የምርጫ ክልሎች ጥበቃ እንደተሟላላቸው ገልጿል።
ነገር ግን ከላይ በተገለጹት አራት ክልሎች 98 የምርጫ ክልሎች፣ አስፈላጊውን የደኅንነት ከለላ ከክልል መንግሥታቱ እያገኙ አለመሆናቸውን አስረድቷል፡፡
ቦርዱ ክልሎች በአስቸኳይ ለቀሪ የምርጫ ክልል ቢሮዎች የጥበቃ ምደባ እንዲያከናውኑ አሳስቦ፣ ሳይመድብ ቀርቶ በጥበቃ አለመኖር ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ የምርጫ አፈጻጸም ችግሮች ቢያጋጥሙ የክልሎቹ መስተዳድሮችና የፀጥታ አካላት ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ አስገንዝቧል።
ምርጫ ቦርድ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. የዕጩዎችን ምዝገባ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፣ የዕጩዎች ምዝገባ ሒደትን አስመልክቶ በተለያየ ወቅት የተለያዩ መረጃዎችን ሲያደርስ እንደነበር አስታውሷል። በተጨማሪም የዕጩዎች ምዝገባን አስመልክቶ ሦስት የተለያዩ ምክክሮችን ከፓርቲዎች ጋር ማከናወኑን ገልጿል፡፡
በመሆኑም በመጀመርያ ዙር ዕጩዎች ምዝገባ የተጀመረባቸው ክልልሎች ወይም በከተማ መስተዳድሮች ማለትም በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በኦሮሚያ፣ በሐረሪ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የዕጩዎች ምዝገባን የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. መጠናቀቁን አስተውቋል፡፡ ነገር ግን የዕጩዎች ምዝገባ ዘግይተው በጀመሩ ክልሎችና ቦታዎች ማለትም በአማራ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ በምዕራብና በምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ በቄለም ወለጋና በሆሮ ጉድሩ፣ በደቡብና በሲዳማ ክልሎች በመርሐ ግብሩ መሠረት የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. መጠናቀቅ የሚገባው ቢሆንም በቢሮዎች መከፈት፣ መዘግየትና፣ እንዲሁም የትራንስፖርትና ሌሎች እክሎችንና የፓርቲዎች አቤቱታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሁለተኛ ዙር የዕጩዎች ምዝገባ እስከ የካቲት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ እንዲራዘም ማድረጉን፣ ፓርቲዎችም በተሰጡት ተጨማሪ ቀናት ውስጥ ምዝገባቸውን እንዲያጠናቅቁ አሳስቧል፡፡