በትግራይ ክልል እየተካሄደ ባለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ምንም ዓይነት ወታደራዊ ስምምነት አለመደረጉንና ዕገዛም እንዳልጠየቀ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) በሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የሕወሓት ኃይሎች ወደ ኤርትራ ሚሳይሎችን ሲተኩሱ የኤርትራ ወታደሮች ድንበር ላይ ስለነበሩ፣ በወቅቱ በነበረው ግርግር በአካባቢው ሊታዩ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትና መንግሥታት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል ከፍተኛ የሆነ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ዝርፊያና ዘግናኝ ግድያ ፈጽመዋል በማለት ክስ እያቀረቡ ነው፡፡

ለአብነትም አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የአሜሪካ መንግሥትና የአውሮፓ ኅብረት ይገኙበታል፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ በሆነ አካል ምርመራ እያካሄደ መሆኑን፣ ምርመራ ማድረግ ለሚፈልጉም ድጋፍ አደርጋለሁ ከማለት ውጪ ገብተዋል የተባሉትን የኤርትራ ወታደሮች በተመለከተ መልስ ሲሰጥ አልተሰማም፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት፣ በትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ከትግራይ ክልል ለቀው እንዲወጡ ማሰባሰባቸው ይታወሳል፡፡

የአሜሪካን መግለጫ በተመለከተ ዲና (አምባሳደር) በበኩላቸው በአሜሪካ በኩል የአማራ ኃይል ይውጣ ተብሎ መነገሩ አስገራሚ ነው ብለዋል፡፡ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የጉራጌ ወይም የትግራይ ተብሎ የሚጠራ ኃይል እንደሌለና ሁሉም በፌዴራል መንግሥት የሚታዘዝ በመሆኑ፣ ይህ ኃይል የፌዴራል መንግሥት በፈለገው ቦታ ሊንቀሳቀስ ይችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የኤርትራን መንግሥት በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ከጋበዘው ሊሳተፍ እንደሚችል፣ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ በመንግሥት በኩል አንድም የተጋበዘ የኤርትራ ወታደር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡

‹‹እንደ ሉዓላዊ አገርና መንግሥት ኤርትራን፣ ሶማሊያን ወይም ሱዳንን መጋበዝ ይቻላል፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ እያልን ያለነው የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራን ወታደር የጋበዙበት ሁኔታ የለም፤›› ሲሉ ቃል አቀባዩ አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የካቲት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል በሚገኘው መከላከያ ሰሜን ዞን ላይ የተወሰደው ዘግናኝ ጥቃት በአገሪቱ ሕጎች መሠረት ከፍተኛ የክህደት ወንጀል እንደሆነና በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ማንኛውም ግለሰብ ወይም አካል ከአገሪቱ ሕግ አይበልጥም ሲል ገልጿል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ሕግ የማስከበርና አገርን የመጠበቅ ግዴታ አለበት ያለው መግለጫው በዚህም፣ ኢትዮጵያ የወሰደችውን የሕግ የበላይነት በማዳከም የታቀደ ማንኛውም ወገንተኛ ጣልቃ ገብነትና በአገርና መንግሥት ላይ የሚወሰድ ፖለቲካ አትቀበልም ሲል አቅርቧል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *