‹‹ሙያ የተለያዩ ሰዎች አባባሎቻቸው በተሻለ መንገድ እንዲጠበቁና ሕዝቡም የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ በማሰብ፣ ሥራቸውን ደንቡ በሚፈቅደው መሠረት ለማከናወን እንዲያስችል የተሟላ ደረጃ የሚያስጠብቁበት አቅም ነው፡፡ ሙያ ምንም እንኳን ለሙያተኛው ጥቅም ወይም ትርፍ የሚያመጣለት ቢሆንም፣ ሙያተኛው አባል ለሆነለት ተቋም ውርደት እንዳያመጣ ሙያተኛውም የተወሰኑ ተግባሮችን እንዳይፈጽም በግልጽ ይከለክላል፡፡ ስለዚህም በኢንዱስትሪና በሙያ መካከል በአሁኑ ጊዜ ያለው ልዩነት በጣም ግልጽና የማያሳስት ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ዋናው ዓላማ የባለአክሲዮኑን የገንዘብ ትርፍ ማዳበር ነው፡፡ ምንም እንኳን ለሰዎች (ለባለሙያው) የዕለት ጉርስ ቢያስገኝላቸውም፣ የሙያቸው ውጤት የሚለካው በሚሰጡት አገልግሎት እንጂ በገንዘብ ብዛት አይደለም፤›› በማለት የተናገረው አሜሪካዊው የሕግ ባለሙያ ጁሊየስ ሄነሪ ኮኸን ‹‹ሕግ ቢዝነስ ወይስ ሙያ?›› በሚል እ.ኤ.አ. በ1924 ባሳተመው መጽሐፉ ነው፡፡
ሰዎች በልምድና በትምህርት የሚያገኟቸውን ዕውቀቶች ወይም ልምዶች ‹‹ሙያ›› ብለው ሲናገሩ ቢሰማም፣ ሙያዎች ሁሉ አንድ ዓይነት ሳይሆኑ የተለያዩ ትርጉሞችና አተገባበሮች አሏቸው፡፡ ከሙያዎች ውስጥ ሕግ አንዱ ሲሆን፣ የተከበረና የላቀ ሙያ ነው፡፡ አሜሪካዊው የሕግ ሊቅ ሮስኮ ፓውንድ እንደገለጹት፣ ሕግ ሦስት መሠረታዊ ሐሳቦችን ይዟል፡፡ የመጀመርያው ሕግ ሙያ በመሆኑ አቋም ያለው መሆን አለበት፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የተለየ ትምህርትን የሚጠይቅና ሦስተኛው ደግሞ ሕዝብን በማገልገል መንፈስ ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ያብራራሉ፡፡
ፓውንድ እንደገለጹት የሕግ አዋቂዎች በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርተው የሚሠሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ፣ በኩባንያዎች፣ በዳኝነት፣ በሕግ አስከባሪነት፣ በፓርላማና በጥብቅና ይሠራሉ፡፡
ሙያው በተለያዩ የሥራ ቦታዎች የሚከወኑ ቢሆንም፣ በዚህ ጽሑፍ ማየት የተፈለገው ግን የጥብቅና ሙያን በሚመለከት ነው፡፡ ጥብቅናን የሕግ ሙያ አድርገውና በሥራው የተሰማሩ ጠበቆች አስፈላጊነታቸው ለሁለት ዓበይት ምክንያቶች ነው፡፡ ለምክርና ለጥብቅና፡፡ የሕግ ምክር ወይም ሐሳብ አብዛኛውን ጊዜ በግል ሊደረግ ይችላል፡፡ የሽያጭ ስምምነት መጻፍ፣ የማኅበራት መመሥረቻ ጽሑፍ መጻፍና መተዳደሪያ ደንብ ማዘጋጀት፣ እንዲሁም ማንኛውንም የሕግ ሐሳብ እንዳስፈላጊነቱ ለደንበኞቹ መስጠትን ያጠቃልላል፡፡
ጥብቅና ግን በግልጽ (በገሃድ) የሚደረግ የሙያ ሥራ ሲሆን፣ በደንበኛው ስም ሆኖ ወይም ተወክሎ በፍርድ ቤት፣ በፖሊስ ጣቢያ፣ በአስተዳደር ቦርድና በሁሉም ቦታዎች ቆሞ ይከራከራል፡፡ ጠበቃ የሚከራከረው በያዘው ጉዳይ አሸናፊ (ረቺ) ሆኖ ደንበኛውን ለማስደሰት ብቻ ሳይሆን፣ የፍርድ ቤት ሥራ አካሄድ በሚገባና በትክክል እንዲመራ ማድረግ ዋናው ተግባሩና ግዴታው ነው፡፡ ጥብቅና ሙያ እንጂ ንግድ ባለመሆኑ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን የማገዝና የመደገፍ ግዴታም እንዳለበት መታወቅ አለበት፡፡ ጠበቃ በርካታ ግዴታዎች ያሉበት ቢሆንም ለመንግሥት፣ ለፍርድ ቤት፣ ለደንበኛውና ለሙያ ባልደረቦቹ ታማኝና በሥነ ምግባር የተመራ መሆን አለበት፡፡
የጥብቅና ሙያ የተጀመረበት ዘመንና ምክንያት በተለያዩ አገሮች የተለያየ ነው፡፡ በኢትዮጵያም የጥብቅና ሙያ ዘመናዊ የሕግ ሥርዓት ከተጀመረበት ከ1934 ዓ.ም. በኋላ የተጀመረ እንደሆነ የሚነገር ቢሆንም፣ የተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች ግን የተለያየ አስተያየት ይሰጣሉ፡፡
የጥብቅና ሥራ የዛሬውን ስያሜ (ጥብቅና) ሳያገኝና የሕግ ችሎታ ሳይኖር ‹‹የአፍ ብልጠት›› ወይም ‹‹ንግግር የሚያውቁ›› ሰዎች ለሌሎች ሰዎች ወይም ባለጉዳዮች ‹‹አፍ›› ሆነው ከ1900 ዓ.ም. በፊትና በኋላ እስከ 1934 ዓ.ም. ድረስ ይቆሙ (ይከራከሩ) እንደበር የሚናገሩት ታዋቂውና አንጋፋው የሕግ ባለሙያ አቶ ታምሩ ወንድምአገኘሁ ናቸው፡፡
የጥብቅናም ሆነ የሕግ ሥርዓት ከመቼ ጀምሮ እንደታወቀ ወይም እንደተጀመረ ከመናገር ይልቅ፣ ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ልዩ ስለሚያደርጋት ነገር ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን አቶ ታምሩ ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ (ክርስቲያንና እስላም) እና ባህላዊ እምነቶች እንዳላትና የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ክርስቲያኑ ‹‹የክርስቶስን ለክርስቶስ (መንፈሳዊ)፣ የሰይጣንን ለሰይጣን (ሥጋዊ) ሲል፣ በእስልምናም እንዲሁ ራሱን የቻለ መመርያ እንደነበራቸው በመግለጽ፣ የሕግ አስተሳሰቦች የተቀረፁት ከእነዚህ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እምነቶች መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሌላው ኢትዮጵያን ለየት የሚያደርጋት በሁለቱም የተጻፉ ሕጎች መኖር እንደሆነም አክለዋል፡፡ ባህሎች እየዳበሩ ሲመጡ ለዳኝነት፣ ለሙግትና ለክርክር አፈታት ሥርዓት መዘርጋት መጀመሩን ‹‹ዳኛ አውጥቶ ዘንግ አቅንቶ›› በሚል በሠለጠነ አካሄድ ለችግሮች መፍትሔ መስጠት እንደተጀመረም አቶ ታምሩ ጠቁመዋል፡፡
ሌላው ታዋቂው የሕግ አማካሪ፣ ጠበቃና የኢትዮጵያ የጠበቆች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም፣ በኢትዮጵያ የጥብቅና አጀማመርና አሁን ስለደረሰበት አጠቃላይ ሒደት ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው፡፡ አቶ ፊሊጶስ እንደሚያስረዱት፣ በኢትዮጵያ የጥብቅና ሥራ የተጀመረው ከዳኝነት ሥራ ጋር ነው፡፡ ምንም እንኳን የመጀመርያው ሕገ መንግሥት በ1923 ዓ.ም. በሥራ ላይ የዋለ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ላይ የእንግሊዝ ዳኞች ተሾመው ዳኝነት መሰጠት የተጀመረው ከ1934 ዓ.ም. የመጀመርያው ፍርድ ቤት በአዋጅ ቁጥር 1/34 ከተቋቋመና በአዋጅ ቁጥር 2/34 የተለያዩ ሕጎችና አዋጆች ከወጡ በኋላ ነው፡፡ ዳኝነት ከወረዳ እስከ ንጉሡ ዙፋን ድረስ ደረጃውን ጠብቆ ይሰጥ እንደነበር፣ ነገር አዋቂ የሚባሉ ሰዎች ‹‹በነገረ ፈጅነት እየተሞሉ›› ይከራከሩ እንደነበር የተለያዩ መዛግብት እንደሚያሳዩ አቶ ፊሊጶስ ተናግረዋል፡፡
ዳኝነትም ሆነ ጥብቅና የሚያስፈልጉት በሕዝቡ ውስጥ የሚፈጠሩ አግባብነት የሌላቸው ችግሮችን ለመፍታት ሲሆን፣ በእነዚህ አካላት የሚሰጠውን የፍትሕ ‹‹በፈረስ አንገት፣ በሠይፍ አንደበት›› ተከራክሮ ማግኘት ስለማይቻል፣ በሠለጠነ መንገድ በኦሪቱ ዘመን ሳይቀር ይካሄድ እንደበር አቶ ታምሩ ያስረዳሉ፡፡
የፍትሕ ሥርዓት መበላሸቱና ዜጎች ‹‹በሕግ አምላክ›› የሚሉበት እንዳጡ የሚነገረው አሁን ብቻ ሳይሆን፣ ከዘመናት በፊትም የነበሩ ሰዎች በደላቸውን ‹‹ግፍ በዛ ናኘ፣ ኩበት ጠልቆ ድንጋይ ዋኘ›› በማለት ይገልጹ እንደነበር በመጠቆም፣ ‹‹እነዚህ ሁሉ የሚያሳዩት የሕግ አስተሳሰቦችን መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አፄ ኃይለ ሥላሴ ‹‹አገር ያለዳኛ አይቀናም›› በማለት በ1934 ዓ.ም. እንግሊዞችን ጠርተው የዳኝነት ሹመት ሲሰጡ፣ ‹‹ሰዎች ተከሰው ሲቀርቡላችሁ የሰው ልጆችን እኩልነትንና የተፈጥሮ ሕግን ርትዕ ጠብቃችሁ ሥሩ›› በማለት፣ አንድ ዳኛ አሁንም ቢሆን ከመፍረዱ በፊት እነዚህን መርሆዎች ማሰብ እንዳለበትና የጠበቃ አስፈላጊነትም ለእነዚህ መርሆዎች መገዛት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል፡፡ ምንም እንኳን ዘመናዊ የሕግ ሥርዓትና የባለሙያ (ዳኛ) ሹመት ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ እያደገና እየዳበረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ዳኛ መሾም የተጀመረው በ16ኛው ክፍለ ዘመን በፍትሐ ነገሥት መሆኑን አቶ ታምሩ ገልጸዋል፡፡ ከ1900 ዓ.ም. ጀምሮ የተበጣጠሱ ሕጎች የነበሩ ቢሆንም፣ በአፈ ንጉሥ ነሲቡ የተቋቋመው የመጀመርያው ፍርድ ቤት እስከ ታች ድረስ የሚደርስና የጠለቀ ባይሆንም፣ ግራና ቀኝ እማኞች ተቀምጠው ነገር የሚያፈሱ ነገረ ፈጆች እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡
የዳኝነትና የጥብቅና ሥራ ዘመናትን የተሻገረ የሙያ አገልግሎት ሆኖ የቀጠለ ቢሆንም፣ እስከ 1992 ዓ.ም. ድረስ ግን የውጭ አገር ዜጎች ሁሉ ጥብቅና ይቆሙ እንደነበር አቶ ታምሩ አስታውሰዋል፡፡ በ1992 ዓ.ም. የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ አዋጅ ከወጣ በኋላ፣ የውጭ አገር ዜጎች ጥብቅና እንዳይቆሙ መከልከላቸውና ጠበቆችም በማኅበር እንዲደራጁ መፈቀዱን አቶ ታምሩ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ፊሊጶስ አገላለጽ ደግሞ ጥብቅና በተለይ የሃይማኖት ትምህርት ባላቸው ነገረ ፈጆች መሥራት ከተጀመረ ዘመናትን ያስቆጠረ ቢሆንም፣ ከ1930ዎቹ ወዲህ ያሉ መዛግብት የሚያሳዩት በውክልና ይከራከሩ እንደነበር ነው፡፡ ትምህርት በተማሩ ባለሙያዎች አገልግሎት መስጠት የተጀመረው ከ1950ዎቹና 1960ዎቹ ወዲህ መሆኑንም አቶ ፊሊጶስ ገልጸዋል፡፡
የመጀመርያዎቹ የሕግ ትምህርት ከፈረንሣይ ተምረው የመጡት ባለሙያ ጠበቆች አቶ አሰፋ ሊበን፣ አቶ ተሾመ ገብረ ማርያምና ሌሎችም እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ፊሊጶስ፣ አብዛኞቹ ግን የሃይማኖት ትምህርት የተማሩና በልምድ የሚሠሩ እንደነበሩ በመግለጽ፣ የአቶ ታምሩን ገለጻ አጠናክረዋል፡፡ ባለሙያዎቹን ጠበቃ ያሰኛቸው በወቅቱ እስከ 1992 ዓ.ም. ድረስ ይሰጣቸው የነበረው የጥብቅና ፈቃድና ሠርተፊኬት አንደነበርም አክለዋል፡፡
ምንም እንኳን የጥብቅና ሙያ ከ1960ዎቹ ጀምሮ እያደገ ቢመጣም፣ ነገር አዋቂዎች በበልሀ ልበላ ጊዜ ጀምሮ ተወክለው ይከራከሩ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት የገለጹት አቶ ፊሊጶስ፣ ሕግ ሳይኖር እንዴት ዳኛና ጠበቃ ሊኖር እንደቻለ ግር የሚለው ቢኖርም፣ ዘመናዊ አስተዳደር ያላት አሜሪካ እንኳን ባልተጻፈ ሕግ (Common Law) እየተመራች መሆኗን ልብ እንዲሉ መክረዋል፡፡ አሜሪካን የጠቀሱበት ምክንያትም ኢትዮጵያ በኦሪቱ በሃይማኖት መጻሕፍት፣ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮም ደግሞ በፍትሐ ነገሥትና በተለያዩ በተጻፉ ሕጎች የምትመራና ሕግ እንደነበራት ለማስታወስ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በአዋጅ ያልወጡ ሆነው እንጂ በዚያን ጊዜ የነበሩ ሕጎች ከአሁኑ ጊዜ ሕጎች ሊሻሉ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡ በወቅቱ ሕዝብና አገር በሃይማኖት መሪዎች ወይም በንጉሥ ስለሚመሩ እንጂ፣ ኢትዮጵያ የ3,000 ዘመን ታሪክ ያላት አገር መሆኗ የሚነገረው ሕዝቧን የምታስተዳድርበት ሕግም ጭምር ስላላት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በወቅቱ የነበረው ችግር የሥልጣን ክፍፍል (Separation of Powers) አለመኖሩ እንጂ፣ ሕጎች በመንፈሳዊም ሆነ በባህላዊ እንደነበሩና አሁንም ሊሠራባቸው እንደሚቻል ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 78 መደንገጉንም አስታውሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ሥር አለመቆየቷ በፍትሕ ሥርዓቷ ወደኋላ ስለመቅረቷ ሲነገር እንደሚሰማ የተናገሩት አቶ ፊሊጶስ፣ ቅኝ ግዛት ጉዳትም ጥቅም እንዳለው አስረድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በተለይ ከአፍሪካ አገሮች ልዩ የሚያደርጋት የራሷን ባህል፣ ሃይማኖት፣ አመለካከትና የማኅበራዊ ሕይወት እሴቶቿን ጠብቃ እንድትኖር እንዳደረጋት ገልጸዋል፡፡ ቅኝ ግዛት ከትምህርት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ጥቅም ቢኖረውም፣ ይህንንም ቀስ በቀስ እንጂ በአንድ ጊዜ ማዘዋወሩ እንደማይመከር አክለዋል፡፡
ሕጎችንም ቢሆን የማይፈጸም ሕግ መውረስ ጥቅም እንደሌለው ከፈረንሣይ የተቀዳውን የፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 2472ን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ ከ500 ብር በላይ መቀባበል በጽሑፍ እንዲሆን ቢደነገግም፣ ሕጉ ተግባራዊ እንዳልሆነና የኢትዮጵያ ሕዝብ በእምነት ብቻ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር እንደሚበዳደር መርካቶ ምስክር መሆኑን በማስረዳት፣ ሕዝብን የሚጠቅም እንጂ ተፈጻሚነት የሌለውን ሕግ መቅዳት ጥቅም እንደሌለው ተናግረዋል፡፡
የሌሎች አገሮችን ሕግ ዝም ብሎ ቀድቶ በማምጣትና በአገር ውስጥ እንዲፈጸም ማድረግ ተገቢ ባለመሆኑ ጠበቆች ዝርዝር ሁኔታዎችን በማስረዳት የሕግ ድጋፍ በመስጠት፣ የአገርን የፍትሕ ሥርዓት ከማሳደግ አኳያ መሥራት እንደሚገባቸውም አስረድተዋል፡፡ ሕግን ዘመናዊ የሚያደርገው ከፓናማና ከእንግሊዝ እንዳለ ቀድቶ (የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና አዋጅ) ሳይሆን፣ የሕዝቡን እሴት ሳይነካ ኋላቀር የሆኑትን በመለወጥና የሚያሠሩትን ቀስ በቀስ እያሻሻሉ በመሄድ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የሙያው ባለቤቶች (ጠበቆች) ከ55 ዓመታት በላይ ሙያቸውን ለማሳደግና በተለይ ከውጭ አገር ተቀድተው የሚመጡ ሕጎች ላይ ለመወያየትና ሐሳብ ለመስጠት ቢፈልጉም፣ ያዳመጣቸው እንዳልተገኘም ተጠቁሟል፡፡ በእነ አቶ ታደሰ ጉሩሙ፣ አቶ አብዬ ሰላሙ፣ አቶ አበበ ወርቄ፣ የአቶ አበበ አባት አቶ ወርቄና ሌሎችም ባለሙያዎች በዕድር መልክ የተጀመረው የጥብቅና ማኅበር እስካሁንም የቀጠለና በ1992 ዓ.ም. በወጣው የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ አዋጅ ድንጋጌ መሠረት የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበር ተመሥርቶ፣ ራሱን እያሳደገና ሙያውን እያጠናከረ ቢሆንም፣ ህልውናው ከአምስት ዓመታት በላይ ሊዘል እንዳልቻለም አቶ ፊሊጶስ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበር ተጠሪነቱ ለፍትሕ ሚኒስቴር ሆኖ የተቋቋመ ቢሆንም፣ በ1997 ዓ.ም. ከነበረው አገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ ስያሜውን ሊቀማ ችሏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በወቅቱ ‹‹ምርጫውን አሸንፌያለሁና አላሸነፍክም›› ውዝግብ ምክንያት፣ የቅንጅት አመራሮች ለእስር ሲዳረጉ ከ70 በላይ የሚሆኑ የማኅበሩ አባላት ለቅንጅቶች ጥብቅና ለመቆም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ፣ ከፍትሕ ሚኒስር ጋር አለመግባባት ላይ መደረሱን አቶ ፊሊጶስ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ጊዜ የተወሰኑ የማኅበሩ አባላት ለብቻቸው የማኅበር ስያሜ እንዲሰጣቸው ሲያመለክቱ፣ ፍትሕ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበርን እንዲወስዱ በመፍቀዱ መሥራቾቹ፣ ከማኅበሩ ጋር ስያሜ የሚያሳትሙት ‹‹መጽሔት›› ብቻ እንደቀራቸውም አብራርተዋል፡፡
‹‹እንዴት እንዲህ ይሆናል?›› በማለት በወቅቱ ፍትሕ ሚኒስቴርን የጠየቁ ቢሆንም፣ ፍትሕ ሊያገኙ ባለመቻላቸው የሙያ ማኅበር መሆኑ ቀርቶ ተጠሪነቱ ለማኅበራትና በጎ አድራጎት ኤጀንሲ የሆነ እንደ ኤንጂኦ የሚቆጠር፣ ‹‹የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር›› ብለው በማቋቋም እስከ 2008 ዓ.ም. ድረስ ለ11 ዓመታት መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት 11 ዓመታት ጠበቃው ፈሪና ተሸማቃቂ ሆኖ መቆየቱን የገለጹት አቶ ፊሊጶስ፣ ምክንያቱ ደግሞ ፈቃድ ሰጪና ነጣቂ ከሆነ ዓቃቤ ሕግ ጋር ተከራካሪ ሆነው በአንድ መድረክ ላይ መሥራታቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ቀድሞ የመሠረቱት የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበር በፍትሕ ሚኒስቴር የፈቃድ ሰጪና ዲሲፒሊን ኮሚቴ አባል እንደነበር አስታውሰው፣ ስያሜው ሲነጠቅ ግን ባለሙያው እንደ ባለሙያ ሳይሆን እንደ ኤንጂኦ መታየት መጀመሩንና በርካታ ተፅዕኖዎች ሲደረጉበት እንደቆዩ አስረድተዋል፡፡ በ1992 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ሙሉ ሥልጣኑን ለፍትሕ ሚኒስቴር የሰጠው ሲሆን፣ በፈቃድ አሰጣጥና ዲሲፒሊን ላይ የማኅበሩ ተወካይ እንዲኖር መፍቀዱ ጥሩ የነበረ ቢሆንም፣ ያንን ማጣት ከባድ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
አንድ አገር የሚመራው በሕግ አውጪው፣ ተርጓሚውና አስፈጻሚው እንደሆነ መገለጹ ከስያሜው ጀምሮ የሕግ ባለሙያው ከማርቀቅ፣ እስከ መጨረሻው ድረስ የሚሰጠው አስተዋጽኦ በንጉሡ፣ በደርግም ሆነ በኢሕአዴግ ጊዜ ለወጡ ሕጎች ከፍተኛና የማይናቅ ሚና መጫወታቸውን አቶ ፊሊጶስ ተናግረዋል፡፡
ጠበቆች በማንኛውም የሕግ ማርቀቅም ሆነ ምክክር ላይ እንዳይሳተፉ መደረጉ፣ ‹‹ፍርድ ቤት መሄድ አይቻልም›› የሚሉ የቤትና ቦታ ማስለቀቅ፣ የገቢዎችና ጉምሩክ፣ የተወረሱ የኪራይ ቤቶች የሚመለከቱ አዋጆች ወጥተው መቆየታቸውንና የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 መጣሱን አስታውሰዋል፡፡
የሕግ ባለሙያው (ጠበቃው) የተጠናከረ የሙያ ማኅበር ቢኖረውና ገለልተኛ ሆኖ ራሱን የሚያስተዳድር ቢሆን ኖሮ ‹‹አይሆንም›› በማለት ተከራክሮ፣ መንግሥትንም ሕዝብንም መርዳት ይችል እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ሕዝብ ዝም የሚለው ስለማያውቅ ሳየሆን በውስጡ ቂም እየያዘ መሆኑን መርሳት ተገቢ አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ጠበቃው (የሕግ ባለሙያው) ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ትጋትና ሥነ ምግባርን አክብሮ መሥራት እንዳለበትና መንግሥትም ‹‹ሕግ የገዥዎች ማስፈጸሚያ ወይም መግዣ መንገድ ነው›› የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ በመተው፣ ‹‹ለሕዝብ መብትና ጥቅም መጠበቂያ መንገድ ነው›› በሚለው ላይ መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ከ2008 ዓ.ም. ወዲህ ወይም ከሽግግሩ በኋላ በተለይ ለጠበቆች ጥሩ ጊዜ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ፊሊጶስ፣ መንግሥት ጠበቆችን በተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች ላይ እያሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሁለትና ሦስት ባለሙያዎች አርቅቀው ሕግ ሆኖ ይፀድቅ የነበረው አሠራር ቆሞ በደንብ ውይይት ተደርጎባቸው፣ ጥናትና የተለያዩ ተሳትፎዎች ተደርገውባቸው ሕጎች እየፀደቁና ሥራ ላይ እየዋሉ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የሕግ ማሻሻያና ሪፎርም አማካሪ ምክር ቤት ላይ የተሰማሩ በርካታ የሕግ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የፌዴራል ጥብቅና አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀና በርካታ ጠበቆች የተሳተፉበት ራሱን የቻለ ነፃና ገለልተኛ የሆነ ማለትም ፈቃድ የመስጠት፣ የዲሲፕሊን ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ኖሮት በሚዋቀሩ ኮሚቴዎች ውስጥ የዓቃቤ ሕግ ተወካይ እንዲኖረው ተደርጎ የተረቀቀ ቢሆንም፣ አሳማኝ ባልሆነ ሁኔታ የመቆጣጠር ኃላፊነቱ ሙሉ በሙሉ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲሆን መደረጉ ቅሬታ መፍጠሩ ታውቋል፡፡
የ1992 ዓ.ም. አዋጅን መተካት ያስፈለገው የጠበቆች ሙያን ከፍ ለማድረግና የጥብቅና ፈቃድ የመስጠት፣ የማገድ፣ የዲስፒሊን ዕርምጃ የመውሰድና የመሰረዝ ሥልጣን ኖሮት ነፃ እንዲሆን ለማድረግ ቢሆንም ፈቃድ በመስጠትና በዲሲፒሊን ኮሚቴ ላይ አባላት እንዲገቡ በማድረግ፣ የመስጠትና የመሰረዝ ሥልጣኑን ግን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲወስድ በማድረግ፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለውይይት እንዲቀርብና እንዲፀድቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ፈቃድ ሰጪና ሰራዥ ከሆነ ጠበቆች ከእሱ ጋር እየተከራከሩ በነፃነት ይሠራሉ ማለት እንደማይቻልና በቀጣይ በሚደረግ ውይይት ምናልባት ፓርላማው ተረድቷቸው፣ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ ለባለሙያው ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ፊሊጶስ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ባሉት ዓመታት ‹‹ምስክሮችን ያላግባብ ጠይቃችኋል›› በማለት የዲሲፒሊን ክስ የቀረበባቸው ጠበቆች እንደነበሩ፣ የእነ አቶ መላኩ ፈንታን የክስ ሒደት በማስታወስ የተናገሩት አቶ ፊሊጶስ፣ በአዲሱም አዋጅ ፈቃድ ከመስጠት እስከ መሰረዝ ያለው ሥልጣን ከተሰጠ፣ ካለፈው አዋጅ ጋር ተመሳሳይ ሊያደርገው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
በአዲሱ አዋጅ ለጠበቆች በርካታ ዕድሎችን ማመቻቸቱንና ሁለትና ከዚያ በላይ ሆነው ጠበቆች የጥብቅና ድርጅት ማቋቋም እንደሚችሉ የፈቀደ ከመሆኑ አንፃር የተሻለ አዋጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ የተጠናከረ ማኅበር እንደሌለና በአዋጁ ሙሉ ሥልጣን ቢሰጥ መሸከም አቅቶት ሕዝብን አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል መግለጹ በአንድ በኩል ትክክል መሆኑን ጠቁመው፣ ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ ከመውሰድ ግን የስድስት ወርና የአንድ ዓመት የመሸጋገሪያ ጊዜ ቢሰጥ የተሻለና የተቀባይነት ያለው አስተያየት ይሆን እንደነበር አክለዋል፡፡ በእርግጥ ‹‹ተጠናከሩና ውክልና ይሰጣችኋል፣ በመቀጠልም አዋጁ ተሻሽሎ ሙሉ ሥልጣኑ ለእናንተ ይሆናል፤›› ማለቱም ጥሩ ተስፋ ቢሆንም፣ ጠበቆች ግን በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች በተጨባጭ ማስረጃ ላይ በመወያየት ኃላፊነቱን ምክር ቤቱ የማኅበሩ እንዲሆን እንዲፈቅድ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ በአዲሱ አዋጅ ሁሉም የፌዴራል ጠበቃ የኢትዮጵያ ጠበቆች ማኅበር አባል መሆኑን በአዋጁ ተደንግጓል፡፡ ጠበቆች ተባብረውና ጠንክረው በሥነ ምግባር ከተመሩ ትክክለኛው የፍትሕ ሥርዓቱ አጋዥ እንደሚሆኑም እየተገለጸ ነው፡፡