በኅዳር 19 እና 20/2013 ዓ.ም የተፈጸመው የጅምላ ግድያ በሰብአዊ ፍጡር ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን እንደሚችል ሪፖርቱ ገልጿል።

አንድ የዓይን ምስክር ለቢቢሲ እንደገለጹት በከተማዋ በተፈጸመው ግድያ በየመንገዱ አስከሬኖች ለቀናት ሳይነሱ መቆየታቸውን ገልጸው በርካቶቹ በጅብ መበላታቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ትግራይ ውስጥ የኤርትራ ወታደሮች መግባታቸውን በይፋ ያስተባበሉ ሲሆን በአምነስቲ ሪፖርት ላይ የሰጡት ምላሽ የለም።

ትግራይ ውስጥ የሚገኘውን የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት የሠሜን ዕዝ ላይ የህወሓት ኃይሎች ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነበር ጥቅም 24/2013 ዓ.ም ወታደራዊ ግጭቱ የተቀሰቀሰው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለአገሪቱ ፓርላማ በዚህ ዘመቻም አንድም ሰላማዊ ዜጋ እንዳልተገደለ ቢገልጹም፤ አብዛኞቹ ያልታጠቁ ልጆችና ወንዶችን በጉዳና ላይ ወይም ቤት ለቤት በተደረጉ አሰሳዎች በኤርትራ ወታደሮች የተገደሉ ሰዎችን ስለመቅበራቸው የዓይን እማኞች ገልጸዋል።

የአምነስቲ ሪፖርት በጥንታዊቷና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ስፍራ በሆነችው አክሱም ውስጥ በሚገኙ ሁለት ቤተክርስቲያናት ውስጥ የቀብር ቦታዎችን የያዙ የተቆፈሩ ስፍራዎችን የሚያመለክቱ ከፍተኛ የምስል ጥራት ያላቸው የሳተላይት ምስሎችን አካቷል።

የኮምዩኒኬሽን መስመሮች መቋረጥና ወደ ትግራይ ለመግባት አለመቻል በግጭቱ ወቅት ስለተከሰቱ ጉዳዮች በወቅቱ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

በአክሱም የነበረው የኤሌክትሪክና የስልክ አገልግሎት ግጭቱ በጀመረ በመጀመሪያው ዕለት ተቋርጦ ነበር።

ሪፖርቱ ፦

የአምነስቲን ሪፖርት በተመለከተ መንግሥታዊው የኢትየጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እንዳለው ምንም እንኳን ያልተጠናቀቀ ቢሆንም በአክሱሙ ክስተት ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።

የኮሚሽኑ የመጀመሪያ ደረጃ ግኝቱ ጥቂት ነዋሪዎችና የህወሓት ታጣቂዎች ለፈጸሙባቸው ጥቃት የኤርትራ ወታደሮች በወሰዱት የበቀል እርምጃ ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰላማዊ ሰዎች በከተማዋ ውስጥ ተገድለዋል ሲል አመልክቷል።

ኮሚሽኑ ጥቃቱ በኤርትራ ወታደሮች የተፈጸመው የህወሓት ወታደሮች አካባቢውን ለቀው ከወጡ በኋላ መሆኑንም ገልጿል።

በተጨማሪ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ተፈጽመዋል ስለተባሉ በርካታ የከባድ መሳሪያ ድብደባዎች ምርመራዎችን እያካሄድኩ ነው ብሏል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአክሱም ከተማ ተፈጽሟል ያለውን ይህንን የሰብአዊ መብት ጥሰት የምርመራ ውጤት የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትርና የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ኃይል ቃል አቀባይ ለሆኑት ለአምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ማቅረቡንና በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዳላገኘ በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።

ይህንን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ከተመለከተ በኋላ ከኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪ በኢሜይል ጥያቄ ቢያቀርብም ለጊዜው ምላሽ አላገኘም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ረቡዕ ለተካሄደው በ46ኛው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ስብሰባ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አገራቸው አሉ በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ አስፈላጊውን ማጣራት እንደምታደርግ ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ በንግግራቸውም ወሲባዊ ጥቃትን ጨምሮ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የመንግሥታቸው ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች እንደሆኑ አመልክተው “በዚህ ዙሪያ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ የድርጊቶቹን ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲሁኑ ለማድረግ ቁርጠኛ ነን” ሲሉ ተናግረዋል።

አክሱም እንዴት ተያዘች?

በምዕራባዊው የአክሱም ክፍል ላይ በኢትዮጵያና በኤርትራ ኃይሎች የከባድ ድብደባ የተጀመረው ኅዳር 10/2013 ዓ.ም እንደነበረ የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

“ይህ ጥቃትም ያለማቋረጥ ለአምስት ሰዓታት ቀጥሏል። በወቅቱ በቤተክርስቲያናት፣ በካፍቴሪያዎች፣ በሆቴሎችና በመኖሪያ ቤታቸው የነበሩ ሰዎች ሞተዋል።

ለጥቃቱ በከተማው ከነበረ የታጠቀ ኃይል የተሰጠ ምላሽ አልነበረም፤ ጥቃቱ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረገ ነበር” ሲሉ አንድ በከተማው ያሉ የመንግሥት ሠራተኛ ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር የሚመሳሰሉና በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ተከታታይ የከባድ መሳሪያ ድብደባን በተመለከተ አምነስቲ ኢንትርናሽናልም የበርካታ ሰዎችን ምስክርነት አሰባስቧል።

ከተማዋ በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላም የኤርትራ እንደሆኑ የተገለጹ ወታደሮች የህወሓት ወታደሮች ወይም “መሳሪያ የታጠቃ” ምንኛውንም ሰው ለማግኘት ፍለጋ አካሂደዋል ይላል የአምነስቲ ሪፖርት።

“ቤት ለቤት በመሄድ በርካታ ግድያዎች ተፈጽመዋል” ስትል አንዲት ሴት ለሰብአዊ መብት ድርጅቱ ገልጻለች።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደሮች “አክሱምን ለመቆጣጠር ባካሄዱት ጥቃት በርካታ የጦር ወንጀሎች መፈጸማቸውን” የሚያመለክት መስረጃ አለ ሲሉ የአምነስቲ ኢንትርናሽናል ባለስልጣን ዴፕሮስ ሙቼና ተናግረዋል።

ለግድያው ምክንያቱ ምንድን ነው?

የዓይን እማኞች እንዳሉት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ወታደሮች አክሱም ውስጥ ነበሩ ፤ የኤርትራ ወታደሮች ደግሞ ወደ አድዋ ከተማ ሄደው ነበር።
አምነስቲ እንደሚለው ከአንድ ሳምንት በኋላ የኤርትራ ወታደሮች ተመልሰው በመጡበት ጊዜ በደንብ ያልታጠቁ የህወሓት ተዋጊዎች በፈጸሙት ጥቃት ውጊያ ተቀስቅሷል።
በዚህም ከ50 አስከ 80 የሚደርሱ አክሱም ውስጥ የነበሩ ታጣቂዎች በከተማዋ አቅራቢያ ባለ ኮረብታ ላይ በሰፈሩ የኤርታራ ወታደሮች ላይ ነበር ጥቃት የፈጸሙት።
በጥቃቱ ላይ የተሳተፈ አንድ 26 ዓመት ወጣት ለአምነስቲ እንደተናገረው “ከተማችንን በተለይ ከኤርትራ ወታደሮች ለመከላከል ፈልገን ነበር… እነሱ እንዴት እንደሚተኮስ ያውቃሉ የግንኙነት ሬዲዮም አላቸው… እኔ መሳሪያ አልነበረኝም ዱላ ብቻ ነበር የያዝኩት” ብሏል።
ውጊያው ለምን ያህል ጊዜ እንደቆየ ግልጽ ባይሆንም ከሰዓት በኋላ የኤርትራ የጭነት መኪኖችና ታንኮች ወደ አክሱም ከተማ መግባታቸውን የአምነስቲ ሪፖርት ያመለክታል።
የዓይን እማኞች እንዳሉት የኤርትራ ወታደሮች ያገኙትን ማጥቃት ጀመሩ፤ ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎችንና በጉዳና ላይ ያገኟቸውን ወንድ ልጆችን በጥይት እየመቱ እስከ ምሽት ድረስ ቀጠሉ።

በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ አንድ ግለሰብ በከተማዋ መንገዶች ላይ ስለተፈጸሙት ግድያዎች ለአምነስቲ እንደተናገረው “በአንድ ህንጻ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ሆኜ በመስኮት በኩል የኤርትራ ወታደሮች ወጣቶችን በጎዳና ላይ ሲገድሉ አይቻለሁ” ብሏል።
ወታደሮቹ የኤርትራ መሆናቸው የተለየው በለበሱት የደንብ ልብስ ወይም በመኪኖቻቸው የሰሌዳ ቁጥር ብቻ አልነበረም። ቤት ለቤት ባደረጉት አሰሳ ወቅት በሚናገሩት የአረብኛ ቋንቋና የትግረኛ ዘዬ ነበር። ግድያው “የበቀል እርምጃ ነው እላለሁ” ሲል አንድ ወጣት ለቢቢሲ ተናግሯል። “ያገኙትን ሰው ሁሉ ገድለዋል። በር ተከፍቶ ወንድ ካገኙ ይገድላሉ፤ በር ካልተከፈተላቸው በር ላይ ይተኩሳሉ” ብሏል።

በአንድ የምሽት ክለብ ውስጥ ተደብቆ በነበረበት ጊዜ የኤርትራ ወታደሮች አንድ ግለሰብን አግኝተው ሲገድሉት መመልከቱን የሚናገረው ግለሰብ “ሰላማዊ ሰው ነኝ፤ የባንክ ሠራተኛ ነኝ’ እያለ ሲለምናቸው ነበር” ሲል ተናግሯል። ሌላ ግለሰብ ደግሞ ኅዳር 20 አብነት ሆቴል አቅራቢያ ከሚገኘው ቤቱ ውጪ ስድስት ሰዎች ርሸና በሚመስል ሁኔታ ሲገደሉ መመልከቱን ለአምነስቲ ገልጿል።

“በአንድ መስመር እንዲቆሙ አድርገው ከጀርባቸው ነበር የተኮሱባቸው። ሁለቱን አውቃቸዋልሁ። የእኔ ሰፈር ነዋሪዎች ናቸው… ‘መሳሪያችሁ የታለ’ እያሉ ሲጠይቋቸው ‘እኛ ሰላማዊ ሰዎች ነን መሳሪያ የለንም’ በማለት ሲመልሱላቸው ነበር።”

ስንት ሰዎች ተገደሉ?
የዓይን እማኞች እንደሚሉት መጀመሪያ አካባቢ የኤርትራ ወታደሮች በመንገዶች ላይ ወደ ወደቁት አስከሬኖች ማንም እንዳይቀርብ ከልክለው ነበር፤ ለመቀረብ የሚሞክሩት ላይ ይተኩሱ ነበር።
የ29 እና የ14 ዓመት የቅርብ ዘመዶቿ የተገደሉባት አንዲት ሴት “መንገዶች በአስከሬን ተሞልተው ነበር” ስትል ተናግራለች።
አምነስቲ እንዳለው የአካባቢው ሽማግሌዎችና የኢትዮጵያ ወታደሮች ጣልቃ ከገቡ በኋላ የተገደሉትን ሰዎች ለቀናት መቅበር ተጀመረ።
ነዋሪዎች በአንድ ጊዜ አስከ 10 የሚደርሱ አስከሬኖችን በፈረስና በአህያ በሚጎተቱ ጋሪዎች በመጫን እያመላለሱ የበርካታ ሰዎች ቀብር የተፈጸመው ኅዳር 21 ነበር።
የመንግሥት ሠራተኛ የሆነው አንድ የዓይን እማኝ እንደተናገረው በአብነት ሆቴል የነበሩ አስከሬኖች አስከ አራት ቀናት ድረስ ሳይነሱ ቆይተዋል።
“አብነት ሆቴልና ሲያትል ሲኒማ አካባቢ ወድቀው የነበሩ አስከሬኖች በጅብ ተበልተው አጥንት ብቻ ነበር ያገኘነው። አጥንት ነው የቀበርነው።
“አክሱም ውስጥ 800 የሚደርሱ ሰዎች ተገድለዋል ብዬ መነገር እችላለሁ።”
ይህንን ምስክርነት ለአሶሺየትድ ፕሬስ የተናገረ አንድ ዲያቆንም የሚጋራው ሲሆን፤ በርካታ አስከሬኖች በጅብ መበላታቸውን ተናግሯል።

ዲያቆኑ የሟቾችን የመታወቂያ ወረቀት የሰበሰበ መሆኑንና በጅምላ ሲቀበሩም እንዳገዘ ይናገራል። ጥቃቱ በተፈጸመባቸው ቀናት 800 የሚደርሱ ሰዎች ተገድለዋል ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።

አምነስቲ ያናገራቸው 41 ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች የተገደሉ ናቸው ያሏቸውን ከ200 በላይ ሰዎች ስም ሰጥተዋል።

ከቀብር በኋላ ምን ተፈጠረ?

የዓይን እማኞች እንዳሉት ከግድያው በኋላ በርካታ ሰዎች ከተማዋን ለቀው በመሄዳቸው የኤርትራ ወታደሮች በስፋትና ዘዴ በተሞላበት መንገድ ዝርፊያ ፈጽመዋል።

ዩኒቨርስቲ፣ የግል መኖሪያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ የእህል መጋዘኖች፣ ጋራዦች፣ ባንኮች፣ መደብሮች፣ ዳቦ ቤቶች ሌሎች ሱቆች የዝርፊያ ኢላማ ነበሩ ተብሏል።

አንድ የወንድሙ ቤት የተዘረፈበት ግለሰብ የኢትዮጵያ ወታደሮች በኤርትራ ወታደሮች የተፈጸመውን ዝርፊያ እንዴት ማስቆም እንዳልቻሉ ለአምነስቲ ተናግሯል።

“ቴሌቪዥን፣ መኪና፣ ፍሪጅ፣ ስድስት ፍራሾች፣ የምግብ ሸቀጦችና ዘይት፣ የጤፍ ዱቄት፣ የማዕድ ቤት መደርደሪያ፣ ልብሶች፣ ፍሪጅ ውስጥ የነበረ ቢራ፣ የውሃ ፓምፕና ላፕቶብ ወስደዋል” ብሏል።

አንድ የከተማዋ ወጣት ለቢቢሲ እንደተናገረው በከተማዋ ያሉ ነጋዴዎች ንብረት የሆኑ 15 መኪኖች እንደተወሰዱ አውቃለሁ ብሏል። ይህም የአክሱም ከተማን ለቀው የሄዱ ሰዎችን በህይወት ለመቆየት የሚያስችል የምግብና የመድኃኒት አቅርቦት በማሳጣት ለከባድ ችግር ዳርጓቸዋል ሲል አምነስቲ ገልጿል። በውሃ መሳቢያ ፓምፖች ላይ የተፈጸመው ዝርፊያ ነዋሪዎች የወንዝ ውሃን ለመጠጥነት እንዲጠቀሙ እንዳስገደዳቸው የዓይን እማኞች ተናግረዋል።

አክሱም ፦
ታሪካዊቷ የአክሱም ከተማ ከጥንታዊዎቹ ሐውልቶች ባሻገር መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ለሙሴ የተሰጠውን አስርቱን ትዕዛዛት እንደያዘ የሚታመነው የቃል ኪዳን ታቦት የሚገኝባት የአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያን ይገኝባታል።

በዚህም አክሱም ከመላው ኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ ተሰባሰቡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የዕምነቱ ተከታዮች የሚታደሙበት ሐይማኖታዊ በዓል በየዓመቱ ኅዳር 21 ይካሄድ ነበር።

በክልሉ ውስጥ በነበረው ግጭት የተነሳም በዚህ ዓመት በዓሉ በተለመደው ሁኔታ ሳይካሄድ ቀርቷል።

በአክሱም ከተማ የመንግሥት ሠራተኛ አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ እንደተናገረው የኤርትራ ወታደሮች ኅዳር 24 ወደ ቤተክርስቲያኗ በመሄድ “ቄሶችን በማስፈራራት ከወርቅና ከብር የተሰሩ መስቀሎችን እንዲሰጧቸው አስገድዷቸው ነበር።”

ነገር ግን ዲያቆኖችና ሌሎች ወጣቶች የቃል ኪዳን ታቦቱን ለመከላከል ወደ ቤተክርስቲያኑ ሄደው ነበር ብሏል።

“ከፍተኛ ብጥብጥ ነበር የተፈጠረው። ወንዱም ሴቱም ተቃውሟቸዋል። እነሱም ተኩሰው ጥቂቶችን የገደሉ ቢሆንም ቅርሶቻችንን ለማስጣል በመቻላችን ደስተኞች ነን።”

የኤርትራ ወታደሮች ፦

የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርቶች የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ግጭት መሳተፋቸው የተጠቀሰ ቢሆን ይህንን ኢትዮጵያም ሆነ ኤርትራ መንግሥታት ማስተባበላቸው ይታወሳል።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የአገሪቱ ሠራዊት ትልቁ ክፍል በሆነው የሠሜን ዕዝ ላይ በህወሓት ኃይሎች ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ሕግ የማስከበር ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄዱን በመግለጽ በዚህም የኤርትራ ጦር አለመሳተፉን ሲያስተባብል ቆይቷል።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን ቢገልጽም በአንዳንድ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ወታደራዊ ግጭቶች እንዳሉ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

(ይህ ፅሁፍ የተዘጋጀው በቢቢሲ አማርኛ አገልግሎት)

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *