ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ሰኔ 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ተፈጥሮ በነበረው ሁከትና ረብሻ ከተገደሉ ሰዎችና ከወደመ ንብረት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በእስር ላይ በሚገኙት እነ አቶ እስክንድር ነጋ (አምስት ሰዎች) ላይ በሚሰሙ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች አሰማም ክርክር ላይ፣ ሰበር ሰሚ ችሎት ዛሬ የካቲት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ክስ ተመሥርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ፣ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ሥዩምና ወ/ሮ አስካለ ደምሌ፣ እንዲሁም በሌላ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ጌትነት በቀለ (በዋስ ናቸው) ሲሆኑ፣ ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ ብይን ከተሰጠ በኋላ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ከየካቲት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲሰሙ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕገ መንግሥትና የሽብርተኝነት ወንጀሎች አራተኛ ወንጀል ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡

ዓቃቤ ሕግ ከቀዳሚ ምርመራ ችሎት ጀምሮ በአዋጅ ቁጥር 699/2003 ድንጋጌ መሠረት ለምስክሮቹ ጥበቃ እንዲደረግለትና ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩለት ያቀረበው ጥያቄ በሥር ፍርድ ቤት የተተገበረለት ቢሆንም፣ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ግን ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አዋጅ ቁጥር 699/2003 ድንጋጌን በመጥቀስ ምስክሮች ማንነታቸው ሳይታወቅ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩለት የጠየቀው፣ ምስክሮቹ ከተከሳሾች ጋር የቅርብ ትውውቅ ያላቸው መሆኑንና ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችልና ዛቻና ማስፈራሪያም እንደደረሰባቸው በማስረዳት ነበር፡፡

ተከሳሾቹ ባቀረቡት የመቃወሚያ ክርክር እንዳስረዱት ዓቃቤ ሕግ እንደገለጸው፣ ምስክሮቹ ከተከሳሾቹ ጋር የቅርብ ትውውቅ ያላቸው ቢሆንም፣ የቅርብ ትውውቅ ያለው ምስክር የተለየ ጥበቃ እንዲደረግለት አዋጁ ያለው ነገር ካለመኖሩም በተጨማሪ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸውም ምንም ዓይነት ማስረጃ አለማቅረቡንና አዋጁም ቢሆን በአንቀጽ 5 (3) ላይ እንደገለጸው፣ ጥበቃ መደረግ ያለበት ለከሳሽ ብቻ ሳይሆን ለተከሳሽም እንደሆነ ደንግጓል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20 (1) ድንጋጌ ከአዋጁ ጋር ተጣምሮ ሲታይም የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢና አጭር በሆነ ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመሰማት መብት እንዳላቸው በመደንገጉ፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ የቀረበው ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ፣ በግልጽ ችሎት እንዲታይ ፍርድ ቤቱን ጠይቀው ነበር፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም መዝገቡን መርምሮ የዓቃቤ ሕግን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በግልጽ ችሎት ቀርበው እንዲመሰክሩ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር፡፡

በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር የተሰኘው ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ያለ ቢሆንም፣ ይግባኝ ሰሚ ችሎት የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አፅንቶታል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በውሳኔው ላይ መሠረታዊ የሕግ ስህተት መፈጸሙን በመግለጽ፣ ጉዳዩን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርቦታል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎት ዛሬ የካቲት 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ተከሳሾች በሌሉበት ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ውሳኔው የሥር ፍርድ ቤቶችን ውሳኔ የሚሽር ከሆነ፣ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን የሚያሰማው በመጋረጃ ጀርባ ይሆናል፡፡ ውሳኔው የሥር ፍርድ ቤቶች የፈጸሙት የሕግ ስህተት እንደሌለ በመግለጽ የሚያፀድቀው ከሆነ፣ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በእነ አቶ እስክንድር ላይ በግልጽ ችሎት ይመሰክራሉ፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *