ሳው ሳይደረግ ተስተጓጉሏል፤›› ሲል ፓርቲው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የምርጫ አዋጁ ቁጥር 1162 የምርጫ ቅስቀሳ ስለማካሄድ በሚል ርዕስ በአንቀጽ 43 ሥር ባሰፈረው ድንጋጌ በዕጩነት ተመዘግቦ ዕውቅና የተሰጠው ተወዳዳሪ፣ ለድምፅ መስጫው አራት ቀን እስከሚቀረው ድረስ ከከተማ አስተዳደርም ሆነ ከክልል መንግሥታት ፈቃድ መጠየቅ ሳያስፈልገው በማሳወቅ ብቻ የምርጫ ቅስቀሳ የማካሄድ መብት እንዳለው ይደነግጋል።

ኢዜማ የምርጫ ቅስቀሳ በይፋ በሚጀመርበት ዕለት ዋዜማና በዕለቱ የገጠሙትን ተግዳሮቶች ከላይ በተቀመጠው መንገድ ለማሳያነት ይቅረቡ እንጂ፣ ተመሳሳይ ብቻ ሳይሆን ከዚህ የከፉ ተግዳሮቶች የገጠሟቸው ፓርቲዎች አቤቱታቸውን ለምርጫ ቦርድ እያሳወቁ ይገኛሉ።

ከእነዚህም መካከል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንጎረንስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች አባሎቻቸው እየታሰሩና እየተገደሉ እንደሆነ፣ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቻቸውም እንደተዘጉባቸው የሚገልጽ አቤቱታ በማሰማት ላይ ናቸው።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ይካሄዳል ብለው እንደማያስቡ በመግለጽ፣ ሁኔታው ካልተስተካከለ ከምርጫ ውድድሩ ራሳቸውን ለማግለል እንደሚችሉም በማሳወቅ ላይ ናቸው።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የፖለቲካና የግጭት ጉዳዮች ተንታኝ መጪው ምርጫ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሁሉ በእጅጉ የተሻለ እንዲሆን መንግሥት የምርጫ ሕጎችን በማሻሻልና የምርጫ አስፈጻሚውን ተቋማዊ ጥንካሬ በማጎልበት፣ እንዲሁም ከቀድመው የተሻለ ገለልተኛ የሆኑ የቦርድ ከባላት እንዲመራ መደረጉ ትልቅ ዕርምጃ ቢሆንም ይህ ብቻውን ወደሚፈለገው ግብ እንደማያደርስ ይገልጻሉ።

ቀጣዩ ምርጫ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሆን መሟላት ከሚገባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ የምርጫ ሒደቱ የሚካሄድበት ዓውድ፣ ሰላማዊና ምቹ ወይም የተረጋጋ መሆኑ ነው ብለዋል።

ይህ ድባብ ሲኖር የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ በሚደረግባቸው አካባቢዎች በነፃነት መንቀሳቀስ ያስችላቸዋል የሚሉት ባለሙያው፣ በሰላምና በነፃነት መንቀሳቀስ ሲቻል ደግሞ ፓርቲዎች አማራጮቻቸውን በቀላሉ ለማኅበረሰቡ ማቅረብና ማስረዳት እንደሚያስችላቸው ይገልጻሉ።

በሰከነ የፖለቲካ ዓውድ ውሰጥ የሚያልፍ የምርጫ ሒደት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን መራጮች ደኅንነታቸው ተጠብቆ ያለ ሥጋትና ፍርኃት ድምፃቸውን በምክንያት ላይ ተመሥርተው በመስጠት የፈለጉትን ፓርቲ መንግሥት አድርገው እንዲመርጡ ያስችላቸዋል የሚሉት ባለሙያው፣ ይህ ሲወራ ቀላልና የተለመደ አገላለጽ ቢሆንም የአንድን ምርጫና ከምርጫው በኋላ የሚኖረውን አገራዊ የፖለቲካ ሁኔታ የሚወስን እንደሆኑ ያስረዳሉ።

ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ሲገመገም ከፍተኛ ጉድለት እንዳለበት የሚገልጹት ባለሙያው፣ ምርጫው በዚህ ድባብ ውስጥ ባይካሄድ ይመርጣሉ።

ነገር ግን ይህንን አሁን ማድረግ የሚቻል አይመስልም፣ ቢቻልም ያንን ማድረግ በራሱ የሚያስከትለው ቀውስ ሊኖር እንደሚችል በመገመት ምርጫ ቦርድ በአፋጣኝ ማድረግ አለበት ያሉትን ያሳስባሉ፡፡

‹‹የምርጫ ቦርድ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን ሁኔታ የሚያሳይ አጠቃላይ የግጭት ሁኔታ ትንተና (ኮንፍሊክት አሰስመንት) ሠርቶ የምርጫ ቅሰቀሳም ሆነ ምርጫ ለማድረግ አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎችን በፍጥነት ማሳወቅ አለበት፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

ይህ ሳይደረግ የሚካሄድ የምርጫ ቅስቀሳ በተለይ ሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ ለሚቃወሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስቸጋሪ የደኅንነት ሥጋት ሲፈጥር፣ ለገዥው ፓርቲ ግን የተመቻቸ የውድድር ሜዳ ይፈጥራል ብለዋል።

ምክንያታቸውንም ሲያብራሩ፣ ‹‹ገዥው ፓርቲ የመንግሥት ሥልጣን ላይ መሆኑ የሚሰጠውን ዕድል ተፎካካሪ ፓርቲዎች አያገኙም። ከወረዳ እስከ ቀበሌ ያሉ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የሚገኙ የገዥው ፓርቲ አባላት በእንደዚህ ዓይነት የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ለመንቀሳቀስ እንደ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አይቸገሩም፡፡ በመሆኑም በዚያ ዓውድ መንቀሳቀስ የሚችል በምርጫውም የተሻለ ዕድል ይኖረዋል፤›› ብለዋል።

የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ ማድረግ ያልቻለ ፓርቲ በአካባቢዎቹ የመራጮችን ድምፅ የማግኘት ዕድሉ የመነመነ ሲሆን፣ ገዥው ፓርቲ ግን ሥልጣን ላይ የሚገኝ በመሆኑ የተሻለ ዕድል ይኖረዋል ሲሉ ሐሳባቸውን ያጠናክራሉ።

በመሆኑም ያለው ሁኔታ ምክንያታዊ ተቀባይነት ባለው ደረጃ ለሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ ምቹ መሆንና አለመሆን በግጭት ጥናት በመለየት ማሳወቅ፣ የሚመለከታቸው አካላት ሁኔታውን እንዲያስተካክሉ ጊዜ መስጠትና ሌሎች ጥረቶችን ማድረግ ይገባል ብለዋል። ሁኔታው ባልተሻሻለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ምርጫው በሌላ ጊዜ እንዲከናወን መወሰን ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ከሁለት ሳምንት በፊት ምርጫውን በተመለከተ ያላቸውን ሥጋትና ተስፋ በሰጡት የቪዲዮ መልዕክት፣ የፀጥታ ሥጋት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ጨምሮ የሚያሳስባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

ከአምስቱ የምርጫ ቦርድ አመራር አባላት አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ብዙወርቅ ከተተ በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ምርጫው የሚካሄድበት ምህዳር ውስብስብ ነው፣ አንዱ ትልቁ ሥጋት የፀጥታው ሁኔታው ነው። ይህንን ሥጋት ለመቅረፍ የመንግሥትም የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሌሎች ባለድርሻ አካላት የጋራ ጥረት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፣ ይህንን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፤›› ብለዋል። ከፀጥታ ሥጋት በተጨማሪ የጊዜ እጥረት እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል።

የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው፣ ‹‹ወደ ምርጫ አፈጻጸም ስንሄድ ሰላማዊነቱን መጠበቅ አንዱ ችግር ይሆናል ብዬ እገምታለው ነገር ግን እየተዘጋጀንበት ነው። በየቦታው ላይ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎች ምንድንናቸው? ወደ ግጭት ሊያመሩ የሚችሉ ምንድንናቸው? ቦርዱ፣ ፓርቲዎችና ሲቪል ማኅበራት ይህ ችግር እንዳይፈጠር እንዴት መከላከል ይችላሉ? የሚለውን እያጠናን የተለያዩ የመከላከያ አሠራሮችን ለመዘርጋት እየሞከርን ነው፤›› ብለዋል።

በአፍሪካ ሥልጣን ላይ ያሉ ገዥ ፓርቲዎች ከላይ የተገለጹትን ዓይነት ተግዳሮቶች በሌሎች ላይ ሲፈጥሩ ይስተዋላል እንጂ፣ እንደ እነዚህ ዓይነት ተግዳሮቶች እነርሱን እምብዛም አይገጥማቸውም ወይም ጨርሶም አያውቋቸውም።

የወቅቱ የኢትዮጵያ ገዥ የፖለቲካ ድርጅት የሆነው ብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ዘመቻ እንቅስቃሴ በይፋ በተጀመረበት የካቲት 8 ቀን ለምርጫ ውድድር ያዘጋጀውን ማኑፌስቶ በይፋ ያስተዋወቀ ሲሆን፣ በተለያዩ የመንግሥት ሚዲያዎችም ሰፊ ሽፋን ተስጥቶታል።

በዚህ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፣ ብልፅግና ፓርቲ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አቃፊና ቃሉን መተግበር እንጂ ብዙም መናገር የማይሆንለት የተለየ ፓርቲ እንደሆነ ገልጸዋል።

እሳቸው በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ፓርቲያቸው መጪውን ምርጫ እንደሚያሸንፍ በእርግጠኝነት ያስታወቁ ሲሆን፣ ይህ እንዳለ ሆኖ ከሁሉ በላይ የሚፈልጉት መጪው ምርጫ ሁሉም በእኩልነት የሚሳተፍበትና ሕዝብ በነፃነት በድምፁ የሚወስንበት እንዲሆን እንደሚሠሩና ይህ እንዲሳካም ሁሉም ባለድርሻ አካል ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በዚሁ ንግግራቸው ወቅት ስለብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ማኒፌስቶ ይዘቶች ገልጸው፣ ‹‹ተፎካካሪ ፓርቲዎች እኔም የትምህርት ፖሊሲ አለኝ፣ እኔም የጤና ፖሊሲ አለኝ ብለው በዚህ በአንድ ወር ውስጥ ይቀርባሉ። ነገር ግን ያ ድርሰት እንጂ ፖሊሲ ሊሆን አይችልም፤›› ብለዋል።

የምርጫ አዋጁ አንቀጽ 143(6) ላይ የሰፈረው ድንጋጌ ማንኛውም ዕጩ ተወዳዳሪ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና ወኪል የሌሎች ፓርቲዎች ወይም ዕጩ ተወዳዳሪዎች የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ እንዲስተጓጎል ወይም እንዲቋረጥ፣ ወይም እንዲበላሽ ወይም እንዲዳከም ማድረግ እንደማይችልና ይህንን ማድረግ የሥነ ምግባር ጥሰት እንደሆነ ይደነግጋል::

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *